የህዳሴ ግድብን ለመሙላት የማንም አገር ይሁንታ እንደማያስፈልጋት ኢትዮጵያ ገለጸች
በህዳሴ ግድብ ላይ የውኃ አሞላል ላይ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትሞላ፣ ሱዳን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ አቤቱታ አቀረበች።
በሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማ መሐመድ ተፈርሞ ከቀናት በፊት ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት የተላከው ደብዳቤ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካለ በህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላል ላይ መግባባት እንደሚቻል ይገልጻል።
ነገር ግን ሦስቱ አገሮች የጋራ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ በተናጠል የህዳሴ ግድቡን ውኃ ለመሙላት መወሰን፣ ወይም ሌላ የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርስ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደማይገባ ሱዳን ለተመድ በጻፈችው ደብዳቤ አሳስባለች።
ስለሆነም ሱዳን የምታደርገውን ጥረት ሁለቱም ወገኖች ተቀብለው ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች በቶሎ እንዲፈቱ፣ ለፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ያቀረበች ሲሆን ዕገዛም እንዲያደርግ ጠይቃለች።
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊ፣ ሱዳን ለፀጥታው ምክር ቤት በላከችው በዚህ ደብዳቤ ሁለት ነገሮችን ለማስቆጠር እንደሞከረች ያስረዳሉ።
አንደኛው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የሞከረችበት እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ ግብፅና ኢትዮጵያ ለተመድ በጻፋት ደብዳቤ የዓባይ ውኃ ለሕዝባቸው ያለውን ፋይዳና በውኃው ላይ ጥገኛ የሆነውን የሕዝባቸውን ብዛት በመግለጻቸው ሱዳንም ይኼንኑ ለማሳወቅ የተጠቀመችበት መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው ዓላማ ግን ሱዳን ለጊዜው ከግብፅ ጋር የቆመች ስለመሆኑ ፍንትው አድርጎ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት ብትጀምር፣ በሌላኛው ወገን በኩል ሊወሰድ የሚችል የአጸፋ ዕርምጃ የአካባቢውን ሰላም ሊያደፈርስ ይችላል የሚል ግልጽ መልዕክት ያለው የግብፅን ማስፈራሪያ የሚያስተገባ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሱዳን አቤቱታዋን ያቀረበችው ሦስቱ አገሮች ወደ ድርድር ለመመለስ ከተስማሙ በኋላ መሆኑም ቀጣዩ ድርድር ወደ ስምምነት አያደርስም የሚል አንድምታ እንዳለው፣ በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ የሚጠይቅ መሆኑን ኃላፊ አክለዋል።
ይኼንን ደብዳቤ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ የትኛውም አገር የፈለገውን ቢናገር ኢትዮጵያ በዕቅዷ መሠረት ግድቡን ከመሙላት የሚያግዳት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በላከቸው ማብራሪያ፣ በሉዓላዊ ግዛቷ ስለምታከናውነው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ከግብፅም ሆነ ከሌላ አገር ይሁንታ እንደማያስፈልጋት፣ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ሕግና መርሆች ተገዝታ እንደምታለማ ማስታወቋ ይታወሳል።