Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳና ብርሃን ባንክ የወለድ ቅናሽ በማድረግ የድጋፍ ዘመቻውን ተቀላቅለዋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክና ብርሃን ባንክ፣ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ለጉዳት የተጋለጡ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለመደገፍ የብድር ወለድ ቅናሽ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሁለቱም ባንኮች የብድር ወለድ ቅናሻቸው በወረርሽኙ ጉዳት የደረሰባቸውን ዘርፎች በማስቀደምና የተሻለ የብድር ወለድ ቅናሽ አድርገው ያስረዱት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት አንበሳ ባንክ ከ0.5 እስከ አምስት በመቶ የብድር ወለድ ቅናሽ ሲያደርግ፣ ብርሃን ባንክ በበኩሉ ከ0.5 እስከ አራት በመቶ የብድር ወለድ ቅናሽ አድርጓል፡፡

የብርሃን ባንክ ወረርሽኙን ተፅዕኖን ለማቃለል በማሰብ ከ0.5 እስከ አራት በመቶ የሚደርስ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ እ.ኤ.አ. ከሜይ 18 ቀን 2020 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ የወለድ ቅናሽ ማስተካከያውም በተለያዩ ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ኮቪድ-19 ያስከተለውን ተፅዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን የገለጸው ብርሃን ባንክ በዚህ ቅናሽ የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት፣ የወጪ ንግድ፣ ሕንፃና ግንባታ፣ የግል ብድር ዘርፎች የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አመልክቷል፡፡

በዚህም መሠረት ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪ ዘርፍ አራት በመቶ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን፣ እንዲሁም ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ደግሞ 3.5 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ለእነዚህ የኢኮኖሚ ዘርፎች የስድስት ወራት የፍሬ ብድርና የወለድ ክፍያ የዕፎይታ ጊዜ ከሜይ 18 ቀን 2020 ጀምሮ እንዲደረግላቸው ባንኩ ወስኗል፡፡ በሌላም በኩል ተበዳሪዎቻችን በኮቪድ-19 ጫና ምክንያት የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ጥያቄ ቢያቀርቡ ጥያቄያቸው እንደ ሁኔታው እየታየ የሚስተናገድ እንደሚሆን ብርሃን ባንክ አስታውቋል፡፡ ብርሃን ባንክ ይህንን የወለድ ምጣኔ ቅናሽ በማድረጉ በዓመት ሊያገኝ የሚችለውን ወደ 100 ሚሊዮን ብር የሚሆን የወለድ ገቢ የሚያሳጣው መሆኑ ታውቋል።

አንበሳ ባንክ ከወረርሽኙ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ በመገምገም ወረርሽኙ ቀጥተኛ ተፅዕኖ በሚያሳርፍባቸው የኤክስፖርት፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ግብርና፣ የአገር ውስጥ ንግድ፣ የትራንስፖርትና የቤቶች ግንባታ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ተበዳሪ ደንበኞቹ ከ0.5 በመቶ እስከ አምስት በመቶ የሚደርስ የማበደሪያ ወለድ ምጣኔ የተለያዩ የብድር ውሎችን ወደ አንድ ለማዋሃድ የብድር ማራዘሚያ፣ የብድር ክፍያ የዕፎይታ ጊዜ መጠየቅና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች ላይ ተጥለው የነበሩ የኮሚሽንና የአገልግሎት ክፍያዎች ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ ተደርጓል፡፡  

የደንበኞች ጥያቄ መሠረት ባደረገ መልኩ ባንኩ ከሦስት እስከ ስድስት ወር የሚቆይ የልዩ የዕፎይታ ጊዜ ተግባራዊ እንዲደረግ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡

ለአስመጪዎች በሌተር ኦፍ ክሬዲትና በሰነድ ዋሌት አገልግሎቶች ተጠቃሚ የሆኑ አስመጪዎች ደንበኞች ከንግድ እንቅስቃሴው መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ በደንበኞች ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማቃለል በደንበኞች ጥያቄ መሠረት ለሚደረጉ የኮንትራት ውል ማሻሻያና ማራዘሚያ ጥያቄዎች የአገልግሎት ክፍያዎች ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ መወሰኑን አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ገልጿል፡፡

ደንበኞች ከገንዘብ ጋር የሚኖራቸውን ንክኪ ለመቀነስና ወደ ቅርንጫፍ መሄድ ሳያስፈልጋቸው በአቅራቢያቸው ከሚገኙ እንደ ኤቲኤምና ፖስ ማሽኖች በመጠቀም ገንዘብ ወጪ ለሚያደርጉ ደንበኞች ያስከፍል የነበረውን የአገልግሎት ክፍያ (ኮሚሽን) ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ መደረጉንና ደንበኞች የሞባይል ባንኪንግና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎችን በመጠቀም ገንዘብ ወጪ ለማድረግም ሆነ ከሒሳብ ወደ ሒሳብ ማንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ቀልጣፋ አሠራር ዘርግቶ ተግባራዊ እንደሚሆኑ አንበሳ ባንክ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በወሰደው የብድር ወለድ ምጣኔ ቅነሳና ልዩ ልዩ የአገልግሎት ከክፍያ ነፃ የማድረግ ውሳኔ ምክንያት በትንሹ እስከ 21 ሚሊዮን ብር ያህል ገቢ እንደሚያሳጣውም ይኸው የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡

ብርሃን ባንክ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሰፊውን ማኅበረሰብና የባንኩን ደንበኞች ማዕከል ያደረጉ በርካታ ተግባራትና ድጋፎች ከዚህ ቀደም ማከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም አንፃር ቀደም ሲል የሌተር ኦፍ ክሬዲት ማራዘሚያ ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን የብድር ማራዘሚያ ኮሚሽንና የተጨማሪ ወለድ ማንሳቱ በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች በ35 ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የንፅሕና አገልግሎት መስጫ የውኃ ታንከሮችን ማዘጋጀቱና እንዲሁም ለጤና ሚኒስቴር ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉም ባንኩ አስታውሷል፡፡ አንበሳ ባንክም ተጨማሪ ድጋፎች አደርጋለሁ ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች