Sunday, April 21, 2024

በሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የአስቸኳይ አዋጁን በሚያስፈጽመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ መካከል አለመግባባት ተፈጠረ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹በሆነ አመለካከትና ፍላጎት ተሠልፈን የምንሳሳብበት ጉዳይ አይደለም›› አቶ ደመቀ መኮንን

‹‹የሁላችንም ዓላማ የዜጎችን መብት መጠበቅ ስለሆነ መግባባት አለብን›› ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

‹‹ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው መግለጫዎች አግባብነት የላቸውም›› ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

‹‹ሕይወት ለማዳን የሚወሰድ ዕርምጃ ሕይወት ማጥፋት የለበትም››  ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተቋቋመው መርማሪ ቦርድ ጋር፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ አለመግባባት መፈጠሩ ታወቀ።

አለመግባባት የተፈጠረው የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ እንዲሁም በአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ የተወሰኑ አንቀጾች ላይ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ በማቅረቡ ነው። በተወሰኑ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ከቀረበው ምክረ ሐሳብ በተጨማሪ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ሊታረሙ ይገባቸዋል የሚላቸውን ኢሰብዓዊ አያያዞች የተመለከቱ መግለጫዎችን ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ እያወጣ መሆኑ፣ በሚኒስትሮች ኮሚቴ ውስጥ የሚሳተፉ የመንግሥት ባለሥልጣናት አስከፍቷል።

አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነት ከተሰጣቸው ባለሥልጣናት በተጨማሪ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን በተለይም ኢሰብዓዊ አያያዞችን ለማስቀረት ትኩረት በማድረግ እንዲከታተል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም፣ በኮሚሽኑ ላይ ቅሬታውን እያሰማ ነው።

የመርማሪ ቦርዱ ቅሬታ መሠረቱ ከሚኒስትሮቹ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተገናኘ የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የመከታተል ሥልጣን የመርማሪ ቦርዱ፣ እንጂ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አይደለም ሲል የሕግ ጥያቄ አንስቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና የማስፈጸሚያ ደንቡ የተወሰኑ አንቀጾች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ቢሆንም መከበር የሚገባቸውን ሰብዓዊ መብቶች የሚጥሱ በመሆናቸው፣ ሊሻሻሉ ይገባል ብሎ ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ለመንግሥት ባቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባልና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጓ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ምላሽ የሰጡበት ደብዳቤ ሰሞኑን ለኮሚሽኑ መላካቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሕጎቹ ላይ ካቀረባቸው የማሻሻያ ጥያቄዎች (ምክረ ሐሳቦች) መካከል አንዱ የሕጋዊነት መርህ (Principle of Legality) የተመለከተ ነው። ‹‹ማንኛውም አገር በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የመንግሥት በሕግ የበላይነትና (Rule of Law) እና በሕጋዊ ሥርዓት የመተዳደር ግዴታ ቀሪ አይሆንም፤›› ሲል ኮሚሽኑ  ያሳስባል።

‹‹የሕጋዊነት መርህ ሌላው መገለጫ በማናቸውም ጊዜ የነፃ ዳኝነት ሥርዓት የተጠበቀ መሆን ነው፤›› የሚለው ኮሚሽኑ፣ አገር በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ለመቆየት ብትገደድ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የተቀመጠውን ገደብ አለመጣሱንና የማይታገዱ መብቶች መከበራቸውን ለማረጋገጥ፣ በነፃ ፍርድ ቤት የመዳኘትና ይኼንኑም የማረጋገጫ ሕጋዊ ሥነ ሥርዓቶች (Judicial and Procedural Remedies) አስፈላጊነት ሊቋረጥ ወይም ሊገደብ እንደማይገባ ያስረዳል።

ከዚህ በመነሳት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ በአንቀጽ ስድስት ሥር ስለዳኝነት፣ የጊዜ ቀጠሮ፣ ፍርድ ቤት የመቅረቢያ ጊዜና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ ያስቀመጠው ገደብና ሌሎች ጉዳዮች ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ዓላማ አንፃር እጅግ አስፈላጊነቱን በመመርመር፣ ከሕገ መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎች ጋር ተጣጥሞ ሊቀረፅ ይገባል ሲል ምክረ ሐሳቡን ለመንግሥት አቅርቧል።

ኮሚሽኑ እንዲሻሻሉ ካለቸው የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ አንቀጾች መካከል በአንቀጽ 6 የተዘረዘሩት ድንጋጌዎች ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል ‹‹የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ እና ሌሎች አዋጆች ላይ የተመለከቱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ተፈጻሚነታቸው ታግዷልየሚለው የደንቡ አንቀጽ 6(1) ድንጋጌ አንዱ ነው።

ኮሚሽኑ ይህንን ድንጋጌ አስመልክቶ ባቀረበው ምክረ ሐሳብ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ቢሆንም ማንኛውም ሰው የፍትሐ ብሔር የውል ግዴታን ባለመፈጸም ምክንያት ያለመታሰር መብት ሊገደብ እንደማይገባ እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች ልዩ ትኩረት ማድረግና የደንቡን መተላለፍ ጨምሮ ሁሉንም ጥፋቶች የማጣራትና በሕግ ተጠያቂነት ማረጋገጥ ሊቋረጥ የማይገባ ተግባርና ኃላፊነት መሆኑን ለመንግስት አመልክቷል።

በማከልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ አንቀጽ 6 ስር ስለ ዳኝነት፣ የጊዜ ቀጠሮ፣ ፍርድ ቤት የመቅረቢያ ጊዜና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ ያስቀመጠው ገደብ እና ሌሎች ጉዳዮች ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ዓላማ አንጻር እጅግ አስፈላጊነቱን በመመርመር ከሕገ መንግሥቱና የዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ሊቀረጽ ይገባል ብሏል።

ሌላው ድንጋጌ በአንቀጽ 6(3) የተቀመጠው ነው ይኼውም፣ ‹‹በፌዴራልና በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሠረት የክልልና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ማስተናገድ ሊያቆሙ ይችላሉ፤›› የሚል ነው።

ኮሚሽኑ እንዲሻሻሉ ብሎ ካቀረባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌዎች በተጨማሪም ሕግ አስከባሪዎች ፈጽመዋል ያላቸውን ጥሰቶች የተመለከቱ መግለጫዎችን እያወጣ ይገኛል። ከነዚህም መካከል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች የሚደረግባቸው ተብለው በአስገዳጅነት ከተዘረዘሩ አካባቢዎች ውጪ የፊት መሸፈኛ አላደረጉም በማለት የሚፈጽሟቸው የዘፈቀደ እስሮች በአስቸኳይ እንዲቆም በማሳሳብ በቅርቡ ያወጣው በመግለጫ ይገኝበታል።

ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን እንዲከታተል ያቋቋመው መርማሪ ቦርድ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ የሆነውን የሚኒስትሮች ኮሚቴ የአንድ ወር የሥራ አፈጻጸም ገምግሞ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት ኮሚቴው ያከናወናቸውን ተግባራት ከሞላ ጎደል አወድሶ ነበር።

ቦርዱ ባካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ሊታረሙ ይገባቸዋል ተብለው ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚያወጣቸው መግለጫዎችና ምክረ ሐሳቦች ሰፊ ትኩረት የተሰጣቸው ነበሩ።

በዚህ ስብሰባ ላይ ኮሚሽኑን የተመለከተ ቅሬታ አስቀድመው ያቀረቡት፣ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ናቸው። ‹‹ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እየገጠመን ያለው መፈታተን በቀላሉ መታለፍ የለበትም። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ደንብ ኮሚሽኑ መተቸቱ በቀላል የሚታለፍ አይደለም፡፡ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ይኼንን ጉዳይ በጥንቃቄ ማስተዋል አለበት፤›› ብለዋል።

መርማሪ ቦርዱ ከደረሱት 664 ጥቆማዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት መንግሥት አዋጁን እያስፈጸመ እንዳልሆነ የሚገልጹ ቅሬታዎች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ ይህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለመፈጸሙን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ሥልጣን የተሰጠው ለመርማሪ ቦርዱ ሆኖ ሳለ፣ ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው መግለጫዎች የቦርዱን ሥልጣን የሚጋፉ በመሆናቸው የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔን ጨምሮ መንግሥት አቅጣጫ ሊሰጡበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኩል የመጡ መፈታተኖችን ቆም ብሎ ከጀርባው ምን እንደተፈለገ ማየት አስፈላጊ ነው ሲሉ፣ አቶ ተስፋዬ በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዚህ ውይይት ላይ የተገኙት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላትም ክብደቱ ይለያይ እንጂ፣ ተመሳሳይ ቅሬታዎችን በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ላይ አቅርበዋል።

ከእነዚህም መካከል የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባልና የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹በሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በቅርቡ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የወጡ መግለጫዎች ያሳስባሉ፡፡ ለሰብዓዊ መብት የምንቆም ሁሉ ተግባራዊነቱን አጥብቀን መሻት አለብን፤›› ብለዋል።

የፀጥታ ኃይሉ ራሱን አደጋ ላይ ጥሎ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያደርገው ርብርብ ተገቢው ሥፍራ ሊሰጠው ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ‹‹የሁላችንም ዓላማ የዜጎችን መብት መጠበቅ ስለሆነ መግባባት አለብን፤›› ብለዋል።

ሌላዋ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባልና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ‹‹ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ተገቢነት የላቸውም። የመብት ጥሰት ገጥሟልና ዕርማት ይደረግበት ቢሆን ሥራው ስለሆነ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ከመጀመርያው አንስቶ ሕጉን የመተቸትና የተወሰኑ አንቀጾች እንዲወጡ የሚጠይቁ ናቸው፤›› ብለዋል። መብቶች የተገደቡት ሕዝብን ለመጠበቅ እንጂ ሌላ ዓላማ እንደሌለው የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ኮሚሽኑ ይኼንን የሚያደርገው ካለመረዳት ከሆነ መነጋገር እንደሚቻል ገልጸዋል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ አዋጁ በሕዝብ ላይ የተጫነ ዕዳ ሳይሆን ሕይወትን ለመታደግ የወጣ እንደሆነ በመጠቆም፣ ‹‹በሆነ አመለካከትና ፍላጎት ውስጥ ተሠልፈን የምንሳሳብበት ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው አዋጅ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ሐሳብ ሲቀርብ አይቻልም ማለት ትክክል አይደለም ብለዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነትና በመሠረታዊ ድንጋጌዎቹ ላይ ኮሚሽኑ ልዩነት እንደሌለው፣ ነገር ግን የተወሰኑ አንቀጾች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ቢሆን ሊገደቡ የማይገባቸው ስለሆነ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኮሚሽኑ አስተያየት መስጠቱን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ባቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ልዩነት እንዳለው መገንዘባቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ይህም በደንቡ አተረጓጎም ላይ ካለው ልዩነት የመጣ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል።

የሐሳብ ላይ ልዩነት ሊፈጠር እንደሚችልና ልዩነቱንም እንደ ተቃውሞ እንደማይወስዱት፣ ከበርካታ የመንግሥት ተቋማት አመራሮች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸውና ኮሚሽኑ የሚያቀርባቸውን ምክረ ሐሳቦችም አብዛኞቹ ተቀብለው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

‹‹የእነሱ ዋና ግብና ዓላማ ለተፈጠረው ችግር ትኩረት መስጠት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሕይወት ለማዳን የሚወሰድ ዕርምጃ ሕይወት ማጥፋት የለበትም፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሰፊ ችግር አይደለም ተብሎ በመታለፉ ምክንያት ነው የተለማመድነው፡፡ ስለሆነም ለእኛ የአንድም ሰው ጉዳይ ቢሆን ያሳስበናል፤›› ብለዋል።

በዚህ ረገድ ያለውን ልዩነት ተነጋግሮ መፍታት እንደሚቻልና በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሰብዓዊ መብቶች አለመጣሳቸውን የመከታተል ሥራ፣ የመርማሪ ቦርድ ሥልጣን እንደሆነ ተደርጎ የቀረበው አስተያየት ፍፁም ስህተት እንደሆነም ተከራክረዋል።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሥራ የማይተካና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ደግሞ፣ ክትትሉ የበለጠ የሚፈለግበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል። ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሰጧቸው እነዚህ አስተያየቶች የኮሚሽኑን ቀጣይ ሥራ ይጎዱት እንደሆነ የተጠየቁት ኮሚሽነሩ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሥራ በየትኛውም አገር ስህተቶቹ ወይም ጥሰቶቹ ከሚመለከተው አስፈጻሚ መንግሥት ጋር የሚያቃርነው መሆኑን ተረድተው ኃላፊነቱን እንደተረከቡ ገልጸዋል።

በመሆኑም አሁን የተፈጠረው አለመግባባት ተፅዕኖ እንደማያሳድርባቸው የገለጹት ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ‹‹መስማት የሚፈልጉትን ሳይሆን መስማት የሚገባቸውን እናስረዳቸዋለን፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -