በሔለን ተስፋዬ
ከተለያዩ የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከላትና የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ 2,754 አረጋውያንን በጋራ የማንሳት ሥራ ጀምረዋል፡፡
ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ከ286 በላይ ኑሮአቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ አረጋውያን ወደ ክብር የአረጋውያን መርጃ ማዕከል በማንሳት ሥራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬተሪ አስታውቋል፡፡
በሜቄዶኒያና በመቅድም ኢትዮጵያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከላት በተከታታይ ቀናት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ አረጋውያንን ከጎዳና ለማንሳት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተገልጿል፡፡
አረጋውያኑን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ወደ ማዕከላቱ ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንደተደረገላቸው የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተክሌ ደሬሳ ተናግረዋል፡፡
ከ200 በላይ አረጋውያን በመንከባከብ ላይ የሚገኘው ክብር አረጋውያን መርጃ ማዕከል ባለፉት አሥር ዓመታት አረጋውያንን ከጎዳና በማንሳትና በመንከባከብ ላይ እንደሚገኙ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ወርቅነሽ ሙንኤ ተናግረዋል፡፡