Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበገለልተኛ ባለሙያዎች የተረቀቀውን የጥብቅና አገልግሎት የሕግ ማሻሻያ መንግሥት አለመቀበሉ ቅሬታ ፈጠረ

በገለልተኛ ባለሙያዎች የተረቀቀውን የጥብቅና አገልግሎት የሕግ ማሻሻያ መንግሥት አለመቀበሉ ቅሬታ ፈጠረ

ቀን:

በሕግና ፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት ሥር ከተቋቋሙ የሥራ ቡድኖች መካከል አንዱ በሆነው የሕግ ማሻሻያ ቡድን የተረቀቀውን የጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ውድቅ ማድረጉ ቅሬታ ፈጠረ፡፡

ቅሬታውን ለሪፖርተር የላከው ዓለም አቀፍ የጠበቆች ማኅበር ሲሆን፣ ማኅበሩ በኢትዮጵያ የተጀመረው የሕግና የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮግራም በገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን እንዲመራ መደረጉን በከፍተኛ ደረጃ አወድሷል፡፡

በሕግ ማሻሻያ ፕሮግራሙ የሕግ ባለሙያዎችን ዕውቀት ለመጠቀም የሥራ ቡድኑ አባል እንዲሆኑ መደረጉና ከሕግ ሙያው ውስጥና ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላት አስተያየትና ምልከታዎቻቸው ተደማጭነት እንዲያገኙ የተደረገው ጥረት፣ በሁሉም አካላት ላይ ዕምነት ያሳደረና ለሌሎች አገሮችም አርዓያ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ለዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  የሰብዓዊ መብት ሪፖርት የሰጠው አድናቆት ለአብነት አስታውሷል፡፡ ይሁንና በገለልተኛ የባለሙያ ቡድኖች ከተረቀቁት ሕጎች መካከል የጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ አንዱ መሆኑን፣ ይኸውም ብቁ በሆኑ ባለሙያዎች ተረቆ የተጠናቀቀና የመጨረሻ ረቂቁንም ቡድኑ በነሐሴ 2011 ዓ.ም ለመንግሥት ማስረከቡን መግለጫው ያመላክታል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ረቂቅ ሕጉን በተመለከተ ምንም ዓይነት ተጨማሪ እንቅስቃሴ ሳይደረግ የቆየ ቢሆንም፣ በታኅሳስ 2012 ዓ.ም. ላይ ያልተጠበቀ አማራጭ ረቂቅ አዋጅ ለውይይት መቅረቡን አመልክቷል፡፡

የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በባለሙያዎች ከተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ጋር በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነት እንዳለው ማኅበሩ አስረድቷል፡፡ በዓቃቤ ሕግ የተረቀቀው አዲስ ሕግ ሳይሻሻል ከፀደቀ የሕግ ማሻሻያ የፕሮግራሙ ሊያሳካቸው ከሚችለውና ከሚገቡ ዓላማዎች አንፃር ሲታይ ወደ ኋላ የሚዳርግ እንደሚሆን፣ ማኅበሩ በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት አዲስ ባዘጋጀው አዋጅ ውስጥ ሳይካተቱ መቅረት የለባቸውም ያላቸውን ነጥቦች ለመንግሥት ማስረከቡን ጠቁሟል፡፡

ከእነዚህም መካከል የጠበቆች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሕጉ ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ የጠበቆች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከአድልኦ ነፃ ሆኖ የሙያ ፈቃድ አሰጣጥን፣ የዕደሳን፣ የዕገዳና የስረዛ ሥርዓትን የሚመሩ፣ ለጥራት ቁጥጥር የሚያከናውኑና ፍትሐዊ የሆነ የቅጣት ውሳኔዎች ማስተላለፍ የሚችሉ ነፃ ተቋማትን የሚያካትት ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕጉ እነዚህ አካላት አስፈላጊ የሆኑ ደንብና መመርያዎችን ማውጣት እንዲችሉ የሚያስችል ሊሆን እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

የአስተዳደር ተቋማት የሚያሳልፏቸውን ውሳኔዎችና የሚወስዱዋቸውን ዕርምጃዎችን የሚከታተሉ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ አካላት መኖር እንዳለባቸው፣ የእነዚህ አካላት ሥልጣን የአስተዳደር ተቋማት ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች ሕጋዊነትን መገምገም ብቻ መሆን እንዳለበትም አስታውቋል፡፡

በሕጉ ውስጥ ስለሕግ ባለሙያው አሠራርና ነፃነትና ሚስጥራዊነት፣ እንዲሁም የጥቅም ግጭትን ማስቀረት የተመለከቱ የሕግ ባለሙያ መሠረታዊ መርሆዎችን የሚዘረዝር ክፍል ሊካተት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የጥብቅና አገልግሎት አዋጅ ከመፅደቁ አስቀድሞ በሕጉ በሥነ ምግባር ደንብ ውስጥ የሚካተቱ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጠቅላላ መርሆችን እንዲያጠቃልልም ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

በባለሙያዎች ቡድን የተረቀቀው አዋጅ ከላይ የተዘረዘሩትን በሙሉ አካቶ የተሰናዳ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይህን ረቂቅ ውደቅ አድርጎ የራሱን ሌላ አዋጅ አርቅቆ ለውይይት አቅርቧል፡፡ ይህ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተሰናዳው ረቂቅ የጥብቅና ፈቃድ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሚሰጥ ይደነግጋል፡፡

ጠበቆች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በጠበቆች ማኅበር ሥር በሚቋቋም ኮሚቴ ተግባራዊ እንዲደረግ ድንጋጌው ያመለከተ ቢሆንም፣ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ግን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ጠበቆች በማኅበራቸው አማካይነት ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸው በረቂቁ የተፈቀደ ቢሆንም፣ በተቋማቸው በኩል ራስን ስለማስተዳደር የሚያስተላልፉላቸው ውሳኔዎች በፍርድ ቤት ቀሪ እንዲደረጉ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ በሕግና ፍትሕ ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤቱ ተረቆ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ውድቅ የተደረገ ሕግ የለም ብለዋል፡፡

አማካሪ ምክር ቤቱ ገለልተኛ ሙያዊ አገልግሎትን ይስጥ እንጂ ሥራውን እያከናወነ ያለው በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር መሆኑን፣ አማካሪ ምክር ቤቱ አርቅቆ ውድቅ የተደረገ ሕግ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን በአማካሪ ምክር ቤቱ ተረቆ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር በጋራ በመሆን ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ፣ ይህም ሁሉም የፀደቁ ሕጎች የተረቀቁበት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የጠበቆች ማኅበር መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገ በዓለም ላይ የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ሲሆን፣ በ1947 ዓ.ም. ነው ተቋቋመው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...