በአዳማ ከተማ በቀበሌ 05 የሚገኘው “ሞኤንኮ ገናናው” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ድልድይ ግንባታው ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወቃል። የድልድዩን ግንባታ በተቋራጭነት የወሰደው እድሪስ አህመድ ጄነራል ኮንትራክተር ሲሆን፣ አሠሪው ባለቤት የአዳማ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ነው። የግንባታው ወጪም 15,058,689.15 ብር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል።
የ25 ሜትር ርዝመት፣ የ10 ሜትር የውስጥ ለውስጥ ስፋትና የ12 ሜትር ቁመት ያለው ይህ ትልቅ ድልድይ፣ የግንባታው ሒደት ሲጓተት ሲራዘም ከርሞ ለፍጻሜ ሊበቃ በተቃረበበት ደረጃ ላይ ሳለ፣ ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ የድልድዩ አካል ዋነኛው ክፍል ቶፕ ስላብ (Top Slab) ተደርምሷል፡፡ባጋጠመውም መደርመስ በግለሰቦች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት አድርሷል፡፡
ለፈረሰው ድልድይ ተጠያቂው መሆን ያለበት ማን ነው? የተጠያቂነት ድርሻ ፅዋውንም ባለድርሻ አካላት በልክ በልካቸው ሊወስዱ ይገባል። ዕጣ ክፍሉ መውደቅ የሆነው የሞኤንኮ ድልድይ ትንሳዔው መቼ ይሆን? ፎቶዎቹ የድልድዩን ወቅታዊ ገጽታ በከፊል ያሳያሉ፡፡
(ስንሻው ተገኘ፣ ከአዳማ)