Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጥሬ ገንዘብ የሚደረገውን ዝውውርን የመገደብ ሚና

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብ አማካይነት የሚደረግ ግብይት፣ ለዓመታት ፀንቶ የቆየ ልማድ ነው፡፡ በዘመናዊ የክፍያና የገንዘብ ዝውውር ዘዴዎች የመጠቀም ዝንባሌም ተሞክሮም ዝቅተኛ በመሆኑ፣ በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ ግብይቶች ለዘመናት ተንሰራፍተዋል፡፡

ይህም አገልግሎት እንዳይቀላጠፍ ከማድረጉም በላይ ለአደገኛና ሕገወጥ ሥራዎች መበራከት ምቹ ሆኗል፡፡ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በሌሎች አማራጮች መቀየር ዘመናዊ የክፍያ ዘዴዎችን የመጠቀም ተገቢነት ትኩረት ቢያገኝም፣ እስከቀርብ ጊዜ ድረስ ይህንን መገደብ የቻለ አሠራር አልተዘረጋም ነበር፡፡ በጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ የሚጥል አሠራር እንዲጣል የሚያስገድዱ ሁኔታዎችም አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን በማስመልከት ባንኮች ጥናት ማካሄድ ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክም በባንኮች የተካሄደውን ጥናት መነሻ በማድረግ ብሎም በራሱ ላይ ካካሄደው የሪፎርም ሥራ በመነሳት፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በዘመናዊ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ከባንኮች ወጪ በሚደረገው የጥሬ ገንዘብ ላይ ገደብ የሚጥል መመርያ አውጥቷል፡፡

በጥሬ ገንዘብ የሚደረገውን ዝውውርን የመገደብ ሚና

በዚሁ መመርያ ዙሪያ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ከግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በየቀኑ በጥሬ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት የሚችሉት መጠን ተገድቧል፡፡ ከተቀመጠው ገደብ በላይ ማንቀሳቀስ ሲያስፈልግም ሌሎች የክፍያ ዘዴዎች መጠቀም እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡

መመርያው በአስገዳጅነት እንዲተገበር ስለተፈለገበት ምክንያት የጠቀሱት ገዥው፣ በኢትዮጵያ ያለ ምንም ገደብ ሰዎች ያሻቸውን ያህል የጥሬ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት የሚችሉበትን ክፍተት በመንተራስ የተለያዩ ወንጀሎች ሲፈጸሙ መቆየታቸውና አደገኛ እየሆኑ መምጣታቸው የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ላይ ገደብ ለማስቀመጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውርንና ወንጀሎችን ለመቆጣጠር መመርያው መውጣቱን የገዥው ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ ሌሎች ኃላፊዎችም መመርያው ከባንክ ውጭ የሚገኘውን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ ያግዛል ብለዋል፡፡

በጥሬ ገንዘብ ከባንክ የሚከፈል ገንዘብ በአብዛኛው የዓለም ክፍል የተመለደ አሠራር እንደሆነ ያስታወሱት ይናገር (ዶ/ር)፣ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለማስፋፋት፣ የታክስ ሥራን ለመቆጣጠር፣ ባልተገባ መንገድ ከባንክ ውጭ የተከማቸ ገንዘብ ወደ መደበኛ ኢኮኖሚ ለማስገባት መመርያ ማውጣት እንዳስፈለገ ገልጸዋል፡፡ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ላይ ገደብ በማስቀመጥ በዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት መፈጸሚያዎች እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱና የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርም ያቀረበው ጥያቄ በመሆኑ መመርያው መውጣቱ ተብራርቷል፡፡

ባንኮች በመመርያው ተጠቃሚ እንደሆኑ የገለጹት የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ተፈሪ፣ ጥሬ ገንዘብን ከአንድ ቅርንጫፍ ወደ ሌላ ቅርንጫፍ ለማዛወር ባንኮች የሚያባክኑት ሀብትና ጊዜ ከፍተኛ በመሆኑ ጭምር ይህንን ሊቀንስላቸው እንደሚችል ይታመናል ብለዋል፡፡ ገንዘብ በጥሬው ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ ማዛወር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም የሚፈልግ፣ ለዚህ ሲባልም የውጭ ምንዛሪ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ መመርያው ግን እንዲህ ያሉ ብክነቶችን ያስቀራል ተብሏል፡፡

ከባንኮች የሚወጣው ገንዘብ ገደብ አልባ እንደነበር የሚገልጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ ከአንድ ባንክ ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን ብር በጥሬው እየወጣ በኬሻ ሲንቀሳቀስ ከልካይ ስላልነበረበት፣ ይህንን ለመገደብ የወጣው መመርያ ፋይዳው እንደሚጎላ ታምኖበታል፡፡

አዲሱ መመርያ ግለሰብ ደንበኞች በቀን 200 ሺሕ ብር፣ በወር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር በጥሬ እንዲያወጣ ይፈቅድለታል፡፡ ኩባንያዎች በቀን የሚፈቀድላቸው እስከ 300 ሺሕ ብር ሆኖ፣ በወር ከ2.5 ሚሊዮን ብር እንደማይበልጥ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ በላይ ማንቀሳቀስ የሚፈልጉ ከሒሳብ ወደ ሒሳብ በቼክና በሲፒኦ ማንቀሳቀስ ይፈቀድላቸዋል፡፡

በመመርያው ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ የባንኮች ፕሬዚዳንቶች እንደጠቀሱት፣ መመርያው ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ከማስፈን በላይ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት ሚና ይኖረዋል በማለት የብሔራዊ ባንክ ገዥውን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡

መመርያውን በሚተላለፉ ላይ ቅጣት ተቀምጧል፡፡ አንድ ባንክ ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን በላይ ከከፈለ፣ በተቀመጠው ገደብ በላይ ባለው የገንዘብ መጠን ልክ ተሰልቶ የ25 በመቶ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ ለአብነት ያህል፣ በመመርያው ከተቀመጠው የገንዘብ ገደብ በላይ አሥር ሚሊዮን ብር የከፈለ ባንክ ቢኖር 2.5 ሚሊዮን ብር እንደሚቀጣ በመመርያው የተቀመጠው የቅጣት ዕርከን ያስረዳል፡፡

በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ የግብይትና የክፍያ ሥርዓት ቀስ በቀስ ወደ  ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት እንዲሸጋገር ማድረግ አንዱ የብሔራዊ ባንክ የሪፎርም ሥራ በመሆን ሲተገበር እንደቆየ የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ መመርያው ቀድሞም የነበረና በአንዳንድ ሁኔታዎች ለትግበራ መዘግየቱን አስታውሰዋል፡፡

በአብዛኛው የዓለም ክፍል ከባንክ ወጪ የሚደረግ ጥሬ የገንዘብ ገደብ ተጥሎበት እንደሚንቀሳቀስ ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘበነ በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በናይጄሪያ አንድ ደንበኛ ከባንክ ማውጣት የሚችለው 1,400 ዶላር ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ 70 ሺሕ ዶላር ይፈቀዳል፤›› በማለት ገደብ ማስቀመጥ በዓለም ላይ የተመለደ አሠራር እንደሆነ አሳይተዋል፡፡ ‹‹እውነቱን ለመናገር ዘግይቷል ካልተባለ በቀር፣ መመርያው መተግበሩ ያን ያህል ጥያቄ ይነሳበታል የሚል እምነት የለኝም፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖም መመርያው ቢዘገይም መውጣቱ አግባብ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ ይናገር (ዶ/ር) መመርያው በመዘግየቱ ምክንያት ኢኮኖሚውን በተለይም አጠቃላይ የግብዓት ሥርዓቱን የሚጎዱ ተግባራት ተባብሰው መቆየታቸውን በመግለጽ የፕሬዚዳንቶቹን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡

መመርያው መተግበር ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ደርሰናል ያሉት  ይናገር (ዶ/ር)፣ በተለይ በቅርቡ ከንግድ ባንክ በተጭበረበረ መንገድ 60 ሚሊዮን ለማውጣት የተሞከረው፣ በተመሳሳይ መንገድ ከአንድ ዳያስፖራ አካውንት ላይ ከኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በሌላ የዳያስፖራ አካውንት ውስጥ ከነበረ ከ356 ሚሊዮን ብር ውስጥ 55 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማድረግ የተቀነባበረው ወንጀል፣ ለመመርያው በቶሎ ወደ ተግባር መግባት አጣዳፊ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ጭምር እየታገዙና ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ባንኮችን ለመዝረፍ የሚሞክሩ ቡድኖችንና አጭበርባሪዎችን እየታዩ በመሆናቸው፣ መመርያው ተግባር ላይ በአፋጣኝ እንዲውል መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ያለውን ነገር እያዩ ዝም ማለት ስለማይቻል፣ ውንብድናን ለመከላከል የሚቻልበትን መመርያ ለመተግበር ጊዜ የምናጠፋበት ምክንያት የለም፤›› በማለት መመርያው መውጣቱ ትክክል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በመመርያው አስፈላጊነት ላይ የባንኮች ማኅበር በሰጠው መግለጫ፣ ከባንኮች  ውጭ የሚገኘውን የገንዘብ መጠን ሊቀንሰው እንደሚችል አመላክቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ጁን 2016 ላይ ከባንክ ውጭ የሚዘዋወረው የጥሬ ገንዘብ መጠን 63 ቢሊዮን ብር እንደነበር አቶ አቤ አስታውሰው፣ በኤፕሪል 2020 ግን ወደ 113 ቢሊዮን ብር መጨመሩን ገልጸዋል፡፡ ከባንኮች ውጭ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ መቀነስ ሲገባው አለመቀነሱ ጤናማ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡ የባንኮች የቅርንጫፍ ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ በመጨመሩ፣ በሰዎች እጅ ላይ የሚገኘው ገንዘብ እያነሰ ወደ ባንኮች መከማቸት ይጠበቅበት ነበር፡፡ ‹‹ሒደቱ ግን ተቃራኒ እየሆነ መምጣቱ ችግር እንዳለና በሰዎች እጅ ያለው ገንዘብ ከመቀነስ ይልቅ መጨመሩን የሚያሳይ በመሆኑ የዚህ መመርያ መውጣት እንዲህ ያለውን ክፍተት ይደፍናል፤›› ብለዋል፡፡

ጠቀሜታው የሚነገርለት የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን የሚገድበው መመርያ የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛል፡፡ አንዳንዶች በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ እጥረት ስላለበት እንደወጣ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት ይናገር (ዶ/ር)፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የገንዘብ መጠን እናውቀዋለን በማለት በየዓመቱ የሚታተመው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ በመግለጽ ምላሽ ሰጥተውዋል፡፡ ለብዙ ጊዜ አገልግሎት በመስጠት የሚወገድ የገንዘብ ኖት ጭምር ተደምሮና ተቀንሶ በጠቅላላው ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ይታወቃል በማለት ይህ ችግር እንደማይሆን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

‹‹በየቀኑ በባንኮች የሚያድረው ገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ በአካውንታቸው ላይ የሚያሳይ ሲስተም አለ፡፡ ከዚህ ውጭ በግለሰቦች ኪስ ውስጥ ያለ ወይም ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ቤታቸው ካዝና ውስጥ የሚያስቀምጡት ይኖራል፡፡ ይኼ በሰዎች እጅ የሚገኘው ገንዘብ በሙሉ ግን ሕገወጥ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በሁሉም ሰው ኪስ ውስጥ ወይም በቤት ጥቂት ገንዘብ ሊኖር ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉትን ገንዘቦች ሕገወጥ ነው ማለት አይቻልም፤›› በማለት ይልቁንም ወደፊት ወደ ሕጋዊ ግብይት ስለሚገባ እንዲህ ያለውን ገንዘብ ሕገወጥ ማለቱ አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹እኛ እያነሳን ያለነው በሕገወጥ ሥራዎች ለግብይት ጥቅም ላይ የሚውለውን ገንዘብ ነው፡፡ አርባና ሃምሳ ሚሊዮን ብርና ከዚያም በላይ ገንዘብ አውጥተው የውጭ ምንዛሪ በጥቁር ገበያው ሲገዙ የሚውሉ ሰዎች አሉ፡፡ እየተነጋገርን ያለነው ስለዚህ ነው፡፡ ወንጀለኞች አሉ፤›› በማለት መመርያው በዋነኛነት ዒላማ ያደረገው ሕገወጦች ላይ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡

ባንኮች በቅርቡ ያጋጠማቸው የገንዘብ እጥረት ይህ መመርያ እንዲወጣ ምክንያት አልሆነም ወይ? ተብለው ከሪፖርተር ለተሰነዘረላቸው ጥያቄም ይናገር (ዶ/ር)፣ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ በተወሰነ መልኩ ጥቂት ባንኮች ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ ይህንኑ ችግር ለመፍታት በብሔራዊ ባንክ በኩል ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ብለዋል፡፡ ባንኮቹም ዕርምጃዎችን በመውሰዳቸው፣ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ያሉት ገዥው፣ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ማከናወን የሚያስችላቸው በቂ የጥሬ ገንዘብ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ ተጨማሪ ካስፈለጋቸውም ከብሔራዊ ባንክ የሚያገኙበት ሁኔታ ስለተመቻቸ፣ በእጃቸው ከሚገኝ ወይም በቀላሉ ሊያገኙት ከሚችሉት የገንዘብ አቅርቦት ጋር የተያያዘ ከባድ ችግር እንደማይታይ ገልጸዋል፡፡

ባንኮቹ ለዚህ መመርያ አፈጻጸም ምን ያህል ተዘጋጅተዋል የሚለው ጥያቄም  ይናገር (ዶ/ር) ምላሽ የሰጡት፣ የመመርያው መውጣት ከባንኮች ፍላጎት ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑን በማመላከት ነበር፡፡ መመርያው እንዲወጣ ባንኮቹ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸውንና ጥናት አጥንተው እስከማቅረብ መድረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡  በተደጋጋሚ በባንኮች ማኅበር በኩል ጥያቄ እንዳቀረቡ የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ ከባንኮች ፕሬዚዳንቶች ጋር በመነጋገር መመርያውን ለማስፈጸም መሠረታዊ ችግር እንደሌለ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራሁ፣ የባንክ ተጠቃሚዎች በዘመናዊ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኙ ዝግጅት መደረጉን በመግለጽ መመርያውን ለመተግበር ባንኮች ዝግጁ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለማጎልበት ሁሉንም ባንኮች የሚያስተሳስረው ‹‹ኢትስዊች›› የተባለው ሥርዓት እንዳለ፣ የኦንላይን ባንኪንግ አገልግሎት በሁሉም ባንክ ስላለ፣ መመርያውን ለማስተግበር አማራጭ የክፍያ ዘዴዎች ተዘጋጅተው ስለሚገኙ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደማይኖር አቶ ፀሐይ አብራርተዋል፡፡

ከባንክ ውጭ ያሉ ድርጅቶች ምን ያህል ተዘጋጅተዋል የሚለው ጉዳይ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ከሪፖርተር በቀረበ ጥያቄ ይናገር (ዶ/ር) በዚሁ ሥጋት ዙሪያ ‹‹የውጭ አገር ድርጅቶች ከየመጡበት አገር የፋይናንስ ሥርዓት አኳያ ብዙዎቹ ይኼ ገደብ ያለባቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ባለሀብቶች ጥሬ ገንዘብ በኬሻ ታጭቆ በመኪና ተጭኖ ከሚኬድበት አገር የመጡ አይደሉም፡፡ እነሱ ስለሚያውቁት ብዙም አሳሳቢ አይሆንም፡፡››

ከዚህም ባሻገር በእስካሁኑ ተሞክሮ ትልልቅ ኩባንያዎች ከባንክ ወደ ባንክ በሚደረግ የሒሳብ ክፍያ እንጂ ጥሬ ካሽ ላይ የተመሠረተ ክፍያ እንደማይፈጽሙ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ከሥራ ባህርያቸው አንፃር በጥሬ ገንዘብ ክፍያ የሚፈጽሙ አንዳንድ ኩባንያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህንን መመርያ እንዲተገብሩ እናደርጋን፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ጉዳይ ካጋጠመ በልዩ ሁኔታ የሚፈቀድበት አግባብ አለ፤›› በማለት ድርጅቶቹ እስኪዘጋጁ ድረስ በልዩ ሁኔታ እየተፈቀደላቸው የሚሠሩበት መንገድ እንደሚያመቻችላቸው ገዥው አስታውቀዋል፡፡  

ከአንድ አካውንት ወደ ሌላ አካውንት ያለ በቂ ደጋፊ ሰነድ በተለየ መንገድ የሚተላለፉ ሒሳቦች ሲኖሩም ይህንን የሚቆጣጠር ሌላ አካል አለ ያሉት ገዥው፣ ይኸውም የፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል ይህንን እንደሚከታተል አስታውሰዋል፡፡ ማዕከሉ አጠራጣሪ የገንዘብ ልውውጦች ወይም ግብይቶች በባንኮች ሲካሄዱ ይቆጣጠራል ይከታተላል ተብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች