Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከጥሬ ገንዘብ ዝውውር በላይ ተጨማሪ ገደቦችን እንደሚያስከትል የሚጠበቀው አዲሱ ሕግ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮሮና ወረርሽኝ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በተለያየ መንገድ እየተገለጸና እየተተነተነ ይገኛል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ መዛመት የጀመረው ይህ ወረርሽኝ፣ ሁሉንም የንግድ መስኮች እየነካካ ነው፡፡ በአንፃሩ ለአንዳድ ቢዝነሶችና አገልግሎቶች የዝማኔ በር እንዲከፈት ሰበብ እየሆነ ነው። በፋይናንሱ ዘርፍ በተለይ ባንኮች ላይ የቱንም ያህል ጫና ቢያሳርፍም፣ በሌላ አቅጣጫ ግን ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት እንዲሠሩና ተጠቃሚዎችም ወደ ዘመናዊ አገልግሎት እንዲመጡ እያገዘ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም። ከባንኮች ውጭ የሚደረግ ገንዘብ እንዲገደብ መደንገጉ ይታወቃል። ከዚሁ ጎን፣ በጥሬ ገንዘብ ባንክ ወደ ባንክ ማዘዋወርን ለማስቀረት አዲስ አሠራር እንዲተገበር መደረጉ ለባንኮች መልካም አጋጣሚ ሆኖላቸዋል።

በመመርያውና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያነጋገርናቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ  ትኩረት ይደረግባቸው በማለት ያነሷቸው ነጥቦች አሉ። ባንኮች ቸገሩበት የነበረውን አሠራር በማስቀረት ከባንክ ወደ ባንክ ገንዘብ እንዲተላለፍ መፈቀዱ ለፋይናንስ ዘርፉ ትልቅ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ ማስተላለፍ በግድ በጥሬ ገንዘብ ወጪ አድርጎ ቆጥሮና አስተካክሎ በጠባቂዎች አጀብ ወደ ሌላኛው ባንክ ማጓጓዝን ጠይቅ ነበር። ይህ አሠራር ጊዜ ከመፍጀቱም በላይ ለከፍተኛ ሥጋት የተጋለጠ ነበር፡፡ ባለሙያው በተቀየረው አሠራር መሠረት ጥሬ ገንዘብ በማጓጓዝ ሒደት የነበረውን ሥጋት የሚያስቀር ከመሆኑም በላይ ወጪ ቆጣቢ ነው ብለውታል።

የኢኮኖሚስቱን ሐሳብ የሚጋሩት የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፣ዘመናዊ አገልግሎትን ከማስፋፋት ባሻገር ባንኮች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡና ፈጠራ የታከለበት አሠራር ውስጥ እንዲገቡ ያግዛቸዋል። ‹‹መመርያ መውጣት ባንኮችን የአዲስ አሠራር ፈጣሪዎች ያደርጋቸዋል፡፡ ደንበኛዬ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት ስለማይችል፣ ምን ዓይነት ተስማሚ አገልግሎት ላምጣለት ወደ ማለቱ ይገባሉ›› በማለት፣ ደንበኞችን ላለማጣትና ገንዘብ በዘመናዊ መንገድ እንዲገባ ለማስቻል ፈጠራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ አስፋው ይገልጻሉ፡፡

በዚህ ብቻ አይወሰንም። ዘመናዊ ባንክ አገልግሎት እየሰፋና ሌሎች የክፍያ አገልግሎቶችም በዚሁ ሥርዓት እንዲገዙ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ሲሆኑ፣ ጥሬ ገንዘብ ከባንክ ወደ ባንክ የማዘዋወሩ አሠራር እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሲሠራበት ቆይቶ አሁን ላይ ግን ማንኛውም ባንክ ከየትኛውም ባንክ ገንዘብ ለማዘዋወር ጥሬ ገንዘብ ማጓጓዝ  አይጠበቅበትም፡፡ ስለዚህ ባንኮች ላይ የነበረውን ጫና ከመቀነሱም በላይ ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለማስፋት ያግዛል ብለዋል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ መመርያው ለግብይት ጥሬ ገንዘብ የሚጠቀመው ተገልጋይ እንዲቀንስ በማድረግ፣ ከጥሬ ገንዘብ ባሻገር ያሉ የክፍያ ዘዴዎችን ማምጣት ዓላማ እንዳለው አቶ አስፋው ጠቅሰው፣ ከደኅንነት አኳያ ያሉ ችግሮችን ለማስቀረት፣ ሥውር ወንጀሎችን ለመከላከል ጭምር ያግዛል ብለዋል። ከባንኮች ተጠቃሚነት አንፃር ማየት ካስፈለገም ምሳሌዎችን መጥቀስ እንደሚቻል አቶ አስፋው ማብራሪያ መረዳት ይቻላል።

ባንኮች እንቅስቃሴ ከጥሬ ገንዘብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ለዚያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ሲያፈሱ መቆየታቸውንና የኦፕሬሽን ወጪያቸውም ከፍተኛ እንደሆነ፣ የገንዘብ መቁጠሪያ ማሽኖች ያውም በውጭ ምንዛሪ እየተገዙ እንደሚመጡ አቶ አስፋው ጠቅሰው፣ ሌሎች ወጪዎች ሲታከሉበት የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ለባንኮች ወጪ መባባስ ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ችግሩ ምን ያህል እንደነበር ለመግለጽም በምሳሌ የጠቀሱት የብር ኖቶች በቀላሉ እያረጁ ተጨማሪ ወጪ ማስከተላቸውን ነው፡፡ በንክኪ ብዛት የብር ኖቶች ጥቂት ካገለገሉ በኋላ ስለሚበላሹ ዳግመኛ ለማሳተም ብቻም ሳይሆን፣ ለሰው ጤናም ጠንቅ እስከመሆን ይደርሳሉ ብለዋል፡፡

ሌላው ቀርቶ አሮጌ የብር ኖቶችን ወደ ኤቲኤም ማሽኖች ለማስገባት አስቸጋሪ እንደሆኑና ማሽኖቹ አገልግሎት መስጠት ሲቸግራቸው ከሚታዩባቸው ችግሮች አንዱ አዳዲስ የብር ኖቶች እንደ ልብ ባለማግኘት አሮጌ ብሮች እየተከተተባቸው በሚፈጠር ብልሽት ጭምር ነው፡፡ ‹‹ማሽኑ እንዳይቆም ባንኮች ሻል ያለውን የብር ኖት እየመረጡ  ይስገቡበታል፤›› ያሉት አቶ አስፋው፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ሲቀንስ የብር ኖቶች እርጅናም እየቀነሰ ረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ ከማገዝ አልፎ፣ ለብር ኖቶች ኅትመት የሚወጣው የውጭ ምንዛሪም እንዲቀንስ ያስችላል ብለዋል፡፡ የመመርያው መውጣት ሌላም ጥሩ ጎን እንዳለው የሚናገሩት አቶ አስፋው፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጋር ያያይዙታል፡፡

ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር የሚሠሩ የውጭ ባንኮችና ሌሎች ዓለም አቀፍ  የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ለችግር ተጋላጭ መሆኑን የሚጠቅሱትም በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተውን የንግድና የግብይት ሥርዓት በማመላከት ነው፡፡ እስካሁን በነበረው ሒደት ለስርቆት የተመቻቸ እንደሆነ በመተቸት፣ አሁን ሥራ ላይ እንደዋለው ዓይነት መመርያ ቀደም ብሎ አለመኖሩ፣ የገንዘብ ዝውውሩ ለውጭ ኢንቨስተሮች የማይመች ሆኖ ቆይቷል ተብሏል፡፡ የመመርያው መውጣት የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ሊያግዝ ይችላል በማለት አቶ አስፋው አስረድተዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበርም የብሔራዊ ባንክ መመርያ አጋዥ እንደሆነ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ሕዝቧ 38 በመቶ ብቻ የባንክ ተጠቃሚ እንደሆነና 62 በመቶ ገና  ባንክ እንዳልተዋወቀ በማውሳት ይህንን ለመለወጥ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር መቀነስ እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት ከፋይም ሆነ ተከፋይ የግድ ወደ ባንክ መምጣት ስለማይጠበቅባቸው የባንክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ሊያሳድገው ይችላል ብለዋል፡፡

ከባንክ ውጭ ያለው ገንዘብም ወደ ባንክ መጥቶ በመደኛው ኢኮኖሚ ውስጥ ካልተንቀሳቀሰ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለውና የገንዘብ እጥረት ሊያመጣ ስለሚችል መመርያው መውጣት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ያጎላዋል ተብሏል።

 ሁሉንም ባንኮች በአባልነት የያዘው ‹‹ኢትስዊች›› መሠረተ ልማት ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው ገንዘብ በማቀናነስ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን የሚያስቀር አሠራር እንዲተገበር ያደርጋል፡፡ ይህ አሠራር እንዲዘረጋ ለረዥም ጊዜ ሲወተወት እንደቆየ የኢኮኖሚ ባለሙያው አስታውሰው፣ የባንክ ደንበኞችም በዚህ እንዲጠቀሙና የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በኦላይንና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች መለወጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን የሚገድበው አሠራር ሥጋትን ከመቀነስ፣ ወጪን ከመቆጠብና ዘመናዊ አሠራርን ከማጎልበት በላይ፣ ባንክ ወደ ባንክ ገንዘብ ለማዘዋወር እንዲሁም ክፍያዎችን ለመፈ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን በመቀነስ ገንዘቡ ከባንክ  ሳይወጣ እንዲቆይ የሚያስችል መሆኑ ጠቀሜታ የጎላ እንደሚሆን ይጠበቃል

አሠራሩ ከኩባንያዎች በተጨማሪ፣ የግል ገንዘብ ለማንቀሳቀስና ልዩ ልዩ ክፍያዎችን ያለ ጥሬ ገንዘብ ለመፈጸም የሚያግዝ ነው፡፡ ይህ ሲሆን፣ ወደ ባንክ የሚመጣውን የገንዘብ መጠን ሊቀንሰው ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ቢደመጡም፣ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያም ሆኑ አቶ አስፋው በዚህ አይስማሙም፡፡ እንደውም ወደ ባንክ የሚሄዱ ሰዎችን ያበራክታል ይላሉ

ይህ ይባል እንጂ በጥሬው የተከማቸ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ከሰሞኑ ቤታቸው ውስጥ ገንዘብ ለማስቀመጥ የካዝና ሸመታ ላይ ተጠምደዋል እየተባለ ነው፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ከባንክ ውጭ አለ ተብሎ የሚነገረው ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የትም ሊቀመጥ አይችልም፡፡ ሰዎች አንድ ነገር መረዳት አለባቸው፡፡ በመመርያው መሠረት ገንዘብ ይንቀሳቀስ የተባለው ሥርዓት ባለው መንገድ ከባንክ ባንክ ክፍያ ይፈጸም ነው፤›› በማለት መመርያው ሕጋዊ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንደማይገድብ አቶ አስፋው አመልክተዋል፡፡

ካዝና ግዥ ላይ የተጠመደ ሰው አደጋ ላይ ይወድቃል በማለት አቶ አስፋው አስጠንቅቀዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ሕጉ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በመገደብ ብቻ ሳይወሰን፣ ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡት ሌላው ጥያቄ፣ ከባንክ ውጭ ምን ያህል ገንዘብ መያዝና በሰዎች እጅ መገኘት እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ እንዲወጣ እያሳሰቡ በመሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ይህ ሕግ ወጥቶ ሲተገበር በድንገተኛ ፍተሻ ወቅት ከተቀመጠው  ገደብ በላይ በቤቱ ገንዘብ የተገኘበት ሰው ይወረስበታል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ መሠረት ወደፊት ከባንክ ውጭ ያለውን ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ለማስገባት የሚያግዝ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል የጠቆሙት አቶ አስፋው፣ ከዚህ በኋላ እንደሚወጣ የሚጠበቀው ሕግ በቤት የሚቀመጠውን የገንዘብ መጠን በይፋ ይደነግጋል ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት የመገበያያ ገንዘብን ድንገት ሊለውጠው ስለሚችል፣ አንድ ሰው በእጁ መያዝ የሚጠበቅበት ገንዘብ 100 ሺሕ ብር ቢሆንና የገንዘብ ለውጡ ሲደረግ ግን 200 ሺሕ ብር ቢገኝበት ገንዘቡን ሊወረስ ይችላል ወይም በተለወጠው ገንዘብ ሊቀየርለት የሚችለው 100 ሺሕ ብር ብቻ ይሆናል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሰዎች ቤታቸው ያስቀመጡትን ገንዘብ ወደ ባንክ ማስገባት እንደሚጠቅማቸው ማሰብ ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ አስፋው፣ ሥራ ላይ የዋለው መመርያም እንዲህ ያሉ ለውጦች እንደማይቀሩ ጠቋሚ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከባንክ ወደ ባንክ በቀጥታ ገንዘብ የማስተላለፍ ዘዴ ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያስታወሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ከዚህ በኋላ የኦላይን የግብይት ሥርዓት እንዲሰፋ ተቋማትም ወደዚህ ሥርዓት በመግባት ግብይታቸውን እንዲለውጡ ያስችላቸዋል ይላሉ፡፡ ኩባንያዎች ማንኛውንም ምርቶቻቸውን በኦላይን በማገበያየት በባንኮች በኩል የገንዘብ ልውውጡ እንዲፈጸም ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጥሬ ገንዘብ ለማዘዋወር የሚከፈለው የኢንሹራንስ ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ጭምር ለባንኮች የወጣው መመርያ ትልቅ ዕፎይታ እየሆነ ነው፡፡ የባንኮች ወጪ ሲቀንስ፣ በከፍተኛነቱ ወቀሳ የሚቀርብበት የብድር ማስከፈያ ወለድ እንዲቀንስ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመመርያው ለመሥራት ሊቸገሩ የሚችሉ ደንበኞች እንደሚኖሩም ይጠበቃል፡፡ ይህ እየታየ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ አስፋው፣ ጥሬ ገንዘብ ማዕቀብ እየተደረገበት በመሆኑ ወደ ዲጂታል ሥርዓት መግባት ግዴታ እየሆነ መምጣቱን መረዳት ያስፈልጋም ብለዋል፡፡

ደንበኞች አሠራሩን እስኪለምዱትና ወደ መስመር እስኪገቡ ድረስ እንደሚቸገሩ ቢታሰብም፣ እንዲህ ያሉ ችግሮች ለፈጠራ ስለሚያግዙ፣ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ለማቆየትና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ተስማሚና ቀልጣፋ አሠራር እንዲዘረጉ ይገደዳሉ፡፡ ይህ እያደረጉ ኅብረተሰቡንም በቴክኖሎጂ የዳበረ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ወጪ ቆጣቢ አሠራር እንደሚያሰፉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች