Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአቶ በረከት ‹‹እኛን ነው ማየት››

አቶ በረከት ‹‹እኛን ነው ማየት››

ቀን:

በአበራ ሳህሌ 

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት አቶ በረከት ስምዖን በተከሰሱበት ጥረት ኮርፖሬሽንን የማስመዝበር ወንጀል፣ ጥፋተኛ በማለት የስድስት ዓመት እስራትና የአሥር ሺሕ ብር መቀጫ ጥሎባቸዋል። ባልደረባቸው አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ደግሞ ስምንት ዓመትና 15 ሺሕ ብር ተቀጥተዋል። ታደሰ በመሀል አገር ይህን ያህል ባይታወቁም በክልሉ ውስጥ በበጎ የሚነሱ አይደሉም። አቶ በረከት ግን በመላው አገሪቱ ከመከበር መፈራትን ያተረፉ፣ እንዲሁም በኢሕአዴግ ዘመን በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የቀኝ እጅ ሆነው በታሪክ ያልፋሉ።

አቶ በረከት በቁጥጥር ሥር የዋሉበት አንድ ዓመት ከሦስት ወራት የሚያህል ጊዜና ሌሎች ወደፊት አስተያየት ሊያሰጡ የሚችሉ ጉዳዮች ተቀናንሰው፣ በማረሚያ ቤት ከሦስት ዓመታት በላይ የሚቆዩ አይመስልም። ጠበቃቸው ደግሞ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል። ከጤና ጋር ተያይዞ አለብኝ ከሚሉት ችግር አንፃር 60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሰውን እስር ላይ ማቆየት ጫናው ቀላል አይደለም። እንዲያም ሆኖ ግን በሰበብ አስባቡ በሚሰጠውም ምሕረት የቅጣት ጊዜያቸውን ሳይፈጽሙ እንደሚለቀቁ ግምት መውሰድ ይቻላል። 

በጉብዝናቸው ወራት አቶ በረከት አገሪቱ ውስጥ ያልመሩት ተቋም አልነበረም። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸው ሕግ ያስወጣሉ። በተለያየ ሁኔታ በሚመሯቸው መሥሪያ ቤቶች አማካይነት ሕጉን ያስፈጽማሉ። የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትርየሬዲዮና ቴሌቪዥን ቦርድ ሰብሳቢ፣ የንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር፣ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር አማካሪ፣ አሁን የተከሰሱበት የጥረት ቦርድ ሰብሳቢ ሌሎችም ያልጠቀስናቸው እንዳሉ በማመን. . .

ለአቶ በረከት ውድቀቱ የሚጀምረው ገና በተያዙበት በጥር 2011 ዓ.ም. ነው። የአመራር ለውጥ እንደተደረገ ወደ ወህኒ መጎተታቸው ለሃያ ምናምን ዓመታት ሲሰበክ የቆየው፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት›› ስንዝር እንዳልተራመደ ማሳያ ነው። አንዴአብዮታዊሌላ ጊዜ ደግሞልማታዊበሚል ስም የሚቆላመጠው ዴሞክራሲ ከሩብ ክፍለ ዘመንም በኋላ ተቋም መገንባት ባለመቻሉ፣ ሥልጣን ከእጅ ሲወጣ የቀድሞ ሹማምንት ዕጣ በተረኞች መልካም ፈቃድ ይወሰናል። 

የተቋም ነገር ሲነሳ አንድ የሚታወስ ጉዳይ አለ። የአቶ በረከት አለቃ ቀድመው ጥያቄ ሳይሰጡ ቃለ መጠይቅ ከተደረጉባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች አንዱ፣ በሰኔ 1997 ዓ.ም. ስቴፈን ሳከር ከተባለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉት አንዱ ነው። በወቅቱ አገሪቱ የምርጫ ጦስ ቀውስ ውስጥ ገብታ መንግሥት ተቃዋሚዎችንየጥፋት ኃይሎች”፣ በኋላም አዲስ አበባ ውስጥ የነበረውን የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብን ባስደነገጠ ሁኔታኢንትራሃምዌየሚል ጭቃ የሚለጥፍበት ወቅት ነበር።

ከሃርድ ቶክ አዘጋጅ ጋር ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስት አገሪቱ የዘር ፍጅት አፋፍ ላይ መሆኗን፣ የዓለም ፍፃሜ እየቀረበ በሚመስል ሁኔታ አስከፊ ቃላትን እየተጠቀሙ ድርጅታቸው አገሪቱን ከእዚያ ሁሉ ጥፋት ለመታደግ ቀን ከሌት እየሠራ እንቅልፍ ማጣቱን፣ አሁን ደግሞ ተቃዋሚዎቹ እንዳስቸገሩት ሳይታክቱ አስረዱ። ጋዜጠኛው ታዲያ ሥልጣን ከያዙ 14 ዓመት እንዳስቆጠሩ አስታውሶ፣ ከእዚያ ሁሉ ጊዜ በኋላ አገሪቱ አደጋ ውስጥ ካለች ጥፋቱ የማነው? የታለ የገነባችሁት ተቋም ብሎ አፋጠጣቸው።አሁንም ከደኑ አልወጣንምነበር መልሱ። 27 ዓመታት በኋላም ያው ነው።

የፖለቲካ ቁማር

አቶ በረከት ፍርድ ቤት በቀረቡ ሰሞን ‹‹እየተሠራብኝ ያለው የፖለቲካ ቁማር እንጂ ሕጋዊ የሆነ የፍርድ ሒደት አይደለም፤›› ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል። የጉዳዩ ቁማርነት ለጊዜው ይቆየንና በእርግጠኛነት መናገር የምንችለው ግን የተከሰሱበት ወንጀል በትክክል መሬት ላይ ባለ፣ አመሠራረቱ ብዙ ከዘረፋ ያልራቀ ጥረት ከተባለ ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ ነው። አቶ በረከት በከሳሾች ጫማ በነበሩበት ወቅት በፈጠራ ክስ የተካኑ ነበሩ። ከዓመታት በፊት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዋል በሚል እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞንና ሌሎች ከደርዘን በላይ ዜጎችን ወህኒ ወርውረዋል።

ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ልብ አንጠልጥል ታሪክ ስንጠብቅ፣ ሳምንት ሳይቆዩ ክሱን የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የግድያ ሙከራ ማድረግ በሚል ቀየሩት። የጠየቀም አልነበረም። አሳዛኙ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ ጽጌ ሀብተ ማርያም የተባሉ 80 ዓመት አዛውንት ይገኙበት ነበር። እኚህ ሰው የተያዙት እውነት ባለሥልጣን ሊገድሉ ሲያነጣጥሩ ይሁን ወይም የግንቦት ሰባት አመራር አባል የአቶ አንዳርጋቸው አባት የመሆን ክፉ ዕጣ ደርሷቸውእነ በረከት ብቻ ያውቃሉ። 

በክስ ሒደቱ ውስጥ የታየው በፕላዝማ ቴሌቪዥን ጠበቃ ይቁምልኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኢንተርኔት ይግባልኝ ዓይነት ስሞታቸው ከክሳቸው ጭብጥ በላይ ቀልብ ስቧል። እንኳን እስር ቤት በመሀል ከተማው አይደለም ኢንተርኔት፣ መብራትና ውኃ በሚጠፋበት አገር ያንን ሮሮ ማቅረባቸው ቀልድ ይመስላል። በክልሉ የሕግ የበላይነት እየታየ ባለመሆኑ፣ ክሱ ወደ አዲስ አበባ ይዛወርልን የሚልም ጥያቄ አቅርበዋል። አቶ በረከት በሚያሳስሯቸው ላይ እንደ ግል ንብረታቸው በሚቆጥሩት ቴሌቪዥንየፍየል ወጠጤዓይነት ዘገባ ያሠሩ ነበር። ከእነዚህ ተከታታይ ፊልሞች አንዱ የነበረውአኬልዳማ18 ዓመት በታች ያሉ ሊያዩት የማይመከር የሚል ቀልድ ነበረበት። ፓርላማ ውስጥ ዘገባው የተጠርጣሪዎችን ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት ይጋፋል የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው፣ በተቃራኒው ከሕዝቡ ጥሩ ምላሽ እያገኙ እንደሆነ ይናገሩ ነበር።  

እርግጥ ነው በተራቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ዕቅፍ አበባ ይዞ የጠበቃቸው አልነበረም። አኬልዳማን ዓይነት ዘገባ ባይሠራባቸውም ፍርድ ቤት ዙሪያ ተኮልኩሎዓይተ በረከትእያለ የሚያንጓጥጣቸው ሕዝብ የሚፈጥረው ድባብ፣ የፍርዱን ሁኔታ የተበላ ዕቁብ ያስመስለዋል። ከእዚያም ቀደም ብሎ እሳቸው ታይተውበታል በሚል በእርጋታዋ በምትታወቀው ደብረ ማርቆስ ቱሪስት ሆቴል የደረሰው ውድመት፣ ከግድያ ሙከራ የሚተናነስ አይደለም።

በእንደዚያ ዓይነት ሁኔታ በሚሰየም ችሎት ፍትሕ ማግኘት ይከብዳል። ዳኞች ከሕዝቡ የሚፈልቁ ናቸው። የሕዝብ አስተያየት አመለካከታቸውን አይጫነውም ብሎ በሙሉ ልብ መናገር ያስቸግራል። አቶ በረከት ከውሳኔው ጋር ያለ መስማማት መብት አላቸው፡፡ ለዚህም ነው ይግባኝ እንደሚጠይቁ የሚነገረው። የተዳኙት ግን19 ዓመቱ ጀምሮእንዲቋቋም በደከሙለት የሕግ ሥርዓት ነው። ብዙዎች ለዚህ አልታደሉም።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...