Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከጥሬ ገንዘብ ወጪ መጠን ገደብ በፊት መቅደም ያለባቸው ተግባራት

ከጥሬ ገንዘብ ወጪ መጠን ገደብ በፊት መቅደም ያለባቸው ተግባራት

ቀን:

በእስጢፋኖስ ስሜ 

የዓለም አገሮች በየፊናቸውና እንዳቅማቸው ልክ ሊቀንሱት፣ ከቻሉም ሊያጠፉት ከሚታገሉት ተግዳሮት አንዱ ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ነው፡፡ መጠኑና የሚያደርሰው ጉዳት ከአገር አገር ቢለያይም፣ በየትኛውም አገር ኢኮኖሚ ውስጥ ኢመደበኛ የሆነ የገንዘብ ዝውውር አለ፡፡

ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ብቻውን የሚኖር ፍጡር አይደለም፡፡ የሚወልዳቸው ክፉና አደገኛ ልጆች አሉት፡፡ ከሚወልዳቸውም ክፉ ልጆቹ በከፊል ሽብርተኝነት፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያና የሰዎች ዝውውር፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ እንዲሁም የግብር ሥወራ በከፊል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እነዚህ የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ልጆች በአገር ላይ የሚያደርሱት ክፋትና ችግር (በኢኮኖሚው፣ በአገር ሰላምና ደኅንነት፣ በሰዎች ደኅንነት) ከባድ ነው ብሎ መናገር ብቻ ክብደቱን አይገልጸውም፡፡ ከእያንዳንዱ የአገራችን ችግር ጀርባ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ አገራችንም በተለይ አሁን ከተጋረጠባት ችግር ጓዳ እንደ አቀጣጣይ ነዳጅ እያገለገለ ያለው አንዱ በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወር ገንዘብ ነው ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡

እንደ ማሳያ በተለያየ ጊዜ በአገራችን በሚደርሱ ሁከቶች ማግሥት መንግሥት መግለጫ ሲሰጥ፣ ሁከቶቹ በገንዘብ (በጥሬ ገንዘብ) ስፖንሰር የተደረጉ እንደነበሩ ሲገልጽ ይሰማል፡፡ ለመንደርደሪያ ይህን ያህል ካልኩኝ ወደ ዋናው ሐሳቤ እገባለሁ፡፡

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስና ለመግታት፣ እንዲሁም የጥሬ ገንዘብ ግብይትን ለመቀነስ ይረዳል ብሎ በማመኑ ከፋይናንስ ተቋማት በሚወጡ ጥሬ ገንዘብ ላይ በቀንና በወር በመመርያ ቁጥር FIS/03/2020 ገደብ አስቀምጧል፡፡

በጥሬ ገንዘብ ግብይት ላይ ገደብ መጣል ለአገራችን አዲስ ቢሆንም፣ በተቀረው ዓለም በአብዛኛው የቆየ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዘገየ ተብሎ ቢወቀስ እንጂ፣ ለምን ተብሎ ቢወቀስ ትርጉም ያለው አይሆንም፡፡ ነገር ግን መመርያው የታለመለትን ግብ እንዲመታ መሠራት፣ መስተካከልና መታረም የሚገባቸው ተግባራት ነበሩ ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁንም ብዙ የረፈደ አይመሰለኝም፡፡

የገንዘብ ዝውውር ከመደበኛው የኢኮኖሚ (ፋይናንስ) ምህዋር ተገፍተው፣ ወደ ኢመደበኛ በሆኑ መንገዶች ያለቅጥ እንዲዘዋወሩ ገፊ ምክንያቶች የሆኑ ነገሮች ቀድመው መታረም ነበረባቸው፡፡

ከነጋዴዎች አንፃር

ነጋዴዎችን ከመደበኛው የፋይናንስ ዝውውር ምህዋር አስጨንቆና ገፍቶ ሳይወዱ በግድ ገንዘባቸውን የገንዘብ ተቋማትን ሳይነኩ እንዲያንቀሳቅሱ ከሚያደርጋቸው አንደኛው የግብር አሰባሰብ ሥርዓታችን ነው፡፡ የግብር አሰባሰብ ሥርዓታችን በመተማመን ላይ የተመሠረተ ነው ለማለት አያስደፈርም፡፡ ይልቁንም የአሳዳጅና የተሳዳጅ ዓይነት ግንኙነት ይበዛበታል፡፡ ምክንያቱም ግብር ሰብሳቢው እስካሁን ድረስ ነጋዴውን ሊያሳምን የሚችል የግብር ሥርዓት መዘርጋት አልቻለም፡፡  እዚህ ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እንዴት ነጋዴውን ገፍቶ የገንዘብ እንቅስቃሴውን እንዲደብቅ እደሚያደርገው በሁለት ምሳሌዎች እንይ፡፡

ምሳሌ አንድ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ግዥ ሲፈጽም (ጥሬም ዕቃም ሆነ ያለቀለት)፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ካልሆነ ነጋዴ ጋር ግብይት ሊፈጽም የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነጋዴ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ስላልሆነ፡፡ ይህንን ችግር ገቢ ሰብሳቢው ተቋም ሳይፈታ ወይም እንደ ችግር ሳይቀበል ሲቀር፣ ነጋዴው መደበቁንም ይጀምራል፡፡ የበለጠ ለማብራራት ነገሩን በቁጥር ምሳሌ እንየው፡፡

አንድ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ የሆነ ነጋዴ ለንግድ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ካልሆነ የ1,000 ብር ግብይት ቢፈጽምና የገዛውን ዕቃ በ1,200 ብር  መልሶ ቢሸጠው፣ የሸጠውም ደረሰኝ ቆርጦ ቢሆን ከግብር አንፃር የሚያመጣበትን ችግር ይህን ይመስላል፡፡

የገዛበትን የሚያወራርድበት ደረሰኝ (መረጃ) ስለሌለው ገቢዎች ትርፍ የሚሉትና ነጋዴው ትርፍ የሚለው ይለያያል፡፡

በዚህ ምክንያት ነጋዴ ላይ የትርፍ ግብር ባላገኘው ትርፍ ላይ ሊጣልበት ስለሚሆን ያለ ደረሰኝ ሽያጩን ለማድረግ ይገደዳል፡፡ ይህ ተግባር ትክክል ባይሆንም፣ መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ፋይናንስ ተቋማትም የሚመጣውም የገንዘብ መጠን ደረሰኝ የተቆረጠላቸው ሽያጮች ብቻ ይሆናሉ፡፡ ደረሰኝ ያልተቆረጠላቸውን ሽያጮች ወደ ባንክ ከመምጣት ይልቅ፣ ነጋዴው ጋ የመቆየትና መልሰው ለተመሳሳይ (ለኢመደበኛ የገንዘብ ዝውውር) ተግባር ይውላሉ፡፡

ምሳሌ ሁለት የተቀሸበ ደረሰኝ (Under Invoice) አስመጪ ነጋዴዎች በበቂ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ስለማያገኙ፣ የሚያመጡት (ወደ አገር የሚያስገቡት) ዕቃ የደረሰኝ ዋጋ አብዛኛውን ጊዜ ከተገዛበት ዋጋ ያነሰ ይሆናል፡፡ ሁለቱም (የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የተቀሸበ ደረሰኝ) በግልጽ የሚታወቁ ሆኖ ሳለ፣ ገቢ ሰብሳቢው ተቋም ችግሮቹ እንደሌሉ ስለሚቆጥር ነጋዴው የገንዘብ ዝውውሩን መደበቁን፣ እንዲሁም ከገቢ ሰብሳቢ ተቋም መደበቁን ይቀጥላል፡፡ 

ከጥሬ ገንዘብ ወጪ መጠን ገደብ በፊት መቅደም ያለባቸው ተግባራትአንድ ዕቃ (ሸቀጥ) ከውጭ የተገዛበት (የመጣበት) የደረሰኝ ዋጋ ብር 10,000 ብር ነው ብንል፣ የተከፈለበት ትክክለኛ ዋጋ ደግሞ 11,500 ብር ብንል፣ ይህ ነጋዴ 1,000 ብር የትርፍ ህዳግ ጨምሮ ለመሸጥ ቢያስብ አጣብቂኙ እንዲህ ይሆናል፡፡

ከግዥው ደረሰኝ ላይ ተነስቶ ልሽጥ ቢል የሽያጩ ዋጋ (10,000+1000) +15% = 12,650 ብር ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በኪሳራ መሸጥ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ለዕቃው የከፈለው ትክክለኛ ዋጋ 11,500 ብር ሆኖ ሳለ ዕቃውን እየሸጠ ያለው ግን 11,000 ብር ስለሚሆን፡፡

ከገዛበት ዋጋ ላይ ተነስቶ ልሽጥ ቢል የሽያጩ ዋጋ (11,500+1‚000) +15% = 14,375 ብር ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ገቢዎችና ነጋዴው ትርፍ የሚሉት ትርፍ ልዩነት ይኖረዋል፡፡

ነጋዴው ትርፍ የሚለው (12,500-11,500) = 1,000 ብር ሲሆን፣ ገቢዎች ደግሞ (12,500-10,000) =2,500 ብር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ገቢዎች የዕቃው ትክክለኛ ዋጋ ብለው የሚወስዱት ሸቀጡ የገባበት የደረሰኝ ዋጋ (10,000 ብር) ሲሆን፣ ነጋዴው ግን የሸቀጡ ዋጋ (ወጪ) ብሎ የሚወስደው ለሸቀጡ የከፈለውን (11,500 ብር) ነው፡፡ በመሆኑም ነጋዴው ትርፍ በሚለውና ገቢዎች ትርፍ በሚሉት መካከል የብር 1,500 (2,500-1‚000) ልዩነት ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ነጋዴው ባላገኘው 1,500 ብር ትርፍ ላይ የገቢ ግብር ሊጣልበት ይሆናል፡፡

ታዲያ ይህ ጣጣ በገቢዎችና በነጋዴው ብቻ የሚያበቃ አይሆንም፡፡ በነጋዴው የባንክ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ነጋዴው በአቅሙ መጠን ሳይሆን ባንክ የሚያንቀሳቅሰው ለገቢዎች በሚሆን ልክ ይሆናል፡፡ ማለትም ወደ ባንክ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገባው ገንዘብ ደረሰኝ የተቆረጠላቸው ሽያጮች ብቻ ይሆናሉ፡፡ የተቀረው ትልቅ መጠን ያለው ደረሰኝ ያልተቆረጠለት ሽያጭ ወደ ኢመደበኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ በዚህ መንገድ ይገባል፡፡

ታዲያ ይህ ዓይነቱ የገቢዎች አሠራር በፈጠረው ፍርኃት የተነሳ ብዙ መጠን ያለው ገንዘብ ባንክን ሳይነካ በኢኮኖሚው ውስጥ ይንቀሳቀሳል፡፡ እንደሚታወቀው አንዴ ከመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት ውጪ የወጣ ገንዘብ መደበኛ ባልሆነው የፋይናንስ ፍሰት ውስጥ ገብቶ መዘዋወር ከጀመረ፣ ተመልሶ ወደ መደበኛው ሥርዓት መምጣት ይከብደዋል፡፡ በተቃራኒው መጠኑና ተዋናዮቹ እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ የዚህ ድግግሞሽ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከባንክ ይልቅ ያለ ባንክ በጥሬ ገንዝብ እንዲከወን አድርጓል፡፡ ይህም የባንኮችን የጥሬ ገንዘብ ክምችትና የተቀማጭ ገንዘብ ላይ ትልቅ ጫና እንዲፈጠር ማደረጉን ቀጥሏል፡፡

ደጅ ያሉ ገንዘቦች ወደ ማደሪያቸው ሳይመለሱ

በሁለተኛ ደረጃ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ ከፋይናንስ ተቋማት ዉጪ እንደሚዘዋወር እየታወቀ፣ ቀድሞ ይህን ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ ወደ መደበኛው ቋት ወይም ወደ ፋይናንስ ተቋማት የሚገቡበትን አስገዳጅ መንገድ ሳይፈጠር፣ ደጅ ባሉበት ሁኔታ የጥሬ ገንዘብ ወጪ ላይ ገደብ መጣሉ ፋይዳው እምብዛም ነው፡፡ ወይም እዚያው ደጅ እንዳለ ይመቻቹ የሚል ይሁንታ መስጠት ይሆናል፡፡

ስለዚህ ከመመርያው በፊት መከናወን የሚገባቸው ተግባራት፣ ማለትም ደጅ ያሉት ገንዘቦች ወደ ፋይናንስ ተቋማት ሳይገቡ፣ እንዲሁም በሕጋዊው ነጋዴና በግብር ሰብሳቢው ተቋም መካከል በግብር አሰባሰብና በባንክ ሒሳብ እንቅስቃሴ ላይ ያለው ያለ መተማመንና ያለ መግባባት ሳይቀረፍ ወይም መስመር ሳይዝ፣ ከባንክ የሚወጣ የጥሬ ገንዘብ ላይ ገድብ መጣሉ ውጤታማ አያደርግም ባይ ነኝ፡፡ እንዲያውም ከላይ ያሉት ችግሮች ቅድሚያ ሳይቀረፉ ይህ መመርያ መውጣቱ በተቃራኒው የፋይናንስ ተቋማት፣ በተለይም ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ውስጥ የበለጠ ሊከታቸው ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡

በመጨረሻም መመርያው እንደ መመርያ በጣም አስፈላጊና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት፣ እንዲሁም በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ የሚፈለፈሉትን ወንጀሎች ለመከላከል፣ የአገርን ሰላምና ደኅንነት ከማረጋገጥ አንፃር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የባንክ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው     [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...