Wednesday, September 27, 2023

በአዲስ አበባ የግል ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲነሳ ተጠየቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ በኮድ ሁለት የግል ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ፣ በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር በመፍጠሩ እንዲነሳ ተጠየቀ።

ጥያቄውን ያቀረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም ለመከታተል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት የተቋቋመው መርማሪ ቦርድ ነው። መርማሪ ቦርዱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠውን የሚኒስትሮች ኮሚቴ የሥራ አፈጻጸም ባለፈው ሳምንት በገመገመበት ወቅት፣ በግል ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብን በመሠረታዊነት የሚስማማበት ቢሆንም የተገፈለገውን ውጤት እንዳላስገኘ አመልክቷል።

የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ጴጥሮስ ወልደ ሰንበት በግል ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ የመንግሥት ሠራተኞች ከቤታቸው እንዲሠሩ፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቶችም እንዲዘጉ መደረጉን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተፈለገው በቤታቸው መቀመጥ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

በግል ተሽከርካሪዎች ላይ ከተጣለው ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ በተጨማሪ የሕዝብ ትራንስፖርቶችም በግማሽ የማጓጓዝ አቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተወሰነ በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎችን ከቤት ውጪ እንቅስቃሴ መግታት ባላመቻሉ የተፈጠረው ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት ለቫይረሱ ሥርጭት ምቹ እንደሆነ ገልጸዋል።

በከተማዋ 220,000 የግል ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ከከተማ አስተዳደሩ እንደተረዱ የተናገሩት የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ፣ የነዋሪዎች እንቅስቃሴን እንደተፈለገው መግታት ባለመቻሉ በግል ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ገደብ ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍላጎት ጫና መፍጠሩን አስረድተዋል።

በመሆኑም የሚኒስትሮች ኮሚቴ በተጣለው ገደብ ላይ ማሻሻያ ማድረግ የሚችልበትን መንገድ እንዲያስብ ጥያቄ አቅርበዋል። ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባል የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፣ ችግሩን እንደሚረዱት በመግለጽ በሚኒስትሮች ኮሚቴ እንደሚታይ ገልጸዋል።

ቀድሞውንም ቢሆን በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የሕዝብ ትራንስፖርት አቅርቦት የፍላጎቱን 60 በመቶው ብቻ የሚሸፍን እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በግማሽ የመጫን አቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ በከተማዋ ያለው የትራንስፖርት አቅርቦት ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረጉን ተናግረዋል።

ይህንን ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታት ከ12 ሰው በላይ የመጫን አቅም ያላቸው ተሽከርካሪዎች ከሁሉም የመንግሥት ተቋማት ተሰብስበው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑን ተናግረዋል።

ይኼንንም እንዲያስፈጽም ለገንዘብ ሚኒስቴር መመርያ መተላለፉን ሚኒስትሯ ገልጸው ተሽከርካሪዎቹን ከመንግሥት ተቋማት የመሰብሰብ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ውጪ በሕዝብ ማመላለስ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ ገብተው እንዲሠሩ መወሰኑንም ገልጸዋል።

በእነዚህ መንገዶች የሚመጣው ውጤት ታይቶ ችግሩን ለመቅረፍ የማያስቻል ከሆነ የግል ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ወይም ሌሎች አማራጮችን የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተመልክቶ ማሻሻያዎችን ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -