Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየሕገ መንግሥት ትርጓሜ ሙያዊ ምልከታ

የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ሙያዊ ምልከታ

ቀን:

በይብዛ ዓይነኩሉ ተስፋዬ

ለኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በሚመለከት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ፣ ጉባዔው በሕግ ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጥ ባቀረበው ጥሪ መሠረት የተሰጠ ሙያዊ አስተያየት ነው፡፡

ጉባዔው ግንቦት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ባቀረበው ጥሪ እንደገለጸው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሙያ አስተያየት እንዲሰጥበት የቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹. . .የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችና ምርጫ በሚደረጉበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰትና በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን፣ የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመን ምን ይሆናል? ምርጫውስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል?›› የሚል ነው፡፡

- Advertisement -

በመሠረታዊ የሕግ መርህ መሠረት አንድ የሕግ አንቀጽ ወይም ክፍል ግልጽ ባለመሆኑ ምክንያት ለትርጉም የተጋለጠ በሚሆንበት ጊዜ፣ በዘርፉ ምሁራን ተቀባይነትን ያገኙ ትርጉም የሚሰጥባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ አሁን በቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጉም ላይም ምንም እንኳን የተለያዩ ሥነ ሐሳባዊ ሥልቶችን ለማቅረብ የሚቻል ቢሆንም፣ ተገቢነት የሚኖረውና ሚዛን የሚደፋው ግን ሕገ መንግሥቱ ከራሱ ውስጥ  ራሱን በራሱ በመተርጎም ትርጓሜውን ሕይወት የሚዘራበት ሲሆን ነው፡፡ ይህም ማለት ለትርጉም ፍለጋ የተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ፍልስፍናዎችን ወይም የተለያዩ አገሮችን ልምዶች ለማሰናሰል ከመድከም በፊት፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተነሳውን ችግር የሚፈታ ድንጋጌ መኖሩን ወይም ፈጽሞ አለመኖሩን በመፈተሽ ላይ በማተኮር ሊታይ ይገባዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ከላይ ለተነሳው የትርጉም ጥያቄ ሕገ መንግሥቱ በራሱ ሊፈታው የሚችልበት በቂ ድንጋጌ ያለው መሆኑን በመግለጽ በተከታዩ ሁኔታ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡

ዝርዝር አስተያየት

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለመታወጅ ለሕዝብ ውይይት ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ወቅቶች የሚነሱ ክርክሮች አንዳንድ ጊዜ እንደ ችግር መንስዔ፣ ሌላ ጊዜ ለችግር መፍትሔ እየሆነ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ የአንድ አገር ሕገ መንግሥት የተጻፈ ወይም ያልተጻፈ ሊሆን የሚችል ቢሆንም፣ በአንድ አገር ውስጥ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው የሚለው ሐሳብ በአብዛኛው ስምምነት ያገኘ ሐሳብ ነው፡፡ በአገራችንም አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ መሆኑን ራሱ ደንግጎ ይገኛል፡፡  ሕገ መንግሥት በዋናነት መንግሥት የሚባለውን የሕዝብ ወኪል  ሥልጣኑንና ኃላፊነቱን የሚወስን በገዥ (መሪ) እና በተገዥ (ተመሪ) መካከል ያለውን ግንኙነት የሚወስን ሰነድ ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት ምንም እንኳን የተደራጀና የሚያዘው ኃይል ቢኖረውም፣ እንደ ፈለገ እንዳይፈነጭ ገድቦ የሚይዘው ልጓም ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ሕዝቦችም ካላቸው ያልተገደበ ነፃነት ቀንሰው መብታቸውንም አሳልፈው የሚሰጡበት የውል ሰነዳቸው ጭምር ነው፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት የመንግሥት የሥልጣን ዘመን ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የአስፈጻሚው የሥልጣን ዘመን ክልሎችን ጨምሮ በአምስት አመታት የተገደበ ነው፡፡ ሥልጣን የያዘው መንግሥትም የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ አንድ ወር አስቀድሞ ሕዝቦች ምርጫ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና ምርጫውን የማጠናቀቅ ኃላፊነት በሕገ መንግሥቱ ተጥሎበታል፡፡ በተለያዩ አገሮች ሕገ መንግሥቶች ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ይህንን ኃላፊነት ለማከናወን የማይችልበት ሁኔታ ከገጠመው መፍትሔው ምን መሆን እንዳለበት በግልጽ የሚያስቀምጥ የመኖሩን ያህል፣ ችግር አይገጥምም ከሚል ዕሳቤ ወይም ሆነ ተብሎ ያለ መፍትሔ የሚተው የሕገ መንግሥት አይነቶችም አሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን በምርጫ ብቻ እንደሚያዝ ቢደነግግም፣ ምርጫ ያለማካሄድ ችግር ቢገጥምስ የሚለውን ታሳቢ አድርጎ ቀጥተኛ መፍትሔ አላስቀመጠም፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ለተፈጠረው አጣብቂኝ ብቸኛ መፍትሔ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልግበት ምክንያትም ሕገ መንግሥቱ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ጊዜው ከማለቁ በፊት አንድ ወር ቀደም ብሎ ምርጫ አድርጎ የማጠናቀቅ ኃላፊነትን የሚጥልበት ቢሆንም፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ይህን ማድረግ ካልቻለ በቀጣይ ሊከተለው የሚገባው መፍትሔ ምን እንደሆነ ባለመደንገጉ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ደግሞ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ በመሆኑ በዚሁ ሒደት ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ይሆናል፡፡

በሕግ መርህ መሠረት ማንኛውም ሕግ (ሕገ መንግሥትን ጨምሮ) ግልጽ የሆኑ አንቀጾች የያዘ ከሆነ፣ ምንም እንኳን ለአንድ ወገን የማይመችና የሚጎዳ ቢሆንም ሊተረጎሙ አይገባም፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምርጫ የማካሄድ ኃላፊነቱን ባይወጣም የሥልጣን ዘመኑ በአምስት ዓመት የተገደበ ነው፡፡ በመሆኑም የአምስት ዓመት የሥልጣን ገደቡ ግልጽ በመሆኑ፣ ምክንያት በመደርደር ወይም የተለያዩ አገሮችን ልምድ በማጣቀስ ለመተርጎም አይቻልም፡፡

ይህ ምርጫ የማድረግ የአምስት ዓመት የጊዜ ገደብ በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት የተሰጠው ግዴታ ‹በማናቸውም ሁኔታ› ውስጥ ቢገኝም እንኳን ሳይሆን ሕዝብ ለመምረጥ በሚችልበት፣ ተመራጭ ሊወዳደር በሚችልበትና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ለምርጫው አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ ለመከወን በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በዚህ “ኖርማል” ሁኔታ ውስጥ የምርጫ ሕግ የማውጣትና የማስፈጸም ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ለመሆኑ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ምርጫን የማድረግ ሥልጣን የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት ሲሆን፣ ለዚህም አስፈጻሚ የሚሆን አካል በሕገ መንግሥቱ ተቋቁሟል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምርጫን በማናቸውም ጊዜ የማካሄድ መብት ያለውና ለዚህም ሕግ የማውጣት ሥልጣን ያለው ቢሆንም፣ ሥልጣኑ ከማብቃቱ አንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ አድርጎ የማጠናቀቅ ግዴታ ግን አለበት፡፡

መንግሥት ይህንን ለማስፈጸም የማያስችለው ተቀባይነት ያለው ሁኔታ ወይም ችግር ቢገጥመው ለምሳሌ መንግሥት በሥልጣን ዘመኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጅ ስለሚችል፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከላይ የተገለጸውን ግዴታ ጭምር የሚገድብ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ሲገጥም ምን ማድረግ እንዳለበት የሚደነግግ የሕገ መንግሥት መልስ የለውም፡፡ በሌላ አነጋገር በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምርጫ ሳያደርግ የሥልጣን ዘመኑ ቢያበቃ ማን ምን ሥልጣን አለው? ምርጫ እንዴት ይከናወናል? ማን ያከናውናል? ሥልጣን ይዞ የቆየው መንግሥት ምን ማድረግ ይችላል? የሚሉትን ሥልጣንን የሚመለከቱ (Powers and Functions) ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ ለማንም የተሰጡ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ጥያቄው የፌዴራል መንግሥት ምን ሥልጣን አለው? ክልሎችስ በዚህ ጉዳይ ምን ሥልጣን አላቸው የሚል ይሆናል ማለት ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን በፌዴራልና በክልሎች የተከፋፈለ ነው፡፡ ምርጫን በሚመለከት የምርጫ ሕግን የማውጣትና ምርጫን አከናውኖ ማጠናቀቅ ለፌዴራል መንግሥቱ የተሰጠ ሥልጣን መሆኑን ቀደም ብለን ዓይተናል፡፡ ስለዚህም ክልሎች እኛ የምርጫ ሕግ እናውጣና እናስፈጽም ለማለት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን አልተሰጣቸውም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ማን ምን ማከናወን እንዳለበት በማይደነግግበት ጊዜ ወይም ሥልጣን ለአንድ አካል ያልተሰጠ በሆነበት ጊዜ፣ ሥልጣን ወደ ፌዴሬሽኑ አባላት  ይሻገራል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(1)፣ “በግልጽ ለፌዴራሉ መንግሥት ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን ይሆናል” በማለት ደንግጓል፡፡ ስለሆነም ምርጫ ሳይደረግ የሥልጣን ዘመንን የማራዘም ወይም ሌላ መፍትሔ የመፈለግ ሥልጣን፣ የፌዴራል መንግሥቱ ሳይሆን የክልሎች ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በማንኛውም ሁኔታ ምርጫ ለማድረግ ካልተቻለ፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምን ይሆናል ለሚለው ምላሽ ለመስጠት የሚችሉት ክልሎች ናቸው፡፡

በሕገ መንግሥቱ የፌዴሬሽኑ አባላት ዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ሲሆኑ፣ በእያንዳንዱ ክልል ከፍተኛው የሥልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፡፡ የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ባለመካሄዱ ምክንያት ሥልጣን ለመረከብ የተወከለ ሕጋዊ መንግሥት ባልተፈጠረበትና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሕጋዊ ሥልጣኑ በሚያበቃበት ወቅት ምን መሆን አለበት ለሚለው ክልሎች የየራሳቸውን መፍትሔዎች ሊያስቀምጡ ይገባል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሎች ተወያይተው ሊወስኗቸው የሚገቡ ነጥቦችን ለይቶ ከዚህ የሕገ መንግስት ትርጓሜ ጋር ሊያካትታቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣

  •  ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ምርጫ ባለመካሄዱ ሥልጣን የሚረከብ መንግሥት በምርጫ እስኪመጣ አሁን ያለው መንግሥት በሥልጣኑ ይቀጥል ወይስ አይቀጥል?
  • የሚቀጥል ከሆነስ በሕግ ከተሰጠው ሙሉ ሥልጣን ጋር ይቀጥል ወይስ በተገደበ ስልጣን?
  • ቀጣይ ምርጫ መቼ ይደረግ? የፌዴራል መንግሥቱ ይወስን ወይስ ክልሎች ምርጫን ያስተጓጎለው ችግር ሲቃለል ይወስኑ?. . . እና የመሳሰሉ ለውሳኔ አመቺ የሆኑ፣ ዝግ አማራጮችን በማቅረብ እንዲወስኑና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ እንዲያሳውቁ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱም ይህንን ለማድረግ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የብዙ ክልሎችና የፌዴራል በመሆኑ፣ እንዲሁም ምክር ቤቱ እንዲህ ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰጠው የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚፈጸምበትን ሥነ ሥርዓትም አብሮ ሊያካትት ይገባል፡፡

ለምሳሌ፣

  • ክልሎች በምን ያህል ጊዜ ውሳኔያቸውን ማሳወቅ እንደሚገባቸው፣
  • ከሁሉም ክልሎች የተሰጡ ውሳኔዎች በድምፅ ስለሚወሰንበት ቁጥር ማለትም ክልሎች ውሳኔያቸው የተለያየ ቢሆን አብላጫ ክልሎች የወሰኑት ተፈጻሚ መሆን ስለሚገባው፣ በምን ያህል ድምፅ (Simple Majority, Absolute Majority Two-third Majority) የመሳሰሉትን አስቀድሞ መወሰን ይገባዋል፡፡

ክልሎች በሚሰጡት ውሳኔ መሰረትና በሚወስኑት ሁኔታ ውስጥ ቀጣይ ምርጫን ለማካሄድ ከተወሰነ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የሚኖረው የፌዴራል መንግሥቱን የያዘው አካል ስለሚሆን፣ ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜ ወይም ሁኔታ በመወሰን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለፌዴራል መንግሥቱ ሊያስተላልፈውና በዚያው አግባብ ሊፈጸም ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...