አቶ ፍትሕ ወልደ ሰንበት የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ እሳቸው የሚመሩት ፌዴሬሽን ለመንግሥት ካቀረባቸው አራት አንኳር የድጋፍ ጥያቄዎች ውስጥ ወሳኝ ለሆኑት ከፊል ምላሽ አግኝቷል፡፡ በፌዴሬሽኑ ሥር ከተካተቱት ውስጥ 1,200 ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና ካፊቴሪያዎችን በማካተት ከ144 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ዕዳ አለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ፌዴሬሽኑ ሆቴሎች በየወሩ የሚከፍሉት የባንክ ብድር ከእነ ወለዱ ለአንድ ዓመት ሳይከፈል እንዲራዘምላቸው እንዲደረግ ያቀረበው ጥያቄ፣ የመንግሥትን ምላሽ እየተጠባበቀ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለታክስ፣ ለሥራ ማስኬጃና ለሠራተኛ ደወመዝ ክፍያ መንግሥት ምላሽ ሰጥቷል ያሉት አቶ ፍትሕ፣ ለአንድ ዓመት የሚቆይ 6.6 ቢሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ ብድር ተጠይቆ ግማሹን እንዳቀረበ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በስድስት ወራት ውስጥ ተከፋይ የሚሆን 3.3 ቢሊዮን ብር ብድር አፅድቆ ሆቴሎች በባንኮች በኩል እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ ይህንን ጨምሮ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ እየታሰበ ስላለውና ሌሎችም ጉዳዮች ሪፖርተር ከአቶ ፍትሕ ወልደ ሰንበት ጋር ያደረገውን ቆይታ፣ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው መስኮች የሆቴልና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አንዱ ነው፡፡ መንግሥትም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ለጥያቄያችሁ ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ማብራሪያ ቢሰጡን?
አቶ ፍትሕ፡- ሒደቱን ለማስረዳት ያህል የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፍ በኢትዮጵያ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በሰፊው እያደገ የመጣ ነው፡፡ ትልልቅ ብራንድ ሆቴሎችም እየተከፈቱ ነው፡፡ ከሰው ኃይል አኳያ በተለይም ባለ ኮከብ ሆቴሎችን ካየን በአንድ ሆቴል፣ ከ300 እስከ 600 የሥራ ዕድል በመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ገቢ አኳያም ከፍተኛ ገቢ እያስገኙ ነው፡፡ ለአገርም ገጽታ ትልቅ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ በርካታ ትልልቅ ስብሰባዎች እንዲመጡ የሆቴሎች መስፋፋት ትልቅ ድርሻ አበርክቷል፡፡ በፍጥነት እያደገ የመጣው ይህ ዘርፍ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ በነበሩ የለውጥ ሒደቶች ሰላም በመደፍረሱ ሆቴልና ቱሪዝም ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ገበያ ጠፍቷል እየተባለ ገና ማንሰራራት ሲጀምር የኮሮና ወረርሽኝ ተከሰተ፡፡ የቀዘቀዘውን ገበያ ጭራሽ ሆቴሎች እንዲዘጉ በማድረግ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የሰዎችን እንቅስቃሴ ከማገድ ባሻገር፣ በየመዝናኛው እንዳይሰበሰቡ ያስከለከለ በሽታ ነው፡፡ ይህ ሙሉ ለሙሉ የሆቴሎችን ህልውና ችግር ውስጥ የሚከት ነው፡፡ በመሆኑም ነገ እንዲያገግሙ የምናወጣው ወጪ ውድ እንዳይሆን ዛሬ ላይ ጥበቃ መስጠት እንዲቻል፣ ፌደሬሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲያስተባብር ቆይቷል፡፡ በዚህ መሠረት አራት ጥያቄዎችን ለመንግሥት አቅርበናል፡፡ ከዚህ ውጪ በእኛ በኩል ስለሚጠበቁ ሥራዎችም አሳውቀናል፡፡
ሪፖርተር፡- ጥያቄዎቹን ቢያብራሩ?
አቶ ፍትሕ፡- ከነበሩን ጥያቄዎች አንዱ አስቸኳይ አዋጅ ታውጆ ሠራተኛ አትበትኑ ተብሏል፡፡ ለአራት ዓመታት የተጠራቀመ የገንዘብ እጥረት ስለነበር፣ ባንኮች ለሠራተኞች ደመወዝ የሚውል ገንዘብ እንዲያቀርቡ ጠይቀናል፡፡ ሆቴል እንደ ሌላው የንግድ ዘርፍ ተዘግቶ ቆይቶ ዝም ተብሎ ተከፍቶ አይገባበትም፡፡ ወጪ የሚጠይቁ የኦፕሬሽን ሥራዎች አሉበት፡፡ ስለዚህ ለዚህ የሚሆን ብድር ከወለድ ነፃ እንዲሰጠን ጠይቀን ነበር፡፡ ምላሽ የተሰጠን ግን ወለዱ በአምስት በመቶ የሚታሰብ ሆኖ ለዓመት የሚቆይ ሥራ ማስኬጃ ብድር ነበር የጠየቅነው፡፡ በስድስት ወራት ተሠልቶ ተፈቅዶልናል፡፡ ለሆቴል ብቻ 5.9 ቢሊዮን ብር ነበር የጠየቅነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ገንዘብ ላይ ነው ግማሹ የተፈቀደላችሁ?
አቶ ፍትሕ፡- አዎን፡፡ በስድስት ወራት ታስቦ ግማሹ ተፈቅዶልናል፡፡ የቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቶችም 600 ሚሊዮን ብር ብድር ጠይቀው ግማሹ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ 3.3. ቢሊዮን ብር ተፈቅዶልናል፡፡
ሪፖርተር፡- በጠቅላላው ግን 6.6 ቢሊዮን ብር ነበር የጠየቃችሁት?
አቶ ፍትሕ፡- እዚያው አካባቢ ነው፡፡ አሁን ግማሹ ተፈቅዶልን ብሔራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች ገንዘቡን አቅርቦ እንዲሰጠን አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ሌሎቹ ጥያቄዎቻችሁ እናምራ፡፡
አቶ ፍትሕ፡- ከሌሎቹ ጥያቄዎች መካከል ለገቢዎች ሚኒስቴር የቀረቡም ነበሩ፡፡ በፌዴራል ደረጃ ለሚገኙ ሆቴሎችና መሰል ተቋማት የታክስ ክፍያቸው ላይ ጊዜ ይራዘምላቸው ነበር ያልነው፡፡ መንግሥት ግን ከዚያም አልፎ ምሕረት አድርጓል፡፡ ክልሎችም ይህንን ተከትለው ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ጥያቄ እያቀረብን ነው፡፡ ምክንያቱም ክልሎች ናቸው በዚህ መወሰን የሚችሉት፡፡ በአማራ ክልል ደረጃ ከፌዴራሉ ጋር ተመሳሳይ ዕርምጃ መወሰዱን ሰምተናል፡፡ ሌሎችም ክልሎች ይህንን እንዲከተሉ እንጠይቃለን፡፡ ሦስተኛው ጥያቄያችን የሆቴሎችን ህልውና እንደነበር ማቆየት የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እስካሁን ያየናቸው የእሳት ማጥፋት አጣዳፊ ድጋፎች ናቸው፡፡ የሆቴሎችን ህልውና ለማቆየት አንዱ ዕርምጃ ሆቴሎቹ በአብዛኛው በብድር ገንዘብ የተገነቡ እንደ መሆናቸው፣ በየወሩ ለባንኮች የሚፈጽሟቸው የብድር ክፍያዎች አሉ፡፡ እነዚህን ክፍያዎች አሁን ማከናወን ስለማይቻል ባንኮቻችን ዕዳው ከእነ ወለዱ ለተወሰነ ጊዜ ሳይከፈል እንዲቆይ እንዲያደርጉልን፣ ከዓመት በኋላ መክፈል ብንጀምር የሚል ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ወደፊትም በማገገሙ ሒደት ላይ ቶሎ የማይመለስ ዘርፍ በመሆኑ ባንኮች በአሥር ዓመታት ውስጥ እንዲመለስ ያበደሩት ብድር ካለ በሃያ ዓመታት እንዲከፈል እንዲያደርጉልን ጠይቀናል፡፡ ወለዳቸውም ሳይቀር ተከፋይ ይሆናል፡፡ ለእኛ ግን የወርኃዊ ክፍያ ጫናው ስለሚቀንስልን መንገዳገድና ተስፋ መቁረጥን ያስቀርልን ነበር፡፡ በሥራው ላይ እንድንቆይም ያስችለናል፡፡ ባንኮች በተወሰነ መንገድ ለዚህ ጥያቄ በየፊናቸው ምላሽ እየሰጡበት ነው፡፡ ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ስናየው የኮሮና ጉዳት የአጭር ጊዜ አይደለም፡፡ መተንበይም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለሦስት ወር ወይም ለአንድ ዓመት የሚቆይ ጉዳት የምንለው ነገር አይደለም፡፡ ቢሆንም ቢያንስ በእኛ በኩል ለአንድ ዓመት የሚቆይ ጉዳት ያስከትላል የሚል ግምት አለን፡፡ በዚህ ደረጃ ድጋፍ እንዲደረግልን ጠይቀናል፡፡ መንግሥት ከባንኮች ጋር እየተወያየ ነው፡፡ አዎንታዊ ምላሽ እንጠብቃለን፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ምናልባት ቱሪዝም ኢትዮጵያ የአንድ ዓመት የባንክ ዕዳ ክፍያ ከእነ ወለዱ እንዲራዘም ቢደረግ፣ እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ዕዳ ወደ የሚቀጥለው ዓመት እንዲሸጋገር መጠየቃችሁን ነበር ተቋሙ ያስታወቀው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ያብራሩልን?
አቶ ፍትሕ፡- የደመወዝና የኦፕሬሽን ጉዳይ አስቀድመን በተነጋገርነው መሠረት ተፈቷል፡፡ ባንኮች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያልተከፈላቸው ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰነዶች አሉ፡፡ እነዚህ እንግዲህ የክፍያ ጊዜያቸው የሚለያዩ ዕዳዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ከአምስት ዓመት በኋላ፣ ሌሎቹም እስከ አሥር ዓመታት ድረስ ሊከፈሉ የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በመሆኑም የአንድ ዓመቱ የዕዳ ክፍያ ምን ያህል ነው የሚለው ዝርዝሩ የለኝም፡፡ በጠቅላላው ዕዳችን 17 ቢሊዮን ብር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እኛ ግን ቢያንስ ለአንድ ዓመት ይከፈል የነበረው ዕዳ ይሸጋገርልን ብለን ጠይቀናል፡፡ ይህን ስንጠይቅ ዝም ብለን ባንኮችን ዕዳና ወለድ አንሱልን ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ነገ አብሮ ተያይዞ መውደቅም ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳይመጣ መንግሥት በሚችለው ደረጃ ባንኮችን እያገዘ፣ ባንኮችም በአቅማቸው እኛን እያገዙ ተባብረን እንድናልፈው የሚጠይቅ የመፍትሔ ሐሳብ እንጂ፡፡ ዛሬ ሆቴል ብቻውን ቢተርፍ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ባንኮቹም መኖር አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ሆቴሎች በጠቅላላው 17 ቢሊዮን ብር ከሆነ ዕዳቸው የአንድ ዓመት የዕዳ ክፍያቸው እንዲራዘም ከተጠየቀ፣ ሒሳቡ ምን ያህል እንደሚሆን ማወቅ እንዴት አስቸገረ?
አቶ ፍትሕ፡- የአንድ ዓመት ዕዳ ክፍያቸው ምን ያህል እንደሆነ ለመተንበይ ችግር የሆነው፣ አንዳንዱ ከፍሎ ለመጨረስ አንድ ዓመት ብቻ የቀረው ነው፡፡ አሥር ዓመታት የሚጠብቅም አለ፡፡ እስከ 15 ዓመታት የሚቆይ የዕዳ ክፍያ የሚጠበቅበትም አይጠፋም፡፡ ይህ ዝርዝር ተጠናቅሮ ካልተያዘ በአንድ ዓመት ውስጥ ተከፋይ መሆን ያለበት ዕዳ ምን ያህል ነው የሚለውን ማወቁ ሊቸግር ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ቱሪዝም ኢትዮጵያ የሆቴሎችና የቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቶች ዕዳ ክፍያቸው በአንድ ዓመት ቢራዘም፣ እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚኖር ያሠላው ከምን ተነስቶ ሊሆን ይችላል?
አቶ ፍትሕ፡- ምናልባት የአዲስ አበባ ሆቴሎች ማኅበር የሠራው አንድ ጥናት ነበር፡፡ ይህንን ተንተርሰው ከሆነ፣ ይህ የኢትዮጵያ ሆቴሎችን በጠቅላላ ስለማይወክል ነው፡፡ እኛ እየተነጋገርን ያለነው በአገሪቱ የሚገኙ ሆቴሎችን ጉዳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ብቻ ከታየ ወደ 1.8 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚሆን ነው የተቋሙ መረጃ ያመላከተው፡፡
አቶ ፍትሕ፡- እነሱ ምናልባት መረጃውን የሚተነትን ግብዓት ይኖራቸዋል፡፡ እኛ ለጊዜው የጠቅላላ ዕዳ መጠኑን ነው ማጠናቀር የቻልነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገር አቀፍ ደረጃ የ1,300 ሆቴሎችን ጥያቄ ነው የምትወክሉት?
አቶ ፍትሕ፡- በእኛ ፌዴሬሽን ውስጥ 2,200 አባል ሆቴሎች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ጥያቄዎችን ያቀረብነው ሠራተኞችን በማስተዳደር ላይ የሚገኙና ሥራው ላይ ያሉትን ነው፡፡ ኮከብ ሆቴሎችን ካየን 450 ገደማ ናቸው፡፡ ነገር ግን የ1,200 ሆቴሎች ጉዳይ ታሳቢ በማድረግ ነው የድጋፍ ጥያቄዎችን ያቀረብነው፡፡ ሆቴልና መሰል አገልግሎቶች የሚለው ስያሜያችን የሚወክለው ሌሎችም ከሆቴል ወዲህ ያሉትን እንደ ካልዲስና ማማስ ኪችን ያሉ በርካታ ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ልንተው አንችልም፡፡ በክልሎችም በርካታ ትልልቅ የሰው ኃይል የያዙ ሬስቶራንቶችና ካፊቴሪያዎች አሉ፡፡ እኛ ግን ቢያንስ በያዙት የሰው ኃይል ግምት ነው 1,200 ተቋማትን በማካተት በሠራነው መሠረት ነው ጥያቄ የቀረበው፡፡ ጥያቄው ምላሽ ማግኘት ሲጀምር ደግሞ አሳሳቢ የሆኑ ነገሮችም አልታጡም፡፡ የተፈቀደውን ገንዘብ አንድ ተቋም ብቻውን ሊወስደው ይችላል፡፡ ይህ ፍራቻም ስላለን ለባንኮች ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ ሥሌቱን ሠርተን ያዘጋጀነውንና ሆቴሎችም የጠየቁትን የኦፕሬሽን ወጪዎች መነሻ በማድረግ፣ ከእኛ ማረጋገጫ እንዲወስዱ በማድረግ ባንኮች የተፈቀደውን ገንዘብ እንዲያከፋፍሉ እየተደረገ ነው፡፡ በጀቱ የተፈቀደበት ከፍተኛ ጣሪያ ምን ያህል ነው የሚለው መጠን እኛ ዘንድ ስላለ መረጃውን ከእኛ እያረጋገጡ እንዲሰጡ እያደረግን ነው፡፡ ገንዘቡ በትክክለኛው መንገድ ለሁሉም እንዲዳረስ ባንኮችም መከታተያ እንዲሆናቸው ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ ከሰኔ ጀምሮ በሚታሰብ አንዳንድ ባንኮች ያዘጋጁትን ሰነድ ተበዳሪዎቹ ሆቴሎች እየሞሉ እንዲወስዱ ጥሪ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የፈቀደላቸውን ገንዘብ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀረበባቸው ሰነዶችም ታይተዋል፡፡ ሒደቱን በምን አግባብ ነው የምትከታተሉት? ለምሳሌ ዳሸን ባንክ 600 ሚሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ ወስዶ እንዲያከፋፍል የሚጠይቅ ደብዳቤ በትስስር ገጾች ወጥቶ ነበር፡፡
አቶ ፍትሕ፡- ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የሚልከው ደብዳቤ ላይ ለሚመለከታቸው አካላትም ግልባጭ እያደረገ ነው፡፡ በጠቀስከው ደብዳቤ ላይ ከሥር የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በግልባጭ ተጠቅሷል፡፡ ሒደቱን በዚህ መንገድ እንድናውቀው እየተደረገ ነው፡፡ ትልቁን ድርሻ የወሰደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 848 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ሁለተኛው አዋሽ ነው፡፡ ሦስተኛው ዳሸን እያለ 17ቱም ባንኮች የየድርሻቸውን ከብሔራዊ ባንክ ወስደዋል፡፡ ልማት ባንክ እዚህ አልተካተተም፡፡ እሱ በሌላ መንገድ ስላለና ተበዳሪ ሆቴሎችም ጥቂት ስለሆኑ፣ በራሱ መንገድ እንደሚያስተናግዳቸው ቃል ተገብቶልናል፡፡ እያንዳንዱን ሒደት እንከታተላለን፡፡ ብሔራዊ ባንክም መረጃ ሲለዋወጥ እኛም በግልባጭ ይደርሰናል፣ እንከታተላለን፡፡ ሒሳቡም የተሠላው ከእኛ በተገኘው መረጃ መሠረት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በሆቴሎች የሚተዳደረው የሠራተኛ ብዛት ስንት ነው?
አቶ ፍትሕ፡- የ1,200 ሆቴሎችን የብድር፣ የሥራ ማስኬጃና የሠራተኛ ደመወዝ እንዲሁም መሰል ድጋፎች እንዲደረጉ ሥሌቱን የሠራነው 144 ሺሕ ሠራተኞችን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ሆቴል የሠራተኛ ብዛት ምን ያህል እንደሆነ የሚገልጽ መረጃ ከእኛ ማግኘት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ባንኮችም የበለጠ የተጣራ መረጃ እንድናገኝ ፈቃደኛ በመሆን ተባብረውናል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ ባንኮች አበድረው ሲመጡ እንደሚለቀቅላቸው ነው ያስተላለፈላቸው መመርያ የሚጠቁመው፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኑ የተነሳበት ዓላማ አለው፡፡ ባንኮችም ከፌዴሬሽኑ በሚያገኙት መረጃ መሠረት ቢንቀሳቀሱ፣ ነገ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጭቅጭቆችን ከወዲሁ መቅረፍ ይቻላል፡፡ አንዳንዱ ሆቴል የተፈቀደውን ገንዘብ ሄዶ ሲጠይቅ አልቋል ቢባል ያጨቃጭቃል፡፡ ይህንን ለመዝጋት ስንል ነው ባንኮች ቀድመው ከእኛ በሚያገኙት መረጃ ላይ ተንተርሰው፣ የሥራ ማስኬጃና የሠራተኛ ደመወዝ ክፍያውን ገንዘብ እንዲያከፋፍሉ የምንጠይቀው፡፡
ሪፖርተር፡- ከውጭ ተበድረው እየሠሩ የሚገኙ ሆቴሎችስ ጉዳይ እንዴት እየታየ ነው?
አቶ ፍትሕ፡- የውጭ አበዳሪዎችን አሁን ማግኘት ያስቸግረናል፡፡ አሁን በአገር ውስጥ ካሉ አበዳሪዎች ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ተጠይቆ፣ እሱንና ለደመወዝ የሚያውሉትን ገንዘብ እንዲያገኙ በሚደረገው ሥራ ላይ ነው ትኩረታችን፡፡ የባንኮች ብድር የክፍያ ጊዜ ይራዘም የሚለው ላይ መንግሥት ገና አልጨረሰም፡፡ እኛም ጥያቄያችን አልተቋጨም፡፡ ባንኮች ግን በየፊናቸው ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡ ለምሳሌ አዋሽ ባንክ ለሦስት ወራት ብድር መክፈያ አራዝሜያለሁ ብሏል፡፡ እኛ ግን ለዓመት ቢሆን የበለጠ ይጠቅመናል እያልን ነው፡፡ ሦስት ወርማ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲያበቃ ያልቃል፡፡ ጉዳቱ ግን ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ማንም ቱሪስት ተደፋፍሮ መንቀሳቀስና አገር መጎብኘትን በቶሎ ላይጀምር ይችላል፡፡ የባንክ ብድር የሚከፈልበትን ጊዜ የማራዘም ጥያቄው ከተሳካልን፣ ዓለም አቀፍ ሆቴሎችም ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል ብለን እናስባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ ለሦስት ወይም ለስድስት ወራት ቅድሚያ የሚሰጣቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በእናንተ ሥር ያሉት ማኅበራትስ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው?
አቶ ፍትሕ፡- ትልቁ ጉዳያችን የነበረው ዘርፉን ማዳንና ሠራተኛ እንዳይበተን ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ላይ እየሠራን ነው፡፡ ጥሩ ሒደት ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ እንዳለቀልን የማገሚያ ሥራዎችና ስትራቴጂዎች ላይ እናተኩራለን፡፡ እንደ ፌዴሬሽን የማገገሚያ ሥራው ላይ የምናስበው ባህልና ቱሪዝም፣ ቱሪዝም ኢትዮጵያና ሌሎችም አካላት ተባብረን ኢትዮጵያን የሚያስተዋወቁ ዓለም አቀፍ ቅስቀሳዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ጎብኚዎችን ሊስብ የሚችል ጥሩ ፓኬጅ ማዘጋጀት ነው፡፡ ሁሉም አገር እንቅስቃሴ ተዘግቶበት ስለቆየ በነፃ እየመጣችሁ ጎብኙን የሚል ሁሉ ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ ደረጃ ሊያፎካክረን የሚችል ዕድል መፍጠር መቻል አለብን፡፡ እነዚህን እያዘጋጀን ነው፡፡ በባህልና ቱሪዝም በኩል እኛም የኮሚቴ አባል የሆንበት የማገገሚያ ስትራቴጂ ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡
ሪፖርተር፡- ሰነዱ ምን ምን ጉዳዮችን አካቷል?
አቶ ፍትሕ፡- በማገገሚያ ወቅት በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ምን መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት ነው፡፡ አስጎብኚዎችን ከማሠልጠን ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ለስድስት ወራት ያህል ሠራተኞች ሳይፈናቀሉ በሥራ ገበታቸው እንዲቆዩ የሚያስችል ድጋፍ አግኝታችኋል፡፡ ከዚያስ በኋላ?
አቶ ፍትሕ፡- የባንኮች ድጋፍ ሠራተኞች ሳይፈናቀሉ ቢያንስ ለስድስት ወራት ማቆየት እንድንችል ያግዘናል፡፡ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው የሥራ ፕሮቶኮል ደግሞ፣ አሠሪና ሠራተኛ በመተሳሰብና በመነጋገር ስምምነት እንዲፈጽሙ የሚፈቅድ ዝርዝር አማራጮች አሉት፡፡ ለምሳሌ ደመወዝ በመቀነስ፣ በማሻሻል፣ የዓመት ዕረፍት በመስጠትና በሌሎችም መንገዶች ሠራተኛ በሥራ ላይ እንዲቆይ ማድረግ የሚቻልባቸውን ዕድሎች አስቀምጧል፡፡ የኦፕሬሽን ሥራው ላይ ሆቴል እንደ ሌላው ዘርፍ ዘግተኸው ሄደህ በፈለግክበት ጊዜ የምትገባበት አይደለም፡፡ ደንበኛ ኖረም አልኖረ ቀን በቀን የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ መብራት ቢጠፋ ለጄነሬተር የሚወጣው ወጪ ብዙ ነው፡፡ ሌሎችም በርካታ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች አሉ፡፡ ይህ ጊዜ አልፎ በማገገሚያ ወቅት መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ሁለተኛው ዙር የኮከብ ምዘና ስለሚመጣ፣ ሆቴሎች አጋጣሚውን በመጠቀም ያሉባቸውን ክፍተቶች አሻሽለውና አስተካክለው ለምዘና ብቁ ሆነው እንዲገኙ እያነሳሳናቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለዚህ ዓመት ከቱሪዝምና ከሆቴል የታሰበ የገቢ መጠን አለ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ዋናው የቱሪስት ገበያ ወቅት እንደ አጋጣሚ ሆኖ የኮሮና ወረርሽኝ መቀስቀስ በጀመረበት ሰሞን ተጠናቋል፡፡ ከቱሪስቶች የሚገኘውን ገቢ ከ65 በመቶ ያላነሰ ማስገኘት ተችሏል የሚሉ መረጃዎችም ነበሩ፡፡ ከዚህ አኳያ ዘርፉ የታሰበለትን ገቢ አስገኝቷል ሊባል ይችላል? ካልሆነስ ምን ያህል ገቢ ሊታጣ እንደሚችል ይገመታል?
አቶ ፍትሕ፡- ዘርፉን ወደ ነበረበት መመለስ የሚሉ አገላለጾች እንሰማለን፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ቱሪስት ነው ስናስተናግድ የቆየነው፡፡ ያውም ያ ሁሉ የስብሰባና የጉባዔ መዓት እየተካሄደ ከአንድ ሚሊዮን ያነሰ ቱሪስት ማስተናገድ ዝቅተኛ አፈጻጸም ነው፡፡ በአገራችን በመደበኛነት በየቱሪስት መዳረሻው እየሄዱ የሚጎበኙ ቱሪስቶች የሚመጡበት ዋናው ጊዜ እንዳበቃ ነው ኮሮና የተከሰተው፡፡ ይህ ማለት ግን ዋናው የቱሪስቶች መምጫ ጊዜ ስላበቃ የሚመጡ ሌሎች ቱሪስቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ በርካታ ስብሰባዎች ይደረጉ ነበር፡፡ በርካቶቹ ተሰርዘዋል፡፡ የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማኅበር ፊፋ ጉባዔ እዚህ በዚህ ዓመት ነበር የሚካሄደው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ግን ተሰርዟል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአኃዝ ምን ያህል ጉዳት እንደ ደረሰና ወደፊትስ ምን ይጠበቃል የሚለው ላይ በባለሙያዎች እያስጠናን ነው፡፡ መረጃ ለመሰብሰብ ያህል ከየሆቴሉ ድረ ገጽ ገብተህ ስታይ፣ አንድ ሆቴል 100 ሠራተኛ እንዳለው የሚገልጽ ነገር ታገኝ ይሆናል፡፡ በአካል ሄደህ ስታይ ግን ከ600 ያላነሰ ሠራተኛ እንዳለው ልታውቅ ትችላለህ፡፡፡ መረጃዎች በየጊዜው ስለሚለወጡና ቀድሞ የተሠራጩ መረጃዎች በየጊዜው ስለማይታደሱ፣ ይህንን የሚያጠራና ተጨባጩን እውነታ የሚያሳይ ጥናት ለመሥራት አስበናል፡፡ መንግሥት የወረርሽኙን ሥርጭት የሚቆጣጠርበትን አሠራር ሳያላላ፣ በዚሁ እያስኬደ በበሽታው የሚሞትብን ሰው ቁጥር ሳይባባስ እንዲቆይ ማድረግ ከተቻለ፣ ሕዝቡም በአግባቡ እየተጠነቀቀ ፈጣሪም አግዞን ይህንን ጊዜ ካለፍነው፣ ነገ የዓለም ሕዝብ ትኩረት ሰጥቶ የሚጎበኘን አንድ የቱሪስት መስህብ ልንሆን እንችላለን፡፡ ይህ ሊመጣ የሚችለው በምንሠራው ልክ ነው፡፡ በአግባቡ በሽታውን መግታት ሳንችል ቀርተን ብዙ ጉዳት ብናስተናግድ ግን በአግባቡ በሽታውን ለመቆጣጠር እንዳልሠራን ዓለም ሊያስብና ወደ እኛ በመምጣት የመጎብኘት ፍላጎቱ ሊቀንስ ይችላል፡፡ አሁን የምናደርገው ጥንቃቄና የመከላከል ሥራ ከበሽታው ለመዳን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም ቱሪዝማችንን ሊጠቅም የሚችል እንደሆነ በማሰብ ጭምር በአግባቡ እንድንጠነቀቅ አሳስባለሁ፡፡