Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል አየር መንገዶች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ከገበያ መውጣታቸውን አስታወቁ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የቻርተር በረራ አገልግሎት የሚሰጡ የግል አየር መንገዶች፣ የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ከገበያ ውጪ መውጣታቸውን አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ የግል አየር መንገዶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አበራ ለሚ (ካፒቴን) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኮሮና ወረርሽኝ በግል አየር መንገዶች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል፡፡ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ከመጋቢት ወር ጀምሮ አብዛኛዎቹ የግል አየር መንገዶች ሥራቸውን ሙሉ ለሙሉ እንዳቆሙ አበራ (ካፒቴን) ተናግረዋል፡፡

የናሽናል ኤርዌይስ ባለቤት የሆኑት  አበራ (ካፒቴን) የግል አየር መንገዶች በአብዛኛው ለቱሪስቶች የበረራ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸውና የቱሪስት ፍሰት ሙሉ በሙሉ በመቆሙ፣ አየር መንገዶቹ ገቢያቸውን እንዳጡ ጠቁመዋል፡፡ ለኮርፖሬት ኩባንያ ኃላፊዎችና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኃላፊዎች የቪአይፒ በረራ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም የአገልግሎት ገበያ እንደተቋረጠ አስረድተዋል፡፡

በፊትም ቢሆን የግል አየር መንገዶች ከመንግሥትና ከባንኮች ድጋፍ ሳያገኙ በራሳቸው እየታገሉ ጠንካራ አቋም ስለሌላቸው፣ የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ለመቋቋም እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የግል አየር መንገዶች ሲወዳደሩ የኢትዮጵያ የግል አየር መንገዶች በእንጭጭ ዕድሜ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እንዳሉት ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት አገር በመሆኗ፣ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍን ማሳደግ ትክክለኛ ስትራቴጂ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጠንካራና ትልቅ ብሔራዊ አየር መንገድ መገንባት የተቻለ ቢሆንም፣ የግል አየር መንገዶች እንዲያድጉ ተመሳሳይ ድጋፍ ባለመደረጉ በዘርፉ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ እኛ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ደስተኞች ነን፡፡ አየር መንገዱ በማይበርባቸው ሩቅ ቦታዎች ቱሪስቶችንና ሌሎች ቪአይፒኦችን በማጓጓዝ ለቱሪዝም ዕድገት የበኩላችንን ዕገዛ የምናደርግ በመሆኑ መንግሥት ሊደግፈን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ሚሊዮን ዶላሮች ኢንቨስትመንት የሚጠይቀው የአየር መንገድ ሥራ የግል ባለሀብቶች እንዲሳተፉበት የሚያበረታታ ሁኔታ እንደሌለም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሚሊዮን ዶላሮች ኢንቨስት እያደረግን ለግል አየር መንገዶች እንደ አንድ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ማበረታታዎች የሉም፡፡ በአብዛኛው ባንኮችም ለግል አየር መንገዶች ብድር አያቀርቡም፤›› ብለዋል፡፡

የግል አየር መንገዶች አብዛኞቹ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ሥራ ያቆሙ ቢሆንም፣ ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ በመክፈል ላይ እንደሆኑ የገለጹት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ሠራተኞቻቸውን ይዘው መቀጠል እንደተቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አብዛኞቹ የግል አየር መንገዶች ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ያቆሙ በመሆኑ ቋሚ ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን ተቸግረዋል፤›› ያሉት  አበራ (ካፒቴን)፣ መንግሥት ለሆቴልና ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠውን ድጋፍ ለግል አየር መንገዶች እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግል አየር መንገዶች ማኅበር ለገንዘብ ሚኒስቴር ባስገባው ደብዳቤ የመንግሥትን ድጋፍ ጠይቋል፡፡ የግል አየር መንገዶች የስድስት ወራት ሥራ ማስኬጃ ወጪ በብድር እንዲሰጣቸው ማኅበሩ መጠየቁን ገልጸው፣ ‹‹የግል አየር መንገዶች ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ስለሆነ መንግሥት ሊታደጋቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች