በየካ ተራራ ላይ ለሪል ስቴት በተሰጠው 40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ምክንያት እንዲነሱ በየካ ክፍለ ከተማ ጫና የተደረገባቸው 17 ባለይዞታዎች፣ በአስተዳደሩ ግፊት እየተደረገባቸው እንደሚገኙና ቅሬታቸውም ሰሚ ማጣቱን ገለጹ፡፡
ለወራት ቅሬታቸውን ሲያስተጋቡ የከረሙት እነዚህ ነዋሪዎች፣ በአሁኑ ወቅት ከይዞታቸው ከመነሳት በቀር አማራጭ እንደሌላቸው እንደነተገራቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለሪል ስቴት በተሰጠው ቦታ አቅራቢያ ሕጋዊ ይዞታ ተሰጥቷቸውና በክፍለ ከተማው ዕውቅና አግኝተው፣ የመኖሪያ ቤቶቻቸውን ግንባታ በማካሄድ ላይ ሳሉ እንዲያቆሙ መደረጋቸው ቅሬታቸውን በማባባስ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደከተታቸው አክለዋል፡፡
ከእነዚህ ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ብርሃን ጎኅ ለተሰኘው ሪል ስቴት ኩባንያ ከተሰጠው ቦታ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንደሌላቸው በክፍለ ከተማው መሐንዲሶች አረጋግጠው፣ በፍርድ ቤት ጭምር አስወስነው መብታቸውን እንዳስከበሩ ይገልጻሉ፡፡ ይህ በሆነበት አግባብ ሁሉንም እንድትነሱ በማለት ለወራት በተናጠልና በቡድን፣ የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከወረዳ አምስትና ከወረዳ ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር በመሆን ነዋሪዎቹ የግድ ከይዞታቸው መነሳት እንዳለባቸው፣ ለግንባታ የሰጣቸው ፈቃድና የይዞታ ማረጋገጫና ካርታም እንዲሰረዝ መደረጉ በብዙ ድካምና ልፋት የገነቧቸውን መኖሪያ ቤቶች እንዲያፈርሱ መገደዳቸውን ይገልጻሉ፡፡
ከተነሺዎች መካከል ለሪፖርተር ቅሬታቸውን የገለጹ ባለይዞታዎች እንዳሉት፣ ለአንድ ወገን ያደላ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ይኸውም ኩባንያው ነዋሪዎቹ ከሚገኙበት ውጪ የሚገኝ ክፍት ሰፊ ቦታ በመኖሩ በዚያ ምትክ ሊሰጠው ሲገባ፣ ስምንት ሺሕ ካሬ በማይሞላ ቦታ ላይ ያረፉ 17 ቤቶች እንዲነሱ ግፊት ማድረጉ ፍትሐዊ አይደለም ብለዋል፡፡ በየካ ተራራ ላይ እንዲነሱ የተደረጉት ነዋሪዎች ሕዝብ ችግሩን ይወቅልን በማለት እነሱ ብቻም ሳይሆኑ፣ ከፍተኛ የደን ሀብት ጭምር እንዲመነጠር መደረጉ እንዳሳዘናቸው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
የአካባቢው ነፋሻማነትና በደን የተሞላ መሆን ለጥበብ ሥራ ጭምር እንዲመቻቸው በማሰብ ወደ አካባቢው ንብረቶቸውን ሸጠው የገቡ የሥነ ጥበብ ሰዎችም፣ በመንግሥት አድራጎት ቅሬታ እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡
ስለጉዳዩ በቅርቡ የተራራው ደን ለሪል ስቴት ፕሮጀክት እየተመነጠረ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህንኑ የሚያረጋግጥና ኩባንያው ከ14 ዓመታት በላይ በክርክር የቆየ ይዞታው ላይ ግንባታ ለመጀመር በመዘጋጀቱ ቦታው እንዲሰጠው እንደተደረገ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ይዞታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የሊዝ ቦርድ የቆየ ይዞታ መሆኑን አረጋግጦ ለሪል ስቴት አልሚው 40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታውን እንዳስረከበ ጽሕፈት ቤት አረጋግጧል፡፡ ነባር ነዋሪዎች ግን ቦታው የአረንጓዴ ይዞታና የፓርክ መገኛ በመሆኑና ለልማትና ለንግድ ሥራ እንዳይውል በመወሰኑ፣ የሪል ስቴት ኩባንያው እንዲያለማ ሳይፈቀድለት እንደቆየ ይናገራሉ፡፡
የክፍለ ከተማው ይዞታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በሰጠው ምላሽ የከተማ አስተዳደሩ በመመርያ ቁጥር 19 መሠረት ለበለጠ ልማት የሚፈልገውን ቦታ፣ ካሳና ሌሎችም ማካካሻዎችን በመፈጸም ባለይዞታዎችን ማስነሳት ሕግ ይፈቅድለታል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ያከራክር የነበረው የአረንጓዴ ቦታ አሁን ‹‹ነፃ ስለተደረገ›› ለሪል ስቴት አልሚው እንደተሰጠ ገልጸው፣ ጉዳዩን ይበልጥ መረዳት የሚፈልግ አካል የከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት በመሔድ መረጃ ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያነሱት ቅሬታ በማስመልከት የየካ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ለሙን በስልክ ለማነጋገር ተሞክሮ፣ ‹‹ሌላ ጊዜ ደውሉ›› ከሚል አጭር ምላሽ ጋር መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
አካባቢው ለመኖሪያነት እንጂ ለንግድና ለሕንፃ ግንባታ ሥራዎች መዋል እንደማይችል ሲሞግቱ ከነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ይገኝበታል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ አካባቢው የንግድ ተቋማት መግባት እንደማይችሉ ሲሞግት ቢቆይም፣ ሊሳካለት ባለመቻሉ ቤቱን ሸጦ ለመውጣት እንደተገደደ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡