Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጀት አጠቃቀምና የኮሮና ወረርሽኝ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጀት አጠቃቀምና የኮሮና ወረርሽኝ

ቀን:

በሞላልኝ መለስ

የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከተከሰተ ጀምሮ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፉም ባሻገር ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ባላቸው አገሮች ጭምር ከባድ የሆነ ማኅበራዊ፣ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል፡፡ ከሌላው ዓለም ጋር በንፅፅር ሲታይ በአሁኑ ወቅት ባለው ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ የሰው ሕይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት የከፋ ባይኖርም፣ ወደፊት በግልጽ የሚታይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር እንደሚያስከትል ዕሙን ነው፡፡

በሽታው የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ብቸኛው መንገድ የበሽታውን ሥርጭት አስቀድሞ መከላከል ብቻ መሆኑን፣ በሽታው ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ ግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፡፡

- Advertisement -

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ ሲባል ቤተ እምነቶች፣ ፍርድ ቤትና ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ እንቅስቃሴ በእጅጉ ተገድቧል፡፡ አዛውንት መጠየቅ አስፈሪ ሆኗል፡፡ በከፍተኛ ማኅበራዊ ትስስር የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአብነት እንደ ዕድር፣ ዕቁብ፣ ሠርግ፣ ማኅበር፣ ወዘተ ያሉ ማኅበራዊ ትስስሮችን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ አቋርጧል፡፡ 

መንግሥት የወረርሽኙን ሥርጭት የመከላከል ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ በእስከ ዛሬው ሁኔታ የኮረና ቫይረስ በአብዛኛው ምናልባትም ከ95 በመቶ በላይ ያህል የተከሰተው የውጭ ጉዞ ካላቸው ሰዎች ጋር የተገናኘ ከመሆኑ አንፃር፣ መንግሥት ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ከ14 እስከ 21 ቀናት የኳራንቲን ማቆያ በማድረግ በሽታው በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥርጭት እንዳይኖረው ለመገደብ የሚያስችል ጠንካራ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የበሽታው ሥርጭት ከፈጠረው ሥጋትና በተለያዩ አገሮች ከተወሰደው የገቢና የወጪ የሰዎች የጉዞ ዕገዳና የዕቃዎች እንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት፣ በአገራችን በኢኮኖሚ ረገድ ከፍተኛ መቀዛቀዝ መታየት ጀምሯል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ከሚፈጥረው አሉታዊ ተፅፅኖ በተጨማሪ፣ በመጪው ዘመን ከፍተኛ የሆነ ምንዛሪ ምንጭ የሆኑት ሐዋላ፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ፣ የኤክስፖርት ሥራዎች በአጭር ጊዜ መሻሻል ያሳያሉ ተብሎ አይገመትም፡፡ 

በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሰማሩበት የሥራ መስክ በኮሮና ቫይረስ በእጅጉ የተመታ ሲሆን፣ ለማገገም ምን ያህል ጊዜ እንደሚያስፈልግ ማንም የኢኮኖሚ ጠበብት ሊተነብይ አይችልም፡፡ የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች የደረሰባቸው አደጋ በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በኤክስፖርቱም ቢሆን የንግድ ግንኙነቶች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ተመልሰው ከአፍሪካ የሚመጡ የእርሻ ውጤቶችን ተቀባዮች በድፍረት ለመውሰድ የሚፈጅባቸውን ጊዜ ማወቅ ያዳግታል፡፡

ዛሬ ዓለም ባልጠበቀው ሁኔታ በየዕለቱ ዋና ሥራው መብላትና መተኛት ብቻ ሆኗል፡፡  እንደ አበባ ያሉ ምርቶቻችን እንደገና ወደ ገበያ የሚወጡበትን ጊዜ ለመገመት ያዳግታል፡፡  እንደ ማንኛውም የዓለም አየር መንገዶች በአፍሪካ ተወዳዳሪ ያልነበረው አየር መንገዳችንም፣ መጪውን ፈተና ተወጥቶ እንደ ቀድሞው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የጀርባ አጥንት የሚሆንበት ጊዜ መቼ እንደሆነ መገመት ያዳግታል፡፡ የመስኩ ጠበብቶች እስከ ሁለት ዓመት ይገምታሉ፡፡

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለመመለስ በዓለም ደረጃ ሰዎች ጉዞ ለማድረግ ሙሉ እምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ መቼ እንደሚመጣ በግልጽ ማወቅ ያዳግታል፡፡  በእነዚህ ሁሉ ሴክተሮች ያሉ ባለቤቶች፣ ሠራተኞችና ሌሎች ተጓዳኝ ባለ ድርሻ አካላት የወደፊት ጉዞ እንዴት እንደሚሆን በሒደት የሚታይ ነው፡፡ ፈታኝ መሆኑ ግን አይቀሬ ነው፡፡

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአገሪቱ ላይ የተደቀነውን ዘርፈ ብዙ ችግር በአሸናፊነት ለመወጣት መንግሥት አቅም በፈቀደ መንገድ በርካታ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡  በቅርቡም ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተከታታይ ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡

ከኢኮኖሚው መቀዛቀዝና የውጭ ምንዛሪ አመንጪ የነበሩት ዋና የንግድ ሥራዎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ምንጭነታቸው ከመድረቁ ጋር በተያያዘ፣ መንግሥት ለከፍተኛ ወጪ ሊዳረግ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ መንግሥት የገቢ ምንጩ በአንድ በኩል በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ቢሆንም፣ የኮሮና በሽታን መከላከል ደግሞ በራሱ ብዙ ተጨማሪ ወጪዎችን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ያፈጠጡ እውነታዎች ማስታረቅ ቀላል ሥራ አይደለም፡፡

መንግሥት ይህን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት የመንግሥት ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ዕርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ እስካሁን የተወሰዱት ዕርምጃዎች ብቻቸውን ግን በቂ ናቸው ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ የበሽታው ሥርጭትና የሚያስከትለው ጉዳት በመጪዎች ወራት የከፋ ሊሆን እንደሚችል በሕክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከሚሰጡት ማሳሰቢያና ከዓለም ሁኔታ በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው፣ በመንግሥት ገቢና ወጪ መካከል የሚኖረው ልዩነት ወደፊት በጣም እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችል መረዳት ከባድ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ወጪውን ለመቀነስ ተጨማሪና ተከታታይ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ወጪዎችን ለመቀነስ ሊወስዳቸው ከሚችላቸው ዕርምጃዎች አንፃር የሚከተሉት ሁኔታዎች በተጨማሪነት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ እናምናለን፡፡

ከሰኔ ወር ጋር በተያያዘ የሚደረጉ “የበጀት መድፋት” እሽቅድምድሞችን መግታት

እንደሚታወቀው ሰኔ ወር የአገሪቱ በጀት መዝጊያ ነው፡፡ ሰኔ ወር በመሠረቱ ለኢትዮጵያውያን ብዙ ነገር ነው፡፡ የክረምት ወራት መጀመርያ፣ የተማሪዎች የትምህርት ዘመን መጨረሻ፣ የዝናብ ወቅት መጀመርያ፣ የእርሻ ሥራ ማብሰሪያ፣ የበጀት መዝጊያ፣ የሚቀጥለው ዓመት በጀት ማቀጃ፣ ወዘተ ነው፡፡

በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኮሮና ይዞ እየመጣ ያለውን የጨለማ ዘመን ለመወጣት እንዴት መንግሥት ቀሪውን በጀቱን መጠቀም እንዳለበት አዳዲስ ሐሳብ ከማቅረብ ይልቅ፣ እንደ ቀድሞው ሁሉ የበጀት ዓመቱ ከማለቁ በፊት በርካታ ጨረታዎችን በማውጣት መንግሥትን በኮንትራት ማሰር የብዙ መሥሪያ ቤቶች የዕለት ተዕለት ተግባር እየሆነ ይስተዋላል፡፡ በጋዜጦች፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ ወዘተ የሚያስተላልፉት የጨረታ ማስታወቂያ መንግሥት በአንድ በኩል የሚያደርገውን ጥንቃቄ፣ በሌላ በኩል እየሸረሸረው መሆኑን ያልተረዳ ያስመስለዋል፡፡

በመሠረቱ መንግሥት ልማት የሚያካሂደው በአብላጫው ከታክስ፣ ከዕርዳታና ከብድር በሚያገኘው ገንዘብ እንደሆነ ዕሙን ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ የመንግሥት በጀት ምንጮች ቢያንስ በሚቀጥለው ዓመት በእጅጉ እንደሚጎዱ መንግሥት ከወዲሁ ተንብዮ ልዩ ልዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር የበጀት ዓመቱ ማለቁን ተከትሎ በየመሥሪያ ቤቶቹ እየወጡ ያሉ ጨረታዎችን በማገድና አንዳንዶቹን ውሎችንም በመሰረዝ፣ መንግሥትን ከተጨማሪ ወጪዎች መታደግ ይቻላል፡፡

ይህ የኮሮና ዘመን እስኪያልፍ ከፍተኛ የሆነ ቁጠባን መሠረት ያደረገ የበጀት አጠቃቀም በግልጽ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል፡፡ በስፋት በመገዛት ወይም በሒደት ላይ ያሉ የቢሮ ዕቃዎች፣ የውጭ ግዥ፣ የተሽከርካሪዎች ግዥ፣ በፍፁም አንገብጋቢ ያልሆኑ የግንባታ ሥራዎች፣ ወዘተ ቢያንስ የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት በቁጥጥር ሥር እስኪሆን ድረስ በመግታት፣ በጀቱን የኮሮና በሽታን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ ለመቀነስ ማዋል ተገቢ ይሆናል፡፡

ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ያልሆኑ ፕሮጀክቶችን ለጊዜው ማገድና ማቋረጥ

የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ሊቋረጡ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቶቹ ባሉዋቸው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዎች ተመዝነው፣ አንገብጋቢ የሆኑና ያልሆኑ ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታቸውና ያላቸው ፖለቲካዊ አንድምታ ከፍተኛ የሆኑት ለአብነት ያህል የህዳሴ ግድብና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ አንገብጋቢ ፕጀክቶች በመሆናቸው ሊቋረጡ የሚችሉ የልማት ሥራዎች አይደሉም፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ካላቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ፣ ከሚይዙት የሠራተኛ ኃይል አንፃር ሲታይ የፕሮጀክቶቹ መቋረጥ በማናቸውም መመዘኛ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን፣ የውኃ ፕሮጀክቶችን፣ ማናቸውም የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን፣ ወዘተ መቋረጥ የለባቸውም፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ ፕሮጀክቶች ግን የኮሮና በሽታን ከመከላከልና የሚያስከትለውን ቀውስ ለመቀነስ ሊከናወን ከሚችለው ተግባር አንፃር ተመዝነው ሲታዩ፣ በአንገብጋቢነታቸው ከኮሮና በሽታ የበለጡ አለመሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በአገራችን የኮሮና በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እየመጣ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ኮሮና በሽታ በአውሮፓ አገሮችና በአሜሪካ ያለውን የመስፋፋትና ጉዳት የማድረስ ሒደት ስንመለከት የምንረዳው፣ በሽታው ከፍተኛ ሕዝብ የሚኖርባቸውን ከተሞች የሚያጠቃ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በአገራችን ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ የሚችለው በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚሆን ግምት መውሰድ ይቻላል፡፡

በመሆኑም የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኮሮና በሽታንና የሚያስከትለውን ቀውስ ለመከላከል ከፍተኛ በጀት ለከተማው መመደብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኮሮና በሽታ በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት አኳያ ይህ ከፍተኛ የሆነ በጀት ከመንግሥት የገቢ ምንጮች በቀላሉ ሊገኝ አይችልም፡፡ በዚህ ዕሳቤ መሠረት መንግሥት ለከተማው ሊመድበው የሚገባውን በጀት ሊያገኝ የሚችለው፣ ለከተማው ከተመደበው በጀት ላይ በመቀነስ ለኮሮና በሽታ የመከላከያ ተግባር በጀቱን በመመደብ ብቻ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንገድ ሥራዎች ከፍተኛ በጀት በመመደብ ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የፕሮጀክቶች አንገብጋቢነት ከኮሮና በሽታ አንፃር ቢመዘን፣ የፕሮጀክቶቹን መከናወን የግድ የሚል አንገብጋቢነት በውስጣቸው አናገኝም፡፡ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ከኮሮና በኋላ ሊከናወኑ የሚችሉ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በከተማዋ ውስጥ በራሱ አቅምና በሥራ ተቋራጮች የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች፣ ከዚህ አንፃር ሊታዩና ሊፈተሹ ይገባል፡፡ በተለይ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች መንግሥትን አዳዲስ ተጨማሪ ወጪዎች ውስጥ የማይከቱ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ይዞታን ከማስከበር አንፃር ነዋሪዎችን ከመኖሪያቸውና ከሥራ ቦታቸው የማያፈናቅሉ፣ እንዲሁም ይዞታዎችንና ሕንፃዎችን የማያፈርሱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የኮሮና ዘመን በአዳዲስ ፕሮጀክቶች ወይም ባሉበት ሁኔታ አገልግሎት እየሰጡ ሊቆዩ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በቂና አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በጥድፊያ ለመጨረስ በሚደረግ ሩጫ፣ የከተማዋን ነዋሪዎች ቤታቸውን በማፍረስ ከመኖሪያቸው ማፈናቀል፣ እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ የገቢያቸው ምንጭ ማቆራረጥ ከበሽታው በላይ የሚያሰቃይ ተግባር ይሆናል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ቀውስ ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ የገንዘብ አቅምን የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር፣ መንግሥት ብቻውን ሊወጣው እንደማይችል በመግለጽ ሁሉም ዜጋ በገንዘብና በሎጂስቲክስ ዕርዳታ እንዲያደርግ ባደረገው ጥሪ፣ ዜጎች ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር አጣዳፊ ያልሆኑ ነባር ፕሮጀክቶችን ባሉበት ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ እንዲቆዩ በማድረግና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ባለመጀመር ከፍተኛ የሆነ የካፒታል ፕሮጀክት ወጪውን በመቀነስ የኮሮና በሽታን ለመዋጋት የሚያስችል የበጀት አቅም በራሱ እንዲፈጥር ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ አስተዳደሩና የከተማው የመንገዶች ባለሥልጣን ለልማት ተነሽ ለሚከፈል ካሳና ለሥራው ከፍተኛ ወጪን የሚያስከትሉ ነባር ሥራዎችን በማስቀጠልና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር ተጠምደው ማየት አሳዛኝ ነው፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ሥራዎቹን በሚታይ ሁኔታ በመቀነስና በሟቋረጥ፣ እንዲሁም የካፒታል በጀት ወጪውን በመቀነስ፣ የኮሮና ወረርሽኝ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ሥጋት የደቀነባትን አዲስ አበባ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመታደግ የሚያስችል የበጀት አቅም መፍጠር ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...