Sunday, December 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየወረርሽኙ ሥርጭት እየጨመረ አብያተ ክርስቲያን ክፍት እንዲሆኑ መፈቀዱ ሥጋት ፈጥሯል

የወረርሽኙ ሥርጭት እየጨመረ አብያተ ክርስቲያን ክፍት እንዲሆኑ መፈቀዱ ሥጋት ፈጥሯል

ቀን:

ካለፉት ሦስት ሳምንታት ወዲህ የኮሮና ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ስለሆነ፣ በተለይ አብያተ ክርስቲያናት ለምዕመናን ክፍት እንዲሆኑ በመፈቀዱ ለወረርሽኙ ሥርጭት መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ሥጋት ማሳደሩ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ከጤና ባለሙያዎች የሚነገራቸውን ተግባራዊ በማያደርጉና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ መሠረት ሕግ በማያከብሩ ላይ ለሕዝብ ጤንነት ሲባል መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

በወረርሽኙ አማካይነት የእምነት ተቋማት በጋራ ሆነው ባስተላለፉት ትዕዛዝ መሠረት፣ ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለአንድ ወር የሚቆይ የፆም፣ የፀሎትና ምህላ ጊዜ ታውጆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምዕመናኑ ፆም ፀሎት ብቻ ሳይሆን ወደ ቤተ እምነቶች ከመሄድ እንዲቆጠቡ ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ስብሰባ እንዳስታወቀው፣ ቀደም ብሎ ሲኖዶሱ ውሳኔ እንዳስተላለፈ ተደርጎ ለምዕመናን የተገለጸው ከእሱ ዕውቀት ውጪ ነው፡፡ በመሆኑም የተዘጉ የአብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ እንዲከፈት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የሲኖዶሱን ውሳኔ በመቀበል ምንም እንኳን ምዕመናኑን በአግባቡ የሚያስተናግዱ የየቤተ እምነቱ ወጣቶች እንዳሉ የተነገረ ቢሆንም፣ ሰሞኑን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ ያሉ ምዕመናን ርቀታቸውን እንደማይጠብቁ፣ እጅግ በጣም በተቀራረበና ለወረርሽኙ በሚያጋልጥ ሁኔታ ተጠጋግተው የታዩ በመሆኑ ለወረርሽኙ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የሚል ሥጋት እየፈጠረ መሆኑን በርካቶች እየገለጹ ነው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊዎችና በየአብያተ ክርስቲያናት ያሉ ቀሳውስት በተለይ ሰሞኑን እየታየ ያለውን የወረርሽኙን ሥርጭት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቀደም ብሎ የተወሰደው ዕርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡ በየቀኑ ቁጥራቸው አነስተኛ ሰዎች በወረርሽኙ እንደተያዙ በሚነገርበት ወቅት ምዕመናን በቤት እንዲፀልዩ ተደርጎ፣ አሁን በየቀኑ በርካታ ወገኖች በቫይረሱ መያዛቸው እየተነገረ ቤተ ክርስቲያንን መክፈት ተገቢ ስላልሆነ እንዲታሰብበትም ጠቁመዋል፡፡

ምንም እንኳን ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ተነጋግረው በመግባባት ይህንን ችግር የማያልፉት ከሆነ፣ ሕዝብን የማዳን ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ ሕዝብ የሚሰበሰብበትን ቦታ የመከላከል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቅድመ ዝግጁነትና ምላሽ ምክትል አስተባባሪ አቶ ዘውዱ አሰፋ እንደገለጹት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚከለክላቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ‹‹በተለይ በአንድ ቦታ ከአራት ሰዎች በላይ መሰብሰብ የለባቸውም፡፡ አፍና አፍንጫ መሸፈንና ርቀትን መጠበቅ ግዴታ ናቸው፡፡ እነዚህን በማያከብሩ ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በግልጽ ተመልክቷል፤›› ብለዋል፡፡ የወረርሽኙ ሥርጭት ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን ጤና ሚኒስትር ጭምር በማሳወቁ የዕምነት ተቋማትም ይህንን ለምዕመኖቻቸው ማስተላለፍና ሕግ እንዲከበር ማድረግ እንዳለባቸው፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በስምምነት ችግሮችን ለመቅረፍና ከዚህ አደገኛው ወረርሽኝ ለመጠበቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ያ ካልሆነ ግን መንግሥት መውሰድ የሚገባውን ዕርምጃ የሚያሳውቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ሰሞኑን እንደገለጹት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኅብረተሰቡ ውስጥ ገብቷል፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚሠራጭ ኅብረተሰቡ በተለይ ከሕክምና ባለሙያዎችና ከመንግሥት የሚተላለፍለትን መልዕክትና መመርያ፣ በመተግበር መተባበር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ እስከ ዓርብ ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 433 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በ15 ቀናት ውስጥ እንደተያዙ ታውቋል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዮሴፍንና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት መጋቤ ካህናት አባ ወልደየሱስን ለማግኘት የተደረገው ጥረት፣ የእጅ ስልካቸውን ሊያነሱ ባለመቻላቸው አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...