Saturday, June 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በዓለም ዕውቅናና ክብር ያላቸውን የመከሩንን ሳይንቲስት ለማሸማቀቅ መሞከር አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ነው

በሻምበል ገብረመድኅን ቢረጋ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ አስተያየት ዓምድ መኮንን ተሾመ ቶሌራ የተሰኙ ግለሰብ፣ “የሳይንቲስቱ ሳይንሳዊ ያልሆነ ሙግት” በሚል ርዕስ የጻፉት ሐተታና ትችት ነው፡፡ ጸሐፊው የሥራ ኃላፊነታቸውን፣ የትምህርት ዝግጅታቸውንና ልምዳቸውን በተመለከተ እንደ ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) የነገሩን ነገር ስለሌለ ምላሼን እንደሚገባው ማዘጋጀት ባለመቻሌና ምናልባት የሚያበሳጭ ሐሳብ ተነስቶ እንደሆነ አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ የምላሼ ዋናው ዓላማ ለአገር በሚበጅ የጋራ ጉዳይ ላይ አተኩረን ለአንድ አገራችንና ለሕዝባችን ይበጃሉ የምንላቸውን ሐሳቦች በማቅረብ የላቀ ጠቀሜታና ዘላቂነት ያለውን ሐሳብ ሕዝቡ እንዲመርጥ አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው፡፡

የጽሑፉን ዝርዝር ለተመለከተ ሰው ጸሐፊው ዶ/ር ተወልደ ብርሃንን መተቸት ሳይሆን ያነሷቸውን ነጥቦች ትክክለኝነት የሚያረጋግጡ ሐሳቦችን እዚህም እዚያም በማንሳት፣ የተነገረውን ሸምድዶ ፍርድ ቤት የቀረበ ምስክር የተነገረው ሲጠፋበት እውነታውን በአስጠኝው ላይ እንደሚመሰክር የሚመስሉ ሐሳቦችን መገንዘብ ይችላል፡፡ ይህ የሚያሳየው ጉዳዩን በአግባቡ ሳይረዱት ከኮንፈረንስ ዕውቀት ተነስተው በቅርባቸው ያሉትን አለቆች ለማስደሰት ወይም የተሻለ ደረጃ ዕድገት ለማግኘት መጣደፍን ነው፡፡ ምንም እንኳን ጸሐፊው ያነሱዋቸው ነጥቦች ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ካነሷቸው ነጥቦች አንፃር ትኩረት የሚሰጣቸውና ምላሽ ካልተሰጣቸው ጉዳት የሚያስከትሉ ባይሆንም፣ ዝም ማለቱ ደግሞ እንደ ጸሐፊው ዓይነት ሳያስተውሉ ለሚነሱ የወደፊት ተችዎች ትምህርት እንዲሆን የሚከተሉትን ነጥቦች አነሳለሁ፡፡

ለአካባቢ መሟገት፣ ዘላቂ የአኗኗር ዘይቤ በመከተል ያሁኑን ትውልድ ፍላጎት እያሟሉ በመጭው ትውልድ ዕጣ ፈንታ መቆረቆርን በተግባር ለማሳየት፣ ሳይንሳዊ ምርምር አድርገው፣ ተግዳሮቶችን በመለየት፣ በባለድርሻ አካላት ግንዛቤና ይሁንታ ላይ የተመሠረተ፣ ማኅበረሰብ አሳታፊ የሆነ ፕሮጀክት ነድፈው እንዲተገበር በማድረግ ተጨባጭ፣ በማኅበረሰቡ ንቁ ተሳትፎና ባለቤትነት የሚካሄድ፣ ችግር ፈቺና አማራጭ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ትግራይ ፕሮጀክት በተሰኘው ፕሮጀክት ለተደረገው ጥረትና ለተገኘው ውጤት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተሰጠውን ዕውቅናና ሽልማት በዓለም አቀፉ መረጃ መረብ አድራሻ https://www.ethioembassy.org.uk/tigray-project-wins-gold-for-land-restoration መመልከት ይቻላል፡፡

ፕሮጀክቱን ከመንደፍ ጀምሮ ክትትል በማድረግና አመራርን በመስጠት የዶ/ር ተወልደ ብርሃን ድርሻ አቻ የሌለው መሆኑን የሚጠራጠር ካለ https://www.oaklandinstitute.org/sites/oaklandinstitute.org/files/Low_Input_Agriculture_Ethiopia.pdf የዓለም አቀፉን መረጃ መረብ አድራሻ በመመልከት ግንዛቤ እንዲወስዱ እንመክራለን፡፡ ማወቅ ለሚፈልግ ሰው ስለ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ብዙ ማለት ቢቻልም፣ ጸሐፊው አያውቁም ተብሎ ስለማይገመት በዚህ ማቆሙን መረጥኩ፡፡

ከላይ በጥቂቱ የተመለከትኩትንና ሌሎች በርካታ የአካባቢና ብዝኃ ሕይወት ጥበቃና ዘላቂ አጠቃቀም ጥናትና ምርምር ማካሄድ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማመላከት፣ ተግባራዊ ፕሮጀክቶችን በማስተግበርና ምርጥ ተመክሮ ተቀምሮ ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ከአገር አልፈው ዓለም አቀፍ ተምሳሌት የሆኑትን ዕውቅ ልሂቅ፣ ከመስመር የወጣ አሠራር ወደ መስመር እንዲመለስ ሙያዊና አባታዊ ምክር ስለሰጡንና ለአገር የሚጠቅም ሐሳብ ስላነሱ ብቻ ማብጠልጠልና ያነሱት ጉዳይ ወንጀል መስሏቸው ለሚታያቸውና ለማያስተውሉ የሚገባቸውን መንገርና በሚገባቸው ቋንቋ ትምህርት እንዲሆን ስል ይህንን ምላሽ ለመስጠት ተገድጃለሁ፡፡

ዶ/ር ተወልደ ብርሃን አሁን ከሚገኙበት ዕድሜና ከአገራቸው አልፈው ለመላው አፍሪካ ብሎም ለሌሎች ታዳጊ አገሮች በሙሉ ዋና ተደራዳሪ ሆነው አንዳንድ ጊዜ ረዥም ሰዓት ከስብሰባ አዳራሽ ሳይወጡና ምግብና እንቅልፍ ሳያምራቸው የሀብታም አገሮች ድርድር ሥልት ሰለባ ላለመሆን ከተወጡት ኃላፊነትና ከከፈሉት መስዋዕትነት አኳያ ከፍተኛ ክብርና ሽልማት በተገባቸው ነበር፡፡ ለነገሩ “ነብይ በአገሩ አይከበርም” እንዲሉ እንደ ጸሐፊው ዓይነት ክብር የሚገባውንና የማይገባውን የማይለዩ፣ ሳያውቁ አውቃለሁ ባይ ስለካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል ዓላማ ለዶ/ር ተወልደ ብርሃን ለማስተማር መሞከርን “ልጅ ለእናቷ. . .” እንደተባለው ብቻ አድርጎ ከመውሰድ ሌላ ምን ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ያነሱት ዋና ጉዳይ ብዙ የተለፋበት በተለይም በሚያሚ ቡድን ተፅዕኖ ምክንያት ከፍተኛ ውጣ ውረድ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅድመ ጥንቃቄ መርሆዎችን (Precautionary Principles) መሠረት አድርጎ እንዲተገበር የተዘጋጀው የካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል ነው፡፡ ይህ የዋናው ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ስምምነት አካል በመሆኑ ኢትዮጵያ ልውጠ ህያዋንን ለማምረትና ለመጠቀም የምትፈልግ ከሆነ፣ ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወር፣ ሲከማችና ጥናትና ምርምር ሲደረግ ከልውጠ ህያው ዕፀዋት ወይም እንስሳት የሚነሱ ያልተጠበቁና አዳዲስ ውጤቶች በአካባቢ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ በጥብቅ ቁጥጥርና ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎባቸው በተወሰነ (ጠበብ ባለ) እና በተከለለ ቦታ ሙከራ ተደርጎ የሚገኘው ውጤት በሰውና እንስሳት ጤናና ሕይወት እንዲሁም በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ በሰፊ ቦታ እንዲመረትና ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስገድድ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የተሟላ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠንቅ ግምገማ (Risk Assessment) ተደርጎ የታወቀ የጠንቅ አስተዳደር ሥርዓት (Risk Management System) እንዲኖር እንደሚያስገድድ ማስረዳታቸው ፕሮቶኮሉን ካረቀቁት አንዱና ዋናው በመሆናቸው “ማን ይናገር የነበረ. . .” አባባል በጉዳዩ ላይ ተግባራዊ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ስለዚህ ጸሐፊው “. . .የእሳቸውን ሳይንቲስትነት የሚመጥንና በሳይንሳዊ አመክንዮ የተደገፈ ሳይሆን፣ በአብዛኛው ሕይወታቸውን ያሳለፉበትን የአካባቢ ጥበቃ ፍላጎት መገለጫና ሳይንሳዊ ያልሆነ ሙግት ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ሲሉ ዶ/ር ተወልደ ብርሃንን መኮነናቸው ከጸሐፊው የመረዳትና የመተንተን ውስንነት የመነጨ ነው፡፡ “ሳይንሳዊ” ማለት የተፈጥሮ ሳይንስ ብቻ ሳይሆን፣ እሱም ማኅበረሰብ፣ አገርና ዓለምን ጭምር ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ማድረግ እንዴት እንደሚቻል ያሳዩትን ችግር ፈቺ ሳይንቲስትና ጸሐፊው እንዳሉት ያሁኑ ቆርጦ ቀጥል (Copy Paste) ትምህርት በእነ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ከተማሩበት ዘመን በተለየና በፈጠነ መልኩ እየዘመነ መጥቷል በሚል የማያዋጣ ክርክር ውስጥ ካልተገባ በስተቀር፣ እሳቸው በተግባር የተፈተነ ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ሣይንስ ዘርፍ በተለይም በዓለም አቀፍ ሕግ ዘርፍ ሳይንሳዊነት ሲተነተን አንድ አገር አባል የሆነበትንና ግዴታ ውስጥ የገባበትን ዓለም አቀፍ ስምምነት ደስ ባለው ጊዜ መጣስ የማይችል መሆኑ “The Principles of State Responsibility” በሚለው የዓለም አቀፍ አካባቢያዊ ሕግ  International Environmental Law ውስጥ በሰፊው የተዘረዘረና ጥሰት ከተፈጸመ የአባል አገሮች መንግሥታት ተጠያቂነት እንዳለባቸው “States are Accountable for Breaches of International Law” ተብሎ የተገለጸ መሆኑን ዶ/ር ተወልደ ብርሃን በጥልቀት ስለሚያውቁ፣ የካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል ከተጣሰ ዓለም አቀፍ ተጠያቂነትን ስለሚያስከትል ይህ ከመሆኑ በፊት ባለባቸው ሙያዊ ኃላፊነት የሚመለከተው፣ የመንግሥት አካል የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ ማሳሰባቸውን ጸሐፊው የተረዱት አይመስልም፡፡

ሌላው ጸሐፊው ያነሱትና ትክክል ያልሆነው ጉዳይ “. . .የግብርና ምርትን ለማዘመንና ለማሻሻል የባዮቴክኖሎጂ በተለይም ዘረመል ምህንድስና (Genetic Engineering) በተወሰነ መልኩ ለምሳሌ በጥጥ ምርት ላይ በጥንቃቄና የደኅንነተ ሕይወት መርህ በመከተል የጀመረችው እንቅስቃሴ ብዝኃ ሕይወትን ለመጠበቅ የተፈጸመውን የካርታኼና የደህንነተ ሕይወት ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮል ስምምነት የሚጥስ ነው የሚል ነው” በማለት ያቀረቡት መከራከሪያ ነው፡፡

የዶ/ር ተወልደ ብርሃን ሥጋት ጸሐፊው እንዳሉት በጥንቃቄና የደኅንነተ ሕይወት መርህ በመከተል የሚደረግ የልውጠ ህያው ቢቲ ጥጥ ሙከራ ወይም አመራረት ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ገና የካርታኼና የደኅንነተ ሕይወት ዓለም አቀፍ ፕሮቶክል ስምምነት ሲረቀቅ ጀምሮ የፕሮቶኮሉ አባል የሆነ አገር አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ሁኔታዎች ካሟላ ልውጠ ህያው ምርት ውጤቶችን ማምረት፣ ማበልፀግ፣ ለገበያ ማቅረብና ከቦታ ወደ ቦታ ማጓጓዝ እንደሚችል ከማንም በላይ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ሲያሳውቁንም ቆይተዋል፡፡

የሥጋታቸው ዋና ምንጭ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰፊው የሚነገረው ልውጠ ህያዋንን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የሚደረገው ሩጫና 130 ሺሕ ሔክታር የተከለለ ቦታ በማድረግ የሚደረጉት የአዋጭነት ጥናቶች የካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮልን መሠረት ተደርጎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 655/2001 እና የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 896/2007 እንዲሁም አዋጆቹን ለማስፈጸም በወጣው የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 411/2009፣ ተያያዥ መመርያዎች መሠረት ስለመሆኑ የሚታወቅ ሁኔታ ባለመኖሩ ነው፡፡

እኛም ሥጋታቸውን የምንጋራው ሲሆን፣ የደኅንነተ ሕይወት አዋጅ ቁጥር 655/2ዐዐ1 ማሻሻል ካስፈለገ በቅድሚያ ነባሩ አዋጅ በተግባር ላይ ውሎ ተግዳሮቶች ተለይተው የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በተለይም የአርሶ አደሮችና ሸማቹ ማኅበረሰብ ይሁንታ እንዲጠየቅ ያደረግነው ጥረት ወደ ጎን ተትቶ ለወትዋቾች (Lobbyists) በሚመች መልኩ በችኮላ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ የተሻሻለው አዋጅ በዓለም አቀፉ የካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮልና በማንኛውም አገር የደኅንነተ ሕይወት ሕግ ማዕቀፎች (Biosafety Framewoks) ዓላማዎች ውስጥ ተካትቶ የማያውቀውንና መካተት የሌለበትን ዘመናዊ ጥበበ ሕይወትን ጨምሮ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃና ዘላቂ አጠቃቀም የሚያገለግል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትንና በቴክኖሎጂ ዝውውር መጠቀምን ማሻሻል የሚል ዓላማ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች አገሮች ደኅንነተ ሕይወት ሕጎች በተለየ ሁኔታ ለአምስት ዓመት የሚፀና ልዩ ፈቃድ አንቀፅ 6 ሆኖ በተሻሻለው አዋጅ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ በጠንቅ ግምገማና አስተዳደር (Risk Assessment and Management) ላይ የሚያተኩረው የደኅንነተ ሕይወት (Biosafety) ጥላ እንዲያጠላበትና በአንፃሩ ምርምሩና ሥርፀቱ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው እየተደረገ ነው፡፡

ይህንን የተሻሻለውን አዋጅ በመጠቀም ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን ጥጥ አቅርቦት ለማሻሻል በሚል በተለያዩና ለጊዜው በውል ባልታወቁ የአገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ስድስት ቦታዎች ልውጠ ህያው ወይም ቢቲ ጥጥ በተከለለ ቦታ ሙከራ (Confined Field Trial) ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የሙከራው ሒደትና ውጤት እስከምናውቀው ድረስ ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም፡፡ ሌላው ቀርቶ በራሳችን ጊዜ ለመከታተልና ለማጣራት እንድንችል ሙከራ የሚደረግባቸው ስድስት ቦታዎች እንዲገለጽልን በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘታችን ምን እየተሠራ እንደነበረ ማወቅ አልቻልንም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቢቲ ጥጡ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በተለይ ጥጥ ፍሬው ለምግብ ዘይት ግብዓትና ለከብት መኖ ፋጉሎ ሊውል ስለሚችልና በዚህም የተነሳ በሰውና እንስሳት ጤና እንዲሁም በብዝኃ ሕይወትና አካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ተገምግሞ እንዲለይና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሊደርስ የሚችል ጉዳት አለመኖሩን ወይም ቢኖርም ወደ ኢምንታዊነት (Insignificant) ደረጃ ዝቅ ለማድረግ የሚወሰደውን ዕርምጃ በተለመለከተ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የተሰጠ ማረጋገጫ የለም፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ International Service for the Acquisition of Agri-Biotech Application: ISAAA በተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ድረገፅ (web site) http://www.isaaa.org/kc/cropbiotechupdate/article/default. asp?ID=16515 ሰኔ 29 ቀን 21ዐ ወይም ጁን 6 ቀን 2ዐ18 Ethiopia Approves Environmental Release of Bt Cotton and Grants Special Permit for GM Maize በሚል ርዕስ ኢትዮዮጵያ JKCH1050 እና JKCH1947 የተሰኙ ሁለት ልውጠ ሕያው ቢቲ ጥጥ ዝርያዎች እንዲመረቱና ልውጠ ህያው በቆሎ ምርምር እንዲካሄድበት የፈቀደች መሆኗን ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ ሪፖርተር ጋዜጣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቅዳሜ ሰኔ 2 ቀን 210 ዓ.ም. ወይም ጁን 9 ቀን 218 ዕትም “GMO Cotton Approved for Plantations” በሚል ርዕስ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚንስቴር የተባለውን ፈቃድ በትክክል የሰጠ መሆኑን የሚንስቴሩን ደኅንነተ ሕይወት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ጉዲና ዋቢ በማድረግ ዘግቧል፡፡

ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት የተጣለበት የፌዴራል አካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን (Environment Forest and Climate Change Commission of FDRE) በየካቲት ወር 2011 .ም. “A Biosafety Framework of Ethiopia: Review of existing legal obligations, mandate overlap and gap analysis, and recommendations for an improved framework” በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው ጥናት ውስጥ “As of 2018, the Environment Forest and Climate Change Commission, as competent authority and as the main regulator involved in biosafety, has given two advanced informed agreements for the environmental release of Bt Cotton after two full seasons of confined field trials.”[1] Moreover, “A special permit has been given for research to begin into GM maize.” .. 2018 ጀምሮ ልውጠ ህያው ቢቲ ጥጥ በይፋ እንዲመረት ሁለት የቅድመ ግንዛቤ ፈቃድ መስጠቱንና ለበቆሎ ሙከራ ልዬ ፈቃድ የተሰጠ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ ጸሐፊው ልውጠ ህያው ቢቲ ጥጥ ማምረት የተጀመረው ዶ/ር ተወልደ ብርሃን የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን ሲመሩ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ለማስመሰል ያቀረቡት መከራከሪያ ከአሥር ዓመት በፊት ከኃላፊነታቸው የተነሱትን ሰው የማይመለከታቸው መሆኑን ተገንዝበው በይፋ ይቅርታ ሊጠይቋቸው ይገባል፡፡   

የአሜሪካ መንግሥት የግብርና መሥሪያ ቤት የውጭ አገሮች ግብርና አገልግሎት ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ወይም እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 5 ቀን 2020 “Agricultural Biotechnology Annual” የግብርና ጥበበ ሕይወት ዓመታዊ ግምገማ ሪፖርት በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው ዘገባ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ቢቲ ጥጥ ለገበያ እንዲመረት፣ በቆሎና እንሰት ልውጠ ህያው ለማድረግ በተከለሉ ቦታዎች ሙከራ እንደደረግባቸው መስማማቱን በይፋ አረጋግጧል፡፡ ይህ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተገለጸው አባባል ቃል በቃል ሲነበብ ከዚህ እንደሚተለው ነው፡፡

The Ethiopian government, from the Prime Minister’s office on down, has publicly showed their interests in commercializing agricultural biotechnology as a tool to achieve food security in the country. In 2018, the country officially approved its first biotechnology crop (Bacillus thuringiensis) Btcotton for commercialization and Confined Field Trail (CFT) on drought tolerant and pest resistant WEMA -TELA Maize. Other crops such as enset (False Banana) which is also at the CFT level where Ethiopian researchers collaborate with the International Institute of Tropical Agriculture (IITA). This project uses genetic engineering to develop varieties of enset that are resistant to the devastating bacterial wilt disease.”

የዶ/ር ተወልደ ብርሃንም ሆነ የኛ ጥያቄ ለምን ፈቃድ ተሰጠ ሳይሆን፣ ፈቃዱ ከመሰጠቱ በፊት መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄ ዕርምጃዎችና ዝግጅቶች ስለመደረጋቸው ኅብረተሰቡ ያወቀው ነገር ስለሌለ ይህ ለምን ሆነ? ነው፡፡

በኛ በኩል ሊደረጉ ከሚገባቸው ቅደመ ጥንቃቄ ዝግጅቶችና ዕርምጃዎች አንዱ የጉዳት ተጠያቂነትንና ካሳን በተመለከተ የካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል አንቀፅ 27 መሠረት ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት አስተዋጽኦ ያደረገችበትና ምሳሌ ሆና ለዓመታት እልህ አስጨራሽ ድርድር ሲደረግበት የቆየው NAGOYA – KUALA LUMPUR SUPPLEMENTARY PROTOCOL ON LIABILITY AND REDRESS TO THE CARTGENA PROTOCOL ON BIOSAFETY የሚለው የካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል አጋዥ ዓለም አቀፍ ስምምነት መስከረም 22 ቀን 2003 .ም. ወይም ... ኦክቶበር 2 ቀን 2010 ድርድሩ ተጠናቆ መፈረሙ የሚታወቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህንን ፕሮቶኮል ማፅደቅና የሕግ አካል ማድረግ በተለይ ከልውጠ ህያዋን በሰውና እንስሳት ጤና ላይ የሚደርስ ጉዳት ሲኖር ተጠያቂነትን ለማስፈንና ካሳ ለማስከፈል እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ የአገሪቱ ሕግ አካል እንዲሆን ስንወተውት የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በኩል ምንም ተጨባጭ ዕርምጃ ሳይወሰድ ከቆየ በኋላ ... ማርች 5 ቀን 2018 ወይም የካቲት 28/2010 .ም. ኢትዮጵያን ሳይጨምር 41 አገሮችን ድጋፍ አግኝቶ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ይህንን ፕሮቶኮል የአገሪቱ ሕግ ሳያደርጉ ማንኛውንም ዓይነት ልውጠ ህያው ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ሆነ በአገር ውስጥ ማምረት የካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮልን መጣስ ነው የሚል ጠንካራ አቋም አለን፡፡

ከዚህም ሌላ የደንነተ ሕይወት አዋጅ ቁጥር 655/2ዐዐ1 ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ያልተደረገ በመሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 11 መሠረት የሕዝብ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ሲባል የጠንቅ ግምገማ እንደደረሰውና ከግንዛቤ የመነጨ ስምምነት ለማግኘት ማመልከቻ ሲቀርብ በሕዝብ ማስታወቂያ አውታሮች በኩል ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሕዝብ አስተያየት ተሰብስቦ እንደ ግብዓት ተጠቅሞ መወሰን እንደሚገባ ተደንግጎ እያለ፣ ይህ ስለመደረጉ ምንም የሰማነው ወይም የተጠየቅነው ነገር ስላልነበረ ተገቢ አይደለም እንላለን፡፡ ተጠይቀን ቢሆን ኖሮ ልውጠ ሕያው ቢቲ ጥጥ ማምረት ጀምረው ብዙ ተጠቃሚ ሆነዋል የተባሉት ለምሳሌ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካና ቡርኪናፋሶ እንዴት አርሶ አደሮቻቸውና ሥነ ምኅዳሮቻቸው እንዲሁም ከብቶቻቸው እንደተጎዱና በተለይ የቡርኪናፋሶ መንግሥት ምንም ዓይነት የቢቲ ጥጥ እንዳይመረት የክልከላ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንዳስቆመ፣ ፈቃድ ጠያቂዎቹም ሆነ ፈቃድ ሰጪ የመንግሥት አካላት በተጨባጭ የሚያውቁት ሀቅ ቢሆንም ተጨማሪ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብና ማስረዳት እንችል ነበር፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው እንዳሉት በሕግ መሠረት እየተሠራ ነው ካሉ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ጥሰቶች ምን ሊሉቸው ነው? ወይስ እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም ሊሉ ነው?

ሌላው ሥጋታችንን የሚያጎላው ጸሐፊው “ዘርፉ ዘረ መሎችን ከአንድ ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ ለማሸጋገር አስችሏል፡፡ የዘረመል ምህንድስና የህያዋንን ባህሪ ስለሚነካካ የሕይወትን መሠረት ሊለውጥ ይችላል፡፡ ይህም የባህሪ ለውጥ መሻሻልም ወደ መጥፋትም ሊያመራ ይችላል፤” ሲሉ ያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን አባባል ሁሉም ሰው እንደሚረዳው መተርጎም ካስፈለገ በተለምዶ የምናውቀው የዕፅዋትን ወይም እንስሳትን ምርት ውጤት ወይም በሽታ መቋቋም ባህርይ ማሻሻል ካስፈለገ ዕፅዋትን ከዕፅዋት፣ እንስሳትን ከእንስሳት ጋር ብቻ በማዳቀል ይሠራ የነበረ ሲሆን፣ የዘረ መል ምህንድስና ሥራ ከተጀመረ ወዲህ ግን የተባይና ባክቴሪያ ዘረ መል ወደ ዕፅዋት ዝሪያ፣ የእንስሳትን ዘረ መል ወደ ዕፅዋት ዝሪያ በተቃራኒ ማሸጋገር የተቻለ በመሆኑ የሰው ልጆች በሃይማኖታቸው ወይም በባህላቸው መሠረት መመገብ የማይፈልጉትን ምግቦች ሳያውቋቸው እንዲመገቡ ይደረጋል ማለት ነው፡፡

ለምሳሌ በዘረ መል ምህንድስና የተለወጠ በቆሎን ስንመገብ በውስጡ የባክቴሪያ፣ የተባይ ወይም የእንስሳት ዘረ መል መኖሩን ሳናውቅ በቆሎ ነው ተብለን እንመገባለን ማለት ነው፡፡ ይህ አዲስና የተለወጠ በቆሎ በውስጡ ከወትሮው የተለየ ባህሪና ይዘት ስላለው ካሁን በፊት የማይታወቁትን የጤና ችግሮች ሊያስከትል እንደሚችል የተጠራጠሩ ባለሙያዎች በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በፈረንሣይ፣ በህንድ፣ በፊሊፕንስና በጀርመን  ለረዥም ጊዜ በአይጦች ላይ ባደረጉት ሙከራ ያገኙት ውጤት እ... 2007 The Documented Health Risks of  Genetically Engineered Foods” በሚል ርዕስ በአሜሪካ አገር ታተመው ሐፍ ውስጥ በሰፊው የተዘረዘረ ሲሆን፣ በመሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቂቶቹ የሞት አደጋ ማስከተል፣ የአንጀት መታወክና የተለያዩ የሆድ ሕመም፣ የተለያየ አለርጂን፣ የአተነፋፈስ ችግር፣ የቆዳ በሽታ፣ መሀንነት፣ የጣፊያና ዘር አካል ጉዳት፣ የዘረ መል አወቃቀር መለዋወጥ፣ በጣም ቀጫጫ መሆን፣ ከወትሮ የተለየ የቁጡነት ባህሪ ማሳየት፣ የኩላሊት ሕመም፣ ለካንሰርና ሌሎች በሽታዎች ማጋለጥ፣ የሕፃናት አለርጂና የጉሮሮ ሕመም ወይም ቶንሲል እንደሚያባብስ፣ rb-GH የተሰኘውን ሆርሞን የተወጉ ላሞችን ወተት መመገብ መንታ መውለድን እንደሚያባብስና የመሳሰሉትን መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ስለዚህ ጸሐፊው እንዳሉት የዘረ መል ምህንድስና ወደ ባህሪ ለውጥ መሻሻልም ወደ መጥፋትም ሊያመራ መቻሉና ውጤቱ ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳት ማስከተል መቻሉን መሠረት በማድረግ ለዜጎቻቸው ሕይወትና ጤንነት፣ ለአካባቢና ለብዝኃ ሕይወት ቅድሚያ የሚሰጡ በርካታ የአውሮ አገሮችና አንዳንድ የአሪካ አገሮች ለምሳሌ ኡጋንዳ፣ ቡርናፋሶ፣ ዚምባብዌ፣ ዛምቢያና አገራችን ኢትዮጵያም ልውጠ ህያዋንን ያለመቀበል አቋም ይዘው የቆዩ ሲሆን፣ አገራችን ኢትዮጵያ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዚህ አቋሟ መለሳለስ ማሳየቷ አሳሳቢ ነው ብንል ጸሐፊው ሳያውቁት የኛን ሥጋት ተጋርተዋል ማለት ይቻላል፡፡ የዘረ መል ምህንድስና የባህሪ ለውጥ ወደ መጥፋትም ሊያመራ የሚችል መሆኑ እየታወቀ በተለይ ከ20 ሚሊዮን በላይ የደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዝቦች በተለይም የጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሐዲያ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ አላባ፣ ሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ካፋ፣ ሸካና ሌሎች ብሔሮች፣ ሔርሰቦችና ዝቦች ማንነት ማረጋጫ፣ የምግብ ዋስትና ረት፣ የማኅበራዊ ደረጃ መለኪያና ባህላቸው የሆነውን እንሰት ያለ ማኅበረሰቡ ዕውቅናና ይሁንታ ልውጠ ህያው ለማድረግ የሚደረገው ሩጫ እንሰት ላይ አይሠራም ካልተባለ በስተቀር እንዴት ሊታሰብ ይችላል፡፡ ጸሐፊውም በሳይንሳዊ አመክንዮ የሚያምኑ ከሆነ ሥጋታችንን ይጋራሉ ብለን እንገምታለን፡፡ ስለሆነ ኃላፊነት የሚሰማ ሁሉ አይሆንም ማለትና ሩጫውን ማስቆም ይገባል፡፡

እስካሁን ድረስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከተከሰቱትና አሁንም በመከሰት ላይ ከሚገኙት የተለያዩ ጠንቆች አንፃር ልውጠ ህያው ዘር ወይም ምርት ወይም የምርት ውጤት ወደ አገር ውስጥ ከመግባቱ ወይም ከመመረቱ በፊት የጠንቅ ግምገማ ማድረግና ችግር ቢከሰት ተጠያቂነትን የሚወስድ አካል እንዲኖር የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ፣ ሰፊው ማኅበረሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከሚከተለው የሕዝብን ጥያቄ መሠረት አድርጎ ከመሥራት ፍላጎት አንፃር ተገቢና ወቅታዊ በመሆኑ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ ደጋግመን ለመወትወት ተገደናል፡፡

በነገራችን ጸሐፊውና ሌሎች በተደጋጋሚ ሲያነሱት የሚሰማው ከልውጠ ህያዋን ጋር በተያያዘ ሥጋታችንን ስናሰማ ባዮቴክኖሎጂን በጥቅሉ እንደምንቃወም ተደርጎ የሚነሳው ሐሳብ ነው፡፡ ይህ ከእውነታ የራቀ መሆኑን አንባቢያን እንዲረዱት እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም ባዮቴክኖሎጂ እጅግ ሰፊ፣ ከጥንት ጀምሮ በቅደመ አያቶቻችን ሳይቀር ሲሠራበት የነበረ መሆኑን፣ በውስጡም ከዚህ በታች እንደተመለከተው በርካታ የዕድገት ደረጃዎች ያሉት መሆኑን እኛም እንደምንረዳ ጸሐፊውና መሰሎቻቸው ተረድተው ከአጉል ማደናገር እንዲታቀቡ ምክራችንን እንለግሳለን፡፡

በዓለም ዕውቅናና ክብር ያላቸውን የመከሩንን ሳይንቲስት ለማሸማቀቅ መሞከር አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ነው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሥጋታችን በዘመናዊ ባዮቴክኖሎጂ ምድብ ውስጥ ካሉት በተለይም ዘረ መል ምህንድስናን በሚመለከቱት ላይ ነው፡፡ ለነገሩ ማንኛውም ሳይንስ በሳይንስነቱ በደፈናው አይጠላም፣ አይኮነንም፡፡ ነገር ግን የሣይንሱ ትኩረት አቅጣጫ፣ የምርምር ሂደቱ ግልፅነትና የመረጃ ተደራሽነት፣ የግኝቱ ባለቤትና የሚቆጣጠረው አካል፣ ግኝቱ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ በማኅበረሰብ፣ በአካባቢና በብዝኃ ሕይወት ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ፣ በግኝቱ የሕዝቡ ተጠቃሚነት፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት፣ ዋና ዋና ተዋናዮች፣ ተሳታፊ ተቋማት፣ የአሠራሩ መዋቅር፣ የእርስ በርስ መስተጋብር ሲተነተን ከሒደቱና ውጤቱ ማን ምን አገኘ፣ ማን በምን ተጎዳ የሚለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ትንተና የሳይንሱን ጠቃሚነት ወይም ጎጂነት ስለሚያሳይ የሕዝብ ፍላጎትና ብሔራዊ ቅጥምን መሠረት በማድረግ ይፈረጃል፡፡

ስለዚህ የዶ/ር ተወልደ ብርሃንም ሆነ የኛ የሌሎች የአካባቢ፣ የሸማቾች፣ የአርሶ አደሮችና የአርብቶ አደሮች መብቶች ተሟጋቾች ዘረ መል ምህንድስናንና ልውጠ ህያዋንን በተመለከተ የምናነሳው ዋና ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ የሚሠራው ማንኛውም ሥራ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት እንዲሆንና የብዙኃኑ ኅብረተሰብ ጥቅም፣ የአካባቢና ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ቅድሚያ እንዲሰጠው ነው፡፡

ከዚህ ውጭ ግልጽነት፣ አሳታፊነትና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ በርግጥም ኢትዮጵያ በይፋ ከካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል መውጣቷን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሳታሳውቅ ሆን ተብሎ ፕሮቶኮሉ ወደ ጎን ተትቶ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን እንደጣሰች ስለሚቆጠርና ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና የፕሮቶኮሉ አባል በሆኑ ዓለም አገሮች ውስጥ ፕሮቶኮሉ እንዲጣስ በር የሚከፍት መጥፎ ምሳሌ በመሆኑ፣ የካርታኼና ደኅንነተ ሕይወት ፕሮቶኮል እንዲከበር የኢትዮጵያ ወጣቶች በሚችሉት መንገድ ሁሉ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ አርዓያችንና አስተማሪያችን ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ያቀረቡትን ጥሪ እኛም እንደግፋለን፣ እናስተጋባለን፡፡ ምክንያቱም አካባቢና ብዝኃ ሕይወት ከአያቶቻችን የወረስነው ሳይሆን ከልጆቻችን፣ ከልጅ ልጆቻችንና ከዚያም በኋላ ተከታትለው ከሚመጡት ትውልድ በአደራ በውሰት ያገኘነውና በኃላፊነት ስሜት ዘላቂነትን በማይጎዳ ሁኔታ ለመጠቀም ብቻ የተፈቀደልን ስለሆነ ነው፡፡ የኛ ዓላማ ጸሐፊው እንዳሉት አገርን ለመጉዳት ሳይሆን ከምንምና ከማንም ጥቅም በላይ የአገርና ትውልድ ጥቅም እንዲቀድም ነው፡፡ ይልቁንስ ሕግ ከሚፈቅደው ውጭ የአጭር ጊዜ ጥቅም ለጥቂቶች ለማስገኘት በሕዝቡ ፍላጎትና በብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚካሄደው ቁማር ጨዋታና ስህተቱ እንዲታረም ገንቢ ሐሳብ ያቀረቡትን የተከበሩና ተቆርቋሪ ሳይንቲስት ለማሸማቀቅ የሚደረገው ጥረት አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ስለሆነ ጸሐፊውም ሆነ ሌሎች ልብ ሊሉ ይገባል እንላለን፡፡  

ለወደፊቱም ቢሆን ልውጠ ህያዋንን በተመለከተ ስለሚተላለፉ ውሳኔዎች ሁሉ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ሸማቾች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ አስፈ አካላትና መላው የኢትዮጵያ ዝብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙ ሁሉ የየበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ጸሐፊውና መሰሎቻቸው አመለካከታቸውን አስተካክለው ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ፣ በቸልተኝነትና በማን አለብኝነት በችኮላ በኢትዮጵያ ልውጠ ህያዋን እንዲስፋፋ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ምክንያት በአካባቢና ብዝኃ ሕይወት ላይ ሊደርስ የሚችለውን አላስፈላጊ ጉዳት፣በአርሶ አደሮች፣ በአርብቶ አደሮችና በሸማቾች ሕይወትና ጤና ላይ ሊደርስ የሚችለውን አላስፈላጊ የመብት ጥሰትና ጉዳት ለማስቀረት ከጎናችን በመቆም እንዲታገሉ አገራዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበር ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]/ [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles