Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናከሱዳን ጋር ግጭት ውስጥ የሚያስገባ ምክንያት ስለሌለ ችግሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ...

  ከሱዳን ጋር ግጭት ውስጥ የሚያስገባ ምክንያት ስለሌለ ችግሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ አሳሰበች

  ቀን:

  ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያና በሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች በድንገት የተነሳው የታጣቂዎች ግጭት ሁለቱን አገሮች ወደ ግጭት ለማስገባት ምክንያት የሌለ በመሆኑ፣ ችግሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ አሳሰበች።

  በሁለቱ አገሮች የድንበር አካባቢዎች በድንገት በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ የሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚደገፉ የታጠቁ ቡድኖች ወደ ሱዳን ድንበር በመዝለቅ ከሱዳን ጦር አባላት ጋር ግጭት እንደፈጠሩ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

  ለሁለት ቀናት በዘለቀው በዚህ ድንገተኛ ግጭት አንድ የሱዳን ጦር አባልና አንድ ሲቪል መገደላቸውን የገለጸው የሱዳን መንግሥት፣ ሌሎች ዘጠኝ ሲቪሎችም መቁሰላቸውን አመልክቷል። ግጭቱ የተነሳው የሱዳን መንግሥት አል ፋሻቅ ብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ በዚህ ቦታ ላይ ሁለቱ መንግሥታት የይገባኛል ጥያቄ ያነሳሉ።

  ግጭቱ ከመነሳቱ ከሁለት ሳምንት በፊትም የሁለቱ መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአዲስ አበባ ተገናኝተው ድንበር ለማካለል መስማማታቸው ይታወሳል። ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በካርቱም የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ በመጥራት፣ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የዘለቁ ታጣቂዎች አድርሰውታል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ማነጋገሩን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።

  የሁለቱ መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የድንበር ውዝግቡን ለመፍታት አዲስ ጥረት በጀመሩበትና ሱዳንም ሁለተኛውን ዙር ውይይት ለማስተናገድ እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት ጥቃት መሰንዘሩን የሱዳን መንግሥት በፅኑ እንደሚያወግዝ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ጉርብትናና ትብብር ሉዓላዊነትንና ነፃነትን ያከበረ ሊሆን እንደሚገባ ማሳሳቡን በመግለጫው አስታውቋል።

  ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚን በጠራች በማግሥቱ (እሑድ ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም.)፣ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መግለጫ ያወጣች ሲሆን፣ በሁለቱ አገሮች መካከል በድንገት የተፈጠረው ግጭት በጋራ እንዲጣራ ጠይቃለች።

  ኢትዮጵያና ሱዳንን ወደ ሙሉ ግጭት የሚወስድ ምክንያት እንደሌለ ኢትዮጵያ እንደምትገነዘብ ያመለከተው መግለጫው፣ ሁለቱ አገሮች በሚዋሰኑባቸው አካባቢ ያሉ የመንግሥት መዋቅር አመራሮችንና አስተዳዳሪዎችን በማሳተፍ በአዋሳኝ አካባቢዎች ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስቧል።

  ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ መንግሥታት በከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው የጀመሩትን ዲፕሎማሲያዊ መስመር በመጠቀም የቆየ ጉርብትናቸውንና ወዳጅነታቸውን በማጠናከር፣ ለድንበር ጉዳዮቻቸው ዕልባት መስጠት እንደሚቻልና እንደሚገባ ኢትዮጵያ የምታምን መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።

  ይህ ድንገተኛ ግጭት በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለውን ጥብቅ ወዳጅነት የማይገልጽ እንደሆነም ኢትዮጵያ በመግለጫዋ ጠቁማለች። ከዚህ መግለጫ በኋላ በሁለቱ አገሮች አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ የመንግሥት መዋቅር አመራሮች የግጭት አካባቢዎቹን በአካል የጎበኙ ሲሆን፣ በሁለቱም በኩል ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎችም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

  የሰሞኑ ግጭት ወደ ቀድሞ መረጋጋቱ የተመለሰ ቢሆንም፣ ሁለቱም መንግሥታት የጦር ሠራዊቶቻቸውን በከፍተኛ ደረጃ በድንበር አካባቢ እያጠናከሩ እንደሚገኙ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው አል ዓረቢያ የተባለ ሚዲያ ዘግቧል።

  የሱዳን መንግሥት ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሳበት የድንበር አካባቢ የጦር ሠራዊቱን የማስፈር እንቅስቃሴ መጀመሩ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለታየው ውዝግብ መነሻ ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።

  የሱዳን ጦር ይህንን አካባቢ ለቆ ከወጣ 25 ዓመታት ማለፉን የጠቀሰው ይኸው ሚዲያ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አካባቢው መሰማራቱ በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ ለሚስተዋለው መካረር ምክንያት መሆኑን ጠቁሟል።

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...