Saturday, June 10, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ምርጫን ‹‹የሞት ሽረት መታገያ›› ያደረገው ኃይል ምን እያለ ነው?

በንጉሥ ወዳጅነው

ምርጫ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝብን በመወከል ውሳኔ የሚያሳልፉ ወኪሎችን የመምረጥ ሒደትን የሚመለከት ሲሆን፣ የተሻሻለው የምርጫ ሕግ አዋጅ 532/1999 በአንቀጽ አንድ ንዑስ አንቀጽ አራት ላይ እንደ ደነገገው፣ “ምርጫ” ማለት በፌዴራልና በክልል ሕገ መንግሥታት እንዲሁም በሌሎች አግባብ ባላቸው ሕጎች መሠረት የሚካሄድ የጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የማሟያ ወይም የድጋሚ ምርጫን የሚያመለከት ነው፡፡

በአንድ ድርጅት ውስጥም ቢሆን በአብላጫ ድምፅ መሪ የሚመረጥበት ሥርዓትም ከዚህ ማዕቀፍ ውጭ እንዳልሆነ መታመን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ በሆነውም መድረክ የሚሠራበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ያለው የምርጫና የዴሞክራሲ ሥርዓት ጅማሮ ካለፉት ሥርዓቶች በተሻለ መልክ የታየው ከሁለት አሠርታትና ተኩል ወዲህ ቢሆንም፣ የምርጫ ታሪክ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንግሥና አንስቶ ‹‹እንደነገሩ የታየ አሠራር ነው›› የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡

2002 .. የወጣው ‹‹ምርጫ በኢትዮጵያ›› የተባለ መጽሔት እንደሚያስረዳው፣ 1923 .. በአፄ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና ዘመን በተካሄደው የመጀመርያው የፓርላማ ምርጫ ወደ ፓርላማው እንዲገቡ የተደረጉት ተወካዮች በራሳቸው በንጉሠ ነገሥቱ የተመረጡ ‹‹መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ፊታውራሪዎችና በወቅቱ በነበረው አሠራር ባላባት የሚባሉት ነበሩ፡፡››

ይህ እንግዲህ የሠለጠነው ዓለም ዴሞክራሲ ከሕዝብ፣ ለሕዝብ፣ በሕዝብ ከሚለው መርህ ጋር ሊታረቅ ይቅርና በዘመኑ በነበረው ተራማጅ ኃይሎች ጥቂት የከተማው ነዋሪም ዘንድ ቢሆን ይሁንታ ያገኘ ምርጫ ነበር ሊባል አይችልም፡፡ የሕዝቦችን የአመለካከት፣ የማንነትና የሃይማኖት ብዝኃነት ሊያስተናግድ ይቅርና በመደብ ደረጃም ከገዥው መደብ ውጭ ዕድል የማይሰጥ ነበር፡፡ ያ ሒደት ብዙ ጣጣና መገፋትን አስከትሎ የ1966 አብዮትን ማስከተሉም አይዘነጋም፡፡

ከንጉሠ ነገሥቱ ቀጥሎ የለውጥ ፈላጊ ምሁሩን ጥረት በማምከን ሥልጣን የጨበጠው፣ ወታደራዊው ደርግ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ የተጠቀመበት መንገድ ጉልበትና መሣሪያ ነበር፡፡ ይነስም ይብዛም የነበረውን ፊውዳላዊ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ከስር መሠረቱ በማፈራረስ፣ በጊዜያዊ የአዋጅ ጋጋታ ፍጹማዊ በሆነ መንገድ የሕዝቡን መብትና የሥልጣን ባለቤትነት የጨፈለቀበት ሁኔታም ነበር፡፡

ወታደራዊው ደርግ የሚመራው መንግሥት የለየለት አፋኝ በመሆኑ ከእነ ጉድለቶቹም ቢሆን በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ታይቶ የነበረውን የዴሞክራሲና የመቻቻል ጭላንጭል ጨርሶ ዘግቶታል፡፡ በዚህም ምክንያት “የዴሞክራሲ ምሰሶ” ለሆኑት ሐሳብን በነፃ የመግለጽና የመሰብሰብ መብቶች ምንም ቦታ የሚሰጥ ሥርዓት አልተፈጠረም ነበር፡፡

እንዲያውም ደርግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈልገውን የተማረ ኃይል በመግደልና በማሰር የፖለቲካ ዋልጌ ድርጊት ላይ በመጠመዱ ጫካ ገብቶ የታገለውና ከአገር የተሰደደው የበዛ ሆነ፡፡ አገሪቱ ለገባችበት የ17 ዓመታት ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት አንዱ መንስዔም ይኼው አምባገነናዊነት ነበር ሊባል ይችላል፡፡ የመምረጥና የመመረጥ መብትም በዜግነት ማግኘት የማይታሰብ  ከመሆኑም በላይ በደርጉና ወደ ኋላ በተመሠረተው የራሱ መንትያ ፓርቲ ውስጥ በአባልነት የተመለመሉ አባላት እንኳን፣ የሕዝብና የህሊና ተጠያቂነትን ዘንግተው ሥርዓቱ ለፈጸማቸው ወንጀሎች ሁሉ ተባባሪ ሆነው የቆዩ ናቸው፡፡ ስለሆነም የምርጫ ተቋምም ሆነ የሰብዓዊ መብት አካላት ሕይወት ባለው መንገድ ሳይኖሩ በስምም ሳይተዋወቁ ቆዩ፡፡ 

ያ ፀረ ዴሞክራሲያዊና ወታደራዊ ሥርዓትም ምንም ያህል መልኩን ለመቀያየር ቢሞክርም በኢትዮጵያ ታሪክ ዳግም እንዳይመለስ የሚያስፈራ ድርጊት መፈጸሙ በታሪክ ድርሳናት ተጽፎ የሚገኝ ነው፡፡ በወቅቱ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በኃይል ከመደፍጠጡም በላይ እንደ ሥጋት የሚያያቸውን አያሌ የመብት ተሟጋቾች፣ ወጣቶችና የመንግሥት ሠራተኞችን በግፍ እየገደለ፣ ቶርች እያደረገና እያሳደደ እስካአሁንም ድረስ ፖለቲካና ኮረንቲን አንድ አድርጎ የሚሳቀቅ ዜጋ ምድሩን እንዲሞላው የገፋ መጥፎ ዘመን የታለፈበት ነበር፡፡

ደርግ በሕዝባዊ ትግል ከተወገደ  ከ1983 ዓ.ም. በኋላ የጀመረው ሕዝባዊና ዴሞክራሲዊ ሊባል የሚችል አዲስ ዕድል ነበር፡፡ በተለይ የሽግግር መንግሥቱ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ለመወከልና ከፓርላማ  ወኪልነት አስከ ቀበሌ አመራርነት ለማሳተፍ የሚያስችል አዲስ የምርጫ አሠራር ይዞ ብቅ ማለቱ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ያም ሆኖ ተረስተው ለነበሩ አናሳ ማንነቶች የሰጠውን ትኩረት ያህል፣ አማራን ለመሰሉት ሰፊ ሕዝቦችና ኢትዮጵያዊ ኅብረ ብሔራዊነት ለሰነቁ ኃይሎች ቦታ ነፋጊ ሆኖ ነበር ጊዜውን ያጠናቀቀው፡፡

በዚሁ መዘዝ ሕገ መንግሥቱ ተረቅቆ ሥራ ላይ ከዋለበት ያለፉት 25 ዓመታት ወዲህ በርካታ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ከሰነዱ አንስቶ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረበት ነው ሊባል አይችልም፡፡ ዜጎች በነፃነት ተደራጅተው ለሥልጣን በሚበቁበት ለመድበለ ሥርዓት የሚረዳ የፖለቲካ  ተሳትፎ እያደረጉ ነው ብሎ በድፍረት ለመናገር ባይቻልም፣ ሌላው ዓለም እየሄደበት ባለው ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ የምርጫ ሥርዓት ወቅታቸውን የጠበቁ ምርጫዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ማንሳት ግን በበጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በዚህም መሠረት ዕድሜው 18 ዓመት የሞላውና በአካባቢው ሁለት ዓመት የኖረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በምርጫ እንዲሳተፍ የሚያስችል አዋጅ 11/1984 በመውጣቱ (ከዚህም ወዲህ እየተሻሻለ በመሄዱ) ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነቂስ መመዝገብና በምርጫ መሳተፍ እየቻለ ይገኛል፡፡ ባሳለፍናቸው ወራት እስከ ተሻሻለው የምርጫ ሕግ ድረስ የፓርቲዎች ምዝገባ፣ ሕጋዊ ዕውቅና፣ የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብቶች በሕግ ዕውቅና እንዲያገኙ የተደረገው ሙከራም በበጎ ሊነሳ ይችላል፡፡

ይህ ጅምር በመኖሩ ነው በየደረጃው ቢያንስ ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው የተለያየበት ሥርዓት ለመዘርጋት የተሞካከረው፡፡ ብሎም ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ዜጎች በውክልና የሥልጣን ባለቤትነት መርህ የመረጧቸው ምክር ቤቶችና የአስተዳደር አካላት ከነጉድለታቸው ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙት፡፡

የሩብ ክፍለ ዘመኑ ዋነኛው የዚህ አገር የምርጫ ፈተና ግን የተጻፈ ሕግና ሥርዓት በአምባገነንነት እየተለወጠ፣ የምርጫ ኮረጆ እየተሰረቀና ምርጫ እየተጭበረበረ የሕዝቡ ፍላጎትና የምርጫ ውጤቶች ‹‹ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ›› እየሆኑ በማስቸገራቸው ነው፡፡ የምርጫ ቦርድን የመሰሉ ወሳኝ የዴሞክራሲ ኤጄንቶችም ለከፋ የገለልተኝነት ሥጋት የተጋለጡ በመሆናቸው ነው፡፡

ይህ በአብዛኛው በመንግሥት በኩል የሚታየው አስቸጋሪ አካሄድ ከመሻሻል ይልቅ በመባባሱ ደግሞ 2010 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በአገሪቱ የተካሄደው ቢያንስ ጥገናዊ ለውጥን አስከትሏል፡፡ አገሪቱ በብዝኃነት የተሞላችና በርካታ አመለካከቶች የሚስተናገዱባት ሆና ስታበቃ፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ግራ ዘመምና መንቻካ በሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ታጥሮ የፈጠረው ችግር አዲስ ለውጥ እንዲቀነቀን ምክንያት ሆኗል፡፡

በእርግጥም አሁንም ድረስ አንድ ዕርምጃ የተራመደና በአገራዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ትግል ላለመዳበሩ ያ አስቸጋሪ ጊዜ አሉታዊ ድርሻ ነበረው፡፡ የሕዝብ ሚዲያዎች ትናንትም ሆነ ዛሬ በገዥው ፓርቲ ተሿሚዎች የሚመሩና አድርባይ ናቸው፡፡ ምርጫ ቦርድ ላይ መሻሻል ቢታይም እስከ ታች ያለው መዋቅር በተለመደው መንገድ የሚሽመደመድ ነው፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታው አጋዥ የሆኑ የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ የተጠናከረ ሰላማዊ ትግል የማድረግ ትግሎቹ አለመጎልበታቸውም እንደ አብነት ይጠቀሳሉ፡፡

ይህን ችግር ለማቃለል በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ የነበሩ የለውጥ ኃይሎች ተሰባስበው ከዘውግ ፖለቲካ ወጥተው አንድ አገራዊ “ብልፅግና“ የተሰኘ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ለመመሥረት ሞክረዋል፡፡ ሌሎች በርካታ በውስጥና በውጭ የነበሩ ፓርቲዎች (ብዛታቸው ከ100 በላይ ነው) በነፃነትና በሕጋዊነት በአገር ቤት ተንቀሳቅሰው፣ የምርጫ ሕጉም ላይ ሌሎች የዴሞክራሲ ምኅዳርን ለማስፋት የሚረዱ ድንጋጌዎችን በጋራ ተችተው ወደሥራ እንዲገቡም አዲሱ መንግሥት በጎ ጅምሮችን ማድረጉ አይካድም፡፡ ቀሪ ሥራዎችም ይኖርበታል፡፡

ይሁንና አብዛኛው በአገሪቱ የሚንቅሳቀሱ ፓርቲዎች በብሔርና ማንነት ላይ ያተኮሩ፣ ሰብሰብ ብለው አገራዊ አማራጮችን በመቅረፅ ረገድም ያልተዋጣላቸው ሆነው መታየታቸው እንደቀጠለ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚፈለገውን ያህል አማራጭ ሐሳቦችና የአመለካከት ብዝኃነቶችም እየተስተናገዱ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደ አገር በሚፈጠርበት ጊዜ እንኳን (የአሁኑ ኮሮናን ልብ ይሏል) ብሔራዊ መግባባትን ፈጥሮ ሕዝብና መንግሥትን ማስቀደም እየተቻለ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ አገሪቱን ባለፉት 28 ዓመታት ገደማ በመምራቱ ሒደት ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ አምባገነኑን የደርግ ሥርዓት በማፈራረስ ረገድም ቢሆን ግንባር ቀደም የነበረው ሕወሓት ሰሞኑን የያዘው አቋም እንደ አብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህ የኢሕአዴግ አስኳል የነበረ ኃይል በዚች አገር ውስጥ ለተጀማመሩ ተግባራት መመስገኑ እንዳለ ሆኖ፣ በዘረፋና ሙስና መበርታት፣ በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ጥርስ ማውጣት፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት መበራከትና በአገር ሉአላዊነት ላይ በታዩ ክፍተቶች ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እኩል አለፍ ሲልም በላይ ተወቃሽ ነው፡፡ በተሃድሶው ‹‹የሕወሓት የበላይነት ነበር›› የሚለው የጋራ ማጠቃለያ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡

(እዚህ ድምዳሜ ላይ የሚያደርሰው ደግሞ ብሔራዊ ድርጅቱ በደኅንነትና ፀጥታ፣ መከላከያ፣ ዋና ዋና የመንግሥት ሥልጣኖች፣ በትልልቅ ኢንቨስትመንትና የባንክ ብድር. . . ዋነኛ መመልመያ አባልነት ብቻ ሳይሆን የብሔሩ ተወላጅነትን በማስመሰል በአገር ሀብት ላይ እንደፈለገ ሲያዝ መቆየቱ በይፋ አጋልጦታል፡፡ አሁንም ይህን ብልሹ መንገድ የሚከተል ባለተራ ካለ ዕጣ ፈንታው ያው መሆኑ ግን  አይቀርም!!)

በእርግጥ  የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)  ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ‹‹አገሪቱ በፌዴራላዊ ሥርዓት ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ሕዝቦች ምድር ሆናለች፤›› ቢባልም እውነታው ሌላ  የነበረ መሆኑም ሊዘነጋ የማይችል ነው፡፡ ዛሬ መካድ እንደማይቻለው በእያንዳንዱ ታዳጊ ክልል ውስጥ በመቶ ሺዎች ሔክታር የእርሻ መሬት ለይስሙላ እየወሰደ፣ ግዙፍ የግንባታ ኮንትራት እየጨመደደ፣ አንዳንዱም ሳያለማ ብድር ከሕዝብ ባንክ  ያጋበሰው ሥርዓቱንና ማንነቱን ተገን እያደረገ ነበር፡፡ የማዕድን፣ የሜጋ ፕሮጀክት፣  ወሳኝ  የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ሀብት ላይ  ያሻውን  የሚያሾረውም በዚሁ የበላይነት ሥሌት ነበር፡፡ የባከነ ሰፊ የአገር ሀብትም ውሾን ያነሳ ውሾ” ሆኖ መቅረቱም የሚያንገበግብ ነው፡፡

ዛሬም ወቀሳውን የሚያበረታበት ግን በአንድ በኩል በሁለተኛው ተሃድሶ እንደሌሎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቆ ካለፈ በኋላ፣ አንዴ ሳይሆን ሁለት ጊዜ በዚያው በግንባሩ ውስጥ የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር በሊቀመንበርነት መርጦ ሲያበቃ ማፈግፈግ በመጀመሩ ነው፡፡ ስህተት ቢኖር እንኳን በትግል መሻገር ሲቻል፣ አንድ ጊዜ በብሔር ፓርቲነት ለመቀጠል፣ በሌላ ጊዜ አብዮታዊነትን አለቅም በማለት መንቻካ አቋም አገሪቱን መልሶ የከረመው አዘቅት ውስጥ ለመክተት ሲንጠራወዝ መታየቱ ነው፡፡

በዚያ ላይ በተጀመረው ለውጥ ባለመደሰቱና ‹‹እኔ ያልመራኋት አገር ብትበተንም ትበተን›› በሚል ስሜት የተለያዩ ፕሮፓጋንዳዎችን መንዛቱ ብዙዎችን እያስገረመ ነው፡፡ በትግራይ ትገንጠል አትገንጠል/በተለያዩ ክልሎች መካከል በሚታዩ የገባ ወጣ ቀውሶች/በታላቁ የህዳሴ ግድብና መሰል ጉዳዮች ላይ በአንቂዎቹና የክልል ሚዲያዎቹ የሚያራምደው ቅስቀሳ በአንድ አገር ከሚኖር ኃይል ፈፅሞ የሚጠበቅ አልሆነም የሚሉ ተችዎች ብዙ ናቸው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ደሃዋ አገራችን ብቻ ሳትሆን፣ ዓለም በኮቪድ 19 እየታመሰ ባለበት ሁኔታ በማንም አገር ያልታየ ‹‹ምርጫው በወቅቱ መካሄድ አለበት!›› የሚል ሕጋዊ የሚመስል ግን፣ ከሞራልና ከሕዝብ ጥቅም ጋር የተጣላ ጥያቄ አንስቷል፡፡ ከዚያም አልፎ በማስፈራሪያ በማስደገፍ የፌዴራሉ መንግሥት ምርጫውን በተያዘው ጊዜ ካላካሄደ የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ ያካሂዳል ብሎ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

ይህ አዝማሚያ ግን ‹‹እልህ ምላጭ ያስውጣል›› እንዲሉ፣ ለትርምስ የሚያንደረድር እንጂ ምርጫ ቦርድ ባልመራውና ባልተሳተፈበት መንገድ ፈፅሞ ዕውን ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ሌላው የሕወሓት ሰዎች ያልተረዱት/አውቀው የተኙበት እውነት አገሪቱም ሆነች ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆነው፣ ሕዝቡም በወረርሽኝ ሥጋት ላይ ወድቆ ምን ዓይነት የተሟላ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል የሚለውን ተጠየቅ ነው፡፡

በመሠረቱ አሁን ባለው የአገራችን ፖለቲካ የምርጫው በጊዜው መካሄድ ሳይሆን ወሳኙ ጉዳይ፣ ምርጫው በበቂ ዝግጅት ነፃ፣ ሕጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ሆኖ መካሄዱ ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የአሁኑ ሥነ ምኅዳር ውስጥ እየተንገዳገደም ቢሆን፣ ዴሞክራሲ እያደገ የመሄድ ዕድል እንዲኖረው ማድረግ ካልተቻለ ዕጣ ፈንታችን ተያይዞ መውደቅ መሆኑ አይቀርም፡፡ ግጭትና ትርምሱም ማቆሚያ ሊኖረው አይችልም፡፡

አሁንም እንደሚታየው ግን የአንዳንድ ፓርቲዎች አካሄድ ከብሔራዊ መግባባት ያፈነገጠ፣ ከሕጋዊ ውይይትና ድርድር ይልቅ ወደ ነውጥና የሁከት ተፅዕኖ ያደላ የትግል ሥልት ፖለቲካውን ፍጥጫ ውስጥ እየከተተው ነው፡፡ ሕወሓትም የ45 ዓመት የፖለቲካና የጦርነት ልምድን እንደ መከታ በማድረግ  በትግራይ ሕዝብ ስም ሌላው ሕዝብ ላይ ጫና ለመፍጠር ማሰቡ የሚመነጨው ከዚሁ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ በራሱ በትግራይ ሕዝብ መወገዝ ያለበት አስተሳሰብ ነው፡፡

ብዙዎች እንደሚሉት ከሁሉ የከፋው የሕወሓትና ደጋፊዎቹ (ፌዴራሊስቶች!?) ሸፍጥና ጥፋት ከሕዝቦች አንድነትና ኅብረት ይልቅ፣ መለያየትና መቃቃር ውስጥ እንዲገቡ ያደረገ የብሔር ፖለቲካን አሁንም እንደነከሱ ለመቀጠል መፈለጋቸው ላይ ነው፡፡ ይኼ እሳቤ ደግሞ በኢሕአዴግ ተሃድሶ ጊዜ ‹‹አላዋጣንም፣ ሊያባላን ነው እናስተካክለው›› ተብሎ የጋራ አመለካከት የተያዘበት ሲሆን፣ ዛሬ እንዴት ተመለሰ? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ነው፡፡

በሌላ በኩል ሕዝቡን በማይታረቁ የእርስ በርስ ንትርኮችና የታሪክ ውዝግብ  ሥር ጠምዶ፣ የአንድ ወገን የበላይነትን ያለተቀናቃኝ ለማረጋገጥ የተቀየደን ፕሮጀክት ለመጣል አለመፈለጉ ነው፡፡ ዛሬም ሕወሓት የወዳጅ/ጠላት፣ የትምክህት/ጠባብነት ትርክት፣ የጥገኛና ልማታዊ ባለሀብት ፍረጃ ያልቀየራቸው ስንቆቹ ናቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መቀነት እንደመሆኑ፣ ለዴሞክራሲና የብዙኃኑ ተጠቃሚነት እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ሕወሓት የያዘው ‹‹ምርጫ ወይም ሞት!!›› አስተሳሰብ ከጀርባው ያዘለው ሴራ የተደበቀ ሊሆን አልቻለም፡፡ ያው በሰበሰበ ተብሎ የተጣለው አስተሳሰቡ ላይ እንደተንጠለጠለ ነውና!!

እስካሁን እንደታየው በአገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት መገንባቱ “እሰይ” ቢያስብልም ክልልም ሆነ የአስተዳሰር ከባቢው በአብዛኛው በጎሳና በማንነት ላይ መደራጀቱን ከሕወሓት/ኢሕአዴግና የኦሮሞ ብሔርተኞች በስተቀር ማንም ይሁንታ የሰጠው አልነበረም፡፡ ምክርና ተግሳፅን መስማት እጅግም የማይወደው አገረ መንግሥቱ ግን ነገሩን ሰምቶ እንዳልሰማ በተለያዩ ማሳሳቻዎች እየመከተ ገፍቶ በመሄዱ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ የተዋለደና የተዋሃደ ሕዝብ በጥርጣሬ የሚተያይና እርስ በርሱ የሚናቆር ከመሆን አልፎ ምን ያህል ለግጭት እንደተጋለጠ ባለፉት ሦስት ዓመታት ጉድ ዓይተናል፡፡

አሁን ያለው የአገሪቱ አመራር ነገሩን በጊዜ መግዣና በብልኃት መንገድ ስለያዘው እንጂ በወሰንና በማንነት ጥያቄ ተፋጥጦ የቆየው ሕዝብም ያልተፈታ የቤት ሥራ ተሰጥቶት እስካሁንም መቀጠሉን ከሕወሓት በላይ የሚረዳው አይኖርም፡፡ ታዲያ እንዴት ወደ ኋላ መመለስ ያዋጣል? በምርጫ ይካሄድ/አይካሄድ ኢሞራላዊ ክርክር ጉልበት ለመፈታተሸ መጋበዝስ ማን ሊጠቅም ይችላል? ቆም ብሎ ማሰብ ግድ የሚል ጭብጥ ነው፡፡

አሁንም  እንኳንስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከቀን ወደ ቀን ሕዝብን እያራደ ይቅርና በታላቁ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ማሳደር የሚፈልጉት ጫናም እንድንለያይ ሳይሆን፣ በአንድ እንድንቆም የሚያስገድዱ ናቸው፡፡ በተለይ እንደ ሕወሓት ላለ በመስዋዕትነት ፌዴራላዊ ሥርዓቱንና ሕገ መንግሥቱን አንብሪያለሁ ለሚል ኃይል ይቅርና ለማንም ቢሆን፣ የአገርና የሕዝብ ጥቅም ለድርድር ሊቀርብ አይገባምና፡፡ ይህን ማመዛዘንና ከታሪክ ተወቃሽነት ለመውጣትስ ለምን አልተፈለገም?

አሁን በመቐለ የመሸገውና በለውጡ የተንገሸገሸው ኃይል አንድ ጊዜ “ፌዴራሊስት ኃይሎች” ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ አገርን ከጨፍላቂዎችና ከብተና ለመመከት እንደተደራጀ ሆኖ “የአዞ ዕንባ” የሚያለቅሰው በቅጥረኞች አደናግሮ፣ ያንን የግፍ ዘመን ለመመለስ ነው ወይስ ሚስጥሩ ምን ይሆን!? የሚሉ ወገኖች በርክተው  መታየታቸው አመክንዮአዊ የሚሆነውም ለዚሁ ነው፡፡

ለማጠቃለል እኛ ኢትዮጵውያን የሚበጀን ከወዲሁ ክፉና ደጉን መዝኖ በመለየት መወሰን ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ያለው ገዥ ፓርቲ  ኖረም ቀረም በወከባና በማጭበርበር መሪህን መርጠሃል”  የሚባል የፖለቲካ ቁማር እንደማንቀበል ነቅቶ መገኘትም ነው፡፡ የምንገኝበት ጊዜ ኮሮናን የመሰለ አደገኛ ወረርሽኝ የተዛመተበት ነው፡፡ ግብፅን የመሰሉ አንዳንድ በአገራችን ጉዳይ ላይ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎችም አልተኙልንም፡፡ ስለሆነም መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ያዋጣል የሚሉትና ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን መንገድ ተከትለው በውይይት ምርጫውን አራዝመው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያካሂዱት መተባበር ብቻ ነው፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ በግራም ሆነ በቀኝ ፣ “በእናውቅልሃለን” ሥሌት ዳግም ለመለያየት፣ ለምዝበራና አፈና የሚያስቡንም ሆነ በሁከትና ትርምስ የሕዝብን ሰላም ለማወክ የሚሹትን ማውገዝም ተገቢ ነው፡፡ ለአገር ሰላምና ደኅንነት ሲባልም ከመንግሥት ጎን ቆሞ ነቅቶ መጠበቅም ግድ ይለናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles