Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዋጋ ግሽበት ያስከትላል የሚል ሥጋት የቀረበበት 48 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ፀደቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዋጋ ግሽበት ያስከትላል የሚል ሥጋት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረበበት የ48 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጥያቄ፣ በስተመጨረሻ በሙሉ ድምፅ ፀደቀ።

የኮሮና ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ለመቋቋም እንዲያስችል ከሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው የ48 ቢሊዮን ብር የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ፣ ዓርብ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ቀርቦ ሰፊ ክርክር ተደርጎበታል፡፡

ምክር ቤቱ በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም. ለ2012 የበጀት ዓመት ያፀደቀው አጠቃላይ በጀት 386.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ በጀት ለድህነት ተኮር ፕሮጀክቶች እንደሚውልና በዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱን ወደ ዘጠኝ በመቶ ለማውረድ ታሳቢ ተደርጎ የፀደቀ ነበር።

 መንግሥት በገጠመው የካፒታል ፕሮጀክቶች ወጪ መሸፈኛ፣ በተለይም የኢኮኖሚ ሪፎሩሙን ለማሳለጥ በሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም. ተጨማሪ 28 ቢሊዮን ብር በጀት ጥያቄ አቅርቦ ለምክር ቤቱ ቀርቦ መፅደቁ ይታወሳል፡፡

 የ2012 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ ከ40 ቀናት በታች ጊዜ በቀሩበት ባለፈው ሳምንት ደግሞ፣ ተጨማሪ 48 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሁለተኛ ጊዜ ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

የዚህን ተጨማሪ በጀት አስፈላጊነት አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ  መስፍን ቸርነት (አምባሳደር)፣ በጀቱ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከልና የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ለመቋቋም እንደሆነ ገልጸዋል።

ከቀረበው ተጨማሪ በጀት ውስጥ ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ምግብና ተያያዥ ድጋፍ ለሚፈልጉ 15 ሚሊዮን ወገኖች እንደሚውል የተገለጸ ሲሆን፣ ቀሪው  ደግሞ በሽታውን ለመቆጣጠር ለጤና ቁሳቁሶች ግዥ የሚውል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ተጨማሪ በጀቱን ለማፀደቅ በምክር ቤቱ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ የተጨማሪ በጀቱ የገቢ ምንጮችን አስረድተዋል። ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያም የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች ለሚፈለገው 48 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት የገቢ ምንጮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም መሠረት 28 ቢሊዮን ብር ከውጭ አገሮች በብድር የሚገኝ እንደሆነ፣ የተቀረው 20 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከአገር ውስጥ ብድር የሚሸፈን መሆኑን አስረድተዋል። በርከት ያሉ የምክር ቤቱ አባላት የተጠየቀው ተጨማሪ በጀት የገቢ ምንጮች ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥና በውጭ ብድሮች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየውን ከ20 በመቶ በላይ የሆነ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ደረጃ ያባብሳል የሚል ሥጋታቸውን በማቅረብ ተከራክረዋል።

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ተጨማሪ በጀቱ ጥቅም ላይ ሲውል፣ ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በወረርሽኙ ምክንያት የንግድ ድርጅቶች የተፈጠረባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጫና መቋቋም እንዲችሉ መንግሥት 60 ቢሊዮን ብር የሚገመት ግብር ማንሳቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ይህ ዕርምጃም የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹ተጨማሪ በጀት ያስፈለገው ወጪያችን በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ገቢያችን በመቀነሱ ነው፤›› ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ከፍተኛ ወጪዎች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከተጨማሪ በጀቱ ውስጥ የጤና ሚኒስቴር በየጊዜው የሚወስደው 15 ቢሊዮን ብር እንደሚመደብ ገልጸዋል። በርካታ ያልታሰቡ ወጪዎች በማጋጠማቸው ወደ ተጨማሪ በጀት መገባቱ ግዴታ እንደሆነ ያስረዱ ሲሆን፣ ለዓብነትም የምግብ ዕርዳታ አቅርቦት የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ከታሰበው በከፍተኛ ደረጃ መጨመራቸውን አስረድተዋል።

ተጨማሪ በጀቱ በዘንድሮ በጀት ማጠናቀቂያ ወቅት ቢቀርብም ለቀጣዩ የበጀት ዓመት የሚያገለግል እንደሆነ፣ ይህም ለ2013 በጀት ዓመት በሚቀርበው የበጀት አዋጅ ላይ ተካቶ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

ተጨማሪ በጀቱ የዋጋ ግሽበት ያስከትላል የሚል ሥጋት በፓርላማው በሰፊው ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፣ የተሰጡት ምላሾች ከተደመጡ በኋላ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች