Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግባቸውን ለመፍታትና በህዳሴ ግድብ ላይ ለመተባበር መስማማታቸውን ገለጹ

ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግባቸውን ለመፍታትና በህዳሴ ግድብ ላይ ለመተባበር መስማማታቸውን ገለጹ

ቀን:

‹‹የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በአስቸጋሪ ጊዜም ቢሆን ተጠናክሮ ይቀጥላል›› አብደላ ሐምዶክ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር

ኢትዮጵያና ሱዳን በሚያዋስናቸው ድንበር ዙርያ ያሉ ግጭቶችንና የይገባኛል ጥያቄዎችን፣ በጥናትና ሁሉን አሳታፊ በሆነ የወሰን ማካለል ለመፍታት መስማማታቸውን አስታወቁ።

ከድንበር ጉዳዮች በተጨማሪ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ለመተባበር ስምምነት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ሁለቱ አገሮች ወደዚህ ስምምነት የደረሱት በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ከግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ከመከሩ በኋላ ነው።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ የሁለቱ አገሮች ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ባደረጉት ፖለቲካዊ ውይይት ሰላማቸውንና ነባር የሆነውን መልካም ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

የፖለቲካ ውይይቱ አብሮ በመኖርና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ የረዥም ጊዜ ግንኙነት በሚያጠናክር መንፈስ መካሄዱን የገለጸው የቃል አቀባይ ጸሕፈት ቤቱ፣ የሁለቱን አገሮች የድንበር ጉዳይ የሕዝቦችን አብሮነትና የግንኙነታቸውን ታሪካዊ ዳራ ግምት ውስጥ በማስገባት ለመፍታት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

የሱዳን መንግሥት በውይይቱ የተሳተፈው በአገሪቱ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑካን ቡድን ይዞ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ቡድን በውይይቱ ተሳትፏል።

ውይይቱ ሰኞ ግንቦት 10 2012 ዓ.ም. ከተጠናቀቀ በኋላ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ሁለቱ አገሮች የወሰን ማካለል ጉዳይን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሻግር፣ እንዲሁም የአካባቢውን ሕዝቦች ዘላቂ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል መንገድ መፈታት እንዳለበት መግባባታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ መሠረት በወሰን አካባቢ የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን ተገቢነት የሌላቸው እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ፣ ሁሉም አርሶ አደሮች ያለምንም ሥጋት ወደ ግብርና ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባ ኢትዮጵያ አቋሟን እንዳሳወቀችና በሱዳን በኩልም ተመሳሳይ አቋም መያዙን አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

ድንበር ማካለልን አስመልክቶ በተካሄደው በዚህ ውይይት የማካለሉ አስፈላጊነት የማያከራክር ቢሆንም፣ ችካል የመትከል ጉዳይ ሳይሆን በጥንቃቄና በውይይት የሚፈጸም ተግባር እንደሆነ በሁለቱም ወገኖች መግባባት እንደ ተደረሰበት አቶ ደመቀ አስረድተዋል።

‹‹ወሰን የማካለል ጉዳይ ታሪካዊ ዳራውን በጠበቀ፣ ወቅታዊ ሁኔታውን ባገናዘበ፣ ያገባኛል የሚሉ አካላት ሙሉ ተሳትፎ ባካተተና የሕዝባችንን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ አግባብ የሚከወን ነው፤›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ መንፈስ በሁለቱ አገሮች መካከል መግባባት እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘም በሁለቱ አገሮች አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የፀጥታና የደኅንነት ችግሮችን በተለይም ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ንግድ፣ ዜጎችን በማገት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ የመቆጣጠርና የዜጎች መብት እንዲከበር ማድረግ እንደሚገባ የመድረኩ ዋነኛ ትኩረት እንደነበረ፣ ችግሮቹንም በዘላቂነት ለመፍታት ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን አመልክተዋል።

የሱዳን ልዑክ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሪፖርት ማቅረቡ ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገው ፖለቲካዊ ውይይት ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል።

የሁለቱ አገሮች አዋሳኝ ድንበር ላይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ከተደረገው ውይይት በተጨማሪ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለመተባበር የተደረገና መግባባት የተገኘበት እንደነበር አመልክተዋል።

‹‹ወይይቱ ስኬታማ እንደነበር በመስማቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ እርግጠኛ ነኝ የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ወዳጅነት በአስቸጋሪ ጊዜም ተጠናክሮ ይቀጥላል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሁለቱ አገሮች ቀጣዩን ዙር ተመሳሳይ ውይይት በመጪው ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. በሱዳን ካርቱም ለማካሄድ ተስማምተዋል። ኢትዮጵያና ሱዳን ረዥም ኪሎ ሜትሮችን የሚያካልል ድንበር የሚዋሰኑ ቢሆንም፣ የድንበራቸው ሕጋዊ ወሰን አልተበጀም።

በድንበር አለመካለል ምክንያት በድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በተደጋጋሚ ከመጋጨታቸውም በላይ፣ ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት በኃይል ወስዳለች ተብሎ ከፍተኛ እሮሮ ይሰማል፡፡ በተለይም የቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የግድያ ሙከራ ከሱዳን በዘለቁ አሸባሪዎች ከተፈጸመ በኋላ፣ በሁለቱ አገሮች ወታደሮች መካከል ግልጽ ውጊያ ከ15 ዓመታት በፊት ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...