Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፅ ከተለወጡ ፖለቲካዊ ሁነቶች ጋር ራሷን አስታርቃ ወደ ትብብር እንድትመጣ ኢትዮጵያ አስታወቀች

ግብፅ ከተለወጡ ፖለቲካዊ ሁነቶች ጋር ራሷን አስታርቃ ወደ ትብብር እንድትመጣ ኢትዮጵያ አስታወቀች

ቀን:

የህዳሴ ግድቡን ለመሙላት የግብፅ ይሁንታ እንደማያስፈልጋት አስታውቃለች

ግብፅ ከአዳዲስ የፖለቲካ ሁነቶች ጋር ራሷን አስታርቃ ከዓባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር በትብብርና የጋራ ጥቅምን በማረጋገጥ መንፈስ እንድትሠራ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ ኢትዮጵያ አሳሰበች።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተፈርሞ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ስቨን የርገንሰን ባለፈው ሳምንት የተላከውን ደብዳቤ ሪፖርተር ያገኘ ሲሆን፣ ደብዳቤው መሸኛ ገጾችን ጨምሮ ዝርዝር ማብራሪያዎች የተካተቱበት ባለ 26 ገጽ ነው።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የመጀመርያ ውኃ ሙሌት በመጪው ሐምሌ ወር ለመጀመር ዝግጅት ማድረጓን በመቃወምና በህዳሴ ግድቡ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት እንቢተኝነት ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን የሚገልጽ አቤቱታ የግብፅ መንግሥት፣ ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በማቅረቡ ነው ኢትዮጵያ ምላሽ ደብዳቤዋን የላከችው።

 በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ተፈርሞ እ.ኤ.አ. ሜይ 1 ቀን 2020 ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የተላከው የግብፅ መንግሥት ደብዳቤ፣ የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቅን በተመለከተ በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመርያ የውኃ ሙሌት በመጪው ሐምሌ ወር ብትጀምር ችግር ሊፈጠር እንደሚችል የሚያስጠነቅቅ ነው።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግብፅ የውኃና የምግብ ደኅንነት ላይ ጉልህ ጉዳት የሚያስከትልና የመቶ ሚሊዮን ግብፃውያን ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ፣ የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያን ውሳኔ በትዕግሥት እንደማያልፈው፣ ነገሩም በአካባቢው ሰላምና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ሊፈጥር እንደሚችል በግብፅ መንግሥት የተላከው ደብዳቤ ያስታውቃል።

በኢትዮጵያ በኩል የተላከው ደብዳቤ ግን ኢትዮጵያ የታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮችን ሥጋት ለማካተት የተጓዘችውን ርቀት የሚያስረዳ፣ እንዲሁም የግብፅ መንግሥት ይኼንን የኢትዮጵያ ጥረት በማደናቀፍ ለዘመናት የቆየውን የዓባይ ውኃን በብቸኝነት የመጠቀም ኢፍትሐዊነት ለማስቀጠል የተከተለውን ስትራቴጂ በአብዛኛው የደብዳቤው አካል ተካቶ ያስረዳል።

በግብፅ በኩል ተደጋግሞ ለተነሳው የግጭት ሥጋት በአንድ መስመር ብቻ የህዳሴ ግድቡ ለአካባቢው አገሮች የግጭት ሥጋትን የሚፈጥር ሳይሆን፣ በሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለአካባቢው የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ያመላክታል። በመደምደሚያው ላይም የግብፅ መንግሥት የተለወጡ ፖሊካዊ ሁነቶችን በማስተዋል ራሱን ከሁኔታዎች ጋር እንዲያስታርቅ የሚያሳስብ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ተመድም ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግብፅ ወደዚህ እንድትመጣ ሊያበረታቱ እንደሚገባ ያሳስባል።

ኢትዮጵያ በላከችው በዚህ ደብዳቤ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህንና ዓለም አቀፍ ሕጎችን አክብራ ግንባታውን እንደምትቀጥል ያስገነዝበች ሲሆን፣ የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌቱንም በዕቅዷ መሠረት በመጪው ሐምሌ እንደምትጀምር አስረግጣ አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ከግብፅና ከሱዳን የተነሳውን ሥጋት ለመቅረፍና መተማመንን ለመፍጠር በራሷ አነሳሽነት ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን መጋበዟን፣ የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ አማካሪ ምክር ቤት እንዲመሠረት ማድረጓን፣ ከሦስቱ አገሮች የተወጣጣ ገለልተኛ የጥናት ባለሙያዎች ኮሚቴ እንዲመሠረት ማድረጓንና በዚህም አማካይነት ሦስቱ አገሮች ያልተግባቡባቸውን የቴክኒክ ጉዳዮች በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት እንዲቻላቸው ጥረት ማድረጓን በደብዳቤው ገልጻለች።

 ከዚህም በተጨማሪ ሦስቱ አገሮች የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የሚመክሩበትንና የሚተባበሩበትን፣ እንዲሁም አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚችሉበትን የስምምነት ማዕቀፍ በአገሮቹ መሪዎች እንዲፀድቅ ሙከራ ማድረጓን ገልጻለች።

ይሁን እንጂ ሁሉም ጥረቶች ወደ ውጤት እንዳያመሩ የግብፅ መንግሥት የተለያዩ እንቅፋቶችንና የማጓተት ሥልቶችን በመከተሉ፣ ስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውሳለች።

በትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ከተዘረዘሩ መመርያዎች መካከል የግድቡ ግንባታ ከቴክኒክ ድርድሩ ጎን ለጎን እንደሚከናወን፣ የቴክኒክ ድርድሩም በ15 ወራት እንደሚጠናቀቅ በግልጽ መጻፉን የሚያስረዳው ኢትዮጵያ የላከችው ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ ስምምነት እንዲደረስና መተማመን ለመፍጠር ባላት ፍላጎት እንጂ፣ በተገለጹት 15 ወራት ስምምነት ባለመደረሱ የትብብር ማዕቀፉ ጊዜው አልፎበታል ብላ ውድቅ ማድረግ ትችል እንደነበር በደብዳቤው ገልጻለች።

 በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሲካሄድ የነበረው ውይይት መንፈሱን በመሳቱ የተቋረጠ ቢሆንም፣ የመጀመሪያውን የግድቡ የውኃ ሙሌት በተመለከተ ከሁለቱ አገሮች ጋር ለመወያየት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሁለቱ አገሮች መሪዎች ከአንድ ወር በፊት ሰነድ ለመላክ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ሁለቱም መሪዎች ጥያቄውን እንዳልተቀበሉ በደብዳቤው አስረድታለች።

የግድቡን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌት በተመለከተ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ሰነድ ሦስቱ አገሮች ላለፋት ዓመታት ሲያካሂዷቸው በነበሩ የቴክኒክ ድርድሮች ያለተቃርኖ ስምምነት የተደረሰባቸው ከመሆኑም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ የምታከናውነው በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆንና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ሕግና መርሆዎችን በመከተል እንደሆነ አስታውቃለች።

‹‹በመሆኑም የህዳሴ ግድቡ የመጀመርያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትን ለማከናወን የግብፅን መንግሥት ይሁንታ የመጠየቅ የሕግ ግዴታ የለብኝም፤›› በማለት አስታውቃለች። በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሲካሄድ በነበረው ድርድር ያልተቋጩ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን የሚገልጸው ይኸው ደብዳቤ፣ ታዛቢዎቹ እ.ኤ.አ. ፌብርዋሪ 13 ቀን 2020 የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት ያቀረቡትን ጥያቄ ኢትዮጵያ የጭብጥም፣ የአካሄድም ጥያቄ በማንሳት እንደማትቀበል ማስታወቋን ይጠቁማል።

 ቀጥሎ በተያዘው ፕሮግራም ላይ ኢትዮጵያ መገኘት እንደማትችል ቀድማ በማሳወቅ ፕሮግራሙ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጥያቄ አቅርባ ሳለ፣ ግብፅና ሱዳን በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ግብፅ በታዛቢዎቹ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ የስምምነት መነሻ ፊርማ መፈረሟን እንደተገነዘበች ገልጻለች።

 ይሁን እንጂ በትብብር መግለጫ ስምምነቱ መሠረት ሁሉም ወገኖች የተስማሙበት ሰነድ ባለመኖሩ፣ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ለመፈረም እንዳልፈለገች ተደርጎ በግብፅ የሚቀርበው ወቀሳ ከእውነት የራቀና አሳሳች መረጃ መሆኑን አስታውቃለች።

በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮች ሦስቱ አገሮች ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የተፈራረሙትን የትብብር ስምምነት የሚጥሱ በርካታ ጉዳዮችን የተስተናገዱበት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል እንደነበረም ገልጻለች።

ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል የማመንጨት አቅምን በከፍተኛ ደረጃ የሚገድብ እንደሆነ፣ የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌት አስተዳደርን የሚያስተጓጉሉ ከተለመዱ መርሆዎች ውጪ የሆኑ መመርያዎች የተቀረፁበት መሆኑ፣ ከህዳሴ ግድቡ ውጪ በመጓዝ በአጠቃላይ በላይኛው የኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስ ላይ ምንም ዓይነት የልማት ተግባራት እንዳይከናወን የሚገድብ፣ የአሁኑንና የወደፊቱን የኢትዮጵያ ትውልዶችን ጥቅም የሚነፍግና ኢትዮጵያ በግዛቷ የገነባቸውን ግድብ ለማስተዳደር ያላትን ሉዓላዊ መብት የሚገፋ መሆኑ፣ እንዲሁም ሌሎቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን ያገለለ የውኃ ክፍፍል እንዲደረግ የሚጠይቅ በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ለተመድ የጻፈችው ደብዳቤ ያመለክታል።

 ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷና በሕዝቦቿ መዋጮ የምትገነባውን የህዳሴ ግድብ ውኃ በፈለገችው ጊዜ የመሙላት ሙሉ የሆነ ሕጋዊ መብት እንዳላት በድጋሚ የሚያስገነዝበው ይኸው ደብዳቤ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ተመድ ግብፅ የምታራምደውን ታሪካዊ የውኃ ተጠቃሚነት የማስጠበቅ አቋም እንድትጥል ሊመክር እንደሚገባ፣ መፍትሔውም ውይይት ብቻ እንደሆነ እንዲያሳስብ፣ እንዲሁም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የፈረሙትን የዓባይ ውኃ የትብብር ማዕቀፍ ግብፅ ፈርማ ሁሉም አገሮች የሚተባበሩበት የተፋሰስ ሥርዓት እንዲፈጠር ጥረት እንዲደረግ አሳስባለች።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...