የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በእግር ኳስ ልማት ወደ ኋላ ለቀሩ አገሮች ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ አባል አገሮች በሚያቀርቡት ምክረ ሐሳብ መነሻ ታዳጊ ወጣቶች የሚፈሩባቸው የማዕከላት ግንባታ ያከናውናል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነውና በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ የሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ አካዴሚ ይጠቀሳል፡፡
የአካዴሚው የግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ በካፍ ወጪ የተሸፈነ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ አሁንም ድረስ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም፡፡ የፕሮጀክቱ ጥንስስ የተጀመረው በቀድሞው የባህልና ስፖርት ምክትል ሚኒስትር አቶ መላኩ ጴጥሮስ ጊዜ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ ክፍተት በዋናነት የሚጠቀሰው መንግሥት የካቢኔ ለውጥ ባደረገ ቁጥር የስፖርቱ ዘርፍ አንዴ ከወጣት ሌላ ጊዜ ደግሞ ራሱን ችሎ ኮሚሽን እየሆነ የተረጋጋና ራሱን የቻለ የተጠሪነት ወሰን ማጣቱ እንደነዚህ ለመሰሉ ፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት ሆኖ መቆየቱ የሚናገሩ አሉ፡፡
እንዲህም ሆኖ ከ12 ዓመት በፊት ግንባታውን አንድ ብሎ የጀመረው ይህ አካዴሚ፣ የግንባታውን ጨረታ ያሸነፈው ግብፃዊ ተቋራጭ ከግንባታ ጥራት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በመሀል እንዲያቋርጥ ተደርጎ መቆየቱ የቀድሞ የፌዴሬሽኑ አመራር ይናገራሉ፡፡
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዛሬ ላይ የደረሰው ይህ ፕሮጀክት፣ በእነ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ የአመራርነት ዘመን የተቋራጭ ለውጥ አድርጎ አካዴሚውን ለማጠናቀቅና ወደ ሥራ ለማስገባት የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም፣ ሳይሳካለት ወደ አቶ ጁነዲን ባሻህ አመራር መሸጋገሩ አይዘነጋም፡፡ በመሀል እንዴትና ማን እንደሚስተዳድረው በውል ሳይታወቅ ቆይቶ ከወራት በፊት አዲሱ የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር በተገኙበት ካፍ አካዴሚውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማስረከቡ ይታወሳል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም የካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ተድላ ዳኛቸው (ዶ/ር) የአካዴሚው ዳይሬክተርነትን እንደያዙ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ይህን አካዴሚ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በባለቤትነት እንዲያስተዳድረው የይዞታ ማረጋገጫ እንዳልተሰጠው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፌዴሬሽኑ አመራር ይገልጻሉ፡፡ በዚያ ላይ ስፖርት ኮሚሽኑ 1.2 ሚሊዮን ብር በመመደብ ተጨማሪ ዕድሳት ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ አመራሩ ያስረዳሉ፡፡
አካዴሚው 42 የመኝታ ክፍሎችን ጨምሮ፣ አንድ ያለቀለት የእግር ኳስ ሜዳ፣ ሁለተኛውን ሜዳ ደግሞ በሒደት መገንባት የሚያስችል ቦታ የያዘ ሲሆን፣ የተለያዩ ጅምናዚየሞች፣ የምግብ አዳራሾች፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖችና ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶችና መቀየሪያ ክፍሎች እንዲሁም አንድ ዘመናዊ አካዴሚ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ሁሉ የያዘ ስለመሆኑ ጭምር ኃላፊው ይናገራሉ፡፡