ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ እያሽቆለቆለ የመጣውን የወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ ለማሻሻል በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው መመርያ ውጤት እያስገኘ በመምጣቱ፣ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ63 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ወርቅ ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ ወደ ባንክ የሚመጣውን የወርቅ ማዕድን መጠን ማሻሻል በመቻሉ ወደፊት ከወርቅ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል፡፡
ማሻሻያው ብሔራዊ ባንክ ለሚቀርብለት ወርቅ ከእስካሁኑ የተሻለ ዋጋ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበውን የወርቅ መጠን እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ የገባው ወርቅ ካለፈው ሙሉ ዓመት የወርቅ ገቢ አኳያ፣ የእጥፍ ያህል ጭማሪ እንዳስገኘ ይጠቁማል፡፡
ባለፈው ዓመት አጠቃላይ የወርቅ ወጪ ንግድ 35 ሚሊዮን ዶላር እንዳስገኘ ያስታወሱት ይናገር (ዶ/ር)፣ አዲሱ መመርያ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በአንድ ወር ብቻ ከ63 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ወርቅ መገኘቱን ነው፡፡
ይህ የግብይት መጠን እያደገ እንደሚሄድ በመታሰቡ፣ በመጪዎቹ ወራትም ከወርቅ የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ማሻሻያው ቀድሞ ከዓለም የወርቅ ዕለታዊ ዋጋ በመነሳት የአምስት በመቶ ብልጫ የሚታሰብበት ዋጋ ለአቅራቢዎች ይሰጣቸው ነበር፡፡ ይህ ተስተካክሎ አብልጫ ባለው ዋጋ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ እየገዛ ይገኛል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በኮሮና ጫና ሳቢያ እየተቀዛቀዘ የመጣው የአገሪቱ አጠቃላይ የወጪ ንግድ፣ በተለይ ከጥቂት ወራት ወዲህ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ መሻሻል እንዳሳየ የባንኩ ገዥ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ቡና ላይ የገበያና የገቢ መሻሻል እንደታየ ጠቅሰዋል፡፡