Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክሕገ መንግሥትና ምርጫ

ሕገ መንግሥትና ምርጫ

ቀን:

በወልዱ መርኔ

በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የሕግና የሥልጣን ክፍተት አስመልክቶ በፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን የተለያዩ ሐሳቦችና አማራጮች እየተደመጡ ነው፡፡ የፖለቲካና የሕግ ክርክሩም በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጋባ ያለበት ጊዜ እንደመሆኑ፣ እኔም እንደ አንድ ዜጋና የሕግ ባለሙያ የተወሰኑ ሐሳቦችን መሰንዘር አስፈላጊ ሆኖ ታይቶኛል፡፡

በዚህ ዓይነት አሁን ካለው ወቅታዊ ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት ጋር ተያይዞ በአንድ በኩል መንግሥት አራት ሕጋዊ አማራጮችን አቅርቦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛውን የሕገ መንግሥት ትርጉም የመጠየቅ አማራጭን ወስኗል፡፡ ጉዳዩ የተመራለትም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔም ሥራዎችን መጀመሩን እየተከታተልን ነው፡፡ እነዚህን በመንግሥት ቀርበው የነበሩ አማራጮችን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ምሁራንና የተወሰኑ ፓርቲዎች የደገፏቸው ሲሆን፣ በአንፃሩ ሌሎች ፓርቲዎች ከሕግ አማራጭ ይልቅ የፖለቲካ መፍትሔ ላይ በማተኮር የተለያዩ ወጥነት የሌላቸውን ሐሳቦች በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሐሳቦች ድርድር ማድረግን፣ የጋራ አመራርና የሽግግር ወይም የባለሙያዎች መንግሥት ማቋቋምን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በተለይም ‹‹የሦስተኛ አማራጭ›› አለኝ ሲሉ ይደመጡ የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌውና አብሮነት ለፌዴራላዊ አንድነት የተሰኘ የፓርቲዎች ስብስብ  ‹‹ሕገ መንግሥታዊው ቀውስ›› መፍትሔ የሚያገኘው የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ነው የሚለውን ሐሳባቸውን ያለመታከት ሲወተውቱ ይታያሉ፡፡ ከዚሁ ጋር አክቲቪስት አቶ ጀዋር መሐመድም የዚሁ ሐሳብ ተጋሪነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሐሳቦች በሰላማዊ መንገድ መቅረባቸው ክፋት የሌለው ቢሆንም፣ ጠቀሜታቸውና ጉዳታቸው መሞገት ያለበት ይመስለኛል፡፡

የመንግሥት አማራጭ

በእኔ በኩል በመንግሥት ከቀረቡ አማራጮች የተሻለ መፍትሔ ተብሎ በተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት ባገኘው የትርጉም ጥያቄ ላይ የተወሰኑ ሐሳቦችን በመሰንዘር፣ በቀረበው የድርድርና የሽግግር መንግሥት አማራጭ ላይ ከሕግ አንፃር የበኩሌን ሐሳብ እነሆ እላለሁ፡፡ በመጀመርያ የወረርሽኙን መስፋፋት ተከትሎ በምርጫ መራዘም ምክንያት የተፈጠረውን ሕገ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን ክፍተት ለመሙላት በባለሙያዎች ተጠንተው በመንግሥት ቀርበው የነበሩ አራቱም አማራጮች፣ በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ላይ የተመሠረቱና ከእነ እጥረታቸውም ቢሆን ከችግሩ ለመውጣት መንገድ የሚከፍቱ መሆናቸውን የሕግ ባለሙያም ሆነ ፖለቲከኛ ነገሩን በቅን ልቦናና በእርጋታ ካስተዋለ ለመረዳት አዳጋች ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(3) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት እንደሆነና የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ እንደሚደረግ ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት የፓርላማውና የአስፈጻሚው የሥልጣን ዘመን እንደሚያበቃ ግልጽ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ምርጫው በወቅቱ ባለመደረጉ ሥልጣኑን የሚረከብ አዲስ ፓርላማና አስፈጻሚ ስለማይኖር፣ ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ሕገ መንግሥታዊ የፖለቲካ ሥልጣን ክፍተትን ለመሙላትና በመንግሥት ሕጋዊ የቅቡልነት ጥያቄ ላይ የሚፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ግልጽ ድንጋጌ ሕገ መንግሥቱ አለማስቀመጡ የታወቀ ነው፡፡ ሆኖም ሕገ መንግሥት በባህሪው አጠቃላይ መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን የያዘ በመሆኑ፣ እንደ ሌሎች የበታች ሕጎች ዝርዝር ድንጋጌዎች እንዲኖሩት አይጠበቅም፡፡ ዊሊያም ዳግላስ በሚባሉ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አገላለጽ ሕገ መንግሥት ጅምላ የሆኑ ጉዳዮች የሚገለጹበት እንጂ ዝርዝር ኮድ አይደለም፡፡ ስለሆነም ግልጽነትና የአተገባበር ክፍተት ሲያጋጥም በትርጉም እየሞሉ የሚዳብር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ይህ የትርጉም ጥያቄ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም ብሎ መደምደም ተገቢ አይመስለኝም፡፡

ከአንዳንድ የፓርቲዎች አመራሮች እነዚህ ይተርጎሙ የተባሉት  የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ግልጽ ስለሆኑ ትርጉም አያስፈልጋቸውም የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ ለእኔ እንደሚገባኝ የሕገ መንግሥት ትርጉም ማለት የቃል በቃል ትርጉም ብቻ አይደለም፡፡ ትርጉም ሲባል ግልጽ የሚመስለውን ድንጋጌ ለመተግበርና ሕገ መንግሥቱን በተሟላና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ሥራ ላይ ለማዋል በማይቻልበትና የተግባር ክፍተት በሚፈጠርበት ጊዜ የሕገ መንግሥቱን ዓውድ በመረዳት አንድን ችግር ለመፍታት የሚወሰድ ዕርምጃ ነው፡፡ ለምሳሌ በሕገ መንግሥት አተረጓጎም ተቀባይነት ካገኙ የትርጉም መርሆዎች የተወሰኑትን እንኳ ብናይ ጉዳዩ ግልጽ ይሆንልናል፡፡ አንዱ ‹‹Textual Structuralism›› የተሰኘው መርህ ትርጉም በሚያስፈልግበት ጊዜ አንድን ድንጋጌ ብቻ ሳይሆን የሕገ መንግሥቱን አጠቃላይ ይዘት መግቢያውን ጨምሮ ሌሎችንም ድንጋጌዎች በመመልከት መተርጎም እንደሚቻል ያመለክታል፡፡ ሁለተኛው ‹‹Purposive Textualism›› የተሰኘውን መርህ ብናይ አንድን ድንጋጌ ከመተርጎም ባለፈ ድንጋጌው ወይም ሕገ መንግሥቱ ከሚያሳካው ዓላማና ግብ አኳያ እንዲተረጎም የሚያስችል ነው፡፡ እንዲያውም ይህ መርህ አንድ ድንጋጌ የሕገ መንግሥቱን ዓላማ ለማሳካት እንቅፋት ከሆነ ጥንቃቄ በማድረግ መተርጎም ያለበት ዓላማውን በሚያሳካ መልኩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የሕገ መንግሥቱን አጽዳቂዎች ሐሳብ የመረዳት ‹‹Originalism›› መርህንም ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህና ሌሎች መርሆዎችም እንደየአግባብነታቸው የሚተገበሩ ናቸው፡፡

ይህን ሁኔታ ለመረዳት በአንድ ወቅት በአጣሪ ጉባዔው የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦበት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ያገኘን አንድ ጉዳይ በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በ1992 ዓ.ም. የስልጤ ሕዝብ በብሔረሰብነት እንዲታወቅ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(4) የብሔር ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ምንነትና የመብት አተገባበር በግልጽ የተደነገገ ቢሆንም ግልጽ ያልነበረውና ትርጉም ይጠይቅ የነበረው ጉዳይ አንድን ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(4) የተመለከተውን መሥፈርት አሟልተሃል ብሎ ዕውቅና የሚሰጠውና መብቱን እንዲተገብር የሚያስችለው ማነው? በምንስ ሥነ ሥርዓት ይወሰናል? የሚለው ነበር፡፡ በወቅቱም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 39(4)፣ 47(3)፣ 52(2)(ሀ) እና 62(1) ድንጋጌዎችን በመተርጎም የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረበበትን አግባብ እናስታውሳለን፡፡ ውሳኔውን ምክር ቤቱ ካሳተመው የሕገ መንግሥታዊ ፍርዶች መጽሔት ቅጽ 1 ማወቅ ይቻላል፡፡

በዚህ በአሁኑ ጉዳይም ጥያቄው የቀረበላቸው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክፍተቱ መፍትሔ የሚሆን ሕገ መንግሥታዊ ውሳኔ ያሳልፋሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክር ቤቱ የሚሰጠውም ውሳኔ የመጨረሻና በሁሉም ዘንድ በመንግሥትም በፓርቲዎችም ላይ አስገዳጅ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 ዓ.ም. በአንቀጽ 56(2) ተደንግጓል፡፡ በአጠቃላይ ይህ በፓርላማው የቀረበው አማራጭ የተፈጠረውን የሕገ መንግሥት ክፍተት ሞልቶ የአገርን አንድነት፣ ደኅንነትና የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስቀጠል አንዱ ሕጋዊ መፍትሔ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

በአንፃሩ የተወሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሚያሰሙትን የድርድር፣ የጋራ፣ የሽግግርና የባለሙያዎች መንግሥት የማቋቋምን መፍትሔ በተመለከተ የግሌን ዕይታ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡ በመጀመርያ የድርድር ሐሳብ አራማጆች ችግሩ የሚፈታው በፖለቲካ ድርድር እንጂ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ አይደለም የሚሉት ትክክል አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ በአገር ጉዳይ ፓርቲዎችም ሆነ ዜጎች ድርሻ ስላላቸው ውይይት አስፈላጊ መሆኑ አይካድም፡፡ ግን ዋናው ጥያቄ የውይይቱ ዓላማ ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት ሳይፋለስ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች፣  በሰላምና በብሔራዊ መግባባት ላይ ከሆነ የሚቻል ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው፡፡ መንግሥትም ፓርቲዎቹ በቀጣይ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ አምጥተው ውይይት ለማድረግ የጋበዛቸው መሆኑን እናውቃለን፡፡ ሆኖም የፓርቲዎቹ የእንደራደር ጥያቄ በግልጽ እንደታየው ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ መሠረት የሌለው የሥልጣን መጋራት ስለሆነ፣ ከሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውጪ በመሆኑ እነሱም እንደ ፓርቲ የቆሙበትንና አገር የሚተዳደርበትን የበላይ ሕግ የሚጥስ ነው፡፡ በዚህ ላይ ፓርቲዎቹ እያቀረቧቸው ያሉ ሐሳቦች ወጥነት የሌላቸው ናቸው፡፡ በአንድ በኩል እስከ ምርጫው ድረስ ፓርላማ የሌለው አስፈጻሚ ብቻ እንዲቀጥል ይሁንታ ሰጥተናል የሚል ድምፅ ይሰማል፡፡ በሌላ አንፃር ተቋማትን በጋራ እንምራ የሚል ሐሳብም አለ፡፡ ፓርቲዎች አማራጭ የሚሉትን እንደ ሐሳብ ማቅረባቸው ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ሐሳቡ የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑ አንዱ ማሳያ ፓርቲዎቹ ለመንግሥት ይሁንታ የመስጠትም ሆነ የመከልከል ሕጋዊ ሥልጣን የሰጣቸው ማን ነው? ይሁንታን የሚሰጠውም ሆነ የሚከለክለው ሕገ መንግሥቱ አሁን በተያዘው ሒደት ተተርጉሞ በሚሰጠው ውሳኔ አግባብ ነው፡፡ በአንፃሩ ፓርላማ በሌለበት አስፈጻሚው ብቻ ይምራ ማለት አገር የወረራ አደጋ ቢያጋጥማት የጦርነት አዋጅ የሚያውጀው፣ በጀት፣ የዕርዳታና የብድር ስምምነት የሚያፀድቀው ማን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ፓርቲዎቹ ያለማሰባቸው አስገራሚ ነው፡፡ ተቋማትን በጋራ እንምራ ማለትም ሥልጣንን በሕግ አግባብ ከሕዝብ በምርጫ ሳይቀበሉ መንግሥት እንሁን ከማለት አይለይም፡፡ 

የአገራችን መንግሥታዊ አስተዳደር የሚመራው በሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚደነግገው የመንግሥት ሥልጣን አያያዝ በውክልና ዴሞክራሲ መርህ (Representative Democracy) የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች የሆኑት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሕግ አግባብ በሚያደርጉት ምርጫ አማካይነት ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የተፈጠረው ክፍተት በሕገ መንግሥት በተቋቋመ የሕገ መንግሥት ተርጓሚ አካል መፍትሔ ያገኛል ተብሎ በሚጠበቅበት ሁኔታ ከሕጋዊ ሥርዓት ውጪ መቋጫ በማይኖረው ድርድርና በሥልጣን መጋራት እንሻገር ማለት ለወቅታዊው ችግር መፍትሔ የማይሰጥ ብቻ ሳይሆን አገርንና ሕዝብን ለአደጋ ማጋለጥ ይመስለኛል፡፡

የሽግግር መንግሥት ጉዳይ

ይህን በአቶ ልደቱ እየተቀነቀነ ያለ ሐሳብ ያወቅሁት ከአንድ ወር በፊት ከአንድ የአገሪቱ ተነባቢ ጋዜጣ ነው፡፡ አቶ ልደቱ ያቀረቡትን የሽግግር መንግሥት ፕሮፖዛል በዝርዝር አግኘቼ ባላነበውም በጋዜጣው ከሰፈረው ማብራሪያ ተነስቼ ሐሳቤን እሰነዝራለሁ፡፡ የፕሮፖዛሉ መነሻ አገሪቱ የምትገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ቁመና ላይ ያለመድረሷ፣ በአገሪቱ ዕርቀ ሰላምና መግባባት ያለመፈጠሩ ዘርፈ ብዙ የቅራኔ ስንጥቆች መኖር እንደሆነ ገልጸው፣ ከምርጫው በፊት አገሪቱን ወደ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት እንዲሁም መዋቅራዊ ችግሮችን ወደሚያስተካክል የሽግግር ሒደት መግባት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ በመቀጠልም የሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት 505 አባላት ያሉት ሸንጎ፣ አስፈጻሚ ካውንስልና የተለያዩ ኮሚሽኖች እንደሚቋቋሙ በፕሮፖዛላቸው ላይ ማስፈራቸውን ተረድቻለሁ፡፡ እኔ ትኩረት የማደርገው በሕጋዊ ጉዳዮች ላይ ቢሆንም፣ ከዚያ በፊት ያቀረቧቸው መነሻ ምክንያቶች ከሕገ መንግሥት ውጪ የሚያስወጡና ለሽግግር መንግሥት የሚያስገድዱ ናቸው ወይ የሚለውን ሐሳብ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡

በእርግጥ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የብሔራዊ መግባባት ማምጣት ተከታታይነት ያላቸውን የውይይት የማስተማር ሥራዎችን በመሥራት የቅራኔ ስንጠቆችን መድፈን ወደ ተሟላ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሒደት መግባት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ለማከናወን ግን ከሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ወጥቶ አገርን ለቀውስ የሚዳርግ የሽግግር መንግሥት አያስፈልግም፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተመሠረቱ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ነፃ እየሆኑና እየጠነከሩ እንዲሄዱ ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲተገበሩ፣ ሁሉንም አካታች ሥርዓት በሒደት እየተገነባ እንዲሄድ ከተደረገ ሒደቱ ቀላል ባይሆንም የአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ከሌሎች አገሮች የሽግግር ሒደት እንደምናየው ሕገ መንግሥቱን አግዶ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት የሚያስገድድ ሁኔታ በአገሪቱ አለ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለሆነም ይህ እንደ አዲስ እየተቀነቀነ ያለውና መቋጫው የማይታወቅ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ሐሳብ፣ አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን አሁንም ድረስ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ከቆየው አፍርሶ የመገንባት የአብዮታዊነት አባዜ ላለመላቀቃቸው ማሳያ ነው፡፡

በመቀጠል በፕሮፖዛሉ የተጠቀሰውን የሽግግር መንግሥት ምሥረታ በተመለከተ ከሕግ አኳያ አንዳንድ ነጥቦችን አነሳለሁ፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ አቶ ልደቱ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት አያስፈልግም በሚል ጠርዝ ላይ ቆመው የሚከራከሩ ካልሆነ በስተቀር ትልቁ ጥያቄ እሳቸው ይቋቋማል ያሉት 505 አባላት ያሉት ሸንጎና አስፈጻሚ ካውንስል የሚቋቋመው በምን የሕግ መሠረት ላይ ነው? ወይስ ወደ 1983 ዓ.ም. ተመልሰን የሽግግር ቻርተር ልንቀርጽ ነው? ለማንም በግልጽ እንደሚታወቀው ሕገ መንግሥቱን አሥር ጊዜ ብናነበውም የሽግግር መንግሥት ስለማቋቋም የሚደነግገው ነገር የለም፡፡

የዚህ ፕሮፖዛል አቅራቢ የሽግግር ሒደቱን ይመራል የተባለው የሽግግር መንግሥት ማለትም ሸንጎ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል በሚደረግ ድርድር አሁን ባለው ፓርላማ መጽደቅ አለበት ይላሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ ውስጥ ሕገ መንግሥቱን የመቀበልና ያለመቀበል በሁለት ባላዎች የቆሙ ተቃራኒ ሐሳቦች ይታዩኛል፡፡ ይህም በአንድ በኩል የሽግግር መንግሥቱ በፓርላማ መጽደቅ አለበት ሲሉ የፓርላማውን ሚናና ላቋቋመው ሕገ መንግሥት ዕውቅና የመስጠት፣ በሌላ በኩል በሕገ መንግሥት የተቋቋመን ፓርላማና አስፈጻሚ አፍርሶ ሸንጎና ካውንስል በማቋቋም የሕገ መንግሥቱን ሕጋዊ ኃይልና ተፈጻሚነት ያለመቀበል ናቸው፡፡ ይህ አካሄድ ‹‹ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ›› የሚለውን የአገራችንን ብሂል ያስታውሰኛል፡፡

በዚህ ዓይነት በፕሮፖዛሉ የተጠቀሰውን የሽግግር መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየትኛው ሕጋዊ ሥልጣኑ ነው እንዲያጸድቅ የሚጠበቀው? ፓርላማው በሕገ መንግሥት ያልተሰጠውን ተግባር በምን አግባብ ነው የሚፈጽመው? ለሚሉት ጥያቄዎች የፕሮፖዛሉ አቅራቢ ምላሽ እንደሌላቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ፓርላማው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 እንደተደነገገው በአብላጫ መቀመጫ መርህ ያደራጀውን የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል አፍርሶ አገር የመምራቱን ሥልጣን ለሽግግር መንግሥት ይስጥ ማለት የፖለቲካ ዕብደት ካልሆነ በስተቀር ምንም የአመክንዮ መሠረት የለውም፡፡ ሌላው በፕሮፖዛሉ የተመለከተው ሕገ መንግሥቱን እንደሌለ የመቁጠርና በሕገ መንግሥቱ የተመሠረተውን መንግሥት ወደ አለመቀበል ፍፁም ኢሕገ መንግሥታዊ የመጨረሻ ጥግ የሄደ ሐሳብ ማሳያው የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው ፓርላማ ሕገ መንግሥቱ ከደነገገው ውጪ ተበትኖ ወይም ራሱን አፍርሶ 505 አባላት ያሉት ‹‹የህዳሴ›› ሸንጎ (እኔ የባቢሎን ሸንጎ ነው የምለው) እንዲተካው የሚለው ነው፡፡

እንደሚታወቀው ፓርላማውም ሆነ አስፈጻሚው አካል ማለትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህልውናቸውን የሚያጡበት ሕጋዊ አግባብ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ አንደኛ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(3) እና 72(3) መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመን ሲያበቃ ሁለተኛ በአንቀጽ 60(1) እና (2) በተደነገገው መሠረት በምክር ቤቱ ፈቃድ የሥልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ፓርላማው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲበተን ወይም በፓርላማው የመንግሥትን ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ከፈረሰና አብላጫነት ካጡ በፕሬዚዳንቱ ጋባዥነት አዲስ መንግሥት ለመፍጠር ወይም የነበረውን ጣምራነት ለመቀጠል ካልቻሉ ይሆናል፡፡

በዚህ ፕሮፖዛል ሐሳብ መሠረት አሁን ካለው የምርጫ አለማካሄድ ችግር ጋር ተያይዞ በመስከረም መጨረሻ 2013 ዓ.ም. የሥልጣን ዘመኑ የሚያበቃውን ፓርላማ ይኸው የህዳሴ ሸንጎ እንዲተካው ተፈልጎ ከሆነም በግልጽ ምንም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም፡፡ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጡ የተላከላቸው አካላት የሚሰጡት ትርጉም ምን እንደሆነ ከወዲሁ ባይታወቅም፣ የሽግግር መንግሥት ሥልጣን ይረከብ የሚል ሐሳብ በሕግ ፊት ብቻ ሳይሆን አሁን አገሪቱ ካለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር አንፃር በሞራል መመዘኛም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡

በሌላ አቅጣጫ ካየነው በአቶ ልደቱና የሐሳቡ አራማጆች በሆኑ ፓርቲዎች የቀረበው ፓርላማውን ተክቶ እንዲቋቋም የተፈለገው ሸንጎም ሆነ የሽግግር ወይም የባለአደራ መንግሥት ምሥረታን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲም ሆነ መንግሥት የመቀበል ሥልጣንም ሆነ መብት በሁለት ምክንያቶች የላቸውም፡፡ አንደኛ ፓርቲውም ሆነ የተወካዮች ምክር ቤት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕገ መንግሥታዊ አካሄድ ወጥተው በጭቅጭቅ (ለዚያውም ከተሳካ) ይቋቋማል ለሚባል በሕዝብ ላልተመረጠ የሽግግር መንግሥት ሥልጣንን ለማስረከብ የሚያስችል ሕጋዊ ውክልና የላቸውም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 በተደነገገው የሉዓላዊነት መርህ መሠረት ሕዝብ የመረጣቸውና የውክልና ሥልጣን የሰጣቸው በሕገ መንግሥቱ መሠረት አገር እንዲያስተዳድሩና እንዲመሩ በመሆኑ፣ ተወካዮች ወካዩ ሕዝብ ከሰጣቸው የውክልና ሥልጣን የማለፍ መብት የላቸውም፡፡ ሁለተኛ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(2) እንደተደነገገው ፓርላማውም ሆነ አስፈጻሚው አካል ሕገ መንግሥቱን የማክበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነት መወጣት አለመወጣት ተራ የንድፈ ሐሳብና የቃላት ጨዋታ ሳይሆን የአገርን ሉዓላዊነት፣ ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡

በተለይም አሸናፊ ፓርቲውን ወክሎ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 74(13) ድንጋጌ መሠረት ሕገ መንግሥቱን ለማክበርና ለማስከበር በፓርላማ ፊት ቃለ መሃላ ፈጽሞ ሥልጣን የያዘና አገርና ሕዝብን ለመምራትና ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ኃላፊነት የተቀበለ ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ድጋፍ እንኳ ያልተረጋገጠ የፓርቲዎችን ወይም ፖለቲከኞችን ፕሮፖዛል ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል ማለት የብልጣ ብልጥ ፖለቲካ አክሮባት መሥራት ካልሆነ በስተቀር የሚታሰብ አይደለም፡፡

በእኔ በኩል እነዚህን ሕጋዊ ሐሳቦችንና መከራከሪያዎችን ለመጠቃቀስና ሐሳቤን ለመግለጽ የሞከርኩት የፕሮፖዛሉ አቅራቢም ሆነ ሐሳቡን የሚጋሩት ፓርቲዎች ይህ ጉዳይ ይጠፋቸዋል ከሚል የየዋህ አስተሳሰብ ተነስቼ አይደለም፡፡ ፍላጎታቸው ሕገ መንግሥቱን ወደ ታሪክነት መቀየርና ከዜሮ በመነሳት አዲስ ሒደት መጀመርና አገሪቱንና ሕዝቧን የፖለቲካ ቤተ ሙከራ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም ነገሩ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንደሚባለው ቢሆንም፣ ሐሳባቸው በሕዝብ ዘንድ ብዥታን የሚፈጥር አልፎም አደገኛ አካሄድ መስሎ ስለታየኝ ይህን ብዥታ በማጥራት ትንሽም ቢሆን ሙያዊ ግዴታዬን ለመወጣት ነው፡፡

በመጨረሻም በእነዚህ ፖለቲከኞች የሚነሱ ሁለት ጉዳዮችን አንስቼ ሐሳቤን እቋጫለሁ፡፡ ይህም የአሁኑ ችግር የሚፈታው በሕጋዊ አግባብ ነው ሲባል የሚያቀርቡት መከራከሪያ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መቼ ሕጋዊ ሆኖ ያውቃል የሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን አናውቅም ካልሆነ በስተቀር መንግሥት ሥልጣኑን የያዘው ሕገ መንግሥቱ በሚደነግገው የአብላጫ መቀመጫ መርህ መሠረት ፓርላማው አደራጅቶት ነው፡፡ በአገር ውስጥ አገርንና ሕዝብን እየመራና ሕጋዊ ተግባራትን እያከናወነ ያለው ይኸው መንግሥት እንጂ ሌላ አካል አይደለም፡፡ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃርም የተለያዩ ተቋማትና መንግሥታት ግንኙነት እያደረጉ ያለው ከማይታወቅ አካል ጋር ሳይሆን አሁን በሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር ነው፡፡ የዚህ ፕሮፖዛል አቅራቢዎችም እንደ ፓርቲ የተፈጠሩትም ሆነ የሚንቀሳቀሱት የሚነጋገሩትም ይህን መንግሥት በፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍና ሕጋዊነት የለውም ከሚሉት መንግሥት ጋር ነው፡፡

እንደ መቋጫ

እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፡፡ የሕግ ባለሙያ ነኝ፡፡ ፖለቲከኛ ባልሆንም የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፡፡ የአገሬ ዕጣ ፈንታ ያለችበት ሁኔታና መድረሻዋ ያሳስበኛል፡፡ የአገሬን ጤንነት ሕመም ላይ የሚጥል ቅጥ አምባሩ የጠፋበት ፖለቲካ ከሐሳብነት አልፎ ደኅንነቷን ሲፈታተን ያሳስበኛል፡፡ ስለዚህ በምችለው ሁሉ ጠማማው እንዲስተካከል የፖለቲከኖች ሐሳብ ለአገር ፈዋሽ እንጂ ሕመም አባባሽ እንዳይሆን ሐሳቤን የመሰንዘር የዜግነትና የሙያ ግዴታ አለብኝ፡፡ ስለሆነም መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ተቀብሏልና ፖለቲካው ከሐሳብ አልፎ ሰላምን የሚያውክ ሲሆን፣ ያለመለሳለስ ሕጋዊ ወሰኑን ሳያልፍ ሕግ ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ሚዛናዊና ጊዜውን የሚዋጅ ሐሳብ ያላቸው ፖለቲከኞቻችን አሁን እያደረጉ እንዳሉት አዎንታዊ ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንፃሩ ከጊዜያዊ የሥልጣን ፍላጎትና የቅርብ ዕይታ መውጣት የማይፈልጉ ፖለቲከኞች መንገዳቸውን በድጋሚ ይፈትሹ፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ በታሪክና በትውልድ ፊት ተወቃሽ ከመሆን ፖለቲካውን ትተው በሌላ የሥራ መስክ ቢሰማሩ ይሻላቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...