ባንኮች በየራሳቸው መንገድ ጥናት በማድረግ ወቅታዊውን አገራዊ ችግር ለማቃላል እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ ሲሆን፣ በዚህም ሳምንት ወጋገን ባንክ፣ ዓባይ ባንክና ዳሸን ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን ስለመቀነሳቸው አስታውቀዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ ባሳደረው ጫና ምክንያት ወጋገን ባንክ እስከ 53 በመቶ ብድር የወለድ ቅናሽ ማድረጉን ሲያስታውቅ፣ ዓባይ ባንክ ደግሞ በተመረጡ ቢዝነሶች ለሦስት ወር የብድር ወለድ ስረዛ አድርጓል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ከተሰማ ወዲህ የተለያዩ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ሰንብቷል፡፡
ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ዕርምጃ መውሰዱን ያስታወቀው ዳሸን ባንክ፣ የቫይረሱ ሥርጭት በተለይ በአንዳንድ በጥናት በተለዩ ዘርፎች ላይ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል በሌሎች ተጎጂ መስኮች ላይ እንዳደረገው ሁሉ በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞቹ እየደረሰባቸው ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመጋራት መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም መሠረት ባንኩ በአበባና አትክልት፣ በሆቴልና ማስጎብኘት፣ በኤክስፖርት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርትና በትምህርት ተቋማት ዘርፎች ለተሰማሩና በሥራ ላይ ላሉ ደንበኞች እ.ኤ.አ. ከሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የወለድ ቅናሽ፣ የብድር ዕፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ ሰጥቷል፡፡
ባንኩ በአበባና አትክልት ዘርፍ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች ቀደም ሲል በዝቅተኛ ወለድ እያበደረ የነበረ ቢሆንም፣ ዘርፉ ከቫይረሱ ሥርጭት ጋር ተያይዞ የደረሰበትን የኢኮኖሚ ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ ተጨማሪ ቅናሽ በማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ ደንበኞች ሰባት በመቶ የወለድ ምጣኔ ብቻ እንዲከፍሉ እንደወሰነም የባንኩ መረጃ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም ተበዳሪዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የስድስት ወር የብድር ዕፎይታ እስከ አምስት ዓመት የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለ ምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ተፈቅዷል፡፡ በሆቴልና ማስጎብኘት ዘርፍ የተሰማሩ ተበዳሪዎች ከዚህ በፊት እስከ 17.5 በመቶ የሚደርስ ወለድ ይከፍሉ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን እ.ኤ.አ. ከሰኔ 1 ቀን ጀምሮ የሚከፍሉት የወለድ ምጣኔ ወደ ሰባት በመቶ እንዲቀንስና ይደረጋል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ ተበዳሪዎቹ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የስድስት ወር የብድር ዕፎይታ እስከ አምስት ዓመት ድረስ የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለ ምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ እንዲያገኙ መወሰኑንም ጠቅሷል፡፡
በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾችም እንዲሁ የወለድ ምጣኔ ለሦስት ወራት ሰባት በመቶ ብቻ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረትም የሦስት ወር የብድር መክፈያ ዕፎይታ ጊዜና እስከ ሦስት ዓመት ያለ ምንም የብድር ማራዘሚያ ክፍያ እንዲስተናገዱ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በማኑፋክቸሪንግ፣ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስና በትምህርት ዘርፎች የተሰማሩ ተበዳሪዎችም በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ለስድስት ወር የብድር መክፈያ ዕፎይታና እስከ ሦስት ዓመት ድረስ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ለመስጠት ይደረጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዳሸን ባንክ ከላይ ለተጠቀሱትና በቫይረሱ ሥርጭት ይበልጥ ለኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደሚዳረጉ በጥናት ለተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨማሪ የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ እንዲደረግላቸውም ወስኗል፡፡ ከ17.5 እስከ 18 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩና በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞች የ1.5 በመቶ ወለድ ቅናሽ ተደርጎላቸው ከ16 በመቶ እስከ 16.5 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡ ከ14 እስከ 17 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩ ደግሞ የአንድ በመቶ ቅናሽ ተደርጎላቸው ከ13 በመቶ እስከ 16 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡ ሆኖም ሁሉም የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ውሳኔዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከታወጀበት ጊዜ በፊት በተበላሸ ብድር ዝርዝር ውስጥ ይገኙ የነበሩ ብድሮችን እንደማይጨምር ዳሸን ባንክ አመልክቷል፡፡
ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰዱን ያስታወቀው ወጋገን ባንክም፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ በማሰብ ለተበዳሪ ደንበኞቹ እስከ 53 በመቶ የሚደርስ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ ማድረጉ የባንኩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አቶ ዓባይ መሀሪ እንደገለጹት፣ ወጋገን ባንክ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ በፈጠረው መቀዛቀዝ ምክንያት በተበዳሪ ደንበኞቹ ላይ እያደረሰ የሚገኘውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሦስት ወራት የሚቆይ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ አድርጓል፡፡
በተለይም ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ ተፅዕኖ ያሳደረባቸው በሆቴል፣ በቱሪዝም፣ በአስጎብኚና የጉዞ ወኪል የሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ የባንኩ ደንበኞች እስከ 53 በመቶ የወለድ ቅናሽ አድርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፎች ለሚገኙ ደንበኞቹ ደግሞ እስከ 39 በመቶ ቅናሽ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ከተወሰኑ የብድር ዘርፎች በስተቀር ከጥር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ ለተደረገባቸው ሌሎች የብድር ዘርፎችም ላይ እስከ ሦስት በመቶ የሚደርስ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ ስለማድረጉ ይኸው የባንኩ መረጃ ያስረዳል፡፡ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሹም 58 በመቶ በሚሆነው የባንኩ አጠቃላይ የብድር መጠን ላይ ተግባራዊ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ወጋገን ባንክ በተለያዩ ወቅቶች በጤናና ማኅበራዊ እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የተጎዱትን ለማቋቋም የገንዘብ ዕገዛ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረገው አገራዊ ጥረት የሚያግዝ የስምንት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ለደንበኞቹም የኤልሲና የግዥ ትዕዛዝ ክፍያን ሙሉ ለሙሉ ያስቀረ መሆኑም የፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
ዓባይ ባንክም ወቅታዊውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት የችግሩ የመፍትሔ አካል ለመሆን እንዲችል ደንበኞችን በዚህ አስከፊ ጊዜ በንግድ ሥራቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስና ለመደገፍ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በለጠ ዳኛቸው ገልጸዋል፡፡ በሁሉም የብድር ዓይነቶች የብድሩን የመክፈያ ጊዜ መሠረት በማድረግ የንግዱ ዘርፍ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመገመት፣ የኮሮና ወረርሽኝ ጉዳትን ከግምት በማስገባት እንዲሁም የባንኩን አቅም ታሳቢ በማድረግ የብድር ወለድ ላይ ከ0.5 እስከ ሦስት በመቶ ድረስ ቅናሽ አድርጓል፡፡ ይህም በሁሉም ብድር ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑ የምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ያመለክታል፡፡ ከዚህም ሌላ በወረርሽኙ ምክንያት ዋነኛ ተጠቂ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ የንግድ ዘርፎች የሆቴልና አስጎብኚ እንዲሁም የአበባ ምርት ላኪና አቅራቢ ዘርፎች ሲሆኑ፣ በእነዚህ ዘርፎች ላይ ከፍ ያለ የወለድ ቅናሽ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም የተነሳ ዓባይ ባንክ ይህንን የወለድ ቅናሽ በማድረጉ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያጣል፡፡ በእነዚህ ቢዝነሶች ላይ ከግንቦት ወር ጀምሮ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ተበዳሪዎቹ እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸውን የዋና ብድርና ወለድ ክፍያ ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የባንኩ የብድር ደንበኞች በዚህ አስከፊ ወቅት ሊያጋጥማቸው ከሚችለው ቀውስ እንዲወጡ ባንኩ ከዚህ ቀደም ያደረገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አስታውቆ፣ የብድር ማራዘሚያ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ደንበኞች እንደየሁኔታው እየታየ እንዲፈቀድ ይደረጋልም ብሏል፡፡ የብድር ማራዘሚያ ጥያቄ በነፃ እንዲሆንና የቅድሚያ ብድር ክፍያ ቅጣትንም ስለማስቀረቱ ታውቋል፡፡
የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝም ዓባይ ባንክ በአገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው ዕርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሷል፡፡