Thursday, March 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኦሊምፒክ ኮሚቴ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች 1.6 ሚሊዮን ብር ደገፈ

ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች 1.6 ሚሊዮን ብር ደገፈ

ቀን:

አንጋፋ አትሌቶች 200 ሺሕ ብር አግኝተዋል

ንግሥት ስፖርቱን እንዲደጉም ተጠየቀ

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች 1.6 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለአንጋፋ አትሌቶች ደግሞ 200 ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከአትሌቶችና ከስፖርት ቤተሰብ በአደራ የሚያስተዳድረውን ገንዘብ በግልጽነትና በታማኝነት መንፈስ በዚህ ክፉ ቀን፣ አትሌቶችና ሙያተኞች ችግር ላይ እንዳይወድቁ፣ የወደቁም ካሉ መነሳት እንዲችሉ በማቀድ ድጋፉን ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ድጋፉን ለማድረግ አስቀድሞ ከአገር አቀፍ ፌዴሬሽኖች ጋር ውይይት ማድረጉንና ፌዴሬሽኖቹም ያቀረቡት ጥናት መሠረት እንደሆነው ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዝግጅት እስካሁን ከተደረጉት ዝግጅቶች በእጅጉ የላቀ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቡ በአጠቃላይ የተሳተፈበት የችቦ ዝውውር ተደርጎ፣ በችግሩ ምክንያት በመሀል እንዲቋረጥ የተደረገበት አጋጣሚ የሚያስቆጭ መሆኑን ያስረዳው የተቋሙ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዚህ ወቅት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችንና አሶሴሽኖችን መደገፍ እንዳለበት በቂ መነሻ እንደሆነው ያስረዳል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሁሉም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች እንዲሁም አንጋፋ አትሌቶች መገኘታቸው ታውቋል፡፡ በዕለቱ በነበረው ሥነ ሥርዓት መልዕክታቸውን ካስተላለፉት መካከል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይጠቀሳል፡፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴው በአርዓያነቱ ሊጠቀስ የሚችል ተግባር ፈጽሟል ያሉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ እግር ኳሱን ጨምሮ ተቋማት የሠራተኞቻቸውን ወርኃዊ ክፍያ ለመክፈል መቸገራቸውን አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ክለቦች አሠልጣኞቻቸውና ተጨዋቾቻቸው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ በማያደርጉበት በዚህ ወቅት መንግሥትም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል፤›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

የስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ

 

በተያያዘ ዜና ኮቪድ-19 ፈተና ለሆነበት የኢትዮጵያ ስፖርት መንግሥት ድጎማ እንዲያደርግ ተጠይቋል፡፡

ብዙዎቹ ስፖርቶች ኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ባለው ተፅዕኖ በመቆማቸውና ገቢ በማጣታቸው ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን በመግለጽ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በዚህ ፈታኝ ወቅት ያደረገው ድጋፍ በትልቁ እንደሚያስመሰግነው የገለጹት የስፖርት  ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር ናቸው፡፡

የስፖርቱ ቤተሰብ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከቁሳቁስ አቅርቦት እስከ ገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ደም ልገሳ በማድረግ አጋርነቱን ማሳየቱን በመጥቀስ ስፖርቱን በበላይነት እንዲመራ ተጨማሪ ኃላፊነት ለተጣለበት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጥያቄው ቀርቧል፡፡

ሚኒስቴሩ ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በመሆን፣ መንግሥት እንደ ሌሎቹ የልማት ዘርፎች ሁሉ ለስፖርቱ የገንዘብ ድጎማ እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡

ሁለቱ መንግሥታዊ ተቋማት በዋናነት ለዚህ ውሳኔ የበቁት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በስፖርቱ ዘርፍ ላይ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ ከባድ እንደሆነ፣ በተለይም ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተወሰዱ ዕርምጃዎች ማለትም ሥልጠናዎችና ውድድሮች መቆማቸው፣ ስፖርተኛውና የስፖርት ቤተሰቡ ለሥነ ልቦናና ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመዳረጋቸው ነው፡፡

በጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ፣ በችግሩ ምክንያት በርካታ የስፖርት ክለቦችና ማኅበራት የመፍረስ አደጋ እንደተደቀነባቸው አውስተው፣ በዚህ የተነሳ አንዳንዶቹ ለስፖርተኞቻቸው ወርኃዊ ክፍያ እስከ መከልከል ደርሰዋል ብለዋል፡፡

ስፖርት ኮሚሽን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በወረርሽኙ ወቅትና ከወረርሽኙ በኋላ ስፖርቱ እንዴት ወደ ነበረበት መመለስ ይችላል የሚለውን የሚያጠናና የጥናቱን ውጤት ለመንግሥት የሚቀርብ አንድ ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙን ጭምር  ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

የተቋቋመው ኮሚቴ አንድ ዓብይና ቴክኒካል ኮሚቴ ያለው ሲሆን፣ ዓብይ ኮሚቴውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ሲመራ፣ ቴክኒካል ኮሚቴው ደግሞ በምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ዱቤ ጅሎ የሚመራ መሆኑ ታውቋል፡፡

ኮሚቴው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በሁሉም ስፖርቶች ላይ እያሳደረ ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስና ጉዳት እንዲሁም መፍትሔዎቹን ጭምር በማጥናት እንዳስፈላጊነቱ ሰነዱን ለመንግሥት የሚያቀርብ አካል እንደሆነም ምክትል ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

ጥናቱን መሠረት በማድረግ መንግሥት ስፖርቱ ለኢትዮጵያ የሚያበረክተውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ እምነታቸው መሆኑን ላመለከቱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ድጋፉ ቢፈቀድ ለስፖርት ተቋማቱ በምን መልኩ ለማከፋፈል ታስቧል? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ‹‹በጥናት የሚመለስ ነው›› በማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከ26 በላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋሙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ያሉ ቢሆንም በጣት ከሚቆጠሩ ስፖርቶች ውጭ ብዙዎቹ የጎላ እንቅስቃሴ የሌላቸው በመሆኑ የኮሚሽኑ መመዘኛ ምን ሊሆን እንደሚችልም ምክትል ኮሚሽነሩ የሰጡት አስተያየት አለ፡፡ ኮሚሽኑ ክፍተቶችን እየተመለከተ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ በፊት እንደነበረው የሚቀጥል ነገር አይኖርም ብለዋል፡፡ ለመንግሥት የቀረበው የገንዘብ ድጎማም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን መታወቅ አለበት በማለት ተቋማቱ በተደራሽነታቸው እንደሚለኩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...