Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከምርጫው በፊት ሦስት ዓበይት ጉዳዮች

ከምርጫው በፊት ሦስት ዓበይት ጉዳዮች

ቀን:

በሰሎሞን መለሰ ታምራት

ዛሬ ወደ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አመራርነት የተሸጋገሩ የቀድሞ ባለሥልጣን በአንድ ወቅት ሲናገሩ፣ ኢትዮጵያ በታላቁ መጽሐፍ ስሟ ተደጋግሞ በመገለጹ የትኛውንም ዓይነት መከራ ታልፋለች ማለት የዋህነት ነው ካሉ በኋላ ሶሪያ ከኢትዮጵያ በተሻለ ስሟ በመጽሐፍ ቅዱስ የተነሳ አገር በመሆኗ ዛሬ ያለችበትን መከራ ለመሻገር እንዳላስቻላት በምሳሌ አስደግፈው አሟርተውብን ነበር፡፡ እኔ የእሳቸውን ያህል ጥናትና ምርምር ባላደርግም ቅሉ፣ በተግባር የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያሳየኝ ይህች አገር ከፈጣሪ ጥበቃም የተሻለ ካለ የምትጠበቅበት አንድ የሆነ አስማት ነገር ሊኖር ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁኝ፡፡ ታሪክን ጠንቅቆ የሚረዳ ሰው ቢኖርማ እንኳን ኢትዮጵያን ተንኩሰው ይቅርና በእጅ አዙርም ጣልቃ ሊገቡ የሞከሩ መንግሥታት የደረሰባቸውን መከራ ሚስጥሩን ለማወቅ በቻለ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ መጥፋት ቢኖርባት ከዛሬው የለውጥ እንቅስቃሴ በከፋ ሁኔታ የ1966ቱ አብዮት ይዞት የመጣው ጣጣ ገደል ይከታት ነበር፡፡ ዛሬ እያየንና እየተሸበርንበት ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ያንጊዜ ከነበረው ሁኔታ ጋር ስናስተያየው የትየለሌ የዛሬውን ሁኔታ እናመሠግነዋለን፡፡ በአገሪቱ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የታጠቁ ወጣቶች ጎራ ለይተው የተጨፋጨፉበትን የእዚያን ጊዜ “ዓብዮት” ያልደረሰበት ሰው ቢነገረው ከቶም ሊያምን አይችልም፡፡ ጥራኝ ዱሩ ብሎ ጫካውን ካጨናነቀው የመሬት ከበርቴና ባላባቱ ውጪ፣ የመንግሥቱ ዋና መቀመጫ በሆነው አዲስ አበባ ውስጥ በእየ ዕለቱ ምሽት ላይ የጦርነት ቀጣና ይመስል ሲተኮስ የሚያድረው ጥይትና ማለዳ ላይ በእየ መንገዱ የሚቆጠረውን አስክሬን፣ ዛሬ በኮረና ቫይረስ ምክንያት ከሚወጡት የጤና ሚኒስቴር መግለጫዎች ጋርም ይሁን “ተከበብኩ” በሚል ጥሪ ከተፈጠረው ግርግር ጋር ፈፅሞ ልናነፃፅራቸው አይቻለንም፡፡ መቼ በዚህ ብቻ ሊበቃን? በሰሜን ኢትዮጵያ ሻዕቢያ የተባለው የኤርትራ ተገንጣይ ቡድን አስመራን ለመያዝ ከበባውን እያጠበቀ ሲሆን፣ በምሥራቅና በደቡብ ኢትዮጵያ በወቅቱ ከነበሩት የአፍሪካ አገሮች አንፃር እስከ አፍንጫው ድረስ የታጠቀው የሶማሊያው ወራሪ ሠራዊት በሩጫ ዕርምጃ ወደ መሀል አገር እየገሰገሰ በነበረበት ጊዜ ያልፈራረሰች አገር በምን ተዓምር ተጠብቃ ያንን ፈታኝ ወቅት ተሻገረች ለማለት ያስችላል? ዛሬ ተረት ተረት የሚመስሉት የመንና ሊቢያ፣ ሶሪያና ሶማሊያ ብትንትናቸው የወጣው እኮ እንደማንኛውም ግጭት የጎረቤት አገሮች ጣልቃ ገብነት ቢኖርበትም ጥቂት ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች በአገር ውስጥ የጀመሩት እንኳ ሰላንቲያ ወደተካረረ ግጭት በመሸጋገሩ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም የከተማ ትግል የሚያስብ፣ ከፋኝ ብለው ጫካ የገቡትም ቢሆኑ ጥቂት ኩርኩም ሲቀምሱ የአስታራቂ ያለህ እያሉ ከማለቃቀስ ውጪ አቅም የሌላቸው ሽፍቶች ናቸው ያሉት፡፡ ከእዚያ ውጪ በተገኘው የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ብቅ እያሉ አሳዳጊ እንደበደላቸው ዱርዬዎች ለጆሮ የሚቀፍ ትንታኔያቸውን ከሚሰጡት ሥራ ፈቶች በስተቀር ነፍስ ያለው ነፍጠኛ እንኳን በሌለበት አገር ኢትዮጵያ ትበተናለች ማለት ቅዱሳት መጻሕፍትን ብቻም ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ታሪክንም ጭምር አለማወቅ ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል? እኔ በበኩሌ በዚች አገር ውስጥ ነፍጥ ይዞ የሚነሳ የትኛውም ተቃዋሚ ራሱን በራሱ ከማጥፋት፣ ተከታዮቹንም ከማስፈጀትና ሌላ ክፉ የታሪክ ጠባሳውን አኑሮ ያልፍ እንደሆነ እንጂ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚል ሞኝ አስተሳሰብ በውስጤ ጭላንጭል እንኳን ቦታ የለውም፡፡

የ66ቱ ዓብዮት የበላቸው ምጡቅ አዕምሮ እንደነበራቸው ያሉ ወጣቶችን ያጣች አገር ዛሬ በማኅበራዊ ሚዲያ አርበኞች ተመርቶ ግርግር የሚፈጥር መንጋ እንደማያፈርሳት ብተማመንም፣ መንጋም ይሁን ታጋይ ምሁርም ይሁን መኃይም በቋፍ ላይ ያለው በጭፍን እየተመራ ወደ ገደል ጫፍ የሚነዳው የወገኖቼ የኢትዮጵያውያን ሕይወት ግን እጅግ በጣም ያሳዝነኛል፣ ግን ምን ማድረግ ይቻላል? ከታሪክ የማይማሩ ሁሉ ታሪክን ለመድገም ይገደዳሉ፡፡ ይህቺ አገር ሊያጠፋት ነው የተባሉ ወቅቶችን አሳልፋ አሁን ላይ የደረሰች ብትሆንም በርካታ ልናገኛቸው የማንችላቸውን ዕድሎች እያሳለፍን በዚህ ወቅት ላይ የተገኘን ኢትዮጵያውያን በድጋሚ ልናገኘው የማንችለው ዕድል እንዳያልፈን ስለሰጋሁኝ የማስታውስበትን መላ ሳስብ ነው ፈጣሪ አልያም ሌላ አጥብቆ የሚታደጋት አንድ ኃይል መኖሩን ለማስረዳት ከላይ ያለውን መግቢያ የዘረዘርኩት፡፡

ዛሬ ከእነ ሥጋቱም ቢሆን የዴሞክራሲን ቱሩፋት ልንቋደስ አንድ ዕርምጃ ሲቀረን በድንገት በተጋረጠብን የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በርካቶችን እያወዛገበ የሚገኘው የአገራችን አጀንዳ በኮሮና ቫይረስና በምርጫ 2012 መካከል የሚዋልል ሆኗል፡፡ ገሚሱ መንግሥት ምርጫውን በወቅቱ የማያከናውን ከሆነ የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ ሥልጣን ያካፍለን ሲል፣ ገሚሱ ደግሞ ምርጫው የት ይሄድብናል ቅድሚያ የመጣብንን ፈተና በአግባቡ እንወጣው በማለት ላይ ይገኛል፡፡ ለየት የሚለው የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ‹‹በክልላችን ምርጫውን አካሂደን ለሕገ መንግሥታችን ያለንን ታማኝነት እንገልጻለን፤›› የሚለው መግለጫም ለዓይነት ያህል ተለይቶ የቀረበ ሐሳብ ነው፡፡ ችግሩ ግን ሁሉም ሐሳቡን ሲያቀርብ ደብለቅ የሚያደርጋት ጉልበት ቢጤ ካልጨመረ የሚሰማ የማይመስለው መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ምርጫው ካልተካሄደ ከመስከረም 30 በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት የለም ሠራዊቱም አይታዘዝም (ለሠራዊቱ ደመወዝ ማን እንደሚከፍለው አልተነገረንም) በማለት መላ ምታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከመስከረም ሰላሳ በፊትም ቢሆን ‹‹የፖለቲካ ቀውሱ ሊከሰት እንደሚችል›› በመተንበይ ላይ ተጠምደዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ስሙን እንጂ በተግባር እንደማናውቀው ያለፈው ሁለት ዓመት ተሞክሯችን አሳይቶናል፡፡ ለስሙም ቢሆን ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል መስማት የጀመርነው ከ1966ቱ ለውጥ በኋላ ሲሆን በወቅቱ የተቋቋሙት ሁሉም ፓርቲዎች የማሌን ርዕዮት የሚከተሉ በመሆናቸው ስለምን ዓይነት ዴሞክራሲ እንደሚያወሩ እንኳን ለተራው ሕዝብ ለራሳቸውም ግልጽ አልነበረም፣ በእዚያን ወቅት እነሱ የሚፈልጉት ዓይነት መንግሥት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሕወሓት ካሳየን ዴሞክራሲ የተለየ ያሳዩን ነበር? ያም ሆኖ እጅግ በጣም ለአጭር ጊዜ (For a Brief Moment) በ1997 ምርጫ እስከ ዋዜማው ድረስ በጨረፍታ እንድናየው ዕድሉን አግኝተን በወቅቱ ኢትዮጵያውያን የፍርኃቱንም ይሁን የፍስሃውን መጠን ለማስተዋል ችለናል፡፡

በሥልጣን ላይ የነበረውም ሆነ በወቅቱ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም በየፊናቸው የ“ዴሞክራሲ” ጠበቃነታቸውን ሊያሳዩን ሲታትሩ ሰንብተው በእዚያችው አጭር ጊዜ እርስ በርስና አንዳቸው ከሌላኛው አንፃር በጋራ ተባብረው ያችኑ በጭላንጭል ያየናትን የዴሞክራሲ ጮራ በአፍጢሟ ደፍተው አሳይተውናል፡፡ በዚህም ሊጎበኘን ብቅ ብሎ የነበረውን ጥቁር እንግዳ አስቀይመውብናል፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ዛሬም ይህንኑ ታሪክ ልንደግመው ዳር ዳር አያልን እንገኛለን፡፡

መቼም COVID-19 (የኮሮና ቫይረስ በሽታ) ለኢትዮጵያ ከፈጣሪ የተላከ ገጸ በረከት ነው የሚል ተከራካሪ ቢነሳ ‹‹ጨርቁን ጥሎ ያበደ ከየት መጣብን ደግሞ›› ተብሎ መፈረጁ የሚቀር አይመስለኝም (ጥሩው ነገር ዛሬ በአገራችን ጨርቃቸውን ባይጥሉም እንደ ዕብድ የሚያስቡ በርካታ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች በመኖራቸው ማንም ከቁብ የሚቆጥረው ሰው አይኖርም)፡፡ እኔ ግን ዓይኔን በጨው አጥቤ የአማርኛው ትርጉም በቅጡ ባይገልጸውም ኮሮና ለኢትዮጵያ (A blessing in Disguise) ነው ብዬ ብገልጸው ቢያንስ “እንዴት? ‹‹ብሎ የሚጠይቀኝ ይኖር ይሆናል እንጂ በቀጥታ ‹‹አንድ ደግሞ ያበደ ፖለቲቪስት (Political Activist)›› መጣ ብሎ የሚፈርጀኝ አይኖርም፡፡

ወደዋናው የጽሑፌ ጉዳይ ስገባም ምርጫም ይሁን የአገሪቷ ሰላምና ጤና መሆን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው በሚለው ተስማምቼ፣ ጉዳዩን ከእዚያም ባለፈ ዘላቂ ጥቅማችንን ባማከለ መልኩ እንዴት ሊከናወን ይችላል ለሚለው ነገር ትኩረቴን መስጠት አስፈልጎኛል፡፡ ዴሞክራሲ የሚፀናው በተቋማት ላይ መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሮናል፣ የእኛኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› የሚለውን ቅፅል ለአገራቸው ብሔራዊ መጠሪያነት የሚጠቀሙ ቢሆንም፣ ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲ የሆኑ አምባገነን መንግሥታት ሥልጣኑን የሙጥኝ ብለው የሚገኙበት ዋነኛው ምክንያት ዴሞክራሲውን የሚቆጣጠሩና ከመስመር ሲወጣም የሚያስተካክሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ የሚፈጠሩ በመሆናቸው ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ለማድረግ እንዲረዳት ለ27 ዓመታት በእስር ያቆየችውንና የነፃነት ምልክት የሆነውን ኔልሰን ማንዴላን ከእስር በመፍታት አዲስ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅ አራት ዓመት የፈጀ አድካሚ ድርድር ማድረግ ነበረባት፣ የሚለወጠው ተለውጦና የሚሻሻለው ሁሉ ተሻሽሎ ወደ ሥራ የገባውና የፀደቀው ግን ከስድስት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1996 ዓ.ም. ነው፡፡ ዛሬ ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት ግሩም ሕገ መንግሥታት መካከል የአንዱ ባለቤት መሆኗንና ሌሎች አገሮች ሞዴል አድርገው ሊወስዱት እንደሚገባ በአንድ ወቅት ከግብፅ ቴሌቪዥን ለቀረበላቸው ጥያቄ የገለጹት ከዘጠኙ የአሜሪካን ከፍተኛው ፍርድ ቤት (US Supreme Court) ዳኞች አንዷና አንጋፋዋ ሩት ጌንስበርግ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው አንድ ሕገ መንግሥት ሊያበረክታቸው ከሚችሉት ታላላቅ ጉዳዮች መካከል የተረጋጋ መንግሥትና የሕግ የበላይነትን ማስፈን የሚችሉ ተቋማትን ማደራጀት መቻሉ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ተመልሰው ራሱን ሕገ መንግሥቱን ከጥቃት የሚከላከሉ ጋሻና መከታ ይሆኑለታል፡፡

በዚሁ ወደቀዳሚው ሐሳቤ ስሸጋገር አገራችን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ትኩረት ሰጥታ ልትሠራባቸው ይገባል ከምላቸው ሦስት አበይት ጉዳዮች መካከል የሕገ መንግሥቱን ጉዳይ መስመር ማስያዝ አንዱና ዋነኛው መሆን አለበት የሚለውን ነጥብ አነሳለሁ፡፡ በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው አዲሱ (የሪፎርም/የሽግግር) መንግሥት ከተቋቋመበት መጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በብዙዎቻችን ዘንድ አጀንዳ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ ከሕወሓት ፕሮግራም ተገልብጦ የተጻፈውና በ1987 ዓ.ም. የፀደቀው የአገራችን ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ይኼው ለአገሪቷ አንዳች ያልፈየደላትን ጥራዝ ጉምቱው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ጊዮርጊስ ማርያም ‹‹ከተጻፈበት ወረቀት በላይ ዋጋ የሌለው›› ብለው ሲተቹት፣ ከቀዳማዊ ኃይሌ ሥላሴ መንግሥት ጀምሮ ለሦስቱም መንግሥታት በሕገ መንግሥት አማካሪነት ያገለገሉት ፋሲል ናሆምም (ዶ/ር) ይህንኑ ሕገ መንግሥት በጨዋ አነጋገር ‹‹ባይቀየርም ሊሻሻል እንደሚገባው›› አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል፡፡

እኔም እንደ አቅሜ በዚሁ ጋዜጣ የ2011 ዓ.ም. ዕትም ቁጥር 2016 ላይ የዘጠኙን ክልሎች አወቃቀርና የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ትርጉምን አስመልክቶ ባቀረብኩት ሃተታ የመጨረሻው ግራ የሚያጋባው ማጣቀሻ ሕገ መንግሥቱ መሆኑን አብራርቼ ነበር፡፡ ዛሬም ይኸው መከረኛ ሕገ መንግሥት አገሪቱን ወደ ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ ሊከታት ጫፍ ላይ ይገኛል፡፡

በማንኛውም መንገድ የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ በምንገባበት ወቅት መፍትሔ ይሰጠናል ብለን ተስፋ የምንጥልበት ሰነዳችን፣ እሱው ራሱ ለግጭቶቻችን መነሻ የሚሆን ክብሪት ጫሪ ሆኖ አረፈው፡፡ ‹የዕብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል› ነው ነገሩ፡፡ እውነቱን ለመናገር ባለፉት 25 ዓመታት ሕገ መንግሥቱን ተገን አድርገን የፈታናቸው ችግሮች አለመኖራቸው ብቻም ሳይሆን ጠያቂ ስለሌለ እየታለፈ ነው እንጂ፣ ለሚፈጠሩት ችግሮች መፍትሔ ሲጠፋ ሕገ መንግሥቱ በጓዳ እየታረመ መሰንበቱንም የሰማነው አሁን በቅርቡ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር “በድንገት” በሞት ሲለዩማን እንደሚተካቸው ባለማወቅ ግራ ለተጋባው የወቅቱ አስተዳደር መፍትሔ ማቀበል አቅቶት የነበረው ታሪከኛው ሕገ መንግሥት ዘግየት ብሎ በፖለቲካ ውሳኔ የተሾሙትን ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ባላየ ባልሰማ ብሎ አልፏቸዋል፡፡

ከእዚያም አልፎ በሁለተኛ ደረጃ የማነሳውን የሕዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠውን ነጥብ ማስፈጸም ያልቻለው ሰነድ ዛሬ የአገራችንን ሕዝብ ብዛት የምናውቀው በግምት እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ይህንኑ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውን ሥራ ቸል ብሎት በግብር ይውጣ ለሌላ ዙር የምርጫ ግርግር ሊያጋልጠን ዳር ዳር እያለ ይገኛል፡፡

በእኔ በኩል ይህንኑ መላ ቅጡ የጠፋውን ሰነድ አስመልክቼ ዛሬም የማቀርበው የመፍትሔ ሐሳብ ‹‹ኢትዮጵያውያን በሕገ መንግሥቱ ላይ ውሳኔ ሕዝብ ይስጡበት›› የሚለውን ይሆናል፣ አሁን የምንገኝበት ወቅትም መልካም አጋጣሚ ነው ብዬ ያልኩትም ለዚሁ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ፓርላማው የምርጫውን ጉዳይ አስመልክቶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕግ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች ጠቅሶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንዲቀርብለት በመጠየቁ፣ ለጥያቄው ምንም ዓይነት መልስ ቢመጣ ሁሉም ውሳኔዎች ለአፈጻጸማቸው ቢያንስ የስድስት ወር ጊዜ የሚጠይቁ የቤት ሥራዎች ይሆናሉ ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ለምሳሌ ግመል በመርፌ ቀዳዳ የማሳለፍን ያህል የጠበበ ዕድል ቢኖረውም፣ ምርጫው በምንም መልኩ ወቅቱን ጠብቆ መካሄድ አለበት የሚል ውሳኔ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳለፈ ብንል እንኳን፣ የምርጫ ቦርድ ያሻውን ያህል ሌት ተቀን ቢሠራ ከስድስት ወር በፊት ምንም ሊያመጣ አይቻለውም፡፡ ቦርዱ የምርጫ ዝግጅቱን በይፋ ያቆመውም ምርጫው ሊከናወን ስድስት ወር ሲቀረው በመሆኑ ከቆመበት አንስቶ ልጀምር ቢል እንኳን ከዚህ ባነሰ ጊዜ ምርጫ የሚባል ነገር ሊታሰብ አይችልም፡፡

በእኔ ግምት ምርጫው በዚህ ዓመት የሚካሄድበት ዕድል ፈፅሞ አይኖርም፣ ለነገሩ በሕገ መንግሥቱ የሚምሉትና የሚገዘቱት ተቃዋሚ ተብዬዎችም ምርጫው ከተባለለት ወቅት ዝንፍ ማለት የለበትም ቢሉም የሽግግር መንግሥት ከተመሠረተና ጥቂት ሥልጣን ካገኙ ምርጫው እስከ መጨረሻው ባይካሄድም ግድ የላቸውም፡፡ አይሆንም እንጂ ይሁን ተብሎ የሽግግር መንግሥት ድርድር ቢጀመርም ከስድስት ወር በፊት ከተጠናቀቀ ፖለቲከኞቻችን በእውነትም ሰጥቶ መቀበል ገብቷቸዋል ለማለት ይቻላል፡፡

ያም ሆኖ ምርጫው መቼም ይሁን መቼም ጊዜ ቢካሄድ እስከ ዛሬ ድረስ ከተከናወኑት ሁሉ አጨቃጫቂ የሚሆንበት ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ዋነኛው የጭቅጭቅ ምንጭ ደግሞ ይኼው ጦሰኛ ሕገ መንግሥት እንደሚሆን በበኩሌ ይታየኛል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 ቁጥር ሦስት ላይ እንደተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ብዛት የሚወሰነው የሕዝብ ብዛትን መሠረት በማድረግ በመሆኑ ክልሎች የሚኖራቸው የመቀመጫ ብዛት አጨቃጫቂ ሊሆን ይችላል፡፡ የምክር ቤቱ የመቀመጫ ብዛት 550 እንዲሆን በ1987 ዓ.ም. ሲወሰን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 50 ሚሊዮን እንኳን ያልሞላበት ወቅት ስለነበር በታሳቢነት የተያዘው አንድ የሕዝብ ተወካይ 100 ሺሕ ሕዝብ ይወክላል በሚል ነበር፡፡

ምንም እንኳን ይህም የሕዝብ ቁጥር ድልድል በአግባቡ ተደርጓል ወይ የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ቢሆንም በሚቀጥለው ምርጫ የሕዝብ ተወካዮቹ ቁጥር ባለበት የሚቀጥል ከሆነ ድልድሉ በምን መልኩ ይሆናል፣ አንድ የፓርላማ አባልስ ለስንት ሕዝብ ተወካይ ሆኖ ይዘልቃል? የሚሉትን ጥያቄዎች ጨምሮ የክልሎች የመቀመጫ ድልድል ለውጥስ ይኖር ይሆናል ወይ፣ ካለስ እነማን አትርፈው የትኞቹ ክልሎች ይከስራሉ የሚለውም ገና ጦር የሚያማዝዝ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀጥል አምናለሁ፡፡

ታዲያ መፍትሔው ምንድነው? ዛሬ የኮሮና ቫይረስ ባመጣው ጣጣ ለገባንበት የሕገ መንግሥት ፈተና በርካታ አማራጮች የቀረቡ በመሆናቸው አንዱን ከሌላኛው ለማነፃፀር ምቹ አጋጣሚ ስለሆነ ሳይረፍድ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ አቅርበን እንድንፈታው ምኞቴ ነው፡፡ እናም በእኔ በኩል ኢትዮጵያውያን በሕገ መንግሥቱ ላይ ውሳኔ ሕዝብ እንድንሰጥበት ዛሬም ምክረ ሐሳቤን አቀርባለሁ፡፡

ውሳኔ ሕዝቡ (Referendum) ከሌሎቹ አማራጮች የተሻለ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያቱ የተለያዩ አማራጮችን ለማቅረብ ማስቻሉም ይሆናል የሚል የግሌ ግምት አለኝ፡፡ ይህም ማለት ለውሳኔ ሕዝቡ የሚቀርቡት ሦስት አማራጮች የሁሉንም ወገኖች ሐሳብ በእኩልነት የሚያቀርቡ ሆነው ስለሚገኙ ዕጣ ፋንታቸውን የሚወስነው በመራጩ ሕዝብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሐሳቡ የተሸነፈበት አካል ውጤቱን በፀጋ የማይቀበልበት ምክንያት ሊኖር ከቶም አይችልም፡፡ እነዚህም አማራጮች አንደኛው፣ ሕገ መንግሥቱ ሳይነካ ባለበት ይቀጥል (አረንጓዴ) ሁለተኛው፣ የሕገ መንግሥቱ የተወሰኑ አንቀጾች ይሻሻሉ (ቢጫ) እንዲሁም ሦስተኛው፣ ሕገ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ ይለወጥ (ቀይ) የሚሉት ይሆናሉ፡፡ በየትኛው ጊዜና በምን መልኩ ይኼንን ውሳኔ ሕዝብ ማካሄድ ይቻላል ለሚለው አጠቃላይ መፍትሔ ስለሚኖረኝ በጽሐፌ ማጠቃለያ ላይ እመለስበታለሁ፡፡

ሌላው ከምርጫ በፊት መፍትሔ ሊያገኙ ይገባቸዋል ከምላቸው ጉዳዮች በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠው አጠቃላይ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ይሆናል፡፡ ከላይ ስለ ሕገ መንግሥቱ ባቀረብኩት ትንታኔ ላይ በጨረፍታ እንደጠቀስኩት የሕዝብ ቆጠራ አስፈላጊነቱ የምርጫውን ያህል ክብደት ተሰጥቶት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ቁጥር አምስት ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል፡፡ ይኼም ብቻ ሳይሆን የምርጫው ውጤት ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚኖረው የምርጫ ክልሎችን አወቃቀር ለመወሰን መሠረት ሆኖ እንደሚያገለግልም ተገልጿል፡፡ በጣም አስቂኙ ጉዳይ (ጊዜው ቀልድ ባይፈቅድም) ሕገ መንግሥት ወይም ሞት የሚሉ አካላት ከላይ የቀረበውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽና የሕገ መንግሥቱን ሌላኛውን አንቀጽ 54 ቁጥር አንድ በተለያየ መነጽር የሚያዩበት ሁኔታ (Double standared)ነው፡፡ ሁለቱም ጉዳዮች በአንድ አረፍተ ነገር የተጻፉ የሕገ መንግሥቱ የተለያዩ ክፍሎች ቢሆኑም አንዱን ፈፅሞ አይለወጥም፣ አይሻሻልም፣ አይተረጎምም ሲሉ፣ ሌላኛውን ግን በተደጋጋሚ ማሻሻልና ማራዘም የተቻለበት ብቻም ሳይሆን መቼ እንደሚደረግ የማይታወቅበትም ሁኔታ ሲከሰት ያሳዩት ዝምታ አስገራሚ ነው፡፡ እነዚሁ የሕገ መንግሥቱ ጠበቆች እንዴት በክልላችን ብቻችንን ቆጠራውን እናካሂዳለን ሳይሉን ቀሩ?

በቅድሚያ ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ ምርጫ ተደርጎ እንደማይታወቅ ሁሉ፣ የተደረጉት የሕዝብ ቆጠራዎችም በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ሆነው ነበር፡፡ ከእዚያም ባለፈ ከፖለቲካ አንፃር እየተቃኘ ለተለያዩ ብሔረሰቦች የቁጥር ድልድል ሲደረግ እንደነበረ የሚገልጹ ቡድኖች ዛሬም ድረስ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እንደዚያም ሆኖ እጅግ አወዛጋቢውና ሦስተኛው የ1999 ዓ.ም. የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ከተከናወነ በኋላም በአሥረኛ ዓመቱ በ2009 ዓ.ም. መከናወን ሲኖርበት በሕግም ያለ ሕግም እየተገፋ ሰንብቶ ዛሬም በእንጥልጥል ተይዞ ይገኛል፡፡ በጽሑፌ መግቢያ ላይ እንዳሳየሁት ኮሮና ይዞልን ካመጣልን ዕድሎች አንዱ የምርጫው መራዘም በመሆኑ በምንም ምክንያት ይሁን መጪው ምርጫ ከመከናወኑ በፊት፣ ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሊካሄድ 20 ቀናት ሲቀሩት የተራዘመው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መደረግ ይኖርበታል፡፡ የኮሮና ወረርሽኙ ጋብ ሲል አገሪቷ የሚኖራት ዋነኛ አጀንዳ የምርጫው ጉዳይ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ለዚሁ አገራዊ ምርጫ ከፍተኛውን ግብዓት ያበረክታል ተብሎ የሚታሰበው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ጊዜ ተወስዶ ቢሠራበት ብዙ ድካምና ጭቅጭቅ ይቀንስልናል፡፡ ቆጠራው በአጠቃላይ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አንድምታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖም ከግምት ውስጥ ገብቶ ነገ ዛሬ ሳይባል በቁምነገር ሊያዝ የሚገባ ጉዳይ ነው እላለሁ፡፡

ሦስተኛውና የመጨረሻው ከመጪው ምርጫ ቀድሞ መከናወን ይገባዋል የምለው ጉዳይ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙትን የተመለከተ ሁኔታን ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ዛሬ ሥልጣን እንዲለቅና ወደ ጠርዝ እንዲገፋ የተደረገው ቡድን በከፈለው የደም መስዋዕትነትም ጭምር ኤርትራ ራሷን የቻለች አገር ከመሆኗም አልፎ በታሪክ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ የተገነጠለችው አገር በፍጥነት ዕውቅና እንድታገኝ ለተባበሩት መንግሥታትና ለሌሎቹም ዓለም አቀፍ ተቋማት ግፊት ሲደረግላት ታይቷል፡፡ ይህንኑ የወረት ፍቅራቸውን በቅጡ እንኳን ሳያጣጥሙት እዚህ ግባ በማይባል ተራ የድንበር ግጭት የ100 ሺሕዎችን ደም ያፈሰሰ ኋላ ቀር ጦርነት አካሂደው ቀድሞ ሲደመምባቸው የነበረውን ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ በይበልጥ አስደንቀውታል፡፡ በቀጣዮቹ 20 ዓመታትም ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች በአካል ተራርቀው፣ በመንፈስ ግን አንድነታቸውና ፍቅራቸው ሳይቀዘቅዝ ቆይቶ በዶ/ር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ግንኙነታቸው ተጠናከሯል፡፡

የሁለቱ አገር መሪዎችም በተገናኙ ቁጥር የሚያሳዩን እንደ ታላቅና ታናሽ ወንድም የሚተያዩበት መንፈስ የሁለት ግለሰቦች ጉዳይ ሳይሆን የሁለቱ አገር ሕዝቦችም ስሜት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይህንንም በዓይናችን ዓይተን ያረጋገጥነው ሲሆን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ለሐሳቡ አመንጪና ቀድመውም ዕርምጃ በመውሰድ ወደተግባር ለለወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የሚገባቸውን ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡ በርካታ ተቺዎች የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ተቋማዊ ሳይሆን በግለሰቦች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው በማለት ቢገልጹትም በበኩሌ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት የአንድ አባት ልጆች ግንኙነት በመሆኑ በግለሰቦች በጎ ፈቃድ የሚፈርስና የሚገነባ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ መሪዎች ቢያልፉም የሁለቱ ሕዝቦች ቅርርብ ግን በምንም ዓይነት መልኩ ሳይሸራረፍ መቆየቱ ብቻም ሳይሆን፣ ጥቂት ቀደም ብሎም ጣሊያን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እንዳይገናኙ አጥር ሠርቶ በመለያየት፣ በባህልና በእምነትም ሊያራርቃቸው ቢያስብም ፈፅሞ ሊሳካለት እንዳልቻለ ታዝበናል፡፡

እነዚሁ በታሪክና በሥነ ልቦናም ጭምር የተሳሰሩ ሕዝቦች ከየትኛውም የቀጣናው ተጎራባች አገሮች በተሻለ ከሚለያያቸው ይልቅ የሚያቀራርባቸው ጉዳይ የበዛ በመሆኑ ከእንግዲህ በኋላ ተለያይተው የሚኖሩበት ዘመን ሊያጥር ግድ ይለዋል፡፡ ቀጣዩ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመሠረተው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ኤርትራውያን እህትና ወንድሞቻችንንም ሊያቅፍ ይገባዋል፣ እግረ መንገዱንም የኤርትራውያን የዘመናት የዴሞክራሲ ጥያቄም መልስ ያገኛል፡፡ እርግጥ ነው ኤርትራ ዛሬ ራሷን የቻለች ሉዓላዊትና ነፃ አገር በመሆኗ በድንገት ብድግ ብለን ‹‹ለምን አንቀላቀልም?› ብለን መፍትሔውን የምናገኝለት ጉዳይ አይደለም፣ እንደዚያም ሲባል መፍትሔ የሌለው ድፍን ያለነገርም አይደለም፡፡ ተቋማዊም፣ ሕጋዊም ሕዝባዊም ሊሆን የሚችል የመፍትሔ ሐሳቤን ከዚህ ቀጥዬ አቀርባለሁ፡፡

      ከታላቋ ጀርመን የረጅም ጊዜ ታሪክ እንደምንረዳው ኦቶ ቮን ቢስማርክ እ.ኤ.አ. በ1871 የተበጣጠሱትን ግዛቶች አገጣጥሞ (Unification of German States) አንድ የጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክን ቢመሠረትም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማጠናቀቂያ ላይ በድጋሚ ለሁለት የመከፈል ክፉ ዕጣ አጋጥሟቸው ነበር፡፡ በሁለት ግዛቶች ውስጥ ብቻም ሳይሆን ፈፅሞ በማይታረቁ ሁለት ርዕዮተ ዓለማት ውስጥ ለ45 ዓመታት ተለያይተው ቆይተው የቀዝቃዛው ጦርነት እንዳበቃና ሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች አለያይታ ከፀባቸው ያለይሉኝታ ስታተርፍ የነበረችው ሶቪየት ኅብረት በተራዋ ከመበታተኗ ጥቂት ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ. በOctober 31 ቀን 1990 ዓ.ም. ተመልሰው አንድ ሊሆኑ በቅተው ዕለቱን “Unity Day” በማለት የሚያከብሩት ሲሆን የሁለቱ ጀርመኖች ውህደትም (Reunification of Germany) በመባል ይታወቃል፡፡

የጀርመን ዳግም ውህደት በጥቂት ወራት ድርድር የተከናወነ ቢሆንም የኢትዮ ኤርትራ ዳግም ውህደት ግን “ተቋማዊ” በሆነ መልኩ የሁለቱንም አገር ሕዝቦች ባሳተፈ መልኩ ሊከናወን ግድ ይለዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት አጠቃላይ ሕዝበ ውሳኔ (Referendum) በሁለቱም አገሮች እንዲከናወን መደረግ ይገባዋል፡፡ ሁለቱም ሕዝበ ውሳኔዎች የተለያየ መልክ ሲኖራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጠው ድምፅ ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ዳግም ትቀላቀል? ወይስ አትቀላቀልም? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብቻ ሲሆን፣ በአንፃሩ በኤርትራ ውስጥ የሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ግን ከዳግም ውህደቱ ጥያቄ በተጨማሪም የውህደቱን ዓይነትም (በፌዴሬሽን ወይም በኮንፌዴሬሽን) የሚወስኑበት ይሆናል፡፡ የሁለቱም አገሮች ሕዝበ ውሳኔ በዳግም ውህደቱ (Reunification) የሚስማማ ከሆነ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ኤርትራንና ሕዝቦቿንም የሚያጠቃልል ሆኖ ይከናወናል ማለት ነው፡፡ አዲስ የሚከፈተው ፓርላማም ታሪካዊ ሆኖ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ተወካዮችን በአንድ ላይ በማቀፍ የዴሞክራሲን ዕፍታ ለሁለቱም አገሮች ሕዝቦች በተመሳሳይ ሰዓት የሚያቋድስ ሆኖ ይመሠረታል፡፡ ነገር ግን ውህደቱ ከሁለቱ አገሮች በአንዱ ውስጥ ተቃውሞ ከቀረበበት እንደ ሁለት ወዳጅ ጎረቤት አገሮች ግንኙነታቸው በመከባበር ላይ ተመሥርቶ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

በመጨረሻም ሕዝበ ውሳኔው መቼና በምን ሁኔታ መከናወን ይችላል የሚለውን ሐሳብ አቅርቤ ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡ በኤርትራ ሕዝበ ውሳኔው አገሪቷን የሚመራው የመንግሥት አካል በሚወስነው መሠረት ቀን ሊቆረጥለት የሚችል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን የፌዴራል ማግሥቱ በሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሕዝቡ የሚሰጥበትን ቀን በመወሰን የማስፈጸሙን ኃላፊነት ደግሞ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይወስዳል፡፡ የምርጫ ቦርዱም ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ከማከናወኑ በፊት አቅሙን የሚፈትሽበትና ጡንቻውንም የሚያጠናክርበትን ዕድል ያገኛል፡፡

በአገራችን የተፈጠረው የፖለቲካ ድባብም ለምርጫ የተመቸ ነው ወይስ አስጊ ሁኔታ ላይ ነው ያለው የሚለውን ሁኔታም የምናረጋግጥበት ይሆናል፣ መቼም አገራዊ ምርጫ ከሚበጠበጥ ከእዚያ ያነሰ አደጋ ያለው ሕዝበ ውሳኔ ቢረበሽ ይዞት የሚመጣው ችግር አነስተኛ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡ በዚሁ አጋጣሚም በተመሳሳይ ዕለት በዚሁ ጽሑፍ መግቢያ ላይ የገለጽኩት ኢትዮጵያውያን በሕገ መንግሥታችን ላይ የሚኖረንን አቋም የምናሳውቅበትን ሕዝበ ውሳኔንም እናከናውናለን፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት ይኼም አይደል? የሕዝብና ቤቶች ቆጠራው ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ ቢደረግም ይቻላል ዞሮ ዞሮ የቆጠራው ፋይዳ ለምርጫው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑ ነውና ከአጠቃላዩ አገራዊ ምርጫ በፊት ከተከናወነ በስኬት እንደተከናወነ ይታሰባል፡፡ ሰላምና ጤናውን ያብዛልን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ ሥራ ይጀምራል

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው...