Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ከሰው መለስ ያሉ ደቂቀ አካላት

ገነነ ተፈራ (ዶ/ር) በብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የደቂቀ አካላት ብዝኃ ሕይወት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የተወለዱት፣ የመጀመርያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በቀድሞዋ አርሲ ጠቅላይ ግዛት ሲሆን፣ በቨርትነሪ ሜዲስን የመጀመርያ፣ በማይክሮ ባዮሎጂና ኢሚኖሎጂ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ ከሚገኘው ብርኖ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቨርትነሪ ሜዲስን ኤንድ ፋርማሲዩቲካል ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ ግብርና ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢሾፍቱ እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የደቂቀ አካላት ብዝኃ ሕይወትዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዶ/ር ገነነን በደቂቀ አካላትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የብዝኃ ሕይወት (ባዮዳይቨርሲቲ) ሥርዓት ሊዘረጋ የቻለበት ምክንያት ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ገነነ፡- በዓለም ውስጥ ሕይወት ያላቸው አካላት የሚጠቅሙ ስለሆነ መነበር (ኮንሰርቬሽን) እንዳለባቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ለተግባራዊነቱ ብዝኃ ሕይወት ወይም ባዮዳይቨርሲቲ የሚባል ሲስተም ተዘረጋ፡፡ ብዝኃ ሕይወት ማለት ሰውን ሳይጨምር በምድር ላይ የሚገኝና ሕይወት ያለው ነገር በሙሉ መስተጋብሩን ጨምሮ በአንድነት አጠቃልሎ የያዘ መጠሪያ ወይም ስያሜ ነው፡፡ ብዝኃ ሕይወት ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ እነርሱም ተክሎች፣ እንስሳትና አኒማልና ደቂቀ አካላት (ማይክሮ ኦርጋኒዝምስ ወይም ማይክሮብስ) ይባላሉ፡፡ እነዚህን ሦስት ሕይወት ያላቸውን አካላት እያንዳንዱ አገር እንዲያነብርና ጥቅም ለይ እንዲያውላቸው የዓለም አቀፉ ስምምነትና የየአገሮች ግዴታ ያመላክታል፡፡ በዚህም የተነሳ በአንድነት ሲነበሩ የአካባቢያቸውን ሥነ ምኅዳር ይወክላሉ፡፡ ተነጣጥለው በየዝርያቸው ከተነበሩ ግን በዝርያ ደረጃ ተነበሩ ይባላሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ውስጥ ይህንኑ የሚከታተል የደቂቀ አካላት ብዝኃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተጠቀሱት ክፍሎች መካከል ደቂቀ አካላት የተባሉት ፍጥረታት ምንድናቸው? የእነዚህን አካላት አፈጣጠርና ለምድራችን ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በተመለከተ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ገነነ፡- ደቂቀ አካላት (ማይክሮ ኦርጋኒዝምስ/ማይክሮብስ) አጉልቶ በሚያሳይ መነጽር ካልሆነ በዓይን የማይታዩ የፍጥረት አካላት ናቸው፡፡ እነርሱም ቫይረሱ፣ ባክቴሪያ፣ ፈንገስ፣ ማይክሮ አልጌና ፕሮቶዘዋ ይባላሉ፡፡ ከሃይማኖታዊ ውጪ በሳይንሶዊ መንገድ ካየን ዓለም ገና ስትፈጠር የነበሩ የመጀመርያው ፍጥረታት ደቂቀ አካላት ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ኦክስጅንና ፎቶሲንተሲስን ለዓለም አበርክተዋል፡፡ እንዲሁም ካርቦንዳይኦክሳይድን የሚመጡ ናቸው፡፡ እንዳው በአጠቃላይ ለቀጣዩም የፍጥረት ዓይነት መነሻ የሆኑ ነገሮችን ያመቻቹ፣ ለእንስሳትም ሆነ ለሰው የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ያለስስት በመስጠት ሕይወት እንድትቀጥል የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እኛ የምንመገበውን ምግብ ጥርሳችን በግርድፉ ከፈጨው በኋላ ወደ አንጀታችን ይገባል፡፡ አንጀታችን ውስጥ በግርድፉ የገባውን እህል አድቅቀውና አዋህደው እንዲሠራጭ የሚያደርጉት ደግሞ ሆዳችን ውስጥ ያሉት ደቂቀ አካላት (ማይክሮ ኦርጋኒዝምስ) ናቸው፡፡ በምግባችን እርሾን ይሠራሉ፡፡ እንጀራ ቢጋገር፣ ዳቦ ቢደፋ፣ ጠላ ቢጠመቅ ወተት ቢረጋ ዝርያቸው ይለያይ እንጂ ይህን የሚያደርጉት ደቂቀ አካላት ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእኛ ጋር ይኖራሉ፣ እኛን ያግዛሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ከአፈር ውስጥ ያለውን ንጥረ ነገር  እየሰባበሩና እየመጠኑ በመስጠት ዕፀዋት እንዲያድጉ እንዲሁም እንስሳት ሆድ አንጀት ውስጥ ያለውን የሚበላ ነገር እንዲብላላ በማድረግ ረገድም ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ እነዚህ ደቂቀ አካላት ከተፈጠሩ ከሁለት ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ሌሎች ሕይወት ያላቸው እንደመጡ ሳይንስ ያስረዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ደቂቀ አካላት በሽታ አምጪ ናቸው ይባላል፡፡ በእዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው? ብዛታቸው/ቁጥራቸው በውል ተለይቶ ይታወቃል?

ዶ/ር ገነነ፡- ደቂቀ አካላት ቁጥራቸው ልክ የለውም፡፡ ምናልባትም በአንድ ትንሽ የሻይ ማንኪያ አፈር ውስጥ እስከ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑ ደቂቀ አካላት እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 0.01 በመቶ ያህሉ የሚታወቁ ሲሆን፣ ከሚታወቁም መካከል በጣም ጥቂቶቹ ናቸው በሽታ አምጪ በመባል የተሰየሙት፡፡ ገና ከጅምሩ ግን አፈጣጠራቸው ሲታይ በሽታ አምጪ አልነበሩም፡፡ በሽታ አምጪ ሊሆኑ የቻሉት የሚኖሩበት አካባቢ ሰው ሲዛባ ወይም ሲጠቃ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለመፈለግ ሲሉ ወደ ሰው ይሄዳሉ፡፡ ከዚህም ያረፉበትን ሰው ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ እነርሱ ግን አይሞቱም ሕይወት ይቀጥላል፡፡ በነገራችን ላይ ደቂቀ አካላት በሁለት መንገድ ነው የሚኖሩት፡፡ ይህም ከአካባቢው ጋር ይላመዳሉ ወይም የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር ለእነርሱ በሚስማማ መልኩ ይለውጣሉ፡፡ በአጠቃላይ ባዮሎጂካል ኢሞርታል (ለዘላለም የሚኖሩት) ከሚባሉት የፍጥረት ዝርያዎች መካከል አንዱ ደቂቅ አካላት ናቸው፡፡ እየተባዙ ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በሽታ አምጪ የሚሆኑበትን ምክንያት በምሳሌ በማስደገፍ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ገነነ፡- ለምሳሌ ያህል አንበሳ የሚኖረው ሰንበሌጥ፣ ጫካና ሌሎች እንስሳት ባሉባቸው አካባቢ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካባቢ በሰው ሲነካበት ወይም ሲራቆትበት ሥነ ምኅዳሩ ይናጋበታል፣ ይበላሽበታል፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ሰው መጠጋቱና መተናኮሉ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ ደቂቅ አካላት አካባቢያቸው ሲናጋ ወይም ኢኮ-ሲስተማቸው ሲዛባ ወደ ሰው በቀላሉ ይተላለፍና ይላመዳሉ፡፡ ሰውነታችን ደግሞ ከእነሱ ጋር ትውውቅ ስላልነበረውና ያንን የመከላከል አቅም ስላላዘጋጀ የመጀመርያው ጥቃት ሞት ነው፡፡ በሒደት ውስጥ ግን ሰውነታችን ያንን የመከላከል ብቃት ይጨምራል፡፡ ይኼም በኢንፉሉዌንዛ የታየ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1918 የነበረው የስፓኒሽ ፍሎ የዚህ ውጤት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ መታሰብ ያለበት አንዱ ትልቅ ነገር ቢኖር የትኛውም የፍጥረት አካል የሚኖረው በመስተጋብር፣ በመረዳዳትና በመተሳሰር ነው፡፡ የተፈጥሮ ሕግም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ ሰው ግን በተፈጥሮ ሲኖር ራሱን የበላይ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ በዚህም የተነሳ ተፈጥሮን እንደፈለገው ለማድረግ ይንቀሳቀሳል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ተፈጥሮን እያሳሳ ይሄዳል፡፡ የአንድ በዓይን የማይታይ ትንሽ የሕይወት አካል መበላሸት ብዙ ችግሮችን ያስከትላል፡፡

ሪፖርተር፡- ደቂቅ አካላት መኖሪያቸው የት ነው?

ዶ/ር ገነነ፡- የትም ነው፡፡ አይኖሩበትም የተባለ ቦታ የለም፡፡ ሰው በማይኖርበት ቦታ ሁሉ ይኖራሉ፡፡ አካባቢን ያሳመሩም እነሱ ናቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- እነዚህን ደቂቅ አካላት ኢንስቲትዩቱ እንዴት ነው የሚያነብራቸውና የሚንከባከባቸው?

ዶ/ር ገነነ፡- ይህንን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት ስለብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት መናገር እፈልጋለሁ፡፡ የብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የሚሠራውን ሥራ ብዙ ሰው አልተረዳውም፡፡  ያለውን ነገር ብቻ የሚጠብቅ ተደርጎ ነው የሚታወቀው ይህ ዓይነቱ ዕይታና አረዳድ ስህተት ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ ትልቁ ሥራው በአገራችን ያልተዛባ ወይም የተመጣጠነ ተፈጥሮ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንዴት አድርጋችሁ ነው ይህንን የምታከናውኑት?

ዶ/ር ገነነ፡- ደኑ ለልማት ሲውል በተጠናና በተጠበቀ መንገድ መሆን አለበት፡፡ መነካትና ዝም ብሎ መጨፍጨፍም የለበትም፡፡ እርሻ ላይ ያሉ የአዝርዕት ዝርያዎች እኛ ዘንድ አሉ፡፡ ለምን ቢባል በአንድ ወቅት እንዳይጠፉ ነው፡፡ የእንስሳት ዝርያዎች አርሶ አደሩ በአግባቡ እንዲጠብቅ እናስተምራለን፡፡ የእንስሳት ዘረ መልን እናቀርባለን፡፡ የተፈጥሮ አካባቢ ከሰው ንክኪ ነፃ እንዲሆን እንሠራለን፡፡ የአካባቢ መጠበቅ ደግሞ በዓይን የማይታዩ ደቂቅ አካላት የተጠበቁ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ከዚህም ሌላ በኢንስቲትዩቱ ለዚህ ሲባል በተዘጋጀ ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ደቂቀ አካላትን እናስቀምጣለን፡፡ በሽታ አምጭ ናቸው የተባሉ ደቂቀ አካላትም ጥቅም ስላላቸው እንይዛቸዋለን፡፡ ጥቅማቸውም ለፈውስ የሚሆን መድኃኒት ከነሱ ማምረት መቻሉ ነው፡፡ እነዚህን ለማንበርና ለመለየት ባክቴሪያ ላይ የሠራ፣ ስለቫይረስ የተማረ፣ በማስተርስና በፒኤች ዲግሪ ደረጃ ፈንገስና ማይክሮ አግሪ ላይ የተማረ ባለሙያና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን የተዘረዘሩት ባለሙያዎችና ቴክኖሎጂዎችን ኢንስቲትዩቱ በተፈለገው መልኩ አላሟላም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ለኢንስቲትዩቱ እንደ አገር የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከጠቀሱት ችግሮች ባሻገር እንደ ችግር የሚያነሱት ሌላ ነገር አለ?

ዶ/ር ገነነ፡- አዎ፡፡ ይኸውም ሠራተኛን በተመለከተ ነው፡፡ ይህም ማለት የደመወዝ ክፍያ አናሳ መሆን፣ ማበረታቻና ማራኪ ነገር ባለመኖሩ ባለሙያዎችን ማቆየት አልተቻለም፡፡ ከዚህም ሌላ በተለይ የእኛ ሥራ በዓይን በማይታይ ላይ ያተኮረ ስለሆነ ከባለሙያዎችና ከበጀት አኳያ ያለው አቅም በእጅጉ አናሳ ነው፡፡ በእርግጥ አንድ ላቦራቶሪ እየተሠራልን ነው፡፡ ይህም በቂና የተሟላ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ሥራችን በተፈጥሮ ወይም በሕይወት ላይ የተመሠረተና በዓይን የማይታይ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በቅድሚያና ልዩ ትኩረት እየተሰጠ ያለው በዓይን ለሚታይ እንቅስቃስ ነው፡፡ ዝርዝር ባለ መልኩ ለማስረዳት ያህል እርሻና ግብርና ምርምር፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ፋርማሲዩቲካል ወዘተ መነሻቸው ብዝኃ ሕይወት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ደግሞ ትልቅ ኢንቨስትመንት መፍሰስ እንዲሁም ሳቢ የሆነ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም መዋል የነበረበት በብዝኃ ሕይወት ላይ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንስቲትዩቱን ዓመታዊ በጀት፣ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አኅጉራት ካሉት ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነትና እየተገነባ ስላለው ግንባታ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ገነነ፡- ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር ግንኙነት ለማድረግ በቅድሚያ እኛ የውስጥ አቅም ግንባታችን ጠንካራ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ ይህንን ሳናሟላ የአኅጉርና ዓለም አቀፍ ግንኙነትን መፍጠር ሳይንሳዊ አካሄድም አይፈቅድም፡፡ ነገር ግን አቅማችንን ገንብተንና ተወዳዳሪ ሆነን ከተገኘን የተጠቀሰውን ግንኙነት ለመፍጠርና በትብብር ለመሥራት መንገዱ ቀና ይሆናል፡፡ እነሱም በፀጋ ይቀበሉናል፡፡ በተረፈ የኢንስቲትዩቱን አቅም ለመገንባት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ሊረባረቡ ይገባል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የኢንስቲዩቱ ዓመታዊ በጀት 70 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለደቂቀ አካላት ብዝኃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ደመወዝን ጨምሮ የተመደበው ሦስት ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በዚህም ሠራተኛ ተቀጥሮበትና ዕቃ ተገዝቶበት እንዴት እንደሚብቃቃ፣ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ አብዛኛው ዕቃ የሚገዛው ከውጭ አገር ነው፡፡ ይህም ሆኖ ላለፉት አራት ዓመታት ያህል በበጀት እጥረትና በጨረታ መራዘም ምክንያት ምንም ዓይነት የዕቃ ግዥ አልተካሄደም፡፡ ግንባታን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ለደቂቀ አካላትና ለእንስሳት ብዝኃ ሕይወት የሚውሉ ሁለት የላብራቶሪዎች ሕንፃ ግንባታ ናቸው፡፡ በ187 ሚሊዮን ብር ውጪ በመገንባት ላይ ያሉት ሁለቱ ሕንፃዎች እያንዳንዳቸው ባለ ሦስት ፎቅ ሲሆኑ፣ በቅርቡ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍ ብሎ ለተዘረዘሩት ችግሮች ዕልባት እንዲፈለግላቸው አግባብ ላላቸው የመንግሥት አካላት አሳውቃችኋል?

ዶ/ር ገነነ፡- በተደጋጋሚ ጊዜ በቃልና በጽሑፍ አሳውቀናል፡፡ በአካል ቀርበንም አስረድተናል፡፡ ይህ ሁሉ ቢከናወንም ምንም ፈቀቅ ያለ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...