Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ባንክ ተጨማሪ የወለድ ቅናሽ በማድረግ ለንግድ መስኮች ድጋፉን አሳይቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ ባንክ የስምንት ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ሰጥቷል

በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ለተለያዩ የንግድ ዘርፎች የብድር ወለድ ቅናሽ ሲያደረግ የቆየው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ተጨማሪ የወለድ ቅናሽ አደረገ፡፡ የወለድ ቅናሹ በሦስት ወራት ውስጥ ከ113 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚያሳጣው ይጠበቃል፡፡

ከባንኩ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ እስካሁን ለተመረጡ የቢዝነስ መስኮች ከ0.5 በመቶ እስከ 4.5 በመቶ የማበደሪያ ወለድ ቅናሽ አድርጓል፡፡ እንደ አዲስ ባደረገው ማሻሻያ ግን ለሁሉም የንግድ ዘርፎች የ0.5 በመቶ የወለድ ቅናሽ እንዲደረግ ወስኗል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባንኩ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በተፈጠረው ጫና ምክንያት፣ ለደንበኞቹ የብድር ወለድ በመቀነስ አጋርነቱን እያሳየ ቆይቷል፡፡ ከእስካሁኑ ማሻሻያ በተጨማሪ እንደ አዲስ በተደረገው ቅናሽ መሠረት ሁሉም የቢዝነስ ዘርፎች ለሦስት ወራት የሚቆይ የ0.5 በመቶ የብድር ወለድ ቅናሽ ተደርጎላቸዋል ብለዋል፡፡

ንብ ባንክ ተጨማሪ የወለድ ቅናሽ በማድረግ ለንግድ መስኮች ድጋፉን አሳይቷል

ንብ ኢንተርናልናል ባንክ በዓለም እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ የተንሰራፋው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በመመልከት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ደንበኞቹን ለመደገፍ ተጨማሪ የብድር ወለድ ቅናሽ ማድረጉን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ በወጪ ንግድ መስክ ከተሰጡ ብድሮች በቀር በሁሉም የንግድ መስኮች ላይ ቅናሽ እንደተደረገ አስታውቀዋል፡፡

የብድር ቅናሹ የንግድ፣ የሕንፃና ኮንስትራክሽን፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ አስመጪዎች፣ በፕሮጀክት ደረጃ የሚገኙ ሆቴሎች፣ በትራንስፖርት፣ በማዕድን ኢነርጂና ውኃ ሥራዎች፣ በግብር እንዲሁም በሌሎች የግል ዘርፍ ለተሰማሩ የባንኩ ተበዳሪዎች እስከ ሦስት ወራት የሚቆይ የ0.5 በመቶ የወለድ ቅናሽ እንዲደረግ የባንኩ ቦርድና ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ እንደወሰነ ታውቋል፡፡ ባንኩ ባደረገው የወለድ ቅናሽ ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያጣ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡

ከወለድ ቅናሽ በተጨማሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚያስከፍላቸው የኮሚሽንና መሰል ክፍያዎች ላይም ለውጥ አድርጓል፡፡ ቀደም ሲል ለባንክ መተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ማራዘሚያ የሚያስከፍለውን ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ያነሳ ሲሆን፣ በቀጥታ ገንዘብ ክፍያ አማካይነት ዕቃ ለሚያስገቡ ደንበኞች ይከፈል የነበረውን የአገልግሎት ክፍያ ማራዘሚያም በ50 በመቶ ቀንሷል፡፡ የኤቲኤም አገልግሎት ክፍያን ነፃ ማደረጉ ተጠቅሷል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት እስከ 4.5 በመቶ የወለድ ቅናሽ አድርጎ የነበረው ባንኩ፣ ከግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ወራት የሚቆይ ቅናሽ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሦስት በመቶ ቅናሽ አድርጓል፡፡ የአትክልት፣ የአበባና ፍራፍሬ እርሻ ኢንቨስትመንቶችን በተመለከተም ባንኩ ከዘርፎቹ ማግኘት የሚገባውን ትርፍ በመተው የወለድ ተመኑ ላይ ቅናሽ በማድረግ በመደበኛ የተቀማጭ ገንዘብ ላይ በሚታሰብ የሰባት በመቶ ወለድ ብቻ እንዲከፍሉ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ንብ ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃርም ወረርሽኙ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል ለሚረገው ጥረት አምስት ሚሊዮን ብር ለብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ መለገሱንና ቫይረሱን በሚገባ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለመጨመር በአዲስ አበባ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች የጥንቃቄ መልዕክቶች እንዲተላለፍ ማድረጉንም የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቢሲኒያ ባንክም የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል፡፡ ባንኩ ባወጣው መግለጫ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚረዱ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያላቸው የእጅ ጓንቶች፣ የእጅ የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና ሳሙና በተለይም በቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑና በተለያዩ ምክንያቶች ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ ሆነው በጡረታ ላይ ለሚገኙ አረጋውያን ማበርከቱን ገልጿል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ወዲህ ለየት ባለ መልኩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ ይህንን የዓይነት ድጋፍ በሁሉም አካባቢዎች በሚገኙ 480 ቅርንጫፎች አማካይነት ለእነዚህ በጡረታ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲደርስ ማድረጉን ገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በ1.3 ሚሊዮን ብር በተመሳሳይ የተለያዩ የጥንቃቄ መሣሪያዎችንና ለምግብነት የሚውሉ እንደ ጤፍና የመሳሰሉትን በመግዛት ለሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በሁሉም አካባቢዎች የዓይነት ድጋፍ አድርያለሁ ብሏል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመቀነስ በሚደረገው ርብርብ የአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኞችም ከወርኃዊ ደመወዛቸው በማሰባሰብ በ1.7 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችንና የምግብ እህሎችን በመግዛት በቀጥታ የቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት፣ ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብለዋል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ ከዚህ አስከፊ ወቅት ይህንን የተጋረጠበትን ችግር ተሻግረን ብሩህ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ከባንካችን ዕሴትና ተልዕኮ አንፃር ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል፡፡

ባንኩ በቅርቡ በመላው ዓለምና በአገራችንም ጭምር የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ አስመልክቶ ኅብረተሰቡና የድርጅቱ ሠራተኞች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ይረዳ ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና እንዲሁም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ማስታወቂያዎቹን አሠርቶ እያስተላለፈ እንደሚገኝም የባንኩ መግለጫ ያመለክታል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችን መታየቱ በመንግሥት በይፋ ከተገለጸበት ጀምሮ ይህንንም ተከትሎ የብሔራዊ ሀብት አሰባሳቢ ከተቋቋመበት እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 16 ቀን 2020 ጀምሮ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት አስተማሪ የሆኑ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በተለያዩ የኅትመት ውጤቶች፣ በሬዲዮና በልዩ ልዩ ዘዴዎች የግንንዛቤ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ባንኩ መሪ ዕቅዱን ለመተግበር የዲስትሪክት ጽሕፈት ቤቶችን ቁጥር ከአምስት ወደ አሥር በማሳደግ መልካም አፈጻጸም በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡ ይኸውም ባንኩ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽነቱን በማስፋት በባንኪንግ ኢንዱስትሪው ውስጥ የገበያ ድርሻውን ለማሳደግ በሒሳብ ዓመቱ 140 ቅርንጫፎችን በመክፈት እ.ኤ.አ. እስከ ግንቦት 31 ቀን 2020 ድረስ አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 480 ከማድረሱም በተጨማሪ፣ አማራጭ የገበያ ማስፋፊያ ሥራዎችንም እየተገበረ ይገኛል ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች