Friday, June 9, 2023

በኮረና ወቅት የጭንቀት ማስወገጃ መንገዶችን እንከተል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የጭንቀት ስሜቶች ሊያድሩብን ይችላሉ፡፡ ከዕለት ተዕለት ኑሮ ሁኔታችን ጋር በተገናኘ እንዲሁም በሽታው ቢይዘኝስ የሚል ሥጋት በየዕለቱ ሲደጋገም፣ ባናስተውለውም ሥነ ልቦናችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡

ጭንቀት ከሚረብሽ ስሜትነቱ በተጨማሪ በራሱ የበሽታ ምንጭ እንደሚሆን ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ የአዕምሯችንንና የሰውነታችንን ጭንቀት ለማቃለል ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ቀላልና የተጠኑ፣ ራስን ከጭንቀት ማላቀቂያ መንገዶች መጠቀም እንችላለን፡፡

በጥልቀት መተንፈስ፡- አተነፋፈሳችንን በማስተካከል ሰውነታችንን እንዲሁም አዕምሮአችንን ማረጋጋት እንደምንችል ስንቶቻችን እናውቃለን፣ መተንፈስ የተፈጥሮ ፀጋ ቢሆንም በረዥም ጊዜ ተደራራቢ ጭንቀት የተነሳ ብዙዎቻችን በትክክል አንተነፍስም፡፡ ይኼንን ለማድረግ ከተቻለ ሰዎች የማይረብሹን ቦታ እንሁን፡፡ እጃችንን ሆዳችን ላይ እናድርግና አየር በጥልቀት ወደ ውስጥ እንውሰድ፡፡ ወደ ውጪ እናውጣ፡፡ ሆዳችን ላይ ባረፈው እጃችን ማደጋገጥ ያለብን አየር ወደ ውስጥ ስናስገባ፣ ሆዳችን እንደ ፊኛ መነፋቱን እንዲሁም አየር ወደ ውጭ ስናስወጣ ሆዳችን ወደ ውስጥ መተንፈሱን ነው፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ከሆነ በትክክል እየተነፈስን አይደለም ማለት ነው፡፡ ይህንን አተነፋፈስ በየትኛውም ሰዓት፣ በተረጋጋ ሁኔታ ሆነን ቢያንስ ሦስት ጊዜ ካደረግን፣ ሰውነታችንን እንዲሁም አይምሯችን ዘና ይላል፡፡

ትኩረታችንን “አሁን” እና “እዚህ” ላይ ማድረግ/ማይንድፉልነስ/፡- በርካታ ጭንቀቶች የሚፈጠሩት ወይ ስላለፈው ስናሰላስል፣ ወይ ደግሞ ስለሚመጣው ስናስብ እንሆነ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ጭንቀት ሲሰማንም ሆነ ሳይሰማን ሐሳባችን እዚህና እዛ ሲዋዥቅብን፣ ለአዕምሯችን ዕረፍት በመስጠት ትኩረታችንን በአሁኑ ጊዜ ላይ፣ ፊት ለፊታችን በምንመለከተው ነገር ላይ፣ አጠገባችን ባለው ነገር ላይ፣ አሁን፣ በቅርብ በስሜት ህዋሳቶቻችን፣ በሚሰሙን ነገሮች ላይ ትኩረት ብናደርግ፣ አዕምሮ ከጭንቀት ፋታ ያገኛል፡፡ ከጭንቀት ይልቅ በመረጋጋት መንፈስ ውስጥ ስንሆን ችግሮቻችንን የመፍታት ብቃታችን ይጨምራል፡፡

አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፡- ከከፍተኛ አካላዊ እንቅስቃሴ እስከ ቀለል ያሉ ጥቂት ዕርምጃዎች ጭንቀትን የመቀነስ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ለማንኛውም አዋቂ ሰው በቀን የሰላሳ ደቂቃ አካላዊ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ይመክራል፡፡ አካላዊ እንቅስቃሴ የሰውነትን ጥንካሬ ከመጨመር በተጓዳኝ የአዕምሮን ጤንነት ለመንከባከብ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ዕረፍት ስሜት የሚሰጠንን ነገር ለማድረግ ሁሌም ጊዜ መመደብ፡-  በሕይወት ሩጫ ብዙ ጊዜ ባይኖረን እንኳን፣ ጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ሰላም የሚሰጡንን ነገሮች ለማድረግ ጊዜ መመደብ ሌሎች የሕይወት ተግባራቶቻችን ላይም ውጤታማ እንድንሆን ያደርጉናል፡፡ ለምሳሌ እንደየዕምነታችን መፀለይ፣ ወደ ዕምነት ተቋማት መሄድ፣ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር በስልክ እንኳን ቢሆን ጊዜ ማሳለፍ፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ሙዚቃ እየሰሙ መደነስ ወ.ዘ.ተ

ተመስጦ (ሜዲቴሽን)፡- የተለያዩ የተመስጦ ዓይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንደኛው ጭንቀት በተሰማን ጊዜ ፀጥታ ያለበት ቦታ ለመሆን በመሞከር ዓይናችንን ጨፍነን መቀመጥ ነው፡፡ አተነፋፈሳችንን ከላይ በተጠቀሰው መሠረት እናስተካክል፡፡ በአዕምሮአችን እጅግ የሚያዝናናን፣ የምንወደው፣ ዕረፍት የሚሰጠን ቦታን ወይም ሁኔታን እናስብ፡፡ ቦታው ወይም ሁኔታው የሚፈጥርብንን ስሜት፣ ለምሳሌ ያየር ሁኔታውን፣ ንፋሱን፣ ፀጥታውን፣ ድምፆቹን ሁሉንም ወደ አዕምሮአችን እናምጣ፡፡ አየር ወደ ውስጥና ወደ ውጪ በጥልቀት መተንፈስ አንርሳ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምቾት እስከሚሰጠን ጊዜ ድረስ እንቆይ፡፡ ሲበቃን ትኩረታችንን ወዳለንበት አካባቢ በመመለስ አየር በጥልቀት እንውሰድና ዓይናችንን እንክፈት፡፡

ጭንቀትዎ ከፍተኛ ሆኖ የዕለት ተዕለት ኑሮዎ ላይ ተፅዕኖ ካሳደረ፣ የባለሙያ ዕገዛ መሻት አስፈላጊ ነው፡፡ በተረፈ ግን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንንና የምንወዳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

(ሰላማዊት ተስፋዬ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -