በሐረጎት አብርሃ
በክፍል አንድ የሙስና ታሪካዊ ዳራ በኢትዮጵያ፣ በዓለም ደረጃ ሙስናን ለመታገል ያሉ የፀረ ሙስና ተቋማት ሞዴሎች ምን እንደሚመስሉ በዝርዝር ማየታችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ በፀረ ሙስና ትግሉ ውጤታማ የሆኑ አገሮች ልምድ፣ የትኛው አገሮች ልምድ ለእኛ አገር ተመራጭ እንደሆነ፣ አሁን በፀረ ሙስና ትግሉ ያሉት ችግሮችና መንግሥት በቀጣይ ሊወስዳቸው የሚገባ መፍትሔዎች ምን መሆን እንዳለባቸው የሚዳስስ ሲሆን በዚህ የማነሳቸው ጉዳዮች ተቋሙ ወክዬ ሳይሆን የግሌ ምልከታዎች መሆኑን በአፅንኦት እገልጻለሁኝ፡፡
የአውሮፓ አገሮች ልምድ
አውሮፓ የበለፀገ የገበያና የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ያላቸው አገሮችን የያዘ አህጉር ሲሆን፣ አገሮቹም ሙስና ለሥርዓታቸው አደጋ ወደ ማይሆንበት ደረጃ ያደረሱ ዜጎቻቸው ከሞላ ጎደል ግዴታቸውን በአግባቡ የሚወጡ፣ መብታቸውን አሳልፈው የማይሰጡ፣ ሙስናን ለመታገል የሚያስችል በአሰተሳሰብ የበለፀገ፣ ንቃተ ህሊናው ከፍተኛ ደረጀ የደረሰ ኅብረተሰብ ያላቸው ናቸው፡፡ ሙስና በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ኢኮኖሚያው ዕድገታቸውን በማስቀጠል የተረጋጋ አገርና ማኅበረሰብ መፍጠር ችለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ለየት ያለ አደረጃጀት መፍጠር ሳያስፈልጋቸው ለአንድ መቶ ዓመታትና ከዛ በላይ በገነቡት መደበኛ የሕግ ማስከበር ተቋሞቻቸው አማካይነት ሙስና በቁጥጥር ሥር ለማዋል አልተቸገሩም፡፡ የሕግ ማስከበር ተቋሞቻቸው አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ያላቸው ቁርጠኝነት፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርና ብቃት በእጅጉ ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በአውሮፓ ያሉ አገሮች በረጅም ጊዜ የገነቡት መደበኛ የምርመራና የክስ ሥርዓት አማካይነት የምርመራና ክስን ሥራዎች በመደበኛው ሥርዓታቸው ውስጥ አድርገው መምራታቸው እነሱ ከደረሱበት የዕድገት ደረጃና ካላቸው የቴክኖሎጂ አቅም አንፃር ሲታይ ተገቢ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ የአፍሪካ አገሮች መደበኛ የሕግ ማስከበር ተቋሞቻቸው ስንገመግማቸው አብዛኛዎቹ የአቅም ጉድለት ያለባቸው፣ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸው ገና ያላደገ፣ ሙስና ካለው ውስብስብ ባህሪ አንፃር ከሌሎች ወንጀሎች በተለየ መልኩ ትኩረት ሰጥተው ለመመርመርና ለመክሰስ የሚያስችል አመቺ ሁኔታና ጠንካራ መዋቅራዊ አደረጃጀት የሌላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም የአውሮፓ አገሮች ሶሻል አወቃቀራቸው ከታዳጊ አገሮች በእጅጉ የተለየ በመሆኑ የአውሮፓ አገሮች ሞዴል ወስደን በአገራችን ተግባራዊ እናደርግ ብንል አስቸጋሪ ሆኖ ይታየኛል፡፡ አገራችን የአውሮፓ አገሮች ሞዴል በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ ሰፊና ውስብሱብን የአገራችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሪፎርሞች ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡
የእስያ አገሮች ልምድ
የእስያ አገሮች ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ያሉ አገሮች ከመሆናቸውም በላይ በፀረ ሙስና ትግሉ ለሌሎች አገሮች ልምድ የሚሆን ውጤታማና መልካም የሆነ ተሞክሮዎች አሏቸው፡፡ በዚህ አፈጻጸማቸው ምክንያት ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ በሚያወጣው ሪፖርት ከቻይና በስተቀር አብዛኛዎቹ አገሮች የተሻለ ደረጃ ይዘው የሚወጡ ናቸው፡፡ ከእስያ አገሮች ውስጥ ሙስናን በመታገል ጠንካራ ልምድ ካላቸው ውስጥ ሲንጋፖርና ሆንግ ኮንግን በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሲንጋፖር በ2017 ከ183 አገሮች አምስተኛ ደረጃ፣ በ2018 ከ180 አገሮች ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ፣ እንዲሁም በ2019 ከ180 አገሮች አራተኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡ ሆንግ ኮንግ ደግሞ በ2017 ከ183 አገሮች 13ኛ ደረጃ፣ በ2018 ከ180 አገሮች 14ኛ ደረጃ እንዲሁም በ2019 ከ180 አገሮች 16ኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡
እነዚህ ሁለቱ አገሮች የፀረ ሙስና ትግሉን በማዕከል ሆኖ የሚመራ ተቋም ያላቸው ሲሆኑ ዋነኛ ትኩረታቸው መልካም ሥነ ምግባር መገንባትና የሰዎችን አስተሳሰብ መቀየርና በዚያው ልክ ተጠያቂነት በአንድ ላይ የሚያረጋግጥ ሁለገብ የሚባለውን የፀረ ሙስና ሞዴል የሚከተሉ ሲሆኑ፣ የማስተማርና የመከላከል የሕግ ማስከበር ሥራንም አንድ ላይ አጣምረው በፀረ ሙስና ትግሉ ለውጥ ያመጡ አገሮች ናቸው፡፡ ለፀረ ሙስና ትግሉ ከፍተኛ ሀብትና ምርጥ የተባሉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመመደብ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ሌት ተቀን ለውጤት ይሠራሉ፡፡ የሙስና ወንጀል የፈፀሙ ሰዎችን መርምረው ያለምንም ምሕረት ለሕግ አቅርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ያስደርጋሉ፡፡ የመንግሥት ሚና ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር በሚሠሯቸው ሥራዎች ላይ ጣልቃ አይገባም፡፡ በዚህ ምክንያት ሙስናን ሙሉ በሙሉ ያላጠፉ ቢሆንም የሰላምና የዕድገታቸው እንቅፋት ወደማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ችለዋል፡፡ ሙስናን መቆጣጠርና መከላከል በመቻላቸው ተከታታይነት ያለውን ኢኮኖሚያ ዕድገት ማምጣት ችሏል፡፡
አገራችን ለረዥም ጊዜ ስትከተለው የነበረው ኢኮኖሚያዊ ፓሊሲ ከእነዚህ አገሮች ጋር የተቀራረበ በመሆኑ፣ የፀረ ሙስና ትግሉ ሲጀምር በወቅቱ የነበረው የማኅበረሰብ አስተሳሰብ አሁን ካለው የአገራችን ነበራዊ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ፣ በድህነት አረንቋ ውስጥ በነበሩበት ወቅት የነበረቻቸውን አንጡራ ሀብት በሙስና እንዳይዘርፍ የወሰዱት ጥንቃቄና የዘረጉት የመከላከያ ሥርዓት፣ በአጠቃላይ ከድህነት ለመውጣት ሙስና መከላከል ከማንኛውም በላይ ቀዳሚ ሥራ መሆኑን ተገንዝበው በፀረ ሙስና ትግሉ ያመጡትን መሠረታዊ ለውጥ ለእኛ አገር በእጅጉ ትምህርት ሊሆን የሚችል በመሆኑ የመንግሥታችን ቁርጠኝነትና ድጋፍ ተጨምሮበት ይህን ሁለገብ የፀረ ሙስና ሞዴል በአገራችን ተግባራዊ ቢደረግ የሕግ የባለይነት በፅኑ መሠረት ላይ እንዲመሠረት እንደ ልምድ ሆኖ ለወሰድ የሚችል ነው፡፡
የአፍሪካ አገሮች ልምድ
የአፍሪካ አገሮች የሚከተሉት ሞዴል የተለያየ ቢሆንም የእስያ አገሮች ልምድ በብዛት የተጠቀሙ አገሮች እንዳሉ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ያስጠናው ጥናት ያሳያል፡፡ በተለይም የሆንግ ኮንግና ሲንጋፓር ልምድ እንደ ምርጥ ሞዴል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሆንግ ኮንግና ሲንጋፖር ሁለገብ ኃላፊነት ያለው አንድ ተቋም በማደራጀት ውጤታማ የሆኑ አገሮች ሲሆኑ የእነሱን ተከትሎ ከአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጥጣሞ በቁርጠኝነት የፈጸሙ የአፍሪካ አገሮች ጠንካራ ሆነው የሚወጥበት ሁኔታ አለ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ልምዱ ቢወስዱትም በአግባቡና በቁርጠኝነት ያልተገበሩ አገሮች ውጤታማ ሲሆኑ አይታዩም፡፡ ሆንግ ኮንግና ሲንጋፖር ጠንካራና ሁሉም ኃላፊነት የያዘ ተቋም ወደ ማደራጀት የገቡበት ታሪካዊ መነሻ ሲታይ በወቅቱ የነበሩት የሕግ ማስከበር ተቋሞቻቸው ለምሳሌ እንደ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት የመሳሰሉት የሙስና ችግር ለመፍታት የሚያስችል አቅምና ሙያዊ ሥነ ምግባር ያልነበራቸው በመሆኑ፣ ከዛ አለፍ ብሎ ተቋማቱ ራሳቸው በሙስና ተዘፍቀው የነበሩ፣ ኅብረተሰቡ ሙስናን በመታገል ረገድ የነበረው ሚና አነስተኛ የነበረ፣ የነበሩት ተቋማት የገለልተኝነትና የነፃነት ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩ፣ በአጠቃላይ ሙስናን በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ለመቆጣጠር የሚያስችል አጠቃላይ ጠንካራ መዋቅራዊ ሥርዓትና ተቋም ስላልነበራቸው ነው፡፡ በዚህ መሠረት ምርመራና ክስ ብቻ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ተቋሞቻቸው ከመሥራት ይልቅ የማስተማር፣ የመከላከልና የምርመራ ሥራዎች አንድ ላይ የያዘ ሁለገብ ሞዴል (Multi Purpose Agency Model) ላይ የተመሠረተ ተቋም ማቋቋም ነው የመረጡት፡፡ የአፍሪካ አገሮች ታሪካዊ ሁኔታ ሲታይም ከሆንግ ኮንግና ሲንጋፖር በወቅቱ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ የማይለይና ተመሳሳይ በመሆኑ ነው ይሄን ሞዴል የመረጡት፡፡ በነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሆንግ ኮንግና ሲንጋፖር ሞዴል መከተላቸው ትክክል ቢሆንም እንደ መሠረታዊ ችግር ሆኖ ያጋጠመው ሞዴሉን ሲወስዱ ከአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጥጥመው በቁርጠኝነት ተግባራዊ ማድረግ አለመቻላቸው ነው፡፡ ሞዴሉን ለመተግበር የመንግሥት ቁርጠኝነት በእጅጉ አስፈላጊ ቢሆንም የአፍሪካ መንግሥታት አብዛኛዎቹ ሙሰኞች በመሆናቸው ሞዴሉን በጥብቅ አልተገበሩትም፡፡ የሙስና ተፅዕኖን ተቋቁመው ሙስናን ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥ ያመጡት አገሮች ቦትስዋና እና ሩዋንዳ ናቸው፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መረጃ መሠረት ቦትስዋና በ2017 ከ183 አገሮች 34ኛ፣ በ2018 ከ180 አገሮች 34ኛ እንዲሁም በ2019 ከ180 አገሮች ለተከታታይ ጊዜ 34ኛ ደረጃ አገኝታለች፡፡ በአንፃሩ ሩዋንዳ በ2017 ከ183 አገሮች 48ኛ ደረጃ፣ በ2018 ከ180 አገሮች 48ኛ ደረጃ እንዲሁም በ2019 ከ180 አገሮች 51ኛ ደረጃ አገኝታለች፡፡
አገራችን ኢትዮጵያም እንደ ቦትስዋና “Multi Purpose Agency Model” ላይ የተመሠረተ ተቋም ከማደራጀት ይልቅ የሙስና መካላከልና የሕግ ማስከበር ሥራ በተለያዩ ተቋማት እንዲሠሩ በማድረግ የፀረ ሙስና ትግሉ የተበታተነ (Disarray) እንዲሆን ያደረገች ሲሆን፣ ሙስና በመከላከል ረገድ ዝቅተኛ ውጤት እንዳታመጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሎ ይታመናል፡፡ ትራንስፖረንሲ ኢትዮጵያ ከወጣው መረጃ በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው አገራችን በ2017 ከ183 አገሮች 107ኛ ደረጃ፣ በ2018 180 አገሮች 108ኛ እንዲሁም በ2019 ከ180 አገሮች 96ኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ ይህን የሚያሳየው ሙስና በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶባቸዋል ከሚባሉ አገሮች ተርታ ሊያሰልፋት ወደሚችል ደረጃ እያመራች ከመሆኑም በላይ ከአማካይ ደረጃ በታች በመሆኗ የፀረ ሙስና ትግላችን አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በጣም አስገራሚ የሚያደርገው ቦትስዋና እና ሩዋንዳ ቀደም ሲል ከ2007 ዓ.ም በፊት አገራችን ስትከተል የነበረውን ሞዴል ልምድ ለመውሰድ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩ ሲሆኑ በወሰዱት ልምድ መሠረት አገራቸውን ፈጣን በሚባል ደረጃ ቀይረዋል፡፡ በአንፃሩ አገራችን የነበረውን አደረጃጀት ማስቀጠል አቅቷት የተሻለ ለውጥ ማምጣት አልቻለችም፡፡
ሊወሰድ የሚገባው መልካም ልምድ
ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው አገሮች ልምድ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ውጤታማ የሙስና መከላከል ሥራ ሊሠሩ የቻሉት ከእኛ የተለየ ጥብቅ የፀረ ሙስና ሕግና ተቋም ስላላቸው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሕዝባቸውና መንግሥታቸው ሙስና ጎጅ መሆኑን ከልብ ተቀብለው ሙስና በተደራጀ መልኩ ለመዋጋት ዜጎቻቸው መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው እንዲሆኑ ሁሉንም አማራጮቻቸውን ተጠቅመው ሌት ተቀን ሰለ ሠሩ ነው፡፡ ለዚህም የትምህርት ተቋማት፣ ሚዲያ፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ መደበኛ ያልሆኑ የማስተማሪያ ዜዴዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ይህ በማድረጋቸው ሕዝባቸው ሠርቶ መበልፀግን ብቻ አማራጭና ባህል እንዲያደርግ ከማድረጋቸውም በላይ የሙስና ትግሉ ባለቤትና ዋናው ተዋናይ ሕዝቡ እንዲሆን ለማድረግ ችለዋል፡፡ ከአውሮፓ ውጭ ያሉት አገሮች ሙስናን በመታገል የሚታወቁና ትርጉም ባለው ደረጃ መቀነስ የቻሉት መልካም ሥነ ምግባር ከመገንባትና ሙስናን ከመከላከል ጎን ለጎን ሙስና የሚፈጽሙና በሙስና ለመክበር የሚፈልጉ ኃይሎች ሲያጋጥሟቸው ነፃ የሆነ የምርመራና ክስ ሥርዓት በአንድ ማዕቀፍ አደራጅተው ለሕግ ማቅረብ በመቻላቸውና ይህን በግንባር ቀደምትነት የሚመራ ተቋም በማቋቋማቸው ነው፡፡ ሙስናን በተለየ ሁኔታ የሚመርምርና የሚከስ የተለየ አደረጃጀት የፈጠሩበት ምክንያት ምርመራ የፖሊስ፣ ክስ ደግሞ የዓቃቤ ሕግ ተፈጥሮዊ ሥራ መሆኑን ዘንግተውት ወይም በአገር ደረጃ አንድ የወንጀል ሕግና ፖሊሲ እንደምያስፈልግ ጠፍቶባቸው ሳይሆን ሙስና የሚፈጸምበት ሥልት፣ ባህሪው፣ ውስብስብነቱና ፍጥነቱ እንዲሁም እነዚህ ተቋማት ራሳቸው በአገልግሎትና ፍትህ አሰጣጥ ላይ ችግር ያላባቸው በመሆኑ ሙስና በመደበኛው የምርመራና የክስ ሥርዓት ለመቆጣጠር እንደማይችሉ በመገንዘባቸው ነው፡፡ የሙስና አደጋ ለመቀነስ ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ የተላቀቀ፣ በተቻለ መጠን የቁጥጥር (Check and Balance) ሥርዓት ለማምጣት ተጠሪነቱ ለሕግ አውጭው የሆነ፣ ደፍሮ በነፃነት የሚታገል፣ የተሟላ የምርመራ ወይም ክስ ሥልጣን ተሰጥቶት የሚሠራ የፀረ ሙስና አደረጃት መፍጠር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን በማመናቸው ጭምር ነው፡፡
በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የአውሮፓ አገሮች ልምድ ወስዶ ተግባራዊ እናድርግ ብንል መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ስለማንችል ተስማሚው ልምድ ሊሆን የሚችለው በፀረ ሙስና ትግሉ ሙስናን የመከላከል፣ የመርመርና የመክሰስ ሥርዓት ላይ አጣምሮ የያዘው የአፍሪካ ወይም የእስያ አገሮች ልምድ ሊሆን ይገባል፡፡ እንደ ምሳሌ ከወሰደንም የሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቦትስዋና ወይም ሩዋንዳ የፀረ ሙስና ተቋማት ልምድ መዳሰስ ብቻ በቂ ነው፡፡ የአፍሪካና የእስያ የፀረ ሙስና ትግል ልምድ የምንወስደው ምንም ችግር የሌለበት ሆኖ ሳይሆን ቢያንስ ከእኛ አገር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር የተቀራረበ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሌሎች ልምዶች በተሻለ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ሙስናን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሞዴል በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
የፀረ ሙስና ትግል ዋና ዋና ችግሮች
በአሁኑ ሰዓት የአገራችን የፀረ ሙስና ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀዘቀዘ፣ የነበረንን ደረጃ እየቀነሰ በአንፃሩ ሙስና በአገራችን የሚያደርሰው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ዘርፈ ብዙ ችግር እየወለደ የመጣ ስለመሆኑ ምንም ሳይንሳዊ ምርምርና ጥናት ሳይስፈልገው በገሀድ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ችግር መፈጠር አያሌ ምክንያቶች ቢኖሩም አንዱና ትልቁ ችግር ግን ሙስና በአገር ደረጃ ለመካለከልና ለመዋጋት የተሳሳተ የፀረ ሙስና ተቋማት አደረጃጀት ሞዴል በመከተላችን ነው፡፡ አገራችን እየተከተለች ያለችው ሞዴል የመከላከልና የሕግ ማስከበር ሥራዎች በተበጣጠሰና በተለያየ ተቋማት እንዲሠሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ሞዴሉ የተመረጠው ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚገባ ተተንትኖ የተመረጠ ሳይሆን መንግሥት በራሴ አሠራር ሙስናን እታገላለሁ ብሎ የወሰደው የተሳሳተ ውሳኔ ነው ብዬ አስባለሁኝ ፡፡
ከመሠረቱ የአገራችን የፀረ ሙስና ትግል የፀረ ሙስና ተቋማት አደረጃጀት ሞዴል ከመምረጥ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉት ነው፡፡ ሙስናን መዋጋት የመንግሥታት ቁርጠኝነት፣ ድጋፍና እገዛ በተሟላ ሁኔታ የማይገኝበት የሥራ ዘርፍ ነው ብዬ ባስቀምጠው ማጋነን አይሆንም፡፡ እስካሁን የነበሩ መንግሥታት ወደ ሥልጣን ሲወጡ ሙስና ለመታገል ሲምሉ ሲገዝቱ ብንሰማቸውም፣ እንታገላለን ለማለት የፀረ ሙስና ተቋማት ለይስሙላ ቢያቋቁሙም በተግባር ግን የተሟላ ድጋፍ የማይሰጡ መሠረታዊ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ እንደአጋጣሚ የተቋቋሙትን የፀረ ሙስና ተቋማት ጥርስ ለማውጣት በሚጥሩበት ወቅት በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት በመኮርኮም የፀረ ሙስና ትግሉ ጉልበት እንዳይኖረው ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተሰጥተውት የነበሩትን የምርመራና የክስ ሥራ ኃላፊነቶች እንዲቀነሱ የተደረጉት ኮሚሽኑ የተሰጠው ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣቱ ወይም ሌላ መሠረታዊ ችግር ኖሮበት ሳይሆን የመንግሥት ቁርጠኝነት መንሸራተት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኮሚሽኑ የፀረ ሙስና ትግሉን ዳር ማድረስ የተቸገረበት፣ ተገቢውን አቅም አጥቶ “ጥርስ የሌለው አንበሳ” እንዲባል ሆኗል፡፡ ቀደም ሲል ክስና ምርመራ በኮሚሽኑ ሥር በነበሩበት ጊዜ ሊያድጉ የሚገባቸው መልካም ጅምሮችና ውጤቶች ቢኖሩትም ተቋሙ ሙስናን በመከላከል ረገድ የተሳካ ሥራ ሠርቶ ውጤታማ ሆኗል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ መሠረታዊ የሆኑ አገራዊ ቁልፍ ምክንያቶች ያሉ ቢሆንም ኮሚሽኑ በተመረጡ ከባድ የሙስና ወንጀሎች ላይ ብቻ ላይ ባለማትኮሩ፣ ሁሉንም የሙስና ወንጀል መመርመር አለብኝ በሚል የተለጠጠ ዕቅድ ምክንያት የተደራሽነትና የአቅም ችግር አጋጠሞት እንደነበር የሚካድ አይደለም፡፡ መንግሥት የራሱ አደረጃጀት የመወሰን ሙሉ ሥልጣን ያለው መሆኑን ባምንም፣ እነዚህ ጉድለቶች በራሳቸው ክፍተት መሆናቸው ሀቅ ቢሆንም በምንም ተአምር ግን የአደረጃጀት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ በቂና መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው ብሎ መውሰድ እቸገራለሁኝ፡፡ መንግሥት ኮሚሽኑ ከዚህ የተለየ ችግር ነበረበት ብሎ የሚያምን ከሆነ ደግሞ በጥናት በማስደገፍ መፍታት ሲገባ የተሰጡትን ማንዴቶች አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ለማንሳት የወሰደው ዕርምጃ የፀረ ሙስና ትግሉን ወደ ኋላ የመለሰ፣ መንግሥትና አገር ይበልጥ የተጎዱበት እንጂ ያመጣው ለውጥ የለም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ኮሚሽኑ ሰፋፊ የሕግ ማሻሻያዎች በፓርላማ በማፀደቅ ወደ ተግባር በገባበት ጊዜ ዓመት ሳይሞላ የኮሚሽኑ ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰዱ የሄደበት ምክንያት ፖለቲካዊ ጥቅም ያስቀደመ ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ መንግሥት ከፀረ ሙስና ትግሉ ለማፈግፈግ የወሰደው ዕርምጃ ነው ብዬ አስባለሁኝ፡፡
መንግሥት የወሰደውን ያልተጠና የአደረጃጀት በአገራችን የፀረ ሙስና ትግል ላይ አዳዲስ ችግሮች ይዞ የመጣ ሲሆን በኮሚሽኑ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡ መንግሥት ተገቢውን ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ በአደረጃጀቱ ለውጥ ምክንያት በኮሚሸኑ ዋና ዋና ተልዕኮዎች ላይ እየተፈጠሩ ያሉትን ችግሮች እንደሚከተለው አቀርባቸዋለሁኝ፡፡
በግንዛቤና በሥልጠና ሥራ ላይ የተፈጠሩ ክፍተቶች
ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባራት አንዱ በመልካም ሥነ ምግባር የተገነባ፣ ሙስናን የሚጠየፍና የሚዋጋ የኅብረተሰብ ለመፍጠር በተለያዩ ዘዴዎች ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በህትመት ሚዲያ፣ ኤሌክትሮኒኪስ ሚዲያ፣ በፊት ለፊት ትምህርትና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የኮሚሸኑ የሕግ ማስከበር ሥራ ለፌዴራል ፖሊስና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከመሰጠቱ ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ትምህርትና ግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይልቅ ለሕግ ማስከበር ትኩረት እየሰጠ መጥተዋል፡፡ በዚህም የኮሚሽኑ የመካለከል ሥራዎች አሳንሶ የማየት አዝማምያ እየተንፀባረቀ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ምርመራና ክስ በኮሚሽኑ በነበረበት ጊዜ የጽንሰ ሐሳቡ ትምህርት ምርጥ ምርመራና ክስ ሥራዎች (ኬዞች) ታግዞ ሲሰጥ የነበረ ቢሆንም ሥራው ለሌላ ተቋም ሲሰጥ ይኼን ማድረግ ስላልተቻለ በትምህርቱ ሳቢነቱና ተዳማጭነት ላይ የራሱ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡ ለሥልጠና የሚጠሩ አካላት ለሚሰጠው ሥልጠና እምብዛም ትኩረት አለመስጠት፣ ከዛ አልፎ በተገቢ ሁኔታ አለመሳተፍ፣ የተሳትፉትም በሥልጠናው ይዘት ይልቅ በኮሚሽኑ አደረጃጀትና ሥልጣን ላይ አታካሮ በመግባት በትምህርቱ አሰጣጥ ላይ ጫና የሚፈጥሩበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ጫና ምክንያት በሙያው ከፍተኛ ልምድ የነበራቸው ባለሙያዎች እንዲለቁ ጫና ፈጥሯል፡፡ ኮሚሽኑ ድጋፍ አደርጎላቸው የተደራጁ የኅብረተሰብ አካላትም ኮሚሽኑ አሁን ባለው ውስን ኃላፊነት ሙስና በመታገል ሊያግዘን ሰለማይችል ወደ ታች ወርደን ለመሥራት እንቸገራለን የሚል ግልጽ ምላሸ በመስጠት አደረጃጀቶቹ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
ለማሳያ ያክል ከ2001 ጀምሮ እስከ 2007 በሙያ፣ በፆታና በብዙኃን ማኅበራት ተደራጅተው የነበሩትን 16 የፀረ ሙስና አደረጃጀቶች (ወደ 920 ማኅበራትና አደረጃጀቶች) ሲሆኑ ከ2007 በኋላ ግን ወደ ስድስት የፀረ ሙስና አደረጃጀቶች( ከ70 ማኅበራት ያልበለጡ) ሆነዋል፡፡ ይህ የሚያሰየው ሕዝቡ ለኮሚሽኑ ሲሰጠው የነበረውን ድጋፍና እገዛ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነሱ ያሳያል፡፡ እንዲያውም ኮሚሽኑ “ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው”፡፡ ኮሚሽኑ አሁን ባለው ቁመና ከሃይማኖት ተቋማት በምን ይለያል፣ ሙስናን መመርመርና መክሰስ ከማይችል ተቋም በጋራ መሥራት ትርፉ ድካም ነው የሚል አሰተሳሰብ ጭምር በስፋት እየተንፀባረቀ መጥቷል፡፡ በሚዲያ የፀረ ሙስና ትምህርት በቅናሽ ዋጋ በማስተላለፍ ለረዥም ጊዜ ሲያግዙን የነበሩ የሚዲያ ተቋማት በአሁን ሰዓት ለማገዝ ዳተኛ እየሆኑ መጥቷል፡፡ እነዚህ ችግሮች ካልተፈቱ በሒደት ለመንገነባት ያሰብነው ማኅበረሰብ፣ አገርና እሴት እውን እንዳይሆን የማድረግ ኃይላቸው ቀላል አይደለም፡፡
በሙስና መከላከል ሥራዎች ላይ የተፈጠሩ ክፍተቶች
ኮሚሸኑ በአዋጅ ከተሰጡትዋና ዋና ተልእኮዎች ውስጥ በመንግሥት መሠሪያ ቤቶች፣ የልማትና ሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ የቅድመ የሙስና መከላከል ሥራዎች መሥራት ሲሆን ይኼን ተግባራዊ ለማድረግ ለሙስናና ብልሹ አሠራር ክፍተት የሚፈጥሩ አሠራሮች የአሠራር ሥርዓት ጥናት ማካሄድ፣ በጨረታና ግዥ አሠራሮች ላይ አስቸኳይ የሙስና መካላከል ሥራዎች መሥራት፣ ተቋማት በራሳቸው አግባብ ሙስና የሚከላከሉበት የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ እንድያዘጋጁ ማድረግ፣ በእነዚህ ዘዴዎች የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችና የተገኙ ግኝቶች ተግባራዊ መሆናቸውን መከታተል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ላለፉት ዓመታት በትላልቅ ፕሮጀክቶች ጨምሮ የተለያዩ የሙስና መከላኪያ ጥናቶች ሲጠኑና ተግባራዊ ሲደረጉ የነበረ ቢሆንም ከ2008 ጀምሮ ግን የምርመራና ክስ ሥራዎች መውጣታቸው ተከትሎ የተጠኑ ጥናቶችና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመው ይገኛል፡፡ ተቋማት የተጠኑ ጥናቶች፣ የተሰጣቸውን ምክረ ሐሳብ ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ ያለመሆንና ኮሚሽኑ ይህን የሚያስገድድበት አቅም ስለሌለው ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተጠኑ ጥናቶች በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ሳይደረጉ ሸልፍ ላይ እንዲቀመጡ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በኮሚሽኑና በተቋማት መካከል ያለው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራዎች ተፈጻሚነት በተመሳሳይ ሁኔታ አተገባበሩ ላይ የተቋማት ፍቃደኝነት የሚጎድልበት ሁኔታ አለ፡፡
ለማሳያ ያህል ከ2004 እስከ 2011 ዓ.ም ደረስ ለመፈም የታቀዱ የአሠራር ሥርዓት ጥናቶች 579 የነበሩ ሲሆን 421 ወይ የዕቅዱ 72.7 በመቶ ለማከናወን የተቻለ ቢሆንም የአደረጃጀት ለውጡን ተከትሎ እነዚህን ጥናቶች ተጠኝ ተቋማት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ሁኔታ ባለመኖሩ ተፈጻሚነታቸው የሚጠበቀውን ያህል ሆኖ ሙስናን በሚፈለገው ደረጃ ለመከላለከል አልቻሉም፡፡
በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሥራዎች ላይ የተፈጠሩ ክፍተቶች
በተመሳሳይ ሁኔታ ኮሚሽኑ ከተሰጡት ትልቅ ኃላፊነቶች አንዱ የተመራጮች፣ ተሿሚዎችና የመንግሥት ሠራተኛ ሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ሥራ ሲሆን ይሄን ሥራ ካለፉት ዓመታት ጨምሮ ብዙ የተለየ ለውጥ ባይኖርም በተሿሚዎች አካባቢ ያለው የማስመዝገብ ሁኔታ ግን በራሱ ክፍተት ያለበት ነው፡፡ የምርመራና የክስ ሥራዎች ከኮሚሽኑ ከተነሳ ጀምሮ ሀብታቸው ያስመዘገቡ ሆነ ያሳደሱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቁጥር ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ያሉ አመራሮች ሀብት ለማስመዝገብ ሆነ በአዋጁ መሠረት ጊዜው ጠብቆ ለማሳደስ ያላቸው ፍላጎት፣ ትብብርና አርአያነት እየቀነሰ መጥተዋል፡፡ ይኼን የኃላፊነት መጓደል ሲከሰት ኮሚሸኑ ተጠያቂነት የምያረጋግጥበት አቅም የሌለው በመሆኑ የባለሥልጣናት የሀብት ምዝገባ አፈጻጸም በሚፈለገው ደረጃ አልሄደም፡፡ አሁን ያለው አፈጻጸም ከበፊቱ ሲወዳደር በእጅጉ የቀነሰ ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ምናልባትም የኮሚሸኑ ማንዴት ከተሻሻለና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ለካቢኔ አባሎቻቸው አቅጣጫ ከሰጡበት በቅርብ ጊዜ የሚሻሻልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡
በተቋማት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ላይ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ
ኮሚሽኑ ሌላ በአዋጁ ከተሰጡት ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ማደራጀት፣ ማብቃትና ድጋፍ መሰጠት ነው፡፡ የመከታተያ ክፍሎቹ ዋና ዓላማ ደግሞ በየተቋሙ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዙሪያ የበላይ ኃላፊ የሚያማክሩ ሲሆኑ ሥራቸው በቀጥታ ከሙስና መካላከል፣ ምርመራና ክስ የሚያገናኛቸው ነው፡፡ ኮሚሽኑ የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥራ በነበረበት ጊዜያት ሥነ ምግባር መኮነኖች ከኮሚሽኑ የነበራቸው ትብብርና ቅንጅት የተጠናከረ ሲሆን የመከላከል፣ የምርመራና የክስ ሥራዎች በአንድ ማዕከል (ከኮሚሽኑ) የሚያገኙበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ሦስት ተቋማት በመሄድ ጉዳያችው ለማስፈጸም የሚገደዱበት ሁኔታ ስላለ ለአላስፈላጊ ምልልስና እንግልት እየተጋለጡ ይገኛል፡፡ ይሄ አልበቃ ብሎ ከሚሠሩበት ተቋም የበላይ ኃላፊ ያገኙት የነበረውን ድጋፍና ተቀባይነት በእጅጉ ቀንሰዋል፡፡ ጂኤጂ የሚባል የመንግሥት አደረጃጀት ከመጣ ወዲህ ብዙ የሥነ ምግባር መኮነኖች የቂም በቀል ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ የሥራ ክፍላቸው አላግባብ እንዲታጠፍ፣ እንዲባረሩ ወይም ከነበሩበት ደረጀ ዝቅ እንዲሉ ዕድል ተደርገዋል፡፡ ይኼን የተፈጠረበት አግባብ ደግሞ ኮሚሽኑ በቂ ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችለው ሥልጣንና ኃላፊነት ስለሌለው ነው፡፡ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ በዚህ በአገር ደረጃ ከ15 ሺሕ ያላነሱ የሥነ ምግባር መኮንኖች ያሉ ሲሆን በዚህ ዓመት ብቻ በፌዴራል ተቋማት ብቻ 169 የሚሆኑ የሥነ ምግባር መኮንኖች በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁ፣ ወደ ሌላ ሥራ የቀየሩ ወይም በጫና ምክንያት የሥራ ለውጥ ያደረጉ ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 144/2000 የተቋቋሙት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በአስቸኳይ ተገቢ ጥበቃ ከመንግሥት ካልተደረገላቸው እንደ አገር በተቋማት የምናደርገው ሙስናን የመከላከል ሥራ መና የሚያስቀር ነው፡፡
ከተለያዩ አካላት ጋር ያለው የቅንጅታዊ አሠራር ችግር
ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገራችን የፀረ ሙስና ትግሉ ሥራ በኃላፊነት እንዲያስተባብሩ የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት ሦስት ናቸው፡፡ እነዚህም የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ናቸው፡፡ በእነዚህ አካላት መካከል ጠንካራና ተከታታይነት ያለው መረጃ የመለዋወጥ፣ የመደጋገፍ፣ በፀረ ሙስና ትግሉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት ተቀናጅቶና ተናቦ በመሄድና አንደ አገር አንድ ጠንካራ የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ እንዲፈጠር በማድረግ በኩል ሰፊ ከፍተቶች ታይቶበታል፡፡ በእነዚህ ተቋማት አለመቀናጀት በተገልጋዮች በተለይ በጠቋሚዎችና ሥነ ምግባር መከተታያ ክፍሎች የሚቀርቡ የአገልገሎት አሰጣጥ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ እንደመጡ ይስተዋላል፡፡
በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. አካባቢ የተወሰነ የጋራ መድረክ በመፍጠር የቅንጅት ሥራዎች ለመገምገምና አቅጣጫ ለመስጠት ጥረት የተደረገ ቢሆንም ግምገማው ከተቋረጠ ሁለት ዓመት አልፎታል ማለት ይቻላል፡፡ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ተቋማቱ በጋራ ሊሠሯቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በመለየት የጋራ መግባባት ስምምነት ሰነድ ተፈራርመው ወደ ሥራ ለመግባት ጅምር እንቅስቃሴ የነበረ ቢሆንም የተፈለገው ለውጥ መጥቷል ተብሎ አይወሰድም፡፡ የፀረ ሙስና አደረጃጀቱን የተበታተነ መሆኑን ሳያንሰው በእነዚህ ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራርና የትብብር መንፈስ አለመጠናከሩ በፀረ ሙስና ትግሉ ትልቅ ዋጋ እንዳያስከፍለን ከወዲሁ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
የኮሚሸኑ የሰው ሀብት አስተዳደር ላይ የተፈጠረው ተፅዕኖ
ኮሚሸኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን የሰው ኃይል ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ ያለበት ቢሆንም የሰው ኃይሉ ጥራት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አዳዲስ ሠራተኞች በመቅጠርና በማሠልጠን ነባርና የተሻለ እውቀት የነበረውን ባለሙያ ለመተካት ጥረት የተደረገ ቢሆንም ቀደም ሲል ተሰጥቶት የነበረውን የተሻለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ባለመቀጠሉ ልምድ የነበረው የሰው ኃይል ማቆየት አልተቻለም፡፡ በተለይም የነበረው ማንዴት መነሳቱ በሠራተኛ ዘንድ አግባብ አይደለም የሚል ቅሬታ በመፍጠሩ ከፍተኛ ዕውቀትና ልምድ የነበራቸው ሠራተኞች ለቀዋል፡፡
የፀረ ሙስና ተቋማት በሕዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ከተፈለገ ከመንግሥት የተሻለ ትኩረት የሚሹ፣ ተገቢውን ጥቅማ ጥቅም እንዲሁም ምቹ የሠራ ሁኔታ ተመቻችቶላቸው ሊሠሩ እንደሚገባ ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ኮንቬንሸን ይመክራል፡፡ ሆኖም ግን በእኛ አገር ያለው ሁኔታ ሲታይ ሙስናን ከሚታገል ሠራተኛ ይልቅ ሬሳ የሚገንዝ ባለሙያ የተሻለ ጥቅማ ጥቅም ያለው፣ አገር ውስጥ ነው ያለነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በፀረ ሙስና ትግሉ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች በአግባቡ እንድንጠቀምባቸው ከተፈለገ አሁን የሚታየው ፍልሰት ለመቀነስ የሚያስችሉ መፍትሔዎች መፈለግ ያስፈልጋል፡፡
የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጠናከር ሊወሰዱ የሚገባቸው ዕርምጃዎች
ሙስና በአገራችን ሊፈጥር የሚችለዉን የከፋ ጉዳት ለመከላከል ውጤታማ የሆነ ሥርዓትና አደረጃጀት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይሄን አደረጃጀት ለመፍጠር ደግሞ መንግሥት ከላይ የተነሱትን ችግሮች ሊፈታ በሚችል መልኩ የፀረ ሙስና ትግሉ ጠንካራና ደካማ ጎን መፈተሽ ማስተካከል የሚያስፈልገውን አደረጃጀት ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሠረት መንግሥት አሁን ያለውን የኮሮና ወረርሽኝና የፓለቲካ ችግር ሰከን ሲል ከላይ ያነሳናቸውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ልምዶችና በአደረጃጀት ለውጥ ምክንያት የተከሰቱ ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት የአገራችን የፀረ ሙስና ትግል ወደፊት የሚወሰድ በጠንካራ አለት ላይ የተገነባ የፀረ ሙስና ትግል እንዲኖር የሚከተሉት ሦስት መሠረታዊ ዕርምጃዎች በአፋጣኝ መውሰድ አለበት ብዬ አስባለሁኝ፡፡
የፀረ ሙስና ተቋማትን አደረጃጃት ማስተካከል
አንደኛና ወሳኝ ብዬ የማስቀምጠው አሁን ያለውን የፌዴራልና የክልል የፀረ ሙስና ኮሚሽን አደረጃጀቶች አሁን ባለው ቁመናና ኃላፊነት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸም ያስችላቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አሁን ያለው አደረጃጃት ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ኮንቬንሽኖች መርሆዎችና ምክረ ሐሳቦች አንፃር ተቃኝቶ ጠንካራ፣ ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነትና ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው የሚሠሩ፣ ያሉትን የፀረ ሙስና አደረጃጀቶች ጠንካራና ደካማ ጎን በመፈተሽ ወደ አንድ የሚመጡበት አግባብ ለማየት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጭምር ተወያይቶበት ለአገራችን አለኝታና በሙሰኞች የሚፈራ የፀረ መስና ተቋም መገንባት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ የምንገነባው ተቋም አሁን እንዳለው ሳይሆን በፌዴራልና በክልል ደረጃ የሙስና መካለከል፣ የመመርመርና የመክሰስ ሥራዎች አንድ ላይ አቀናጅቶ የሚመራና አሁን የተበታተነውን የፀረ ሙስና ትግል የሚያስቀር አደረጃጀት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ይሄን ተግባራዊ ለማድረግ በፌዴራል ደረጃ ኮሚሽኑ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በአዋጅ ሲቋቋም በአዋጅ ቁጥር 235/1993፣ በአዋጅ ቁጥር 433/1997 እንደገና በማሻሻያ በአዋጅ ቁጥር 883/2007 ተሰጥተውት የነበሩት የምርመራና የክስ ሥራዎች እንዲመለሱለትና ተቋሙ እንደ አዲስ ተጠናክሮ እንዲወጣ ለፀረ ሙስና ትግሉ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል፣ የፋሲሊቲና በቂ የበጀት ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በዚህ ጉዳይ ላይ ወሳኝ ውሳኔ ያስተላልፋሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር እንዲጠናከር ድጋፍ መስጠት
ሙስና የመካለከልና የመዋጋት ሥራ የአንድ ተቋም ኃላፊነትና ተግባር ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ትብብር ይጠይቃል፡፡ አሁን ላለው የፀረ ሙስና ትግል መዳከም አስተዋጽኦ አንዱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በተናበበ መንፈስ አለመሥራታቸው ነው፡፡ በመሆኑም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ የፌዴራልና የክልል የፓርላማ ተቋማት፣ ፍርድ ቤቶች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ ጠቅላይ ኦዲተር፣ የሚዲያና የደኅነነት ተቋማት በጋራ የሚመክሩበትና አቅጣጫ የሚሰጡበት ሥርዓት መፈጠር የግድ የምንልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ በተለይም መንግሥት ሙስና የመካላከል የመርመርና የመክሰስ ሥራዎች በአንድ ተቋም ሆኖ የሚሠራበት አግባብ ለማየት ፍላጎት የሚያጥረው ከሆነ፣ የመጨረሻ አማራጭ የባለድርሻ አካላት ጨምሮ ሦስቱም ተቋማት ማለትም የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ፌዴራል ፖሊስና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጋራ ተናበውና ተቀናጅተው ካለፈው በተሻለ ሁኔታ ሊሠሩበት የሚችሉበት ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ከምንጊዜም በላይ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን ማጠናከር
በፀረ ሙስና ትግሉ የሕዝብና የፀረ ሙስና ተቋማት ሚና ትልቅ ቢሆንም የመንግሥታት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ ድጋፍና እገዛ ከሌለው ግን የትም መድረስ አይችልም፡፡ ተጀምሮ የነበረውን የፀረ ሙስና ትግል በሒደት የተኮላሸው የመንግሥታት ድጋፍና እገዛ በሚፈለገው ደረጃ ያልነበረ በመሆኑ ነው፡፡ ይኼ ችግር በሁሉም አገሮች ያለ ቢሆንም በአገራችን ግን በእጅጉ ገዝፎ እናገኘዋለን፡፡ ለአብነት ማንሳት ቢቻል እንኳ በስኳር፣ መብራትና ማዳበሪያ ፕሮጀክቶች ላይ የተፈጠረው ምዝበራና የሀብት ብክነት መነሻው መንግሥት ጠንካራ አመራር ባለመስጠቱና ተጠያቂነት ባለማረጋገጡ ነው፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የመንግሥት ኃላፊዎች ወደ ሙስና ሲገቡ ያለ ምሕረት ተጠያቂነት የሚያረጋገጥ ሥርዓት ከወዲሁ መፍጠር፣ ሁሉም የመንግሥት ግዢዎች ሕጎች ብቻ ተከትለው እንዲከናወኑ፣ ሙስና ለመዋጋት የተቋቋሙ የፌዴራልና የክልል የፀረ ሙስና ተቋማት በሚገባ ማጠናከር የመንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና መፍትሔ የሚሹ አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸውና መንግሥት ሳይውል ሳያድር ለእነዚህ ጉዳዮች ትኩረት ይስጥ እላለሁኝ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር አውታሮች ማስተባበርያ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡