Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ለሁለት የቴሌኮም ኩባንያዎች ፈቃድ በመስጠት በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ ማግኘት የሚችልበት ዕድል እንዳለው ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ሁለት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኢትዮጵያ ሥራ መጀመር የሚችሉበትን ፈቃድ ለመስጠት የፍላጎት መግለጫ መጠየቂያ በማውጣት፣ ከሽያጩ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ ማግኘት የሚችልበት ሰፊ ዕድል እንዳለው ተገለጸ፡፡

የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ፕራይቬታይዜሽን ሒደትን በመምራት የሚሳተፉትና የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በአሁኑ ወቅት ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ችግር ላይ ቢወድቅም የቴሌኮም ኩባንያዎች ግን ከፍተኛ ገቢ ማግኘት የቻሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡

‹‹በኮሮና ምክንያት የገበያው አለመረጋጋት ከፍተኛ ቢሆንም፣ በርካታ የቴሌኮም ኩባንያዎች እየተጠቀሙ እንጂ እየተጎዱ አይደለም፡፡ ሌላ ፍላጎቶች ሊገደቡ ይችላሉ እንጂ፣ የስልክ ቢል መክፈል የማይቆም በመሆኑ ኩባንያዎች ገበያቸው እያደገ  መጥቷል፤›› ያሉት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ሌላው ጉዳይ የብድር ገበያው ጥሩና አዋጭ ኢንቨስትመንት በማጣት በአፍጢሙ ቢደፋም፣ የቴሌኮም ኩባንያዎች ግን አዋጭ በሆነ መንገድ ብድር እያገኙ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያም ያልተነካ የቴሌኮም ገበያ ሲታከልበት፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ትልቅ የገበያ ልውውጥ ሊፈጠር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ ብዙ ገንዘብ ለማስገኘት ጥሩ አጋጣሚ ነው፤›› ያሉት ብሩክ (ዶ/ር)፣ እስካሁን ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ የነበሩ ኩባንያዎችን ጨምሮ ማንኛውም አቅምና ብቃት ያለው ኩባንያ እንዲሳተፍ ዕድል የሚሰጥ የፍላጎት መግለጫ ጥሪ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡ ሊገኝ የሚችለው ገንዘብ ምን ያህል እንደሚሆን ለተጠየቁት ሲመልሱ፣ ‹‹አየር ላይ ያለውን ስፔክትረም በመክፈት ፈቃድ መስጠት ከፍተኛ ገቢ ለአገሪቱ ያስገኛል፡፡ ትልቅ ገቢ ይገኛል፡፡ ይህ ነው ብዬ የገንዘቡን መጠን ልጠቅስ ባልችልም፣ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚገኝ መናገር እችላለሁ፤›› ብለዋል፡፡  

የፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱን በኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ሥልጣን የተሰጠው ባለሥልጣኑ እየመራው ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የቴሌኮሙዩኒኬሽንለግሉ ዘርፍ የመክፈት ሒደት ዋናው አካል እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከያዘው ፈቃድ በተጨማሪ ሁለት የቴሌኮም ፈቃዶችን በቴሌኮሙዩኒኬሽን ሥራ ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች የመስጠቱ ሒደት፣ መንግሥት በዘርፉ ውድድርን ለመፍጠር ካቀዳቸው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች አንዱ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ካለው ይዞታ የ40 በመቶው ድርሻም ፍላጎቱ ላላቸው ተጫራቾች ተላልፎ የተቋሙን አቅም የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡

ባለሥልጣኑ በኅዳር ወር 2012 .ም. ከተደረገው የባለድርሻ አካላት ምክክር ወዲህ የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ እንደቆየ ያስታወሱት ብሩክ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ኩባንያዎች በእኩል ሰዓትና በአንድ ላይ መረጃዎችን በአንድ ጊዜ ማግኘት የሚችሉበት የኦንላይን ዕድል እንደሚዘረጋ፣ ይህም የተዛባ መረጃ ለኩባንያዎቹ ተሰጥቶ ችግር እንዳይፈጠር ከሚል መነሻ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽንን በአማካሪነት ቀጥሮ አስተማማኝ የሕግና የቁጥጥር ማዕቀፍ ለመዘርጋት የሚያስችሉ መመርያዎችን የማርቀቅ ሥራዎች እንዳከናወነ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን መስክን ለግሉ ዘርፍ የመክፈት ሒደትና በዲጂታል ኢኮኖሚ ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ ለማጎልበት መንግሥት ቁርጠኛ እንደሆነ ሲገለጽ፣ አገር አቀፍ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ ፈቃዶች መሥፈርቶችን ለሚያሟሉ ሁለት የቴሌኮሙዩኒኬሽኩባንያዎች፣ በኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 መሠረት በውድድር ላይ በተመሠረግልጽ ጨረታ ፈቃድ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡

ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫውን እስከ ሰኔ 15 ቀን 2012 .ም. 6 ሰዓት ድረስ ማስገባት እንደሚችሉስለፍላጎት መግለጫው ዝርዝር መመርያ ከባለሥልጣኑ ድረ ገጽ ማግኘት እንደሚቻል ተቋሙ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ነሐሴ 6 ቀን 2011 .ም. በኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 መሠረት ራሱን ችሎነፃና ገለልተኛ ሆኖ በፌዴራል መሥሪያ ቤትነት ተቋቁሟል፡፡ ባለሥልጣኑ ተወዳዳሪ የገበያ ሥርዓትን ኢኮኖሚያዊ አቅምን ያገናዘበ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች