Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሲጋራ ማሸጊያ ላይ የጤና ጉዳት ምሥል እንዲታተም የሚያስገድደው ሕግ ተግባራዊ መሆን ሊጀምር...

የሲጋራ ማሸጊያ ላይ የጤና ጉዳት ምሥል እንዲታተም የሚያስገድደው ሕግ ተግባራዊ መሆን ሊጀምር ነው

ቀን:

መንግሥት ትምባሆ አምራቾች በሲጋራ ምርት ማሸጊያ ላይ ሲጋራ የሚያደርሰውን የጤና ጉዳት የሚያሳይ ምሥል እንዲያትሙ የሚያስገድደውን ሕግ ማስተግበር ሊጀምር ነው።

የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለፈው ዓመት በፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1112/2011 መሠረት፣ የትምባሆ አምራቾች አስገዳጅ የጤና ጉዳት ማስጠንቀቂያዎችን በትምባሆ ምርቶቻቸው እያንዳንዱ ማሸጊያ ላይ በጽሑፍና በምሥል እንዲያስቀምጡ እንዲያስገድድ ሥልጣን ይሰጠዋል።

የትምባሆ አምራቾች አስገዳጅ የጤና ማስጠንቀቂያ መልዕክቶቹን በምርቶቻቸው ማሸጊያ ላይ እንዲያስቀምጡ የሚያስገድደው የአዋጁ አንቀጽ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረው አዋጁ ከፀደቀ ከአንድ ዓመት በኋላ በመሆኑ፣ ይኸው ጊዜም በሕጉ መሠረት ለመዘጋጃነት ውሎ በመጠናቀቁ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በአስገዳጅነት ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር አዋጁን ከሚያስፈጽመው የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባለሥልጣኑ ትምባሆ ማጤስ የሚያደርሰውን የጤና ጉዳት የተመለከተ የምሥል ማስጠንቀቂያ አሰናድቶ፣ ለዚህም አስፈላጊውን የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት አግኝቶ ማጠናቀቁን፣ እንዲሁም የምሥል ማስጠንቀቂያውን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የትምባሆ ምርትና ንግድ ላይ ተሳታፊ ከሆነ ባለድርሻዎች ጋር ምክክር አድርጎ ማጠናቀቁን መረጃው ያመለክታል።

በመሆኑም ከመጪው ዓርብ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ማናቸውም የሲጋራ ምርት ማሸጊያዎች የጤና ጉዳት ምሥሎቹን መያዝ ይኖርባቸዋል ተብሏል።

የአዋጁ አንቀጽ 57 (1) ማንኛውም የትምባሆ ምርት ማሸጊያ አስፈጻሚው አካል በሚያወጣው መሥፈርት መሠረት፣ በጊዜ ቀመር የሚቀያየር የጤና ማስጠንቀቂያ ጽሑፍና ባለቀለም ምሥል በአንድ ላይ መያዝ እንዳለበት ይደነግጋል።

 የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ አስፈጻሚ አካሉ በሚያወጣው መሥፈርት መሠረት የጤና ማስጠንቀቂያውን ለመክበብ የሚውለውን ቦታ ሳይጨምር፣ በትምባሆ ምርቱ የውጭ ማሸጊያ በእያንዳንዱ የፊትና የኋላ ገጽ ከ70 በመቶ ያላነሰ መሆን እንደሚገባው ደንግጓል።

 በማንኛውም የትምባሆ ምርት የውጭ ማሸጊያ ላይ የሚቀመጥ የጤና ማስጠንቀቂያ ጽሑፍና ምሥል አቀራረብ የምርቱን ባህሪ፣ ጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ወይም ልቀቱን በሚመለከት የተሳሳተ አረዳድ በሚፈጥር መንገድ ወይም አንድ የትምባሆ ምርት ከሌላ የትምባሆ ምርት ያነሰ ጉዳት እንዳለው አድርጎ መግለጽም በአዋጁ መሠረት የተከለከለ ነው።

የንግድ ምልክትን ወይም ቀለምን በመጠቀም ወይም በጽሑፍ አንድ የትምባሆ ምርት አነስተኛ የታር መጠን እንዳለው ወይም ሌላ ተመሳሳይ መንገድን በመጠቀም፣ የትምባሆ ምርቱ የሚያደርሰው የጤና ጉዳት አነስተኛ አድርጎ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መግለጽ የተከለከለ እንደሆነም በአዋጁ ተደንግጓል።

 ከላይ የተገለጹትን ድንጋጌዎች መተላለፍ እስከ ሦስት ዓመት እስራትና ሁለት መቶ ሺሕ ብር እንደሚያስቀጣም ተደንግጓል። አዋጁ በአንቀጽ 61 ባስቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ማንኛውንም የትምባሆ ምርትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማስተዋወቅ፣ ወይም ስፖንሰር ማድረግ የተከለከለ ነው። በሌላ በኩል በአንቀጽ 61(3) ድንጋጌ በችርቻሮ መሸጫ ሱቆች የትምባሆ ምርትን ለሸማች ዓይን በሚታይ ቦታ መደርደር የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል።

 ሱቆች የትምባሆ ምርትን ለሸማቾች በእሽግ ፓኬት ካልሆነ በስተቀር በፍሬ መሸጥ እንደማይችሉም አዋጁ ይደነግጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ትምባሆን ለመከላከል የተደረጉ ጥናቶችን መሠረት አድርጎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን መመርያ፣ የምሥል ማስጠንቀቂያዎችን በትምባሆ ምርቶች ማሸጊያ ላይ በአስገዳጅነት መጠቀም ትምባሆ ተጠቃሚዎችን ለመቀነስ ከዋሉ ውጤታማ ሥልቶች አንዱ በመሆኑ አገሮች እንዲተገብሩት ያሳስባል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...