Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም የሕግ ማዕቀፎችን ማጠናቀቁን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም የሚያስፈልጉትን የሕግ ማዕቀፎች አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ሰሞኑን እንደገለጹት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የካፒታል  ገበያ ማቋቋም ነበር፡፡ በዚህም ሲባል ሰፋ ያሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

የሕግ ማዕቀፎች በመጠናቀቃቸው በባለድርሻ አካላት በቂ ውይይት ከተደረገ በኋላ፣ ቅርፅ እንደሚይዝ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ በማቋቋም በቅርቡ  ወደ ሥራ እንደሚገባ እምነታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባካሄዳቸው ሪፎርሞች የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ የካፒታል ገበያ ለመፍጠር አሁን ከደረሰበት ደረጃ በተጨማሪ ተንቀሳቃሽ ንብረት በዋስትና በማስያዝ ዜጎች የብድር ተጠቃሚ የሚሆኑበት አዲስ አዋጅ ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኗል ብለዋል፡፡  

በኢትዮጵያ በአብዛኛው የብድር አሰጣጥ በቋሚ ንብረት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የተንቀሳቃሽ ንብረት አዋጅ ተግባራዊ ሲደረግ፣ ተንቀሳቃሽ ንብረት ያላቸው ከሰብል ጀምሮ ደንና የደን ውጤቶች፣ የቤት እንስሳት፣ የአዕምሯዊ ንብረት፣ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የተያያዙ ሰነዶችና የመሳሰሉትን በማስያዝ ዜጎች ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ፋይናንስ ተደራሽ ለማድረግ በገጠርም በከተማም ሊሠራበት የሚችል ነው፡፡ ለዚህ አዋጅ ተግባራዊነት ዝግጅት መደረጉንና በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ገዥው አስታውቀዋል፡፡  

ሌላው የሪፎርሙ አካል መሆኑን የገለጹት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን ችሎ የሚሠራበት አዋጅ መውጣቱን፣ በዚህም መሠረት እስካሁን ከስድስት በላይ ከወለድ ነፃ ባንኮች ፈቃድ ለማግኘት መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡ በተለይ አንደኛው ባንክ መሥፈርት አሟልቶ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  ከወለድ ነፃ ባንክ ሥራ መጀመር ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር በገጠርና በከተማ የፋይናንስ ተደራሽነትን ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ አቅምና ዕገዛ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡  

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ስለሌለ የብድር መረጃ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ እንደነበር፣ ብድር የወሰደ ሰው ወይም ድርጅት መረጃው ተሟልቶ የማይገኝ በመሆኑ፣ ይህንን ለማስቀረት የባንክ ተበዳሪዎች የመረጃ ቋት እንዲጠናከር መደረጉን አክለዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ወደ 260 ሺሕ የሚጠጉ የተበዳሪዎች መረጃ ብቻ የነበረ መሆኑን፣ ይህ አኃዝ አሁን ወደ 3.1 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን እንዲደረጉም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ባንክ ሄዶ ብድር ሲጠይቅ፣ የብድር ጥያቄ የቀረበለት ባንክ ስለዚያ ሰው ከእኛ የብድር መረጃ ቋት ቢሮ መረጃውን በቀላሉ ለማግኘት ይችላል፤›› ብለው፣ ይህ ማንኛውም ባንክ  ተበዳሪን በሚመለከት የተሻለ መረጃ እንዲያገኝ የሚያደርግ ሥርዓት መሆኑን፣ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

የባንኮችም ሆነ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ተበዳሪዎች መረጃ የመያዙ ሥራ  አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ የብድር አሰጣጡ ከሥጋት የነፃ እንዲሆን እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን ያወሱት ይናገር (ዶ/ር)፣ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉት የተለያዩ አዋጆችና መመርያዎች እንዲወጡና እንዲሻሻሉ መደረጋቸው ነው ብለዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያደርግ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ መደረጉን በምሳሌነት ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች