➤ በአዋጁ ጊዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ሁሉም ጥፋቶች ተመሳሳይ ቅጣት መጣሉም ተገቢ አይደለም ብሏል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ማስፈጸሚያ ደንቡ የተወሰኑ ድንጋጌዎች ከሰብዓዊ መብቶች መርሆችና ከኢትዮጵያም ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር ሥጋት የሚፈጥሩ በመሆናቸው ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል ያላቸውን ድንጋጌዎች በመለየትና ምክንያታዊ ትንታኔ በማከል ለሕዝብ ይፋ አደረገ።
ኮሚሽኑ ሥጋት ናቸው ያላቸው ድንጋጌዎችን በመለየትና የሕግ ጥሰት ባህሪያቸውን በመተንተን እንዲሻሻሉ ሲል ምክረ ሐሳቡን ለመንግሥት አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ የሚንስትሮች ኮሚቴ ምክረ ሐሳቦቹን እንደማይቀበል በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በኩል ለኮሚሽኑ ሰሞኑን በጽሑፍ አሳውቋል።
ይህንንም ተከትሎ የመብት ጥሰት ሊያስከትሉ ይችላሉ ያላቸው ድንጋጌዎች ላይ ዝርዝር የሕግ ትንታኔና ምክረ ሐሳቦቹን ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽኑ የመብት ጥሰት ሊያስከትሉ ይችላሉ ብሎ ከለያቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና የማስፈጸሚያ ደንቡ ድንጋጌዎች መካከል የሚከተሉት ሥጋቶች በጥቅሉ ቀርበዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ከወንጀል ሕግ መርህ ውጪ በተለጠጠና ሰፋ ባለ መልኩ ሊተረጎሙ የሚችሉ የወንጀል ጥፋቶችንና ክልከላዎችን የያዘ መሆኑ፣ በዓይነትና ክብደታቸው ሰፊ ልዩነት ላላቸው የተለያዩ ጥፋቶችንና አነስተኛ የደንብ መተላለፎች ጭምር በአንድ ዓይነት እስከ 3 ዓመት የሚደርስ እስራት ወይም እስከ ብር 200,000 የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት መደንገጉ እንዲሁም፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በሚመለከት የግላዊነት ሕይወት መብትን፣ የኮቪድ-19 ታማሚዎችን ለግል ሚስጥርና ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሊጎዱና ለመድልዎ ሊዳርጉ የሚችሉ በአብዛኛው ቀጪና ወንጀል ተኮር የሆኑ አካሄዶችን የተከተለ መሆኑ በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አዋጁ ለወረርሽኙ የመከላከል ሥራ የግል ንብረት መውሰድን በሚመለከት ለመንግሥት የሰጠው ሥልጣን ሰፊ መሆኑ ለመብት ጥሰት የሚዳርግና ባለንብረቶች ላይ የተለጠጠ ግዴታን የሚጥል መሆኑ፣ በደንቡ ላይ ከተቀመጡት ድንጋጌዎች መካከል በመናገርና በሚድያ ነፃነት ላይ በጥብቅ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ከሆነው በላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ድንጋጌዎች መካተታቸው፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግና በሌሎችም ሕጎች የተመለከቱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በደምሳሳው መታገዳቸው ተገቢ ባለመሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኮሚሽኑ ጥያቄ ያቀረበባቸው ድንጋጌዎች ነበሩ።
በማስፈጸሚያ ደንቡ ድንጋጌ መሠረት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊታገዱ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ፣ የእስረኞችን ጉብኝት በሚመለከት ጠቅላላ ክልከላ መቀመጡ፣ የንግድ ነፃነት ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ጫና የሚጥሉ ድንጋጌዎች በደንቡ መካተታቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሶ ማሻሻያ ጠይቆባቸው ነበር፡፡