እነሆ ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፡፡ ሸፍጠኝነት በገነነባት ምድር ላይ የምትንከላወሰው የምስኪኖች ሕይወት፣ ዛሬም ውክቢያ በበዛበት ጎዳና ላይ ትውተረተራለች። በማይሞላ ኑሮ አንድ ትጉህ ሰው አንድ እንጀራ ፍለጋ የሚያባክነው ጊዜ፣ ለሸፍጠኞች ደግሞ የዓመት ቀለብ መሰብሰቢያ ሊሆን እንደሚችል ሲታሰብ ያንገበግባል፡፡ የኑሮ ስንክሳር አላላውስ ያላቸው ምንዱባን በማያገባቸው ገብተው የሰው ጉዳይ ሲፈተፍቱ፣ እንኳንስ ሆዳቸውን ሊሞሉ የዕድሜያቸውን ገመድ የሚበጥስ ሴራ ሲሸረብባቸው አያውቁትም፡፡ ይህንን የተረዱ ምክር ቢጤ ሲለግሱ ይገለፍጡባቸዋል፡፡ ‹አዕምሮ አልሠራ ሲል ሰበብ ደርዳሪ› ይሆናል እንደሚባለው፣ ስንቶች የሸረኞች መጫወቻ ሆነው ሳያውቁት የክፋት መሣሪያ በመሆን ይህችን ምድር ሳያልፍላቸው ተሰናብተዋታል፡፡ ሴረኞች ግን በእነሱ ሕይወት ላይ ተንጠላጥለው ባልደከሙት በረከትና ፀጋ ይንፈላሰሳሉ፡፡ የቀለዱባቸውን ምስኪኖች ‹ታጋይ፣ ጀግና፣ ሰማዕት. . .› እያሉ ያሾፉባቸዋል፡፡ ለመታሰቢያ የሚሆናቸው ምልክት ግን የለም፡፡ በገሃድ የሚታዩት ምልክቶች ግን ወዛቸው የሚያብረቀርቅ አዳዲስ መሣፍንት ናቸው፡፡ የሴረኞቹ የልጅ ልጆች ማለት ነው፡፡ ዓለም እንዲህ ናት!
ይኸው ነው ወትሮም የመንገድ ወጉ። እልፍ ሲሉ እልፍ ሊታፈስ ወይም ያሰቡት ሳይሆን ሲቀር በማሱት ወድቆ ለመገኘት መቻኮል። የራስ ያሉት ሲከዳ፣ ልብ ብቻ ወዳጅ ሆኖ ሲቀር የማታ ማታ የሰው ልጅ ለቅሶና ሳቁ ሊደባለቅበት፣ ይህ ነው ወትሮም መንገዱን የሞሉት ምስኪኖች የማይጻፍና የማይተረክ ታሪክ። ፈዞ የደመቀ፣ በመታከትና በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መሀል የሚንገታገት ሀቅ። ‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል› እንዲሉ። ይኼኔ መቃብር ውስጥ የተኙቱት መናገር ቢችሉና ቢጠየቁ፣ ‹‹ቆመንም ያው ወድቀንም ያው› ማለታቸው አይቀርም። በሕይወት ያሉት ደግሞ፣ ‹አርሶም ቂጣ ነግዶም ቂጣ› ከማለት አይታቀቡም፡፡ ዓለም ከእነ ቃርሚያዋ በአደባባይ ተራቁታ ትዝብት ውስጥ ከታን የምንታይበት ጐዳና ይህንን ይመስላል። ይህ ሁሉ ጉድ ላያችን ላይ ቢያናጥርም፣ እነዚያ ተስፋና ጉጉት የሚሏቸው የስሜት መዘውሮች እስካሉ ድረስ ሕይወት ብትዳከምም፣ እየጨሰችም ቢሆን እስከ መጨረሻው ህቅታ ትራመዳለች። ከመቆም መራመድ፣ ከመሞት መቆየት ብዙ እያሳየው ምስኪኑ መንገዱን ይያያዘዋል። ሲያሻው ደግሞ ከማጉረምረሙ፣ ከምፀቱ፣ ከተረቡ፣ ከብሶቱ ጋር ያዋዛዋል። ሁሉም በሰዶ ማሳደድ ቀለበት ውስጥ በምኞቱ ገመድ ታስሮ፣ ትናንት ያቆመውን ዛሬ እያስታወሰው ማላጅ ማልዶ፣ አርፋጅ አረፋፍዶ ከጐዳናው ጋር በሥልትና በጥበብ ግቡን እስኪመታ ይወዛወዛል። ወዝወዝ እንዲሉ!
ወያላው ስድስት ተሳፋሪዎች ለማግኘት ላንቃው እስኪሰነጠቅ ቢጮህም ከሁለት ተሳፋሪዎች በላይ መጫን አልቻለም፡፡ ‹‹እዚህ አገር ረፈድ ካለ ሥራ ላይኖር ነው ማለት ነው…›› እያለ ያጉረመርማል፡፡ ጎረምሳው ሾፌር በተሰላቸ ድምፅ፣ ‹‹እንኳን ኮሮና ተጨምሮበት የታክሲ ሥራ ቀን ቀን አድርቅ አይደል እንዴ. . .›› እያለ ይመልስለታል፡፡ ሁለት ዘናጭ ወጣት ሴቶች ሲቀላቀሉ ወያላው ፊቱ በፈገግታ ተሞላ፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ አንድ አዛውንትና አንድ ለግላጋ ታዳጊ ሲቀላቀሉ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ወያላው ‹‹እንዴት አረፈዳችሁ መንገደኞቻችን ይህ የበረራ ቁጥር. . . ነው፡፡ ጉዞአችን የተቃና እንዲሆን እየተመኘሁ በማንኛውም አጀንዳ ላይ የመነጋገር መብታችሁ ያልተገደበ ስለሆነ፣ ካሁን በኋላ ያሻችሁን እንድታወሩ በካፒቴናችን ስም አበሥራችኋለሁ. . .›› ማለት ሲጀምር ለግላጋው ወጣት፣ ‹‹በአስቸኳይ አዋጁ መሠረት በሕግ የተገደቡ መብቶች ስለሚታወቁ፣ ማንኛውንም ጉዳይ አውሩ ስትል ‹ክላሽ› አያደርግም ወይ. . .›› ብሎ ያላሰብነውን ነገር ሲያመጣብን ዓይናችን ፈጠጠ፡፡ ጉዞው ሲጀመር አጀንዳ ተወረወረልን ማለት ነው!
‹‹እንዲያው ግን እዚህ አገር የእኛ ሰው ሟርት ብቻ ነው የሚያውቀው ልበል?›› ስትል አንደኛዋ ዘናጭ ዘንካታ አብራት ካለችው ቢጤዋ ጋር አንሾካሾከች። ‹‹ምነው ወጋችንን ሟርት አልሽውሳ? የሐሳብ መለዋወጫ መድረክና ፍላጎት እየጠፋ መሰለኝ፣ አዳሜ በፌስቡክ ከጦርነት ያልተናነሰ ትግል እየጀመረ አገር ካላተራመስኩ የሚለው. . .›› እያለ ወያላው ፈገግ አሰኛት። የምንሰማው ወሬ ዋና ፍሬ ነገሩ ሲበለት ተሳፋሪዎችን በሁለት ከፍሎ ያነጋግር ጀመር። ገሚሱ የሚወራውና የሚደረገው የጥቂቶች ፍላጎት እንጂ ብዙኃንን አይወክልም ሲያስብለው፣ ገሚሱ ደግሞ ጥቂቶች የሚፈነጩት በብዙኃኑ ቸልተኝነት ስለሆነ መብታችንን አሳልፈን መስጠት የለብን ያሰኘው ጀመር። አዛውንቱ የሁለቱ ጎራ ገላጋይ ለመሆን የፈለጉ በሚመስል ስሜት፣ ‹‹የሰው መብት መዳፈርና መብትን አሳልፎ መስጠት እኩል ስለሚያስጠይቁ፣ አንደኛውን ስንከላከል ሌላውን ደግሞ ያላግባብ እንዳናጠቃ እንጠንቀቅ. . .›› ሲሉ በዝምታ ውስጥ የነበረ ጎልማሳ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ አዛውንቱ ሁኔታው አላማራቸውም መሰል፣ ‹‹ምነው አጠፋሁ እንዴ?›› ሲሉት አንገቱን በቁጭት እየነቀነቀ ዝም አለ፡፡ ‹ሆድ ይፍጀው› መሆኑ ነው!
ጉዟችን ቀጥሏል። ጉርድ ሾላን አለፍ ከማለታችን አንድ ተሳፋሪ ድንገት ‹‹ወራጅ!›› ብሎ ያለመጠን ጮኸብን። ‹‹ኧረ ምን ነው? መውጣት እንጂ መውረድ ደግሞ እንዲህ ያስጮሃል እንዴ?” ሲል ወያላው በሩን እየከፈተ ታክሲውን አስቆመለት። የወያላው ንግግር በሌላ የትርጉም አንቅልባ ሲታዘል አፍታም አልፈጀ። ‹‹ሲወርዱ ነው እንጂ የሚያስጮኸው። ታክሲውም ሹመቱም ከወረዱ ወዲያ መቼ በቀላሉ ይገኝና?›› አለ ጎልማሳው ምፀት ደብለቅ አድርጐ። የወረደው እንደ ተሸኘ “ታክሲ!” ብላ አንዲት ሴት ተጣራች። ያለችው ሩቅ ነው። የለበሰችው ሚኒስከርት ነው። እሷ እስክትደርስብን ያለን ዕድል በትዕግሥት መጠበቅ ብቻ ነው። ‹‹አሁን በዚህ ቀትር እንዲህ አሳጥሮ መልበስ መጋኛንና ለካፊን አጣፋኝ ለማለት ካልሆነ ምን ያስፈልጋል?›› ሲል አንዱ ገና በቅርብ ያላያትን ቀዘባ ይተቻል። ‹‹መቼ እሱ ቸገረን ወንድሜ! ከሚለብሱት የሚተቹት፣ ከሚሠሩት የሚያብጠለጥሉት መብለጣቸው ነው እንጂ የሚገርመው። ትችት ብቻ! ከሚኒስከርት እስከ ዳዴ የሚለው ዴሞክራሲያችን የትችት ውሽንፍር ማርከፍከፍ አይሰለችም ግን?” ትላለች ወጣቷ። በዕድሜ ሦስት አራት ዓመት የሚቀድማት ወጣት በፊቷ ሞገስ ለማግኘት ይመስላል ያለችውን ደግፎ ያወራል። መደጋገፉ ከራስ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ከጋራ ዓላማ አንፃር ቢጨምር እንዴት አሪፍ ነበር!
አዛውንቱ የተጀመረው ወግ ከንክኗቸው ኖሮ፣ ‹‹ልጆች ምነው የጀመርነውን ወግ ሳንቋጭ በእንጥልጥል ተዋችሁት?›› ብለው ጥያቄ ሲያቀርቡ ጎልማሳው እየተንጠራራ፣ ‹‹አባታችን ትውልዱ መጀመር እንጂ መጨረስ አይሆንለትም፡፡ አንዱን ሳያበስል ወደ ጥሬው ይንደረደራል፡፡ አንድ ብሔራዊ ጉዳይ ተነስቶ በወጉ ሳይብላላ፣ ሌላ ማደናገሪያ በአቋራጭ ሲመጣ እንደ ግሪሳ ግር ብሎ ይነጉዳል፡፡ ስለምርጫና ስለመንግሥት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ጉባዔ ተዘርግቶ ምክረ ሐሳብ አዳምጥ ሲባል እከሌና እከሊት ተዳሩ፣ እነ እከሊት ሺሻ አቦነኑ፣ እከሊት የምትባል ጠንቋይ አይሏት ወፈፌ ውሎና አዳር ይወዘውዘዋል፡፡ አሉባልታ ወሬ ላይ ተጥዶ ውሎ ያድራል፡፡ አገሬ እያለ እየጮኸ ግለሰባዊ መናኛ ጉዳዮች ቀልቡን ይሰርቁታል፡፡ ኮሮና ገዳይ ወረርሽኝ ነው ተብሎ ሦስት ወራት ሙሉ ተጠንቀቅ እየተባለ ሲመከር ከርሞ፣ በራሱ መዘናጋት ቁጥሩ ሲያሻቅብ መንግሥት ላይ ያሳብባል፡፡ የኮሮናን ወረርሽኛና የግብፅን ሴራ ለመመከት ከመንግሥት ጋር አብሬ ቆሜያለሁ ባለ ማግሥት፣ የሴረኞች ሰለባ ሆኖ መንግሥት ለማፍረስ ይተባበራል፡፡ የአገር ጠንቅ የሚባሉትን እቃወማለሁ እያለ በተዘዋዋሪ የእነሱን አጀንዳ ለማስፈጸም ይሯሯጣል. . .›› እያለ በብስጭት ሲናገር ደም ሥሩ ተገታትሮ ነበር፡፡ ስንቶች ይሆኑ እንዲህ እያረሩ ዕድሜያቸውን የሚገፉት!
ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ስንሄድ አሁንም አንድ ተሳፋሪ “ወራጅ!” አለ። ታክሲው ወዲያው ቆመ። ‹‹መልካም ቀን!›› ብሎ ወያላው በሩን ከፈተለት። ታክሲያችን መንቀሳቀስ ሲጀምር አዛውንቱ፣ ‹‹አንተም እኮ የነገርከን የአንዱን ወገን ብሶት ነው. . .›› ሲሉት ጎልማሳው ገርመም እያደረጋቸው፣ ‹‹እዚህ ችግር ውስጥ ሁላችንም አለንበት፡፡ አሠላለፋችን የቱ ጋ እንዳለ የማወቅ ኃላፊነት የግላችን ብቻ ነው. . .›› ብሎ ሲመልስላቸው አጨበጨቡለት፡፡ ታዳጊው ልጅ ፊቱን ወደ ጎልማሳው መለስ አድርጎ፣ ‹‹ጋሼ እኔ በበኩሌ ያልከው ሁሉ ገብቶኛል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ችግር ላያችን ላይ ሲዘፈዘፍ ለምን ይሆን መገንዘብ ያቃተን?›› አለው፡፡ ጎልማሳው ታዳጊውን በፍቅር እያየው፣ ‹‹አየህ አንተ የበራልህ ነህ፡፡ ምክንያቱም ትጠይቃለህ፡፡ እዚህ አገር አንድ ወሬ ሲሰማ እሱን አንጠልጥሎ ይዞ ከመሮጥ ውጪ ለምን? እንዴት? መቼ? የት? ማን? የሚሉ እጅግ በጣም ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ አገሪቱ የሐሰተኛ ወሬ ፋብሪካ ሆናለች፡፡ መጠየቅን የመሰለ የዕውቀት ማዕድ እያለ ድንቁርና ይጫወትብናል፡፡ ተው ስንባል አንሰማ፣ አድርጉ ስንባል ስንፍና፣ ችግር ሲፈጠር ሰበብ አስባብ ማብዛታችን ይደንቃል፡፡ እኔ ታክቶኝ ዝም ማለት ከጀመርኩ ብቆይም፣ አላስችል እያለኝ መናገሬን አልተውም፡፡ እንዳንተ ያለ ልባም ሲገኝ ደግሞ በል በል ይለኛል…›› ሲል ሁላችንም ጆሮአችንን ቀስረን ሰማነው፣ አዛውንቱ ሳይቀሩ፡፡ ልካችን ሲነገረን ብንሰማ እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳ!
ወደ ሲኤምሲ እየተቃረብን ነው፡፡ የረፋድ ዜና ከወደ ሬዲዮው ይሰማል፡፡ የጤና ሚኒስትሯ በአዲስ አበባ ከተማ የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል እንደሚቻል ሲናገሩ የታክሲያችን ተሳፋሪዎች ደነገጡ፡፡ በተለይ ልደታና አዲስ ከተማ ክፍላተ ከተሞች የአዲስ አበባ የኮሮና ማዕከል መሆናቸው ሲነገር፣ ጥግ ላይ የተቀመጠ ጎረምሳ የአፍና የአፍንጫ ጭንብሉን ገለጥ አድርጎ፣ ‹‹የፈራነው ነገር መጣ ድሆ ድሆ… አያችሁ ይኼ መንግሥት ተኝቶ ከርሞ ሊያስፈጀን እኮ ነው…›› እያለ ሲወራጭ ወያላው ሁለት እጆቹን ራሱ ላይ አድርጎ፣ ‹‹ሾፌር አቁም! አንተም በሕግ አምላክ ጭንብልህን ቶሎ አጥልቅ! ካልሆነ 8335 ደውዬ ነው ወደ ኳራንቲን የምልክህ!›› ሲለው ታክሲያችን በአንዴ የጦር ቀጣና መሰለ፡፡ ያ ጎልማሳ በጎረምሳው ድርጊት እየተበሳጨ፣ ‹‹አየህ አቶ ሰበቡ! የራስህን ኃላፊነት መወጣት ስለማትችል፣ አፍና አፍንጫህን ገልበህ ጣትህን ሌላ ቦታ ትቀስራለህ፡፡ ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የጤና ሚኒስትሯ በተደጋጋሚ እባካችሁ አደራ አትዘናጉ ሲሉ እዚህ አገር አልነበርክም? አንተና ቢጤዎችህ አይደላችሁ እንዴ ቤተ እምነቶች ለምን ይዘጋሉ? ገበያ መሄድ ለምን እንከለከላለን ስትሉ የከረማችሁት? ጫትና ሺሻ ቤት ታጭቃችህ በጠራራ ፀሐይ የምትያዙት እኛ ወይስ እናንተ? መጠጥ ቤት በሌሊት አዘግታችሁ ስትሳከሩ የምታነጉ እናንተ አይደላችሁ እንዴ? ለመሆኑ ጭንብል ካላወልቅክ ድምፅህ አይሰማም ያለው ማን ሆኖ ነው ቁና ቁና እየተነፈስክብን የምታቅራራብን? አንተና ቢጤዎችህ የራሳችሁ ጥፋት አልበቃ ብሎ እኛንም ታነካኩናላችሁ፡፡ ምድረ ሰበበኛ አነካኪ ሁሉ. . . ሴረኞች እያኘኩ የሚተፉትን እያነሳችሁ እያላመጣችሁ ጭንቅላታችሁን ከምታበላሹ፣ እንደዚህ ታዳጊ ዕውቀት ለመቅሰም ትንሽ ጥረት ብታደርጉ ትጠቀሙ ነበር፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ማስተዋል ተጋርዶባችኋል፡፡ ለዚህም ነው አዕምሮአችሁን ማሰራት አቅቷችሁ ሰበብ ደርዳሪ ሆናችሁ የቀራችሁት. . . ምድረ ሰበበኛ. . .›› እያለ ጎልማሳው በንዴት ሲናገር፣ ጎረምሳው በድንጋጤ በድን የሆነ ይመስል ነበር፡፡ እኛም የጎልማሳው ብሶት ሲዘረገፍ ሳይታወቀን ሲኤምሲ ደርሰን ‹‹መጨረሻ!›› ስንባል ነው የነቃነው፡፡ እንዲህ በግልጽ ካልተነገረን አልገባን እያለ መቸገራችን እኮ የታወቀ ነው! መልካም ጉዞ!