Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ዘመኑን የማይዋጅ አስተሳሰብ ፈላጊ የለውም!

  አገር በሥርዓት መኖር ካልቻለች የሕዝብ ሕይወት እንደሚመሰቃቀል ከሚያመላክቱ በርካታ ጉዳዮች መካከል አንደኛው፣ አንድ አጣዳፊ ጉዳይ ሲያጋጥም በየአቅጣጫው የሚስተዋለው መወራጨትና መደነቃቀፍ ነው፡፡ በሕጋዊ መንገድ መፈታት ያለበት ችግር ሲኖር፣ ፖለቲካዊ መፍትሔ ካልሆነ በስተቀር ተብሎ ሱሪ በአንገት ይባላል፡፡ ሕጋዊ ችግር አጋጥሞ መፍትሔ ለመስጠት አዳጋች ሆኖ በመስኩ ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጥበት ግብዣ ሲቀርብ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ድምፅን ማሰማት እየተቻለ ለፖለቲካ ፍጆታ እንዲውል በማድረግ ዓላማውን እንዲስት ይደረጋል፡፡ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ወቅቱን የሚመጥን መፍትሔ ይዞ ከመቅረብ ይልቅ፣ ትችትና ማሳጣት ውስጥ እየተገባ ዋናው ችግር አደጋ ይደቅናል፡፡ ኢትዮጵያ ከእንዲህ ዓይነቱ ነገረኛና ሸረኛ ደባ ውስጥ ስትገባ የሚጎዳው፣ ያለ ኃጥያቱ የሚቀጣው ምስኪን ሕዝብ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደታየው ግጭት ሲቀሰቀስ ለዕልቂት፣ ለመፈናቀልና ለዝርፊያ ይጋለጣል፡፡ ኮሮናን የመሰለ አደገኛ ወረርሽኝ ሲከሰትም፣ ከጎስቋላ ኑሮው በተጨማሪ ሕይወቱ ከሞት ጋር ይፋጠጣል፡፡ በሕይወቱ ላይ የሚቆምሩ ፖለቲከኞች ደግሞ ለፖለቲካ ሒሳባቸው ማወራረጃ እያደረጉት፣ ኢኮኖሚያዊ መሽመድመድ ሲያጋጥመውና የሞት ሰለባ ሲሆን ለስታትስቲክስ ግብዓትነት ያውሉታል፡፡ ዘመኑ ከደረሰበት አስተሳሰብ ጋር ከሚጣሉ ድርቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ 

  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የኮሮና ወረርሽኝ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከውጭ ሲገባ የነበረው ወረርሽኝ፣ አሁን ደግሞ አገር በቀል ሆኖ የማኅበረሰባዊ ሥርጭቱ መስፋፋት በየቀኑ ሪፖርት እየተደረገ ነው፡፡ መዘናጋት በስፋት በመስተዋሉ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች መጠጥ ቤቶች፣ ቁማር ቤቶች፣ ጫትና ሺሻ ቤቶች ውስጥ በቡድን በመሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው በተለያዩ ጊዜያት ተይዘዋል፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከተፈቀደው በላይ ተሳፋሪዎችን በመጫን ሕግ ይጥሳሉ፡፡ ተሳፋሪዎችም ሕጉን በመጣስ ተባባሪ ይሆናሉ፡፡ ቤተ እምነቶች ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት እንዳይሰጡ ስምምነት ላይ ተደርሶ አማኞች ፀሎታቸውን በቤቶቻቸው እንዲያከናውኑ ቢደረግም፣ በተለያዩ ግፊቶችና ቅስቀሳዎች ሰዎች በቤተ እምነቶች መሰባሰብ ጀምረዋል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ መታገስ እያቃተ በአገር ላይ መዘዝ ለማምጣት የሚደረገው ሩጫ ያስተዛዝባል፡፡ ሌላው በጣም የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ድርጊት መሠረታዊ የሆኑ የጥንቃቄ መመርያዎችን ማክበር ባለመቻል ለሚደርሰው ችግር፣ እንደተለመደው የሰበብ ፈላጊዎች መብዛት ነው፡፡ ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ወዲህ ያሉትን ከሁለት ተኩል ወራት በላይ የነበሩትን የመዘጋጃ ጊዜያት የሚያስታውስ ማንም ትሁት ሰው፣ በእንዝህላልነት ምክንያት ወረርሽኙ ማኅበረሰባዊ ሥርጭቱ መስፋፋት ሲጀምር ሰበብ ደርዳሪዎች ሐሰተኛ ወሬዎችን ሲፈበርኩ በቀላሉ ይረዳል፡፡ የራስን ኃላፊነት ሳይወጡ ሌላ ላይ ጣት መቀሰር አያዋጣም፡፡ ዘመኑን የማይመጥን ኋላቀር ድርጊት ስለሆነ፡፡

  ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር ቅደም ተከተል ያስፈልጋታል፡፡ እጅግ በጣም አንገብጋቢ የሚባሉ ጉዳዮች ቅድሚያ ሲሰጣቸው፣ ሌሎች ደግሞ እንደ አንገብጋቢነታቸው ደረጃ ቅደም ተከተል ይኖራቸዋል፡፡ ቀዳሚውን ከተከታዩ ለማወቅ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ ዕቅድ ደግሞ በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ ለክትትልና ለቁጥጥር አመቺ ሆኖ ይቀረፃል፡፡ በጊዜ ሰሌዳ እየተመራ አፈጻጸሙ ይለካል፡፡ በመሀል ችግር ሲያጋጥም ማስተካከያ ይደረግለታል፡፡ በሥርዓት የሚመራ ድርጅትም ሆነ አገር ስኬትን የሚጨብጠው ሥራውን በአግባቡ መምራት በመቻሉ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ በመላምትና በደመነፍስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጥፋት እንጂ ጥቅም የላቸውም፡፡ ይህንን ጉዳይ ዘርዘር አድርገን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሰፊው ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ስንዳስስ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ለስኬት የሚበቁት ወይም ለውድቀት የሚጋለጡት፣ ከዕቅዳቸው እስከ አፈጻጸማቸው ባለው ሒደት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን መሰናክሎች በተቋቋሙበት መጠን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት በችግርነት ከሚወሱ ጉዳዮች መካከል አንደኛው በሥርዓት አለመመራት ሲሆን፣ ለዚህ በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሰው ለተቋማት ግንባታ የተሰጠው አናሳ ግምት ነው፡፡ መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር የነበረውን እንዳለ ማፍረስ እንጂ፣ የተሻሉትን ይዞ በማስቀጠል የበለጠ ለማጠናከር ጥረት ስለማይደረግ አገር በጣም ተጎድታለች፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታም የዚህ ውርስ ችግር ነው፡፡ ከዘመኑ ጋር የማይጣጣም ኋላቀርነት ማለት ይህ ነው፡፡

  ከግለሰብ ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች አመራር በመስጠት ላይ ያሉ ፖለቲከኞች፣ የመንግሥት ሹማምንት፣ የማኅበራት መሪዎች፣ የግል ተቋማት አስተዳዳሪዎች፣ ልሂቃን፣ ተመራማሪዎችና ሌሎችም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለማስወገድ የሚቻለው ከፍተኛ የሆነ የባህሪ ለውጥ ሲኖር ብቻ እንደሆነ ሊረዱ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥር የሰደዱ ዘመን ተሻጋሪ ለአገር የማይበጁ ቅራኔዎች አፍጥጠው እየታዩ ነው፡፡ እነዚህ ቅራኔዎች ትውልዱን ጭምር ጎራ እያስያዙ አገርን ለማፈራረስ በግብዓትነት እያገለገሉ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ልዩነትን አክብሮ የጋራ ጉዳዮቹ በልጠውበት በአንድነት ይኖር የነበረ ሕዝብ፣ አሁን ግን በግራና በቀኝ ተወጥሮ የዘመናት እሴቶቹ እየተሸረሸሩ ነው፡፡ በአንድነት የሚያሻግሩት ሰንሰለቶቹ እየተበጣጠሱ ወደ ክፍልፋይነት የሚለውጡ ቅስቀሳዎች እየተለፈፉለት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኮሮና መቅሰፍት እንዴት ተጠብቆ ይህንን ክፉ ጊዜ ማለፍ እንዳለበት ሳይሆን፣ የትናንት ሰቆቃዎች እየተተረኩለት እንዲናውዝ እየተደረገ ነው፡፡ ኮሮና ዓለምን በመቅሰፍት በትሩ እየቀጠቀጠ ኢትዮጵያ በራፍ ላይ ደርሶ፣ የሚቀድመውን ከሚከተለው መለየት ዛሬም ዳገት ሆኗል፡፡ በሥርዓት ተረዳድቶ ከዚህ መቅሰፍት ለማምለጥ አዋጭ ዕቅዶችን ለመንደፍ ሳይሆን፣ እርስ በርስ ተነዳድፎ ለመጥፋት የሚደረገው መቅበዝበዝ ከፍቷል፡፡ ለዚህ ዕርባና ቢስ ድርጊት የሚከፈለው አላስፈላጊ መስዋዕትነት ያስቆጫል፡፡ ቁጭት ደግሞ ለዚህ ለሠለጠነ ዘመን የማይፈይድ ዕዳ ነው፡፡

  ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ችግሮች አሳልፋለች፡፡ በእነዚህ ችግሮች ምክንያትም የተለያዩ ትውልዶች ከሚገባው በላይ ተሰቃይተዋል፡፡ በዘመነ ፊውዳሊዝም አብዛኛው ሕዝብ በገዛ አገሩ ገባር ነበር፡፡ ‹መሬት ላራሹ› የሚባለውን ዝነኛ መፈክር አንግቦ ለማኅበራዊ ፍትሕ የተነሳው ትውልድ፣ በየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት ንጉሣዊ ሥርዓቱን ከሥር መሠረቱ ፈንቅሎ ቢገረስሰውም፣ አብዮቱ እስከ አፍንጫው ድረስ በታጠቀ ወታደራዊ ኃይል ተቀለበሰ፡፡ የዘመኑ ትውልድ ከታጠቀው ኃይል ጋር ግብግብ ገጥሞ አገሪቱ በደም ታጠበች፡፡ ወታደራዊውን ሥርዓት ለመፋለም በረሃ የገባው ኃይል ከ17 ዓመታት የነፍጥ ትግል በኋላ ሥልጣነ መንበሩን ቢቆጣጠርም፣ ነፃ አውጭነቱ ወደ አምባገነንት ተቀይሮ ለ27 ዓመታት በሕዝብ ላይ ባደረሰው ከፍተኛ መከራ ምክንያት በሕዝባዊ ቁጣ በሌላ አስተዳደር ተተክቷል፡፡ በገዥነት የቆየው ኢሕአዴግ የሚባል ግንባር ከስሞ ታሪክ ሆኗል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ምንም ቋሚ ነገር እንደሌለ አልገባ የሚላቸው ግን፣ ዛሬም ያንን መሰል ሥርዓት መልሶ ሕዝብ ላይ ለመጫን የባጥ የቆጡን ሲቀባጥሩ ይሰማሉ፡፡ ዘመኑን በማይመጥን ፕሮፓጋንዳ የሰለቸ ትረካቸውን እያቀረቡ፣ ያንን የሰቆቃ መራር ጊዜ በማር ለውሰው እንደገና ለማምጣት ይዳዳቸዋል፡፡ ሕዝብ አንቅሮ ተፍቶ በማዕበሉ ወደ ዳር ቢገፋቸውም መግባባት አልተቻለም፡፡ ባረጀና ባፈጀ ዘመኑን የማይዋጅ ‹ተጨፈኑ ላሞኛችሁ› ነጠላ ዜማቸውን ያንጎራጉራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ጭምር ናቸው ከሕዝብ ጫንቃ ላይ አንወርድ ብለው የሚያላዝኑት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእነሱን ዓይነት ሞዴል የተከተሉ ሥርዓተ አልበኞች፣ ሕዝብና አገርን መቀመቅ ሊከት የሚችል ትንቅንቅ ውስጥ ለመግባት ዳር ዳር እያሉ ነው፡፡ ለዘመኑ በማይመጥን አስተሳሰብ ‹ውረድ እንውረድ› እየተባባሉ ፉከራ ውስጥ ናቸው፡፡  ዘመኑ ለአሮጌ አስተሳሰብ ቦታ እንደሌለው አልገባቸውም፡፡

  ኢትዮጵያ አሁንም ማዕበል እንደሚያንገላታት መርከብ ከአንድ ጥግ ወደ ሌላው እየተላጋች ነው፡፡ በለውጡ የተጀመረው ሽግግር በሕዝብ ተቀባይነት ባገኘ ምርጫ ተጠናቆ፣ አዲስ ጎዳና ለመያያዝ የተሰነቀው ተስፋ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ጠውልጓል፡፡ የጠወለገው ተስፋ ለይቶለት እንዳይመክን ይህንን አደገኛ ጊዜ በብልኃት መሻገር ሲቻል፣ ከወዲሁ የሚስተዋሉ መፍረክረኮች የበለጠ ተስፋ የሚያስቆርጡ ናቸው፡፡ የአብዛኞቹ ተፎካካሪ ኃይሎች ቀልብ ሥልጣን ላይ ተሰንቅሮ ማስተዋል የጎደለው የቃላት ጦርነት ውስጥ ተገብቷል፡፡ ወትሮም ለሕግና ለሥርዓት ባልታደለች አገር ውስጥ፣ ለአጉራ ዘለልነት የሚያመቻቹ መዘላለፎች ከየጎራው ይሰማሉ፡፡ እባካችሁ በስክነት ችግራችሁን ፍቱ ብለው የሚወተውቱ አርቆ አሳቢዎች አዳማጭ አጥተዋል፡፡ ነገር ለማጋጋል ካልሆነ በስተቀር ለቁምነገር ደንታ የሌላቸው ደግሞ፣ እንደ ‹ዕብድ ገላጋይ ዱላ ለማቀበል› እየፈጠኑ ነው፡፡ ምርጫንም ሆነ ኮሮናን በአግባቡ ፈር ስለማስያዝ ሳይሆን፣ ለፖለቲካ ፍጆታ የማዋል አባዜ በየፈፋው እያስተጋባ ነው፡፡ ማንን እንደሚጠቅም የማይታወቅ አጀንዳ በየጊዜው እየተፈበረከ ሕዝብ ግራ እንዲጋባ ይደረጋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ያሳስባል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ከታሪክ ተጠያቂነት ራሱን ማዳን የሚችለው፣ አገሩን ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ጎትቶ ሲያወጣ ብቻ ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ አገር አመራር ሰጪዎች ድረስ ድርጊታቸውን በፅሞና ካልመረመሩ፣ አገራቸውን መቼውንም ቢሆን መታደግ አይችሉም፡፡ ኢትዮጵያ ከሥልጣንም ሆነ ከጥቅም በላይ መሆኗን በተግባር ካላረጋገጡ፣ በስሟ መነገድም ሆነ በሕዝብ ላይ መቆመር ይቀጥላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ለበለፀገ ዘመን አይመጥንም፡፡ ይዋል ይደር እንጂ ከመሰሪዎች ሴራ በስተጀርባ ያለውን ጉድ የሚረዳ ትውልድ ሲመጣ፣ አሮጌ አስተሳሰብ ይወገዳል፡፡ ትውልዱን የማይመጥንና ዘመኑን የማይዋጅ አስተሳሰብ ፈላጊ የለውምና!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

  በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

  ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

  በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

  ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

  በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...

  ወጋገን ባንክ ከገጠመው ቀውስ በማገገም በ2014 የሒሳብ ዓመት የተሻለ ትርፍ አገኘ

  ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው ከተስተጓጎለባቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል ነው!

  በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው የሚጨፈጨፉበት ምክንያት ብዙዎችን ግራ ከማጋባት አልፎ፣ የአገርና የጠቅላላው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰበ ነው፡፡ መንግሥት...

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...