መንግሥት ከጀመራቸው የሕግ ማሻሻያዎች መካከል በፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅን ፓርላማው ለእረፍት ከመበተኑ በፊት እንደሚያፀድቅ ታወቀ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ ግንቦት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በረቂቁ ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ ‹‹የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ›› የሚል ስያሜ ከተሰጠው ረቂቅ አዋጅ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙኃንን የተመለከተ የፖሊሲ ሰነድም ቀርቦለታል።
ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን የተመለከተ የመንግሥት የፖሊሲ ሰነድ እንዳልነበረ የሚታወቅ ሲሆን፣ ምናልባትም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ይህ ሰነድ ለአገሪቱ የመጀመርያው የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ሊሆን እንደሚችል የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አስተዳደር የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማጎልበት ከጀመራቸው ተግባራት መካከል፣ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ጉዳዮችን የተመለከቱ አፋኝ ሕጎችን ለማሻሻል የጀመረው ጥረት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በበጎነት ከሚጠቀሱት ውስን ተግባራት መካከል ግንባር ቀደሙ መሆኑ አይዘነጋም፡፡
የሕግ ማሻሻያዎቹ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በተቋቋመ ገለልተኛና ታዋቂ ባለሙያዎችን ባቀፈ ብሔራዊ የሕግ ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት አማካይነት ተጠንተው የተረቀቁ ናቸው።
ከእነዚህ የሕግ ማሻሻያ ሥራዎች መካከል በሥራ ላይ የሚገኘውን የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅና ሌሎች የመገናኛ ብዙኃንን የተመለከቱ ሕጎችን ማሻሻል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው።
በዚህ ዘርፍ የሚገኙ ሕጎችን ለማሻሻል በብሔራዊ አማካሪ ምክር ቤቱ ሥር ሆኖ ኃላፊነቱን የወሰደው የባለሙያዎች ቡድን፣ ማሻሻያዎቹን አከናውኖ የተለያዩ አዋጆችን አርቅቆ በአማካሪ ምክር ቤት በኩል ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ካስረከበና የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋምም የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ካስረከበ በርከት ያሉ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ የተነሳም የፖለቲካ አቋም ለውጥ ሳይደረግ አልቀረም የሚል ጥርጣሬ በዘርፉ ባለድርሻዎች ላይ አሳድሮ የነበረ ቢሆንም፣ በስተመጨረሻ ቅዳሜ ዕለት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ ከፍተኛ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ የመገናኛ ብዙኃን በስም ማጥፋት ወንጀል እንዳይጠየቁ የሚለው ድንጋጌ ግንባር ቀደም ሲሆን፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን በሕግ ተገድቦ ማፍሰስ እንዲችሉ የተካተተው ድንጋጌ ሌላኛው ነው፡፡
ሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት የውጭ ዜግነት ያለው ማንኛውም ሰው፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው ጨምሮ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤት እንዳይሆን ይከለክላል። አዲስ በተረቀቀው አዋጅ ላይ ግን የውጭ ዜግነት ያላቸው እስከ 25 በመቶ ብቻ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው የሚፈቅድ ረቂቅ ድንጋጌ መካተቱን ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ለመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ የሚሰጠውና የሚቆጣጠረው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሚባለውን ተቋም በድጋሚ የሚያቋቋም ድንጋጌን እንዳካተተ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ ተቋም ‹‹የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን›› በሚባል አዲስ ስያሜ በድጋሚ እንዲቋቋም በረቂቁ ከቀረበው ድንጋጌ በተጨማሪ፣ የተቋሙ ቦርድ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አይችሉም፡፡ እንዲሁም የተቋሙም ተጠሪነት በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ድንጋጌ አካቷል።
መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን የሚፈጸሙ ስህተቶችን በራሱ በቀጥታ እንዲታረሙ ማድረጉ በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ፣ የመገናኛ ብዙኃን ራሳቸውን በራሳቸው የሚቆጣጠሩበትና የሚያርሙበት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የመቋቋምን አላጊነት እውቅና በመስጠት የዚህ ምክር ቤት አደረጃጀና አሠራር እንዲጠናከር የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ረቂቅ ድንጋጌ ተካትቷል።
አሁን ባለው ሕግ የበይነ መረብ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ብቻ የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎቶችን የሚሰጡ የጽሑፍም ሆነ የምሥል መረጃ የሚያቀርቡ ድረ ገጾች፣ መመዝገብና ፈቃድ እንዲወስዱ የሚያስገድድ ድንጋጌ የለም። ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን እንዲህ ያሉ መገናኛ ብዙኃንም መመዝገብና ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ይደነግጋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ምን እንደሆነ ሪፖርተር ለኅትመት እስከገባበት ዓርብ ምሽት ድረስ አልታወቀም። ይሁን እንጂ ይህ ረቂቅ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓመቱ የሥራ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከማብቃቱ በፊት እንዲፀድቅ፣ በመንግሥት በኩል ፍላጎት መኖሩን ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል።