Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች የወለድ ቅናሽ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል 

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው የቢዝነስ ዘርፎች ሦስት ባንኮች ለተበዳሪዎቻቸው የወለድ ቅናሽን ጨምሮ ሌሎች የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያዎች ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ማሻሻያዎች ማድረጋቸውን ያሳወቁት ንብ ኢንተርናሽናል፣ ቡና ኢንተርናሽናልና ደቡብ ግሎባል ባንኮች ናቸው፡፡ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በቫይረሱ ተፅዕኖ ከፍተኛ  ተጎጂ ዘርፎች የባንኩ አመራር ቦርድና ሥራ አስፈጻሚው ባደረጉት ስብሰባ፣ ለሆቴልና ቱሪዝም፣ ለአስጎብኚ ድርጅቶች፣ ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ተበዳሪዎች ከግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሚታሰብና ለሦስት ወራት የሚቆይ የወለድ ቅናሽ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ካደረገው እስከ 4.5 በመቶ የሚደርስ የወለድ ቅናሽ በተጨማሪ፣ ለሆቴልና ቱሪዝም የሦስት በመቶ ቅናሽ ማድረጉን ባንኩ ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የአትክልት፣ የአበባና ፍራፍሬ ኢንቨስትመንቶችን በተመለከተ፣ ባንኩ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን የትርፍ ህዳግ በመተው የወለድ ተመኑ ላይ ቅናሽ አድርጓል፡፡ በዚህም በመደበኛ ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚታሰበውን የሰባት በመቶ ወለድ ብቻ ለማስከፈል እንደወሰነም ንብ ባንክ አስታውቋል፡፡

ወረርሽኙ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ የሆቴልና ቱሪዝም ብድር ላይ የወለድ ቅናሽ ማድረጉን ያስታወሱት የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ፣ ለነዚህ ዘርፎች የ4.5 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ተጨማሪ የሦስት በመቶ ቅናሽ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ለአስጎብኚ ድርጅቶችም የሦስት በመቶ የብድር ወለድ ቅናሽ እንደተደረገ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ ንብ ባንክ የብድር መክፈያ የዕፎይታ ጊዜን ለሦስት ወራት እንዳራዘመ ተገልጿል፡፡

ለባንክ መተማመኛ ሰነድ (L/C) ማራዘሚያ የሚከፈለውን ኮሚሽን አስቀርቷል፡፡ እንዲሁም በቀጥታ ገንዘብ ክፍያ አማካይነት ዕቃ የሚያስገቡ ደንበኞች ይከፍሉ የነበረውን የአገልግሎት ክፍያ ማራዘሚያ በ50 በመቶ እንደቀነሰው ንብ ባንክ አስታውቋል፡፡ ከዚሁ ጎን፣ ሕመም ያለባቸው ሠራተኞች የሚሠሩበት ክፍል መጨናነቅ ያለበትና በዕድሜ የገፉ ሠራተኞች በቅድሚያ ፈቃድ እንዲወጡና ሌሎች ሠራተኞችም በፈረቃ እንዲሠሩ በማድረግ፣ የባንኩ ሠራተኞች በቫይረሱ ምክንያት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የሁለት ወራት የብድር ክፍያ እንዲራዘምላቸው ስለመወሰኑም ታውቋል፡፡

የንብ ባንክ ፕሬዚዳንት እንደገለጹት፣ ባንኩ ድጋፎችን ለማድረግ በወሰዳቸው ዕርምጃዎች ገቢዎቹን ለመተው ተገዷል፡፡ በተለይ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ላይ በድምሩ የ7.5 በመቶ ወለድ ቅናሽ በማድረግ ከዚህ ዘርፍ ምንም ዓይነት ትርፍ ከማግኘት መታቀቡን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በበኩሉ ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ፣ የተበዳሪዎችን ጫና ለማቃለልና የአገር ኢኮኖሚ ሚዛን እንዲጠበቅ የበኩሉን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡

ባንኩ ማሻሻያ ካደረገባቸው አገልግሎቶቹ መካከል የብድር ማራዘሚያ አንዱ ነው፡፡ የብድር ማራዘሚያ ኮሚሽን ማስከፈያን በተመለከተ፣ የማራዘሚያ ክፍያዎች እ.ኤ.አ. ከማርች 31 ቀን 2020 ጀምሮ ለሁለት ወራት ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን ይፋ አደርጓል፡፡

ቡና ባንክ እንዳስታወቀው፣ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የባንኩ ደንበኞች በቋሚነት እንደሁኔታው እስከ 0.75 በመቶ የሚጠጋጋ የብድር ወለድ ቅናሽ አድርጓል፡፡ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የተደረገው ቋሚ የወለድ ቅናሽ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለኮሮና ተጋላጭ ዘርፎችም በልዩ ሁኔታ ተጨማሪ የብድር ወለድ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ በሆቴል፣ ቱሪዝምና ሆርቲካልቸር መስክ ለተሠማሩ የባንኩ ተበዳሪዎች ልዩ የብድር ወለድ ቅናሽ ሲደረግ፣ ዘርፎቹ በሚያጋጥማቸው የገበያ ዕጦት ችግር ምክንያት እንዳይቸገሩ  ለሦስት ወራት የሚቆይና ምጣኔው እንደ ደረጃው እስከ 2.5 በመቶ የሚሰላ የወለድ ቅናሽ አስተዋውቋል፡፡

ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ የሆኑት እነዚህ ዘርፎች የተበደሩት ገንዘብ አመላለስ ሒደትም በባንኩ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ የዋናውን ብድርና የወለዱን ክፍያ ወዲያውኑ እንዳይፈጽሙ፣ የመክፈያ ጊዜውም ከሦስት ወር በኋላ መክፈል እንዲጀምሩ የሚፈቅድ ሥርዓት በባንኩ ተዘርግቷል፡፡ በወጪ ንግድ ሥራ ለተሰማሩ ደንበኞች እንደ ሁኔታው እየታየ እስከ አምስት በመቶ ወለድ የሚከፍሉበት መንገድ እንዳመቻቸ ያስታወቀው ቡና  ባንክ፣ በኮሮና ምክንያት በየወሩ ከአምስት ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገቢ እንደሚያጣ አልሸሸገም፡፡

ተበዳሪዎች ላይ የሚደርሰውን የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ ለማቃለል  ማሻሻያዎች እንዳደረገ ያስታወቀው ደቡብ ግሎባል ባንክም፣ የኮሮና ወረርሽኝ በፈጠረው ተፅዕኖ የሥራ መቀዛቀዝ መከሰቱን በማውሳት፣ ለሆቴል ዘርፍና ለአበባ አምራቾች የወለድ ቅናሽ አድርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት ለሆቴሎች ከሁለት እስከ 2.7 በመቶ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ሲደረግ፣ ለአበባ አምራቾች ከ1.9 በመቶ እስከ 2.4 በመቶ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ማድረጉን ደቡብ ግሎባል ባንክ አመላክቷል፡፡ በኦቨርድራፍት አገልግሎት ላይ ለሆቴሎች የ2.6 በመቶ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ሲደረግ፣ ለአበባ አምራቾች የ1.6 በመቶ የወለድ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ ይህ ቅናሽ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2020 ድረስ እንደሚቆይ ባንኩ አስታውቆ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ እያበረከተ መቆየቱን አስታውሷል፡፡ ወደፊትም የሚጠበቅበትን ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡

ከሦስት ባንኮች ንብ ባንክ በብድር ወለድ ላይ ካደረገው ቅናሽ ባሻገር በአገር አቀፍ ደረጃ ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ሁለት ሚሊዮን ብር ለግሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች