Sunday, April 21, 2024

ከሕገ መንግሥት ትርጓሜ እስከ የሽግግር መንግሥት በሚሉ ሐሳቦች የሚዋልለው ፖለቲካ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በነበሩት የመጀመርያዎቹ ሳምንታት፣ የወረርሽኙን አደገኝነትና ሊያደርስ የሚችለውን ዕልቂት ታሳቢ ያደረጉ ውይይቶችና የጥንቃቄ ምክሮች የዜጎች ዋነኛ ጉዳይ በመሆናቸው፣ የአገሪቱ የፖለቲካም ሆነ የማኅበራዊ ጉዳዮች ልሂቃን ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ወደ ጎን አድርገው ነበር፡፡

በወረርሽኙ የተነሳ ጭርታ ውጦት የሰነበተው ፖለቲካውና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ከሰሞኑ ግን ግዝፍ ነስተው ተመልሰዋል፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ዘንድሮ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን ጠቅላላ ምርጫ ማከናወን እንደማይችል የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ምርጫውም ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን ይፋ አድርጓል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔውን ይፋ ካደረገ በኋላ ደግሞ ጭርታ ወሮት የሰነበተው የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ወደነበረበት የሙግትና የጭቅጭቅ አመሉ የተመለሰ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የንትርኩ መንስዔ ደግሞ በሥራ ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመኑን ዘንድሮ የሚያገባድድ በመሆኑ ነው፡፡ ምርጫው ሲራዘም መንግሥት ቅቡልነትም ሆነ ሕጋዊነት አይኖረውም የሚል መከራከሪያ በማቅረብ፣ የተለያዩ ለመፍትሔ ተብለው የሚቀርቡ ጽንፍ የረገጡ ሐሳቦች መሰንዘር ጀምረዋል፡፡

ይህን የፖለቲካና የሕገ መንግሥት ቅርቃር (Deadlock) ለመፍታትና ምርጫው እስከሚከናወን ድረስ የአገሪቱ የዕለት ተዕለት እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምን ሊመስሉ ይችላሉ? ምንስ መምሰል ይኖርባቸዋል በሚሉ መሠረታዊ ሐሳቦች ላይ የፖለቲካ ተዋንያኑ ይሻላል የሚሉትን ሐሳብ በመሰንዘር ላይ ናቸው፡፡

ከሕገ መንግሥት ትርጓሜ እስከ የሽግግር መንግሥት በሚሉ ሐሳቦች የሚዋልለው ፖለቲካ

ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱ የሕግ ምሁራን የተፈጠረውን የሕገ መንግሥት ክፍተት፣ እንዲሁም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለመጠቆም ተጠምደው የተለያዩ መጣጥፎችን በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን የፖለቲካና የሕገ መንግሥት አጣብቂኝ በተመለከተ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚሰነዝሩት የመፍትሔ አቅጣጫ በተጨማሪ፣ መንግሥት መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ሐሳቤች ከሳምንታት በፊት ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡

መንግሥት በአማራጭነት ያቀረባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል፣ እንዲሁም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉ ናቸው፡፡

በእነዚህ በመንግሥት በቀረቡት አራት አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አቋሞችን እያራመዱ ሲሆን፣ መንግሥት ደግሞ ከቀረቡት የመፍትሔ አማራጮች መካከል የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የሚለው እንዲከናወን መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የመንግሥት አቋም ከተሰማ በኋላ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተወሰኑት ከቀረቡት አራት የመፍትሔ ሐሳቦች ይሆናል የሚሉትን በመደገፍ ላይ ሲገኙ፣ የተወሰኑት ደግሞ አራቱም የመፍትሔ ሐሳቦች ‘አገሪቱ አሁን ለገጠማት ፖለቲካዊና ሕገ መንግሥታዊ ችግር መፍትሔ ሊሆኑ አይችሉም፣ አሁን የገጠመንን ችግር በዘለቄታዊ መንገድ ልንቀርፈው የምንችለው የሽግግር መንግሥት በመመሥረት ነው’ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ሲያቀነቅኑት የነበረውን ሐሳብ አጠናክረው በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡

ከመንግሥት ወገን ከቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅና ምክር ቤቱን መበተን የሚሉት በፓርቲዎች ይሁንታ ያልተቸራቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ሲሆኑ፣ ከቀሩት ከሁለቱ ማለትም ሕገ መንግሥት ማሻሻልና የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉት ደግሞ ለመጨረሻ አማራጭነት በፓርቲዎቹ ተመርጠዋል፡፡

ለአብነት ያህልም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የሕገ መንግሥት መሻሻልን የመረጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ደግሞ የሽግግር መንግሥት ወይም ተቋም ይመሥረት የሚለውን ሐሳብ እያቀነቀኑ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ካቀረባቸው አራት አማራጮች መካከል የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚለውን የመረጠ ሲሆን፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔም በጉዳዩ ላይ የባለሙያ ግብዓት ለማካተት እንዲቻል ለሕገ መንግሥት ምሁራን ጥሪ አስተላልፏል፡፡

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ እንዲሁም የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን በአባልነት ያቀፈው ትብብር ለኅብረ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም (ትብብር) አሁን በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት የተወሰነ የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት በሥልጣን እንዲቀጥል ይጠይቃሉ፡፡

ሆኖም ትብብሩ፣ ‹‹በዚህ ጊዜ ውስጥ ሥልጣን ላይ ያለው አስፈጻሚ አካል የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ከማከናወንና ምርጫ ለማካሄድ ከማገዝ ውጪ ሕግ ወይም አዋጅ ማውጣት፣ ማሻሻል ወይም ያሉትን ሕጎች መሻርና አዳዲስ አደረጃጀት መዘርጋት የለበትም›› ብሎ እንደሚያምንም በመግለጽ፣ ሕገ መንግሥቱ እንዳለ ሆኖ አሁን ላጋጠመው አዲስና ያልተለመደ ፈተና በሁሉም ወገኖች የጋራ ስምምነት መሠረት ‹‹አዲስና ያልተለመደ›› ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ፣ ‹‹በኮቪድ 19 ምክንያት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የገጠመውን ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ (አጣብቂኝ) ለመሻገር›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ባለ 8 ገጽ የመፍትሔ ሐሳብ አብራርቷል፡፡

በዚህም መሠረት፣ ‹‹አሁን ያለው መንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካል ለአንድ ዓመት ሥልጣኑ እንዲራዘም ሆኖ፣ ጠቅላላ ምርጫው በግንቦት ወር 2013 ተጠናቆ አዲስ የሚመረጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀደም ሲል በተለመደው ጊዜ ሥራውን እንዲጀምር ማድረግ›› የሚል የመፍትሔ ሐሳብ ሰንዝሯል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ መድረክ ‹‹ከገባንበት ፖለቲካዊና ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ለመውጣት›› በሚል ባቀረበው ባለ 17 ገጽ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ፣ ‹‹ከገባንበት ማጥ መውጣት የሚቻለው የተሳካ ምርጫ እስክናካሂድ ድረስ የመንግሥትን እንቅስቃሴ በጋራ የሚመለከትና የሚቆጣጠር፣ የሁሉም ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ገዥውን ፓርቲ አካቶ የሚቋቋም ስብስብ እንዲኖር›› ማድረግ ሲቻል ነው የሚል ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

የአገሪቱ ችግሮች መሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መሆናቸውን የሚገልጸው መድረክ የሚፈለገው መፍትሔም ከጊዜያዊ ማስታገሻዎች የዘለለ መሆን እንደሚኖርበት በመጠቆም፣ ‹‹አሁን የገባንበትን የፖለቲካና የሕገ መንግሥት ቀውስ ለመፍታት ጭምር ድርድር ያሻል፡፡ መንግሥት ተሯሩጦ ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ሥልጣኔን አራዝማለሁ ቢል አገራችንን የሚያረጋጋ ሳይሆን፣ ወደ ባሰ ቀውስ ሊከት ይችላል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለድርድር፣ ለብሔራዊ መግባባትና የጋራ መፍትሔ ለማምጣት ዝግጁ ሊሆን ይገባዋል፤›› በማለት ለዓመታት ሲያቀርበው የነበረውን ‹‹የእንደራደር›› ጥሪ ዛሬም አቅርቧል፡፡

የመንግሥትን የሕገ መንግሥት ትርጓሜ አካሄድ ክፉኛ የተቸረው መድረክ፣ ‹‹ተርጓሚው አካል ማለትም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥልጣን ዘመኑ እያለቀ ያለና የገዥው ፓርቲ አባላት ብቻ ያሉበት ስለሆነ፣ ገለልተኛ ሆኖ ሕገ መንግሥቱን ይተረጉማል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፤›› ሲልም በጉዳዩ ላይ ያለውን ተቃውሞ በማሰማት የድርድር ጥያቄ አቅርቧል፡፡

‹‹በአገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በክልልም የሚዋቀር የጋራ ባለድርሻ አካላት ስብስብ በአስቸኳይ እንዲቋቋም›› በመጠየቅ፣ በዚህ ዓይነት መድረክ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከዚህ የመፍትሔ ሐሳብ በተቃራኒው ደግሞ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ ‹‹አጠቃላይ ምርጫ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝና አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ባለ 12 ገጽ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ፣ ‹‹አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ መፍትሔ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ነው፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

የሽግግር መንግሥት ማቋቋም አሁን ካለው ችግር ሊያወጣ እንደማይችል የሚሞግተው ፓርቲው፣ ይህ የማይሆንበት ምክንያት ደግሞ፣ ‹‹ጠንካራ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ከሚያስፈልጉት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ጠንካራ የውይይትና የድርድር አቅምና ባህል መኖር ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እውነተኛ የመደማመጥ፣ የመረዳዳትና አብሮ የመሥራት ታሪክ የሚጎድላቸው የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች/ቡድኖች በጋራ የሽግግር መንግሥት መሥርተው አገር ሊመሩና ወደ ዴሞክራሲ ሊያሸጋግሩ ይችላሉ ብሎ ማሰብ ለአብዛኛው ሕዝባችን አሳማኝ አይደለም፤›› የሚል ነው፡፡

‹‹አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት፣ የፌዴራል  ሥርዓትም ሆነ መንግሥት መሩ የዴሞክራሲ ሽግግር ሒደት ቀላል የማይባሉ ጉድለቶች ያሉባቸው ቢሆንም፣ እነዚህን ችግሮች በአንድ ጀንበር ለመለወጥ መሞከር ተጨማሪ የፖለቲካ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመሆኑም የሽግግር መንግሥት መመሥረት እንደ አገር ካላንበት ችግር መውጫ መንገድ ሊሆን አይችልም፤›› ሲል አቋሙን አንፀባርቋል፡፡

በመሆኑም ሕገ መንግሥትን ከማሻሻል አንፃር በአገሪቱ ተጨባጭ ተሞክሮ መኖሩን፣ ማለትም የቀረጥና የግብር፣ እንዲሁም የሕዝብና የቤት ቆጠራን የተመለከቱ አንቀጾች ማሻሻያ እንደተደረገባቸው በማስታወስ አሁንም መፍትሔው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ነው በማለት የመፍትሔ ሐሳቡን ሰንዝሯል፡፡ በተለይ የሕዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ የተደረገው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የምርጫ መራዘምን ተከትሎ አሁን ለተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ ‹‹ትክክለኛ ተሞክሮ›› ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል በማለት፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ የምርጫ 2012 መራዘምን ተከትሎ ለተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ የተሻለ አማራጭ ነው›› በማለት ለሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ ኢዜማም ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል የሚለው የመፍትሔ የተሻለ ሐሳብ መሆኑን መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

አገሪቱ ከገባችበት ቅርቃር አንፃር ተዋንያኑ የተሻለ የሚሉትን ሐሳብ እየሰነዘሩ ቢገኝም፣ መንግሥት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የሚለው የመፍትሔ ሐሳብ የተሻለ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ነው፡፡ በተቃራኒው የሽግግር መንግሥት ሐሳብን የሚሰነዝሩት ወገኖች ደግሞ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደ መጨረሻ ቀን በመውሰድ መንግሥት ከዚያ በኋላ ቅቡልነት ሊኖረው ስለማይችል፣ የተሻለው የመፍትሔ አማራጭ ድርድር እንደሆነ በመወትወት ላይ ናቸው፡፡ የአገሪቱ ቀጣይ ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታም በእነዚህ ሁለት ፅንፍ የያዙ ‹‹የመፍትሔ›› ሐሳቦች መሀል እየዋለለ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -