Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች በሚወጣ የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ጣለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግለሰቦችና ኩባንያዎች ከባንኮች ሊያወጡ የሚችሉትን የጥሬ ገንዘብ መጠን የሚገድብ መመርያ ከማክሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ መተግበር መጀመሩን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡ ከተቀመጠው የገንዘብ ገደብ በላይ የከፈለ ማንኛውም ባንክ የከፈለውን 25 በመቶ እንደሚቀጣም ታውቋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) መመርያውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ከዚህ በኋላ ማንኛውም ግለሰብ ከባንክ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚችለው በቀን 200 ሺሕ ብር ወይም በወር አንድ ሚሊዮን ብር ይሆናል፡፡

ኩባንያዎች ደግሞ በጥሬ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት የሚችሉት የገንዘብ መጠን በቀን 300 ሺሕ ብር ወይም በወር 2.5 ሚሊዮን ብር መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት ግለሰቦችና ድርጅቶች በቀንና በወር በጥሬ ገንዘብ በመመርያው ከተጠቀሰው በላይ የገንዘብ መጠን ማውጣትና ግብይት መፈጸም ከፈለጉ ግን ከአካውንት ወደ አካውንት ማዘዋወር፣ ወይም በቼክና በሲፒኦ መጠቀም እንደሚኖርባቸው ይናገር (ዶ/ር)  አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ያለውን ውሳኔ ለመወሰንና ለመተግበር የተፈለገባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች በሰፊው ያብራሩት ይናገር (ዶ/ር)  እንደ ምክንያት ከጠቀሷቸው ውስጥ  በኢትዮጵያ ያለ ገደብ ገንዘብ ማውጣት የሚቻል መሆኑን በመገንዘብ የተለያዩ ወንጀሎች እየተፈጸሙ መሆናቸው አንደኛው ነው ብለዋል፡፡ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታትም የዚህ መመርያ አስፈላጊነት ታምኖ ሊተገበር መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹በርካታ የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮች በተለያዩ ጊዜያት በመታየታቸው፣ እንዲሁም ገደብ በሌለው ሁኔታ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት አደጋው የከፋ መሆኑን በቅርቡ የተፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች በምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤›› ያሉት ገዥው፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 60 ሚሊዮን ብር ለማውጣት ተደረገ የተባለውን ሙከራ አስታውሰዋል፡፡

የመረጃና የደኅንነት ሰዎች ተከታትለው ጉዳዩን ባይደረሱበት ኖሮ፣ 60 ሚሊዮን ብር እንዳይወጣ የሚያግድ የሕግ ክልከላ አልነበረም ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በአንድ የዳያስፖራ አካውንት ላይ ከነበረ 365 ሚሊዮን ብር ውስጥ 55 ሚሊዮን ብር ለማውጣት መሞከሩን በማስታወስ፣ በኢትዮጵያ ያለ ገደብ ገንዘብ ማውጣት ስለሚቻል ሰዎችን ለማጭበርበርና ለመዝረፍ በር ከፍቷል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ያለ ገደብ በጥሬ ገንዘብ እንዲወጣ ሲሠራበት የነበረው አሠራር ለሕገወጥ ተግባራት ተጋላጭ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በጥሬ ገንዘብ ከባንክ የሚከፈል ገንዘብ በአብዛኛው የዓለም ክፍል የሚሠራበት መሆኑን ገልጸው፣ ይህ መመርያ የወጣው የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮ በማየት ጭምር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በጥሬ ገንዘብ ከባንክ የሚወጣን የገንዘብ መጠን መገደብና በሌሎች ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን መፈጸሚያዎች ገንዘብ ማንቀሳቀስ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፣ ይህም በባንኮች ማኅበር አማካይነት በቀረበ ጥያቄ መሠረት የተወሰደ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ለመመርያው መውጣት ምክንያት ናቸው የተባሉ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችንም በዝርዝር አመላክተዋል፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ባንኮች የሚወጣው ገንዘብ ገደብ ስለሌለው የፈለገ ሰው 50 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ አውጥቶ በኬሻ ይዞ መሄድ ይችላል፤›› ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ እስካሁን ያለው አሠራር ገደብ የሌለው ሆኖ በመቆየቱና ይህንን ለመገደብ ይቻል ዘንድ የወጣው መመርያው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡  

መመርያው እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተጨማሪ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ አንድ ግለሰብ አሥር ሚሊዮን ብር ቢፈልግ መመርያው የሚፈቅድለት ሁለት መቶ ሺሕ ብር ስለሆነ ይህንን በጥሬ ገንዘብ መውሰድ ይችላል ብለዋል፡፡

የመመርያው መውጣት ሕገወጥነትን ለመከላከል መሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስገነዘቡት ገዥው፣ ከዚህ ጎን ለጎን ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን እያጎለበቱ ለመሄድ ጭምር እንደሚያግዝ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በመመርያው የተቀመጡትን ሕግጋቶች መተግበር ግዴታ መሆኑን፣ ግዴታን ያለመወጣት ደግሞ የሚያስቀጣ እንደሆነ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከመመርያው ውጪ አንድ ባንክ ከተፈቀደው ገንዘብ በላይ ከከፈለ ከተቀመጠው ገደብ በላይ ባለው የገንዘብ መጠን ልክ ተሠልቶ 25 በመቶ እንደሚቀጣ፣ እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም ከገደቡ በላይ  አሥር ሚሊዮን ብር የከፈለ ባንክ ቢገኝ ቅጣቱ 2.5 ሚሊዮን ብር ይሆናል በማለት ነበር፡፡

ከብሔራዊ ባንክ ገዥው ገለጻ መገንዘብ እንደተቻለው በመመርያው ያልተሸፈኑ አዳዲስ ችግሮች፣ ወይም መመርያውን ለመፈጸም የሚያስቸግር ነባራዊ ሁኔታዎች ካጋጠሙ ግን፣ በልዩ ሁኔታ ገንዘብ ለማውጣት የሚፈቀድበት አሠራር በመመርያው መካተቱ ነው፡፡ ይህንን በልዩ ሁኔታ የሚፈቀድ ወጪን የባንኮች ፕሬዚዳንቶች እንዲያስፈጽሙ ሥልጣን እንደተሰጣቸው ይናገር (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች