የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን እንዲከታተልና በምርጫ ወቅት ምርጫ መታዘብ እንዲችል የሚፈቅድ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓርብ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል።
በረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ከተካተቱ የማሻሻያ ድንጋጌዎች መካከል፣ ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ጊዜ ወቅትና በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን እንዲከታተልና ምርጫ እንዲታዘብ የሚፈቅዱ ድንጋጌዎች ይገኙበታል።
የረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ መግቢያ ነባሩን የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻል ያስፈለገበትን ምክንያት ያስገነዝባል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተቋቋመበትን የሰብዓዊ መብቶችን ግንዛቤ የማስፋፋት፣ የማስጠበቅና የማስከበር ሥራ በተገቢው መንገድ እንዲያከናውን ማስቻልና የማስፈጸም አቅሙን ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ረቂቁ መዘጋጀቱን በመግቢያው ላይ የሰፈረው ሐተታ ያስረዳል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኮሚሽነሮች አመራረጥና አሿሿም አሳታፊና ግልጽ ማድረግና የኮሚሽኑን የመዋቅር፣ የሠራተኛ ቅጥርና አስተዳደር፣ እንዲሁም የበጀት ነፃነት ማረጋገጥን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ማሻሻልና የተቋሙን ተዓማኒነት፣ ተቀባይነትና ውጤታማነት ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑንም መግቢያው ያስገነዝባል። ከቀረቡት ረቂቅ የማሻሻያ ድንጋጌዎች መካከልም በሥራ ላይ በሚገኘው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ ስድስት ሥር፣ ተጨማሪ ሦስት ንዑስ አንቀጾችን የሚያካትት ነው። በዚህም መሠረት በሥራ ላይ በሚገኘው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 6 ሥር ኮሚሽኑ፣ ‹‹በምርጫ ወቅት በምርጫ ታዛቢነትና በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ክትትል ማድረግ እንደሚችል›› የሚገልጽ ድንጋጌ አንቀጽ 6(11) ሆኖ እንዲካተት በረቂቁ ተካቶ ቀርቧል።
‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ስለሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ክትትል ማድረግ›› የሚል ድንጋጌ አንቀጽ 6(12) ሆኖ በረቂቅ አዋጁ ተካቷል። በዚህ አንቀጽ ሥር ሦስተኛው አዲስ ድንጋጌ ሆኖ የቀረበው ደግሞ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውንም ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎችን ወይም በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ሰዎች ያሉበትን ሥፍራና ማናቸውንም የሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያለ ቅድመ ማስታወቂያ መጎብኘት›› የሚል አዲስ ድንጋጌ አንቀጽ 6(13) ሆኖ እንዲካተት ቀርቧል።
ይህ ረቂቅ ማሻሻያ የቀረበው የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአሁኑ ወቅት ተጥሎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወሰኑ ድንጋጌዎች፣ ከሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አንፃር ያላቸውን ሕጋዊነት ኮሚሽኑ በመተቸት እንዲሻሻሉ ባለበት ወቅት፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ላይ ተስተውለዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተመለከቱ ሪፖርቶችን ይፋ አድርጎ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ውድቅ በተደረገ በሳምንቱ ነው።
ባለፈው ሳምንት ዕትም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተቋቋመው መርማሪ ቦርድ ጋር፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ አለመግባባት ስለመፈጠሩ መዘገቡ ይታወሳል።
የአለመግባባቱ መነሻ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ እንዲሁም የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ የተወሰኑ አንቀጾች ላይ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ በማቅረቡ ነው።
ኮሚሽኑ የመብት ጥሰት ሊያስከትሉ ይችላሉ ብሎ ከለያቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ማስፈጸሚያ ደንቡ ድኖጋጌዎች መካከል፣ አዋጁና ማስፈጸሚያ ደንቡ ከወንጀል ሕግ መርህ ውጪ በተለጠጠና ሰፋ ብሎ ሊተረጎሙ የሚችሉ የወንጀል ጥፋቶችንና ክልከላዎችን በመያዙ፣ ሊሻሻል እንደሚገባ ያቀረበው ምክረ ሐሳብ ይገኝበታል። በዓይነትና ክብደታቸው ሰፊ ልዩነት ላላቸው የተለያዩ ጥፋቶችና አነስተኛ የደንብ መተላለፎች ጭምር በአንድ ዓይነት እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እስራት፣ ወይም እስከ ብር 200,000 የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት መደንገጉ ትክክል አለመሆኑን በመጥቀስ በምክረ ሐሳቡ እንዲሻሻል ጠይቋል።
የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግና በሌሎችም ሕግ የተመለከቱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በደምሳሳው መታገዳቸው ተገቢ ባለመሆኑ፣ ማሻሻያ እንዲደረግ በኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ የቀረበ ሌላው ጥያቄ ነው።
በተጨማሪም አዋጁ ለወረርሽኝ የመከላከል ሥራ የግል ንብረት መውሰድን በሚመለከት ለመንግሥት የሰጠው ሥልጣን ሰፊ መሆኑ ለመብት ጥሰት የሚዳርግና በባለንብረቶች ላይ የተለጠጠ ግዴታን የሚጥል መሆኑ፣ በደንቡ ላይ ከተቀመጡት ድንጋጌዎች መካከል በመናገርና በሚዲያ ነፃነት ላይ በጥብቅ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ከሆነው በላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ድንጋጌዎች በመካተታቸው ሊሻሻሉ እንደሚገባቸው፣ ካመለከተባቸው ድንጋጌዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ፓርላማው የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ በተወያየበት ወቅት፣ አንድ የምክር ቤት አባል ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሰብዓዊ መብቶች መከበራቸውን እንዲከታተል የሚፈቅደው ረቂቅ ማሻሻያ ድንጋጌ፣ በአስቸኳይ አዋጅ ወቅት ከሚቋቋም መርማሪ ቦርድ ኃላፊነት ጋር የተናበበ መሆኑ ረቂቁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ እንዲያጤነው ጠይቀዋል። ምክር ቤቱ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁን በዝርዝር እንዲመለከት ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ መርቶታል።