Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሆቴል ባለሙያዎች ከሥራ ገበታቸው እየተቀነሱና ደመወዝ እየተከለከሉ እንደሚገኙ አስታወቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ የሚውል አስቸኳይ ብድር የለቀቀላቸው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ባለሀብቶች፣ ለሠራተኞቻቸው መክፈል የሚጠበቅባቸውን ደመወዝ በአግባቡ እንደማይከፍሉና አንዳንዶቹም ክፍያ እንዳቋረጡ የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር ገለጸ፡፡

ማኅበሩ ዓርብ፣ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ከየትኛውም የንግድ ዘርፍ በተሻለ መንገድ ድጋፍ የተደረገላቸው ባለኮከብ ሆቴሎች ከመንግሥት የተሰጣቸውን ድጋፍ ለተገቢው ዓላማ እንዳላዋሉት አስታውቋል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንቦች መሠረት ደመወዝ በአስገዳጅነት መከፈል እንዳለበት የሚነግገውን ሕግ እየጣሱ መሆነቸውን በማስታወቅ ማኅበሩ ሆቴሎችን ኮንኗል፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ይልቅ ለኢትዮጵያ ሆቴሎች የተለየ ድጋፍ በማድረጉ ለመንግሥት ምሥጋና ያቀረቡት የማኅበሩ አመራሮች፣ አንዳንድ ሆቴሎች ግን የተሰጣቸውን ድጋፍ ወደ ጎን ሲያደርጉ መታየታቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት ለሥራ ማስኬጃና ለደመወዝ ክፍያ እንዲያውሉት ሦስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ቢያደርግላቸውም፣ አንዳንድ ሆቴሎች ግን ጭራሹን ደመወዝ መክፈል እንዳቆሙ አውስተዋል፡፡ አንዳንዶቹም ደመወዝ ቆርጠው እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ልዑልሰገድ መሰለ፣ ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ ያልከፈሉ፣ ሲከፍሉም ቆራርጠው የሚከፍሉ ሆቴሎች ከአድራጎታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል፡፡ ‹‹የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ እንዳይወድቅ መንግሥት ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረግ፣ ሆቴሎች የስድስት ወር ደመወዝ እንዲከፍሉ አግዟል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የሆቴሎች ብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ማድረጉን፣ ሆቴሎች ከጠየቁት በላይም ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡ መንግሥት የሦስት ወር የገቢ ግብር ላይ ማሻሻያ ማድረጉ እየታወቀ፣ ሠራተኞችን ማባረርና ደመወዝ መቀነስ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

የሆቴልና የቱሪዝም እንቅስቃሴ በ98 በመቶ በመመታቱና ሁለት በመቶውም ቢሆን በለይቶ ማቆያነት የተመረጡ ሆቴሎች የሚሠሩበትን ድርሻ የሚወክል ነው ያሉት አመራሮቹ፣ የበሽታው ክስተት ጊዜያዊ ችግር መሆኑ እየታወቀ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ያገለገሉ ሠራተኞችን፣ ‹‹አታስፈልጉም ተብሎ ማስወጣት ከባህልም ከሞራልም አንፃር አሳፋሪ ተግባር ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ ሆቴሎች ስለመኖራቸው መረጃ እየደረሳቸው እንደሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በመተሳሰብና በመደጋገፍ መንፈስ ሠራተኞችን በማቆየት የሆቴል ባለቤቶች የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡  

በአንፃሩ ሠራተኞችን ይዘው ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ተጋግዘን እንሻገራለን፣ እናልፋለን በማለት የሚሠሩትንም አመስግነዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዬ የምንለው በዘፈን ብቻ ሳይሆን በተግባርም መሆን አለበት፡፡ ሆቴልና ቱሪዝም ወድቆ እንደማይቀር ማሰብ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ የማኅበሩ ቦርድ አባል፣ የምርምርና ሥልጠና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይታሰብ ሥዩም በበኩላቸው፣ የወረርሽኙ ተፅዕኖ የሚታወቅና በኢትዮጵያም እያየለ እንደመጣ ጠቅሰው፣ የዳበረ ዘርፍ ባላቸው ጎረቤት አገሮች ያልተተገበረ ድጋፍ በኢትዮጵያ መንግሥት መሰጠቱን አወድሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት ካወጣቸው መመርያዎች ውስጥ ሠራተኞች እንዳይቀነሱ የሚከለክል፣ ደመወዝ ማቋረጥ እንደማይቻል የሚገልጽና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማስፈጸም የወጣውን የሠራተኛና አሠሪ ፕሮቶኮል በማስፈጸም ረገድ ክፍተት እንዳለ ማኅበሩ መገንዘቡን አቶ ይታሰብ ገልጸዋል፡፡ መመርያዎች አለመከበራቸው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እየታየ ያለውን ክፍተት እንደፈጠረው ገልጸው፣ እስከታች ወርደው ተፈጻሚነታቸውን መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

‹‹የሆቴል ሠራተኞች ከገቢያቸው እስከ 70 በመቶ ይገኝ የነበረው ከሰርቪስ ቻርጅ ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አሁን ‹‹ሥራው ስለሌለ ሠራተኞቹ ይህን ገቢ እያጡ ነው፡፡ በመሆኑም እየተጎዱ ባሉበት ወቅት፣ ጭራሹኑ የሚያገኙዋትን ጥቂት ደመወዝ በመቀነሳቸው ችግር ውስጥ እየከተታቸው ነው፤›› ያሉት አቶ ይታሰብ፣ ማኅበሩ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት አንዳንድ ሆቴሎች ከአሥር እስከ 50 በመቶ ደመወዝ ስለመቀነሳቸው ተጨባጭ መረጃ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ይህ አግባብ ባለመሆኑ በአፋጣኝ እንዲታረም አሳስበዋል፡፡  

ከ130 ያላነሱ አባላት ካሉት የአዲስ አበባ ሆቴሎች ባለንብረቶች ማኅበር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ ተነጋግሮ መፍትሔ ለመፈለግ ማኅበራቸው ጥሪ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ገልጸዋል፡፡ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑትና በሆቴል ሙያ ዘርፍ ከ40 ዓመታት በላይ በማገልገል የሚታወቁት ወ/ሮ ስንዱ ጌታቸው በበኩላቸው ወቅቱ ብዙ እንዳስተማረ፣ ችግሩን በጋራ ተሳስቦ ማለፉ ለወደፊቱ ጊዜ መሠረት እንጂ አንዱ ሌላውን የሚገፋበት እንዳልሆነ በመግለጽ ቅሬታቸውን አስተጋብተዋል፡፡

‹‹አንዳንዶች ሠራተኛውን እንደ ቤተሰብ ይዘው ሲሠሩ፣ ሌሎች ግን ሠራተኞቻቸውን ሲጥሉ ይታያል፡፡ ለሠራተኛው እየታሰበ አይደለም፡፡ መተሳሰብ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

በማኅበሩ አመራሮች እንደ ዋና ችግር የተነሳው የሆቴሎች የሠራተኛ ቅነሳና የደመወዝ መከልከል ተግባር እንዲታረም የሆቴሎቹ ስም በይፋ ይገለጽ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፣ አቶ ይታሰብ ‹‹እኛ እነኝህ ናቸው ብለን ማንሳት አልፈለግንም፡፡ ሆኖም እስካሁን ችግሩን በመረጃ ከደረስንባቸው ሆቴሎች ባለቤቶች ጋር ለጉዳዩ በጋራ መፍትሔ ለመስጠት እየተሞከርን ነው፡፡ በዚህ ጥረት የተወሰኑ ሆቴሎች ማስተካከያ በማድረጋቸው ቅድሚያ በግንባር ችግሩን ለመፍታት በዚህ መንገድ መሞከሩ ይበጃል ብለዋል፤›› ብለዋል፡፡

ባለ ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ከኢኮኖሚ ጉዳት ባሻገር ለሥነ ልቦና ችግር እየተዳረጉ ነው ያሉት የማኅበሩ ኃላፊዎች፣ ‹‹ሠራተኛን ማባረር ነገ ዋጋ ያስከፍላል፤›› በማለት ሆቴሎችን አስጠንቅቀዋል፡፡

ሠራተኛ ያባረሩ፣ ደመወዝ የቀነሰኑ የ14 ሆቴሎች ጉዳይ በእጃቸው እንደሚገኝ ያስታወቁት የማኅበሩ አመራሮች፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት እንዳቀረቡ ጠቅሰው አንዳንዶቹ ‹‹እኛ ተበድረን ለሠራተኛ አንከፍልም፤›› እንደሚሉ ይህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአግባቡ አለመተግበር ያመጣው አጉል መዳፈር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በማኅበሩ አመራሮች የተጠቀሰው ሌላው ነጥብ በለይቶ ማቆያነት እያገለገሉ የሚገኙ ሆቴሎች፣ ‹‹ሰርቪስ ቻርጅ›› ቢሰበስቡም፣ ለሠራተኞቻቸው አያስተላለፉም ብለዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ለማወቅ ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ ማኅበሩ ገልጿል፡፡ ወደፊት ምን ዓይነት የማገገሚያ ስትራቴጂዎች መተግር እንዳለባቸው ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ገልጸው፣ በአንዳንድ ተቋማት ሆነ ተብለው እየተጋነኑ የሚወጡ መረጃዎች በጥንቃቄ መታየት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች