Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበተሻረ ሕግ መብታችንን ማጣት የለብንም ያሉ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች አቤቱታቸውን ለመንግሥት አቀረቡ

በተሻረ ሕግ መብታችንን ማጣት የለብንም ያሉ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች አቤቱታቸውን ለመንግሥት አቀረቡ

ቀን:

‹‹ሁሉንም በሚጠቅም እንጂ በተሻረ ሕግ የተሠራ ነገር የለም››

የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር

‹‹ተቋሙ አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎች ተቀብሎ ለመመለስ ዝግጁ ነው››

- Advertisement -

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን

የቀድሞዎቹ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴርና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ያጠኑትን መነሻ በማድረግ፣ ለልማት ሲባል የመሬት ይዞታ ስለሚለቀቅበትና ካሳ ስለሚከፈልበት ሁኔታ ወጥቶ የነበረው አዋጅ ቁጥር 455/97 በአዋጅ ቁጥር 1161/2012 ተተክቶ የተሻረ ቢሆንም፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደርና የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የተሻረውን ሕግ በመጠቀም መብታቸውን ሊያሳጧቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ነጋዴዎችና ነዋሪዎች ለከተማ አስተዳደሩና ለሚመለከታቸው ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አቤቱታቸውን አቀረቡ፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ነጋዴዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች አቤቱታቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ለቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና ለሌሎችም በርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ያቀረቡ ቢሆንም፣ ከዕንባ ጠባቂ ተቋም በስተቀር ሌሎቹ ተቋማት ምላሽ ሊሰጧቸው ስላልቻሉ የክፍለ ከተማውንና የመንገዶች ባለሥልጣንን ሕገወጥ አካሄድ በፍርድ ቤት ማሳገዳቸውን ሪፖርተር ያገኘው ማስረጃ ያረጋግጣል፡፡

ባለሦስት ኮከብ ሆቴል፣ ዘመናዊ የመኖሪያ ሕንፃዎችና ከ400 በላይ በንግድ ሥራ የተሰማሩባቸው ሱቆች በመንገድ ልማት ምክንያት እንደሚፈርስባቸው አቤቱታ እያቀረቡ ያሉት ባለይዞታዎች ቁጥር ከ40 በላይ መሆናቸውን፣ ለምክትል ከንቲባው ጽሕፈት ቤትና ለተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ያስገቧቸው አቤቱታዎች ያስረዳሉ፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማና የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በተሻረ ሕግ መብታቸውን ሊያሳጧቸው መሆኑን እየገለጹ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አቤቱታ እያቀረቡ የሚገኙት ነጋዴዎችና ነዋሪዎች፣ ‹‹መብታችን ሊጣስ ነው›› የሚሉት ከቱሉ ዲምቱ በቦሌ ቡልቡላ አድርጎ እስከ ቦሌ ሚካኤል አደባባይ ተሻግሮ ወደ ሩዋንዳ መዞሪያ ሌላ አደባባይ ላይ የሚቆምና በመሠራት ላይ ባለ የተላላፊ መንገድ ግንባታ ምክንያት መሆኑን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡

ለተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የቀረቡት አቤቱታዎች እንደሚያስረዱት፣ መንገዱ በቦሌ ቡልቡላ አድርጎ በቦሌ ወረዳ አንድ ቦሌ ሚካኤል አደባባይን በማቋረጥ ተሻግሮ፣ ወደ ሩዋንዳ በሚያዞረው አደባባይ ላይ ይቆማል፡፡ ከቦሌ ድልድይ ወደ ሳሪስ በሚወስደው ቀለበት መንገድ በቀኝ በኩል የሚገኙ በመገንባት ላይ ያሉ ባለስድስትና ከዚያም በላይ ርዝመት ያላቸው ሕንፃዎችና ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች አሉ፡፡ ባለሦስት ኮከብ ኡግባድ የሚባል ሆቴልና በርካታ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች፣  ሬስቶራንቶችና ሻይ ቤቶች በድምሩ 181 ግንባታዎችን እንደሚነካና የተወሰኑትን ሙሉ በሙሉ እንደሚያፈርስ አቤቱታዎቹ ያስረዳሉ፡፡ የነጋዴዎቹና የነዋሪዎቹ ተቃውሞ ‹‹ለምን ልማት ይኖራል?›› የሚል ሳይሆን፣ ወደ ሳሪስ በሚወስደው አቅጣጫ ያለው የቀለበት መንገድ ስፋት በቂ መሆኑንና ከቦሌ ቡልቡላ እስከ ቦሌ ሚካኤል አደባባይ የሚሠራው ተላላፊ መንገድ፣ ከዋናው አስፋልት አምስት ሜትር ላይ በሚገኘው ወደ ሩዋንዳ ማዞሪያ አደባባይ ላይ የሚቆም በመሆኑ፣ መጨናነቅ ከመፍጠር ባለፈ የሚሰጠው ጥቅም እንደሌለ በመግለጽ የዲዛይን ለውጥ እንዲደረግላቸው መሆኑን በአቤቱታቸው ጠቁመዋል፡፡

ከአካባቢው ነዋሪዎች ውስጥ የምህንድስና ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የዲዛይን ሥራና ጥናት አብረው ለማድረግ ያቀረቡትን ጥያቄ ክፍለ ከተማውም ሆነ ባለሥልጣኑ እንዳልተቀበላቸው ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ያሠራውን የመንገድ ዲዛይን የማየት መብት እንዳላቸው በመግለጽ ኮፒ እንዲሰጣቸው ያቀረቡትን ጥያቄም እንዳልተቀበሉ ገልጸዋል፡፡ ነጋዴዎቹና ነዋሪዎቹ ምንም እንኳን ተቋማቱ እያከናወኑት ያለው ሥራ አሳማኝ ያልሆነና ግልጽነት የጎደለው ቢሆንም፣ ‹‹ለአገርና ለከተማ ልማት ነው›› ስላሉ በደፈናው በመቀበል የመብት ጥያቄ ማንሳታቸውን በሰነዶቹ ተመልክቷል፡፡

ነጋዴዎቹና ነዋሪዎቹ ለተቋማቱ በጻፉት ደብዳቤ እንዳብራሩት ምንም እንኳን የመንግሥት ዓላማ አንዱን እያለማ ሌላውን ማፍረስ እንዳልሆነ ቢታወቅም፣ ለልማት ነው ስለተባለ ልማቱን እንደግፋለን፡፡ በመሆኑም አዲስ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2012 ድንጋጌ ከአንቀጽ 2 (ከ2 እስከ 6) ባሉት ንዑስ ድንጋጌዎች መሠረት ካሳ ተሠርቶ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡

የነጋዴዎቹና ነዋሪዎቹን ጥያቄ የተመለከተው የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ጽሕፈት ቤትም ሆነ የወረዳ አንድ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የሰጧቸው ምላሽ እንደሚያስረዳው፣ በአዋጅ ቁጥር 455/97 ድንጋጌና የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ድንጋጌ መሠረት ይዞታቸውን እንዲለቁና የተሠራላቸውን የካሳ ክፍያ፣ ምትክ ቦታና የአንድ ዓመት የቤት ኪራይ እንዲወስዱና በሦስት ወራት ውስጥ እንዲለቁ የሚያሳስብ ነው፡፡

አዋጅ ቁጥር 455/97ን አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1161/2012 በአንቀጽ 28 (1 እና 2) ድንጋጌ መሻሩን በመግለጽ ካሳ የሚሠራላቸው በአዲሱ አዋጅ መሆኑን፣ በአዲሱ አዋጅ 1161/2012 አንቀጽ 8(ሀ) ድንጋጌ መሠረት ይዞታቸው ለልማት ከተፈለገ ከአንድ ዓመት በፊት ሊነገራቸውና ሊወያዩበት ሲገባ የተነገራቸው በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም. መሆኑን፣ ካሳ ሊሠራላቸው የሚገባውም በአዲሱ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት በተመሰከረለት ባለሙያ የይዞታው ግምት፣ ንግድ ፈቃድ አውጥተው የአከራይ ተከራይ ለመንግሥት እየከፈሉና ተከራዮችም ለመንግሥት ታክስ እየከፈሉ መሆናቸው ተረጋግጦ፣ የሚያገኙትን ገቢና የሚያጡትን ኪሳራ ተሠርቶ መሆን ሲገባው ይህንን ባለማድረጉ አካሄዳቸው ሕገወጥና በተሻረ ሕግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ (ኢንጂነር) ያስገቡላቸውን አቤቱታ ተመልክተው፣ አካባቢውን ቢጎበኙ መፍትሔ እንደሚሰጧቸው የሚናገሩት ነጋዴዎቹና ነዋሪዎቹ፣ እነሱ እያሉ ያሉት ‹‹ሕግ ይከበር›› እና በሕጉ መሠረት ማግኘት የሚገባቸው እንዲሰጣቸው እንጂ፣ የልማቱ ደጋፊዎች ለመሆናቸው ምንም ዓይነት ጥርጥር እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከይዞታቸው ላይ እንዲነሱ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ነዋሪ አቶ ወንድይፍራው ከበደ እንደገለጹት፣ በአካባቢው ከ30 ዓመታት በላይ ኖረዋል፡፡ ቀለበት መንገድ ሲገነባ ጀምሮ አካባቢው ሲፈርስ አሁን ለአራተኛ ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ቦሌ ክፍለ ከተማና የከተማው መንገዶች ባለሥልጣን በየካቲት ወር ሰብስበው ሲያነጋግሯቸው፣ ‹‹ይዞታው ለልማት ስለሚፈለግ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. ትነሳላችሁ›› እንዳሏቸው፣ ጊዜው የኮሮና ወረርሽኝ በመሆኑ ኮሚቴ በማቋቋም ከአስተዳደሩ የተለያዩ አካላት ጋር አምስት ጊዜ ሲወያዩ፣ ከተወካዮቹ ጋር ተስማምተው ቢለያዩም በጎን ሌሎች ኃላፊዎች ደብዳቤ እየላኩ እንደሚፈርስ እያስፈራሯቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግራ ቢገባቸው ‹‹ለልማት ከሆነ በሕጉ መሠረት አስተናግዱን›› ሲሏቸው፣ የቀድሞውንና የተሻረውን ሕግ ጠቅሰው ደብዳቤ በመጻፍ ካሳና ምትክ ቦታ እንዲወስዱ ከማስፈራራት ያለፈ ምንም ምላሽ እንዳልሰጧቸው አክለዋል፡፡ መንግሥት የሚያቅደው ከግለሰብ የተለየ መሆን እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ወንድይፍራው፣ አንድ መንገድን አራት ጊዜ እያፈረሱ ነዋሪውን ከማማረር በዕቅድና በዲዛይን አስተካክለው ቢሠሩ፣ እነሱም ከችግር ይድኑ እንደበር ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ያላወቃቸው ጥቂት በየተቋማቱ የተሾሙ ግለሰቦች መንግሥትና ሕዝብን ለማጋጨት ሆን ብለው እየሠሩ በመሆናቸው፣ ‹‹ተው›› ሊባሉ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዲዛይን ሲሠራ ካሳውንም በተገቢው የሕግ ድንጋጌ አስልቶና ሠርቶ ጥያቄ ቢያቀርብም ውዝግብ ውስጥ ከመግባት ያድናቸው እንደነበር ጠቁመው፣ ድሮ ይሠራበት የነበረውን የዘልማድ አሠራር መከተል አሁንም እንዳልቀረም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ምህንድስና ሳይንስ ነው፡፡ አንድና አንድ ሁለት እንጂ ሦስት አይሆንም፤›› የሚሉት ነዋሪው፣ የቦሌ አስተዳደር ኃላፊዎችም ሆኑ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች፣ ሕንፃውን የሚነካው በከፊል እንደሆነና አንድ ምሰሶ ብቻ ነው የሚነካው እንደሚሉ፣ ሕንፃ መሠረቱ ከተነካ ሕንፃ ስለማይሆን ሁሉም እንደሚፈርስ በማስረዳት፣ መንግሥት ሁሉንም በየሙያው ካላሰማራ በካሳም ይሁን በክስ ወጪው ከፍተኛ እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት ነጋዴዎችን ግብር ምሮ እንደ አዲስ ሥራ እንዲጀምሩ እያበረታታ ባለበት ሁኔታ፣ ሌሎች ነጋዴዎችንና ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ‹‹ለልማት ነው ሊል አይችልም›› ብለዋል፡፡ አዲስ አዋጅ ያወጣውም የቀድሞው አዋጅ ነጋዴውንም ሆነ ባለይዞታውን ጎጂ  ስለሆነ እንደሆነም አክለዋል፡፡ ከቡልቡላ ቦሌ ሚካኤል የሚመጣው መንገድ በጣም ብዙ የንግድ ተቋማት፣ የእምነት ተቋማትና መኖሪያ ቤቶችን የሚያስነሳ ቢሆንም፣ ያ ሳይነካ ቦሌ ጫፍ ላይ (ሚካኤል አጠገብ) መጥቶ ሱሪ በአንገት የተባለበት አሠራር፣ ነገሮቹን ሁሉ በትኩረትና በልዩ ሁኔታ እንዲያዩ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል፡፡ አስተዳደሩ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መሆኑን ጠቁመው፣ አስተዳደሩ የቤትና የመንገድ ግንባታ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ስለሆኑ፣ ወደፊት ሊሠራቸው ላቀዳቸው ከመቶ ያላነሱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የሚመደበው በጀት ከፍተኛ በመሆኑ የተለየ ትኩረትና በሙያው ብቃት ያለው የሰው ኃይል መመደቡን ማረጋገጥ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የተጀመረ ፕሮጀክት ሳይጠናቀቅ አዲስ ባይጀመርም መልካም መሆኑን አክለዋል፡፡ ልማት ደጋፊ ቢሆኑም ሕግ የወሰነላቸውን መብት ማጣት ስለማይፈልጉ፣ ጉዳዩን በፍርድ ቤት ማሳገዳቸውን ጠቁመዋል፡፡ ምክትል ከንቲባውም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን ተገንዝበው፣ ተገቢው የካሳ ክፍያ በአዲሱ ሕግ ተሰልቶና ሕጉ የሚፈቅድላቸውን ማንኛውንም መብት እንዲያገኙ ትዕዛዝ እንዲሰጡላቸው ጠይቀዋል፡፡

ለምክትል ከንቲባው፣ ለቦሌ ክፍለ ከተማ፣ እንዲሁም ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ‹‹ሕግ ይከበር፣ በሕግ እንዳኝ›› በማለት አቤቱታ እያቀረቡ ስለሚገኙት የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ነጋዴዎችና ነዋሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዲ ፉፋን ሪፖርተር አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ አብዲ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በአገር ደረጃ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙም ከፍተኛ መሆኑን ግንዛቤ መወሰድ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ የሚያስነሳቸው ሦስት ቤቶችን ብቻ መሆኑንና ሌሎቹ እስከ ሦስት ሜትር የሚሆን አጥር ብቻ እንደሚነካባቸው አክለዋል፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ የሚገባቸው ካሳም ተሠርቶላቸዋል ብለዋል፡፡

የካሳ ክፍያን በሚመለከት ደንብና መመርያ ባይወጣላቸውም (ሰሞኑን ደንቡ ወጥቷል) ከይዞታቸው ለሚነሱት ነዋሪዎች በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 1161/2012 ድንጋጌ መሠረት፣ የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ እንዲሠራላቸው መደረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የይዞታ ግምቱም በአዲሱ አዋጅ እንደሚሠራላቸው አክለዋል፡፡ በመመርያ ዝርዝሩ ስላልወጣ የሚቀረው ነዋሪዎቹ በአከራዩዋቸው የንግድ ቤቶች ይሠሩ የነበሩ ነጋዴዎችን በሚመለከት የሚሠራው የማቋቋሚያ ክፍያ መሆኑን ጠቁመው፣ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መመርያው እንደ ደረሳቸው ለእነሱም ሠርተው እንደሚሰጡ አቶ አብዲ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከተማውን ከመቀየር በተጨማሪ ለትራፊክ ፍሰት መጨናነቅን የሚቀንስ መሆኑንና ከጂቡቲ መውጫ መንገድ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ፣ ጥቅሙ ሰፊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በከተማው ማስተር ፕላን መሠረት የተሠራ መሆኑንና ክፍለ ከተማው የማስፈጸም ኃላፊነት ስላለበት እየሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ልማቱ ለሕዝብ የሚጠቅም በመሆኑ፣ ‹‹መንግሥትን ቢተባበሩ ይሻላል›› ብለዋል፡፡

በተሻረ ሕግ የተሠራና የሚሠራ ነገር እንደሌለና የሚሠራው ነዋሪውን የሚጠቅም ብቻ መሆኑን ተናግረው፣ ምንም እንኳን እንደሚነሱ የተነገራቸው በየካቲት ወር ቢሆንም ምልክት የተደረገው ከሁለት ዓመታት በፊት በመሆኑ ነዋሪዎቹ ግንዛቤ እንዳላቸው በመጠቆም፣ አዋጅ ቁጥር 1161/2012 ከአንድ ዓመት በፊት ለተነሺዎች መነገርና እንዲዘጋጁ ማድረግ ተገቢ መሆኑን የሚገልጸውን እንደፈጸሙ አስታውቀዋል፡፡

ሪፖርተር ያናገራቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ጣሰው ስቡ በተጨማሪ እንዳብራሩት፣ የካሳ ግምት እየሠሩ ያሉት በአዲሱ አዋጅ ነው፣ በተሻረው አዋጅ አይደለም፡፡ ‹‹አዋጅ ቁጥር 1161/2012 ወጥቷል፡፡ ደንብና መመርያ ሳይወጣ የዘገየ ቢሆንም፣ ሰሞኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቡን አውጥቷል፡፡ መመርያው ግን ገና አልተዘጋጀም፡፡ መንገዱ የሚሠራው ለዜጎች ጥቅም፣ ለከተማችን ዕድገትና ለአገርም ዕድገት እንዲያመጣ ነው፡፡ ከቦሌ እስከ ሳሪስ እንዲሁም ከቡልቡላ ወደ መስቀል ፍላወር የሚሄደውን የትራፊክ ፍሰት የሚያሳልጥ መንገድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ነዋሪውን ሰብስበው መወያየታቸውንና የካሳ ሥራም ማገባደዳቸውን አቶ ጣሰው ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች  አሉ፡፡ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ ተከራይ ከአካባቢው ሥራውን ለቆ ስለሚሄድ፣ በሌላ ቦታ ሄዶ እስከሚላመድና ሥራውን በደንብ መሥራት እስከሚችል ድረስ ስለሚሰጠው ክፍያ፣ በአዋጁ መቀመጡን ጠቁመው እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን አረጋግጠዋል፡፡ መመርያው ስላልወጣ የጠቀሱት የተሻረውን አዋጅ ቁጥር 455/97 መመርያ ቁጥር 19 መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አዲሱ መመርያ ሲወጣ በዚያ እንደሚሠራላቸው ገልጸዋል፡፡ ካሳ ሲሠራ በየዓመቱ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያ ዋጋን በማጥናት በእያንዳንዱ ግብዓት ያለውን የዋጋ ለውጥ ስለሚያቀርብላቸው፣ የሚሠሩትም በእሱ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ለተነሺዎች የካሳ ግምትም ሆነ ማንኛውንም ነገር የሚሠራላቸው በአዋጅ ቁጥር 1161/2012 መሆኑን አቶ ጣሰው አስረድተዋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ነጋዴዎቹና ነዋሪዎቹ የጠየቁትን በፕሮጀክቱ ጥናት ላይ እንዲሳተፉና የዲዛይን ኮፒ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ለምን እንደከለከላቸውና ሌሎች ጥያቄዎች ከሪፖርተር የቀረበለት ቢሆንም፣ ምላሹን በጽሑፍ አቅርቧል፡፡ ባለሥልጣኑ እንደሚለው የመንገዱ ርዝመት 5.5 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ከቦሌ ቡሉቡላ ወደ ቦሌ ሚካኤል ቀለበት መንገድ በ15፣ በ20 እና በ30 ሜትር የጎን ስፋት ያላቸው ሦስት መዳረሻ መንገዶች እንዳሉት አስታውቋል፡፡ መንገዱ ከቂሊንጦ እስከ ቦሌ ሚካኤል የሚሠራው የ23.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ግንባታ አካል መሆኑን ጠቁሞ፣ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የሚችልና ቀለበት መንገዱን ተከትሎ በቦሌ ሚካኤል አደባባይ ላይ የሚሻገር 600 ሜትር ርዝመት ያለው የላይና የታች መተላለፊያ እንዳለው ከመግለጽ ውጪ የት ድረስ እንደሚሄድ አልጠቀሰም፡፡ መንገዱ የፈጣን አውቶቡስ ትራንስፖርት (BRT) መስመርን በማጎዳኘት የሚገነባ መሆኑን ባለሥልጣኑ በምላሹ ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም በማስተር ፕላኑ መሠረት በቀለበት መንገዱ ላይ የሚሠራው የፕሮጀክቱ አካል፣ ከ32 እስከ 40 ሜትር የነበረው የጎን ስፋት 46 ሜትር እንዲሰፋ መደረጉን አክሏል፡፡

መንገዱ በከተማ አስተዳደሩ የተመደበ 267.9 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘለት፣ አሰር ኮንስትራክሽን በተባለ አገር በቀል የሥራ ተቋራጭ እየተከናወነ መሆኑን ባለሥልጣኑ ጠቁሟል፡፡ የግንባታ ክትትሉንና ቁጥጥሩን ሃይዌይ ኢንጂነርስና ኤምቲኤስ የተባሉ አማካሪ መሐንዲሶች እየተከናወነ መሆኑንና በሁለት ዓመታት እንደሚጠናቀቅም አክሏል፡፡ የፕሮጀክቱ ባለቤት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን መሆኑንና ኅብረተሰቡን አቃፊ እንጂ ገፊ እንዳልሆነ ገልጾ፣ የልማት ተነሺዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በተወካዮቻቸው አማካይነት ተቀብሎ ሲያነጋግር፣ የተፈጠሩ ብዥታዎች ካሉ ተቀብሎ ለማነጋገር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ፕሮጀክቱ የሚነካቸው 181 ቤቶች መሆናቸውን ጠቁሞ፣ በርካቶቹ አጥራቸውን የሚነካ እንደሆነ፣ በከፊልና ሙሉ በሙሉ የሚነሱ እንዳሉም አረጋግጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...