የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዓርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከአረንጓዴ አሻራ ብሔራዊ አስተባባሪ ቡድን አባላት ጋር በመሆን በሐዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ ላይ ችግኞችን በመትከል በይፋ አስጀምረዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፣ የ2012 ዛፍ ተከላ መርሐ ግብር ከዓለም የአካባቢ ቀን ጋር በቅርርብ የሚካሄድ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወትን ለማስጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ዕድገትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ዝናባማ ወቅት በአንድ በኩል ኮቪድ-19ን በመከላከል በሌላ በኩል ደግሞ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ ዝግጅት መደረጉንም ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡ ኮቪድ-19ን በጥብቅ በመከላከል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የ2012 ችግኝ ተከላን በንቃት እንዲሳተፍም ብሔራዊ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ፎቶዎቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፌደራልና ከክልል መንግሥታት ከፍተኛ ሹማምንት እንዲሁም ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ችግኝ ሲተክሉ ያሳያሉ፡፡
ፎቶ፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት