Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባንኮችም ተረጂ እንዳይሆኑ   

ወቅቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ በርካታ ፈተናዎች ከፊታችን በመደቀናቸው ከጥንቃቄም በላይ በሆነ አኗኗር መንቀሳቀስ ግዴታ ይሆንብናል፡፡ መስከን እንደሚያስፈልገን የሚያመላክቱ ጉዳዮች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ አሳሳቢ ችግሮች አፍጥጠው ሲመጡ እየታዩ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ተወላግዶ እንዳይወድቅ የሚያግዙ ዕርምጃዎችን አልሞና አቅዶ በፍጥነት መተግበር የሚፈለግበት ወቅት ነው፡፡

የቱንም ያህል ፈተና ቢበዛ፣ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ እየተመለከቱ መፍትሔዎችን ከሥር ከሥር እያበጁ መራመድ መካሪ አያሻውም፡፡ የከበደ ነገር ቢመጣ እንኳ አደጋውን መቀነስ የሚቻለው በዚህ አግባብ ነውና፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ የማይነካ የኢኮኖሚ ዘርፍ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት መስክ፣ የኑሮና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አለ ለማለት ይቸግራል፡፡ ከዚህ አንፃር በሽታው በተጓዳኝ የሚያስከትለው ጉዳት በአሁኑ ወቅት ከምናየውም በላይ የከፋ እንዳይሆን በመንግሥት በኩል ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም፣ ዘላቂ መፍትሔ ግን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ሊሰጥ የሚችለው ድጋፍ በአቅሙ ልክ የተገደበ በመሆኑ ነው፡፡ ከታክስ የሚሰበስበው ገቢ ከወዲሁ እየቀነሰ ነው፡፡ በዕርዳታና ብድር የሚያገኘው ድጋፍም ዕርግጡ አልታወቀም፡፡ ለጋሽ አገሮች የራሳቸውን እሳት ለማጥፋት በሚራወጡበት በዚህ ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገሮችን እንዳይዘነጉ ለሚቀርበው ጥሪ ምላሻቸው ከተገመተውም ከተጠበቀውም በታች እየሆነ ነው፡፡

ይህ በሆነበት ወቅት እስካሁን በመንግሥት ተላልፈው የሚተገበሩ ውሳኔዎች ለችግር ማቃለያ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆኑ በመገንዘብ፣ ዕገዛ የተደረገላቸው አካላት የራሳቸውን ጥረት ማከልና በራሳቸው መፍትሔ መፈለግ የግድ ይሆንባቸዋል፡፡ በድጋፍና በጊዜያዊ ዕርምጃ እሳት ማጥፋት ዘላቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ሁሉም የበኩሉን ማዋጣትና የሚችለውን ማድረግ ግድ ነውና እንቅስቃሴዎቻችንን ከዚህ አንፃር መቃኘቱ ለሁሉም ይበጃል፡፡ ከፊታችን የሚጠብቀንን መገመት ስለማይቻል የሁሉም አካል ርብርቦሾች ለሁላችን መዳንን ሊያተርፍልን ይችላል፡፡  

አንዳንድ የንግድ መስኮች ኮሮና በተከሰተ ማግሥት ለማሸብረክ ተገደዋል፡፡ አንዳንዶችም ጉዳታቸው ውሎ አድሮ እየታየ ነው፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ካለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንፃር በርካታ ጫናዎች ወደ ፋይናንስ ተቋማት እየተወረወሩ ነው፡፡ የቢዝነስ ዘርፉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከባንኮች ጋር የብድር ግንኙነት ያለው በመሆኑ፣ ኢኮኖሚው ላይ የሚያርፈው ተፅዕኖ ባንኮችን ሳይነካ አያልፍም፡፡ በሌሎች ዘርፎች እየደረሰ ያለውን ጉዳት ባንኮች እንዲጋሩት ያደርጋል፡፡

ከኮረና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የቢዝነስ መቃወስ ምክንያት አቅማቸውን እየገመቱ የወለድ ማሻሻያዎችን እያደረጉ ነው፡፡ የብድር ማራሚያም እየፈቀዱ ነው፡፡ የአገልግሎት ክፍያዎችን እየቀነሱና እያስቀሩ ነው፡፡ የብድር ወለድ ምጣኔን ለወራት በሚታሰብ መጠን የቀነሱ አሉ፡፡ የብድር ማራዘሚያው ጉዳይ በሁሉም ባንኮች በኩል ማመልከቻ እየቀረበበት ነው፡፡ ደምበኞቻቸውን ለመታደግ የኮሮና ቫይረስ ጠፍቶ ወደ ትክክለኛው መንገድ ነገሮች ይመለሳሉ በሚል ተስፋ፣ ባንኮች በየወሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገቢያቸውን እያስቀሩ፣ ለወቅቱ ችግር የበኩላቸውን እያደረጉ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ የሚያደርጉት ነው፡፡

ይህ ተግባራቸው እስካሁን እያደረጉ ባሉት ድጋፍ ብቻ ይወሰናል ማለት አይቻልም፡፡ በርካታ ተበዳሪዎች ገንዘብ እየጠየቁ ወደ ባንኮች የሚመጣ ገንዘብ በተቋረጠ ቁጥር የባንኮችን አቅም ሊፈታተን ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ብሔራዊ ባንክ ይህንን ችግር በቅርብ እየተከታተለ ጣልቃ መግባቱ እየታየ ነው፡፡ ለባንኮች የ15 ቢሊዮን ብር ድጎማ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ ተጨማሪ በመስጠት የተጎዱ ዘርፎች እንዲያንሰራሩ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የባንኮች ጉዳት የሚታየው ውሎ አድሮ በመሆኑ፣ እነሱም ዕገዛ የሚጠይቁበት ጊዜ ሩቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ወደ ኪሳራ እንዳይገቡ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለባለአክሲዮኖች የሚከፋፈል የትርፍ ድርሻ ዘንድሮ መኖር አለመኖሩ አጠራጣሪ ይመስላል፡፡

 መጪውን ጊዜ በመገመትና ችግሩ ከዚህም የከፋ ከሆነ ብሎ የቀደመ ዕቅዶቻቸውን በመከለስ ጭምር ሊጠይቃቸው ይችላል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የወቅቱን ችግር በመጋፈጥ በትብብር መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ተደጋግፎ ማለፉንና አላስፈላጊ የሆኑ ውድድሮችን ገታ በማድረግ በአጠቃላይ ኢንዱስትሪውን ከጉዳት የመታደግ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በአጠቃላይ መጪውን ጊዜ ብቻቸውን የማይገፉት አይሆንም፡፡ አሁን ሌሎችን የመደገፍ ሥራቸው ነገ እነሱንም የበለጠ ሊጎዳ የሚችልበት ዕድል እንዳይኖር ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

 መንግሥት በባንኮች በኩል ለተጎዱ የንግድ ዘርፎች ቅድሚያ በመስጠት ለብድር የሚውል የተወሰነ ገንዘብ እንዲለቀቅ እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ነገ ከነገ ወዲያስ እንዴት ያስኬዳል የሚለውን ዛሬ ሆኖ ማወቅ ስለማይቻል፣ መንግሥት ነገን ያማከለ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ አለበት፡፡ ባንኮችም ለነገ ብለው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ስለዚህ እንዲህ ያልታሰቡ አገራዊ ችግሮችን በአግባቡ ለመስጠት ራሳቸውን የፋይናንስ ተቋማት ባለሙያዎች ያካተተ ምክክርም የሚጠይቅም ነው፡፡ ያለው ገንዘብ በአግባቡ ተጠቅሞ ይህንን ጊዜ ለመሻገር እንዲቻል አሁንም የበለጠ መሠራት አለበት፡፡ የባንኮችን ጉዳይ ካነሳን በተለይ የግል ባንኮችን የፈጠሩት የየባንኮቹ ባለአክሲዮኖቹ ናቸውና የእነሱን ዕገዛና ትብብር የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁን ከምናየው የባንኮች እንቅስቃሴ አንፃር ባንኮች እንደ ከዚህ ቀደሙ ትርፍ በትርፍ ላይ የሚያገኙበት አይደለም፡፡ ገበያቸውን እየቀነሱ በመሆኑ ኪሳራ ባይታሰብም የትርፍ ምጣኔዎቻቸው ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ የባንኩ ባለቤቶች ወይም ባለአክሲዮኖችም እንደ ከዚህ ቀደሙ የትርፍ ክፍፍል ያገኛሉ ተብሎ ላይጠበቅ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ባንኮች ትርፍ አያስመዘግቡም ማለት ሲሆን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ በአንድም በሌላ ምክንያት እነሱ ላይ የሚያርፍ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እየተፈጠረ ያለው ችግር ባንኮች ላይ ከአሁን በባሰ በሚቀጥለው ዓመት ላይ የሚታይ ሊሆን ስለሚችል ዘንድሮ ትርፍ ተብሎ ሊመዘገብ የሚችለው ገንዘብ ባንኮች አቅም ለማሳደግ እንዲውል የሚያደርግበት ምክንያት ላይኖር ይችላልና ባለአክሲዮኖች ይህንኑ ታሳቢ አድርገው በመቆየት ቀዳሚ ጉዳያቸው ባንካቸውን ቀጣይ ማድረግ ላይ መሆን ይገባል፡፡ እርግጥ አሁን እየታገለው የኢኮኖሚ መቀዛቀዙ እንዲሁም ወቅታዊን ችግር ሊፈጥር ቀደም ብሎ በሠሩት ሥራ አትራፊ መሆናቸው ባይቀርም የትርፋቸውን ትርፍ ግን በቀጣይ ፈተናቸው ማገገሚያ ማድረግ ይችሉ ዘንድ መታሰብ አለበት፡፡ ምክንያቱም ከወዲሁ ጉዳቱን ለመቀነስ ይችሉ ዘንድ ትርፋቸውን ወደ ካፒታል ማዞርም ሊመጣ ይችላል ብሎ ማሰብ ከዚያ በኋላ የተሻለ ይሆናል ማለት ነው፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት