Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉ በመረጣቸው ድርጅቶች ላይ ቅሬታ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የናይጄሪያው ባለሀብት ንብረት የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካና የሳዑዲ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼክ መሐመድ አል አሙዲ ንብረት የሆነው ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ በተመሳሳይ ወቅት ለዕድሳት በሚል ምርት ማምረት ማቆማቸውን ምክንያት በማድረግ፣ ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉ የተመረጡ ድርጅቶችን መንግሥት መምረጡ ቅሬት አስነሳ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአንድ ሳምንት በፊት ባስተላለፊው ውሳኔ ነጋዴዎች ቅሬታ በማቅረባቸው፣ ግንቦት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. አምራቾችና ድርጅቶች ማለትም የአምባሰል የንግድ ሥራዎች ድርጅት፣ የወንዶ ኢንቨስትመንት ኩባንያ፣ ቢፍቱ አዱኛ ቢዝነስ ሼር ኩባንያ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ተወካዮች በንግድና ኢንዱስትሪ በሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሰብሳቢነት ሲከራከሩ መዋላቸውን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በዋናነት አከፋፋዮቹ የተመረጡት ድርጅቶች እንዲሆኑ ውሳኔ ላይ ያደረሰው፣ ዳንጎቴና ደርባ ለዕድሳት ብለው ምርት በማቆማቸው በተፈጠረ የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ ንረት ምክንያት መሆኑም ታውቋል፡፡

አብዛኛውን የሲሚንቶ ምርት የሚሸፍኑት ዳንጎቴና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርት ማምረት በማቆማቸው፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ያላቸውን ምርት በመያዝና እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ማድረጋቸው መንግሥት የራሱን ውሳኔ እንዲወስን እንዳነሳሳው ታውቋል፡፡ ሌሎቹ የሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤቶች ለሚኒስትሩ ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት፣ እነሱ ለሚያመርቱት ሲሚንቶ በኩንታል የተወሰነላቸውን ትርፍ ከማግኘትና ለአከፋፋዮች ከመስጠት ባለፈ ምንም ያደረጉት ነገር የለም፡፡ የቫት ተመዝጋቢ በመሆናቸው ሁሉም አሠራራቸው የሚታወቅና በኦዲተር የሚረጋገጥ መሆኑን በማስረዳት፣ ለምን ግዳጅ ውስጥ እንዲገቡ እንደተፈለገ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ነጋዴዎቹንና እንዲያከፋፍሉ የተመረጡትን ድርጅቶች ተወካዮች ካወያየ በኋላ፣ 12 አከፋፋዮችን በመጨመር ከአምስቱ ድርጅቶች ጋር እኩል ድርሻ ኖሯቸው እንዲያከፋፍሉ ውሳኔ ላይ መደረሱም ታውቋል፡፡

ድርጅቶቹ በየዕለቱ 340,280 ኩንታል ሲሚንቶ ከፋብሪካዎቹ በመረከብ እንዲያከፋፍሉም ተነግሯቸዋል፡፡ ድርጅቶቹ ምርቱን እንደሚያከፋፍሉ ተገልጿል፡፡ መንግሥት በሚወስነው ዋጋ ብቻ እንዲያከፋፍሉ፣ ቸርቻሪዎች ደግሞ ከአከፋፋዮች በተረከቡት ዋጋ ላይ በኩንታል 20 ብር ብቻ ትርፍ በማግኘት እንዲያከፋፍሉ፣ መንግሥት ከወሰነው በላይ ሲሸጡ ከተገኙ ግን ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቁ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች