Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ከሁለት ወራት በላይ ራሴን ከእንቅስቃሴ አቅቤ በመክረሜ፣ እስቲ አየር ልቀበል በማለት ራቅ ብዬ ለመሄድ በጠዋት ነበር ከቤቴ የወጣሁት፡፡ እየፈራሁም ቢሆን ባቡር ተሳፍሬ ጉዞ ጀመርኩ ወደ ቃሊቲ፡፡ ከባቡር ወርጄ እግሬን በደንብ እያፍታታሁ ለአንድ ሰዓት ያህል ተንቀሳቀስኩ፡፡ የናፈቀኝን ንፁህ አየር እየማግኩ እስኪ ደክመኝ ድረስ በእግሬ ከተጓዝኩ በኋላ ሜዳ ላይ አረፍ ብዬ ብዙ ቆየሁ፡፡ ደመናው ሲዞር ዝናብ የሚዘንብ ስለመሰለኝ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ ታክሲ ተራ አመራሁ፡፡ ከዚያም ከቃሊቲ ወደ ሳሪስ በሚጓዘው ዶልፊን ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ተሳፈርኩ፡፡ ለሦስት የሚያስቀምጠው መቀመጫ ላይ አንድ አዛውንት ቄስ፣ ከፊታቸው ያለው ወንበር ላይ አንዲት በሃያዎቹ መጨረሻ ላይ የምትገኝ ሴት፣ ኋላ ወንበር ላይ ደግሞ እኔ ተቀምጠናል፡፡ አዛውንቱ ቄስ በመስኮቱ በኩል ተቀምጠው የፀሎት መጽሐፋቸው ላይ አተኩረዋል፡፡ መሀል የተቀመጠችው ሴት ደግሞ ጭንቅ ጥብብ የሚያደርጋት ነገር ያለ ይመስል እየደጋገመች ‘እህህ…እህህ…›› ትላለች፡፡ ምን ሆና ይሆን?

ወያላው በሩን ዘግቶ ሾፌሩን ‘ሳበው’ ሲለው የዚህች ወጣት ሴት ጭንቀት ቀጥሏል፡፡ አንዳንዱ ሰው ‘ምን አገኘህ/ሽ?’ ሲባል ደስ እንደማይለው ባውቅም፣ የዚህች ሴት ጉዳይ ግን ስለከነከነኝ፣ ‹‹የእኔ እህት ምን ሆነሻል?›› ስላት፣ ‹‹ምን የማልሆነው አለ? ሰማዩ ተደፍቶብኝ እኮ ነው?›› ስትል ደነገጥኩ፡፡ አባባሏ መረር ያለ ነገር ውስጡ የያዘ ስለመሰለኝ ለጊዜው ፀጥ አልኩ፡፡ ሰማይ የተደፋበት ሰው ምን ማለት ነው? ይህንን እያሰላሰልኩ ከቆየሁ በኋላ ጥያቄዬን ቀጠልኩ፡፡

‹‹ሳይሽ ወጣት ነሽ ለምንድነው ሰማይ የሚደፋብሽ? እስኪ የሆንሽውን ንገሪኝ…›› በማለት እዚህና እዚያ ሳልል ድፍን አድርጌ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹ወይ ወጣትነት? ልጅነቴን ሳላጣጥመው ማለፉ ሲቆጨኝ፣ ወጣትነቴ ደግሞ እንደ ጤዛ ረግፎ ሞቴን ያስመኘኛል…›› እያለች እንባዋ ሲዘረገፍ የባሰ ደነገጥኩ፡፡ የራሴን ልጅነትና ወጣትነት እያስታወስኩ፣ በጎልማሳነቴ ዘመን የሚፈታተኑኝን ችግሮች ሳስብ ራሴንም ባር ባር አለኝ፡፡ ግን ይህች ሴት በጣም አሳዘነችኝ፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን አዛውንቱ ቄስ ከእኛ ጋር የሉም ማለት ይቻላል፡፡

‹‹በእርግጥም ብዙዎቻችን ከስንት ችግርና መከራ ጋር ነው በየቀኑ እየተጋፈጥን የምንኖረው፡፡ የአንዳችን ከሌላችን ጋር በዓይነትም ሆነ በመጠን ቢለያይም የችግርና የመከራ ገፈት ቀማሾች ነን፡፡ ለብቻ ከመብሰክሰክ ግን ሲተነፍሱት ትንሽ ቀለል ይላል…›› እያልኳት በስንት መከራ አግባብቼ የሚከተለውን አሳዛኝ ጉዳይ ነገረችኝ፡፡ በሕይወታችን ውስጥ በየዕለቱ የሚገጥሙን የፍትሕ ዕጦትና የድህነት ጉስቁልና ምን ያህል አንገብጋቢ እንደሆኑ ይህንን መጠነኛ ማሳያ፣ ነገር ግን የአገር ነቀርሳ የሆነ ጉዳይ ተከታተሉ፡፡

ይህች እኔ በሃያዎቹ መጨረሻ የገመትኳት ወጣት ሴት ዕድሜዋ 32 ነው፡፡ ወላጅ አባትና እናቷ በልጅነቷ ሞተው ያደገችው ጠላና ካቲካላ እየሸጡ ድህነትን ከሚታገሉ አክስቷ ጋር ነው፡፡ መሀን አክስቷ በተቻላቸው መጠን እሷን ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ቢውተረተሩም፣ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለች በ15 ዓመቷ እሳቸውም ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ፡፡ ሰማይና ምድር የተደፉባት ዘመድ አልባ ታዳጊ አክስቷ ቤት ውስጥ እየኖረች ሻይ፣ ቡና፣ ሳንቡሳና አንባሻ መሸጥ ትጀምራለች፡፡ የማታ ትምህርቷንም ትቀጥላለች፡፡

አንድ ቀን ምሽት ኃይለኛ ዝናብ እየጣለ ሳለ ድንገት የቤቱ በር ይንኳኳል፡፡ ማን ይሆን የመጣው ብላ ስተከፍት ሁለት ጎረምሶች ዘለው ይገባሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ተጋግዘው ልብሷን ላይዋ ላይ ቀዳደው ይደፍሯታል፡፡ ክብረ ንፅህናዋም ይገሰሳል፡፡ ከብዙ ቆይታ በኋላ ስትነቃ ራሷን ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አገኘችው፡፡ እንደ ምንም ለመነሳት ብትሞክር ኃይለኛ የራስ ምታትና እንደ ተደበደበ ሰው መላ አካላቷን ቅጥቅጥ ስሜት ይሰማታል፡፡ መነሳት ባለመቻሏ የተኛችበት ይነጋል፡፡

ከረፋፈደ በኋላ በመከራ ተነስታ ለመቆም ብትሞክር ሕመሙ በጣም በርትቷል፡፡ እንደ ምንም ብላ ከባልዲ ውስጥ ውኃ ቀድታ በመጠኑ ከተጣጠበችና ራሷን ካረጋጋች በኋላ፣ በምሽት የተፈጸመባት ድርጊት ታወሳት፡፡ እንደ ተለመደው ሻይ፣ ቡናና የመሳሰሉትን የሚፈልጉ ሰዎች ቢመጡም ‘አሞኛል’ ብላ መለሰቻቸው፡፡ የተፈጸመባትን አስከፊ ድርጊት ለማን ትንገር? ስትፈራ ስትቸር ፖሊስ ጣቢያ ሄደች፡፡ የደረሰባትን ስትነግራቸው የግለሰቦቹን ማንነት ጠየቋት፡፡ አታውቃቸውም፡፡ የሰው ምስክር ተባለች፡፡ በምሽት ብቻዋን ባለችበት ኃይለኛ ዝናብ እየዘነበ የምን ምስክር ነው? ግራ ገባት፡፡ ‹‹በቃ እናንተ ቤት ሰብረው እንደሚዘርፉ ሌቦች፣ ይህንን ድርጊት የፈጸሙትን በፖሊሳዊ ሙያችሁ ተከታትላችሁ ለሕግ አቅርቡ…›› ብትል ማን ይስማ? የእሷ አቤቱታ በዚህ ተዘጋ፡፡

ከዚያ መደፈር ጋር በተያያዘ ፅንስ ይዛ ኖሮ ጊዜው ሲደርስ ሴት ልጅ ተወለደች፡፡ እናት ናትና የአብራኳን ክፋይ አባቷን ሳታውቅ ማሳደግ ጀመረች፡፡ አይሆኑ ሆና ያሳደገቻት ሴት ልጇ 14 ዓመት ሆናት፡፡ በትምህርቷም ጎበዝ ናት፡፡ አንድ ቀን እሷ ጉልቷን የምትቸረችርበት ቦታ ላይ እያለች ልጇ ፍዝዝና ድንግዝግዝ ብላ መጣች፡፡ ‹‹ገና ሳያት ደነገጥኩ፡፡ በእኔ ላይ የተፈጸመው ድርጊት እሷንም እንደደረሰባት ገባኝ…›› ብላ ለቅሶዋን ስትለቀው አንጀቴ ተንሰፈሰፈ፡፡ በእርግጥም ልጇን አንድ ጎረምሳ በሥለት አስፈራርቶ ደፍሯታል፡፡ ወይ ዕድል?

ይኼ አገር ያወቀው ጥጋበኛ ጎረምሳ እናትና ልጅን እያስፈራራ መቆሚያ መቀመጫ አሳጣቸው፡፡ ለፖሊስ ወይም ለቀበሌ ቢናገሩ በጩቤ ተዘልዝለው ሜዳ ላይ እንደሚጣሉ አስፈራራቸው፡፡ እናት እንደ ምንም ብላ ነገሩን ለፖሊስ ብትናገርም፣ ልጅቷን ካላመጣሽ ዞር በይ ተባለች፡፡ ልጂት ደግሞ በየጊዜው ላይዋ ላይ የሚመዘዘውን ጎራዴ መሰል ጩቤ እያስታወሰች እንቢ አለች፡፡ እናት ፖሊሶቹን እስቲ ቤት ድረስ መጥታችሁ በሰቀቀን ውስጥ ያለችውን ልጅ አናግራችሁ የምርመራችሁ መነሻ ይሁን ብትል የበፊቱ ዓይነት መልስ ተሰጣት፡፡ ‹‹ልጄ አሁን ከማንም ጋር መተያየትም ሆነ መነጋገር አትፈልግም፡፡ ከዚያን ቀን በኋላ በቀንም ሆነ በሌሊት ያቃዣታል፡፡ ጥጋበኛው ጎረምሳ በየቀኑ እየመጣ ዋ! እያለን ነው… በየጊዜው ተደብቄ ሄጄ ለፖሊስ ብናገርም እኔንም ወፈፌ አደረጉኝ…›› ብላ ሳሪስ ሳንደርስ ታክሲውን አስቁማ እየተንሰቀሰቀች ወርዳ ተለየችን፡፡ ኧረ የፍትሕ ያለህ የሚሉ ነፍሶች በዝተዋል፡፡

(ዳግም አርዓያ፣ ከጎተራ ኮንዶሚኒየም)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...